Thursday, March 23, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበአዲስ አበባ በጅምር የቀሩና አገልግሎት እየሰጡ ያሉ ሕንፃዎች ቆጠራ እየተደረገ ነው

በአዲስ አበባ በጅምር የቀሩና አገልግሎት እየሰጡ ያሉ ሕንፃዎች ቆጠራ እየተደረገ ነው

ቀን:

  • በሁለተኛ ምዕራፍ ቆጠራ የመኖሪያ ቤቶች ይካተታሉ ተብሏል

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የግንባታ ፈድና ቁጥጥር ባለሥልጣን በጅምር የቀሩ ሕንፃዎችን ጨምሮ፣ አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙ ሕንፃዎችን ቆጠራ እያደረገ መሆኑ ታወቀ፡፡

ባለሥልጣኑ ተጀምረው የቆሙ ሕንፃዎችን መረጃ ሰብስቦ መያዝ ተፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ቆጠራ እያደረገ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡ ከሁለት ዓመታት በፊት ይህ ዓይነቱ መረጃ ተሰብስቦ የነበረ ቢሆንም፣ የመረጃ አሰባበሰቡ የተደራጀ ባለመሆኑ ቅሬታዎች በመቅረባቸው የአሁኑ ቆጠራ መጀመሩን ገልጿል፡፡

የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን የግንባታ ፈቃድ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዳዊት ሁንዴሳ (ኢንጂነር) ለሪፖርተር እንዳስረዱት፣ የመረጃ ማሰባሰቡ ባለቤት ያልተገኘባቸው ሕንፃዎችን መረጃ ሰብስቦ በማደራጀት ውሳኔ ለመስጠት ያመቻል፡፡ ግንባታቸው ተጀምረው የቆሙ ከG+0 ጀምሮ ሁሉም ዓይነት የሕንፃ ዓይነቶች የጥናቱ አካል መሆናቸውን ገልጸዋል

ከሁለት ዓመታት አስቀድሞ በተደረገው የመረጃ ማሰባሰብ ጅምር ሕንፃዎቹ ከተለዩ በኋላ የተለያዩ መረጃዎች ይቀርቡ እንደነበር፣ አንዳንዶቹ ሕንፃዎች ባለቤት የላቸውም ተብለው ከተለዩ በኋላ ሰነድ የቀረበባቸው በመሆናቸው፣ ችግሩን ለማጥራት እንደገና መረጃ መሰብሰብ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን ምክትል ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

አንድ ሕንፃ ባለቤት እያለው ባለቤት የለውም ከተባለ የመልካም አስተዳደር ችግር እንደሚፈጥር በሌላ በኩል ሕንፃዎች ብዙ ወጪ ወጥቶባቸውና ተጀምረው ከቆሙ ችግራቸው ምንድነው የሚለውን ለመለየት መረጃ ማሰባሰቡ አስፈላጊ በመሆኑ፣ ከተለየው ችግር በመነሳት የመፍትሔ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ይረዳል ብለዋል፡፡

የመረጃ መሰብሰብ ሥራው በሁሉም ክፍላተ ከተሞች እየተደረገ እንደሚገኝ የተገለጸ ሲሆን፣ ሥራውን ሊያከናው የሚችል የባለሙያዎች ቡድን ተደራጅቶ በዚያ መሠረት እየተሰበሰበ ይገኛል ተብሏል፡፡

የሚሰበሰበው መረጃ ማናቸውም ከተማ ውስጥ የሚገኙ ግንባታቸው ተጀምሮ የቆሙ ሕንፃዎችን የሚመለከት ሲሆን፣ በሒደቱ ለሕንፃ ባለቤቶች በማስታወቂያ ከይዞታ ማረጋገጫና የመሬት ባለቤትነት ጀምሮ እስከ ግንባታ ፈቃድ ድረስ ያለውን መረጃ እንዲያቀርቡ እንደሚደረግ፣ ከቀረበው መረጃ በመነሳት የማጥራት ሥራ እንደሚከናወን ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡

የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን የቀረበውን መረጃ ትክክለኛነት ሲያጣራ፣ ግንባታዎቹ በምን ምክንያት ነው የቆሙት? (በግብዓትና በፋይናንስ ችግር ወይስ በፍርድ ቤት ክርክርና ሌሎችም) የሚሉትን ከለየ በኋላ፣ ግንባታው እንዲጠናቀቅ ምን ዓይነት መፍትሔ ያስፈልገዋል በሚለው ላይ አቅጣጫ ይሰጥበታል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም ሕንፃው ባለቤት የሌለው ከሆነ በከተማ አስተዳደሩ የበላይ አካል የመጨረሻ ውሳኔ የሚሰጥበት መሆኑ ታውቋል፡፡

የሕንፃዎችን መረጃ የማጥራቱ ሥራ በሁለት ወራት ውስጥ የሚጠናቀቅ እንደሚሆን የተገለጸ ሲሆን፣ የሚቀርበውን መረጃ መሠረት በማድረግ ሪፖርት እንደሚቀርብና ያንን መነሻ በማድረግ በየደረጃው ውሳኔ እንደሚሰጥበት ታውቋል፡፡

ተጠናቀው አገልግሎት እየሰጡ ያሉ ሕንፃዎች የዚህ ጥናት አካል እንደማይሆኑ የተጠቆመ ሲሆን፣ ነገር ግን የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን በከተማው ውስጥ ያሉ ጠቅላላ ሕንፃዎችን የመመዝገብ ሥራ በተናጠል መሥራት እንደጀመረ ታውቋል፡፡

ግንባታቸው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት የጀመሩም ሆነ አገልግሎት መስጠት ያልጀመሩ የግል፣ የመንግሥትና የሃይማኖት ተቋማት ሕንፃዎችን የመመዝገቡ ሥራ የተለያየ ጥቅሞች እንዳሉት ያስረዱት ዳዊት (ኢንጂነር)፣ ከተማው ውስጥ ያለውን ሀብት በዘመናዊ መልክ አደራጅቶ ለመጠቀም ከማስቻሉ በተጨማሪ ለጥናትና ምርምር፣ ለንብረት ታክስና ለሌሎችም ጥቅም ይሰጣል ብለዋል፡፡

በመጀመሪያው ዙር የጥናቱ ምዕራፍ ባለአንድ ወለልና ከዚያ በላይ ያሉ ሕንፃዎች መረጃ የሚሰበሰብ ሲሆን፣ ይህ ሥራ እንደተጠናቀቀ የG+0 ሕንፃዎችና የመኖሪያ ቤቶች ቆጠራ ይከናወናል ተብሏል፡፡

ሕንፃዎችን የመመዝገቡ ሥራ ከተጀመረ ሁለት ሳምንታት እንደሆነው ተገልጾ፣ በጊዜዊነት ጥናቱ በሦስት ወራት ይጠናቀቀል የሚል ዕቅድ መያዙን ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ሕንፃዎችን ብዛት አስመልክቶ ያለው መረጃ በዘመናዊ መንገድ ባለመደራጀቱ በትክክል ቁጥሩ ይህን ያህል ነው የሚለውን ለመናገር እንደሚያዳግት የተናገሩት ምክትል ዳይሬክተሩ፣ የዚህ ጥናት ዋነኛ ዓላማውም ለዚህ ምላሽ ለመስጠት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን የሚያካሄደው መረጃ የመሰብሰብና የማጣራት ሥራ ባዶ ቦታዎችን እንደማይመለከት፣ ይህንን መረጃ የመሰብሰብ ሥልጣን የተሰጠው ለአዲስ አበባ መሬት አስተዳደርና የመሬት ይዞታ ምዝገባ ኤጀንሲ መሆኑን አክለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...