Friday, March 31, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበደቡብ ክልል በተካሄደው ሕዝበ ውሳኔ በወላይታ ዞን ከፍተኛ የሕግ ጥሰቶች መፈጸማቸው ተገለጸ

በደቡብ ክልል በተካሄደው ሕዝበ ውሳኔ በወላይታ ዞን ከፍተኛ የሕግ ጥሰቶች መፈጸማቸው ተገለጸ

ቀን:

  • ቦርዱ ውድቅ ለተደረገው የወላይታ ዞን ሕዝብ ድምፅ ተጨማሪ ገንዘብ ያስፈልገኛል ብሏል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም. ባካሄደው ሕዝበ ውሳኔ፣ በወላይታ ዞንና በሌሎች አካባቢዎች ከጅምሩ በታዩ ክፍተቶች ላይ ሕጋዊ ዕርምጃ እንዲወሰድ ለፀጥታ አካላት ቢያሳውቅም፣ ተገቢው ዕርምጃ ባለመወሰዱ፣ በሕዝበ ውሳኔው የመጨረሻ ውጤት ላይ ከፍተኛ የሆኑ የሕግ ጥሰቶች መፈጸማቸውን አረጋግጫለሁ አለ፡፡

ምርጫ ቦርድ ከ435 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ በጀት በደቡብ ክልል በሚገኙ 11 አደረጃጀቶች፣ ራሱን የቻለ አንድ ክልል ለመመሥረት ያካሄዱትን ሕዝበ ውሳኔ ድምፅ አሰጣጥ አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

በሕዝበ ውሳኔው ሒደት የወላይታ ዞን የድምፅ አሰጣጡ ተዓማኒነት የሌለውና በአጠቃላይ ውጤቱንም የሚያዛባ በመሆኑ፣ በቦርዱ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 1133/2011 አንቀጽ 7 ንዑስ አንቀጽ 20 መሠረት የሕዝበ ውሳኔ ድምፅ ሰጪዎች ምዝገባ ውድቅ ተደርጎ፣ ምዝገባውና ድምፅ አሰጣጡም በድጋሚ እንዲደረግ ቦርዱ መወሰኑን አስታውቋል፡፡

የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ በወላይታም ሆነ በሌሎች የምርጫ አካባቢዎች የተከሰቱ የሕግ ጥሰቶች የወንጀል ተጠያቂነት እንደሚያስከትሉ በመጠቆም፣ የፌዴራል ፖለስ በአፋጣኝ ምርመራ አድርጎ ሕጋዊ ዕርምጃ እንዲወሰድ ተጠይቆ የነበረ ቢሆንም፣ በጊዜው ዕርምጃ ባለመወሰዱ መጠነ ሰፊ ችግር ሊከሰት መቻሉን አስረድተዋል፡፡

በወላይታ ዞን ከአጠቃላይ ሒደቱ ከ96 በመቶ በላይ የሕግ ጥሰት መፈጸሙን የገለጹት ሰብሳቢዋ፣ ከጅምሩ ለተከሰተው ጥሰት ዕርምጃ ባለመወሰዱ የባሰ ችግር መፈጸሙን ጠቅሰው፣ አሁንም ቢሆን ዕርምጃው ቶሎ መወሰድ እንደሚኖርበት አሳስበዋል፡፡

በወላይታ ዞን በሚገኙት ስምንት ማዕከላት ውስጥ ከተደራጁት 1,112 የምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ፣ በ277 ምርጫ ጣቢያዎች የድምፅ ሰጪዎች መዝገቦች በናሙናነት ተወስደው ምርመራ የተደረገ መሆኑን፣ ከተመረመሩት ጠቅላላ 350 መዝገቦች ውስጥ 337 መዝገቦች ከፍተኛ የሆነ ጥሰትና ግድፈት እንደተገኘባቸው ተገልጿል፡፡

ተፈጸሙ ከተባሉት ጥሰቶች መካከል ከ18 ዓመት በታች ያሉ ዜጎች ድምፅ መስጠታቸው፣ ለሌላ ሰው መምረጥ፣ የድምፅ መስጫ ወረቀቶችን ማጨቅ፣ ሚስጥራዊነትን መጣስ፣ የታዛቢነት ባጅ ሳይኖራቸው በምርጫ ጣቢያ ታዛቢነት መገኘት የሚሉት ይገኙበታል፡፡

የቦርዱ መረጃ እንደሚያሳየው፣ ቦርዱ በናሙናነት ከወሰዳቸው ከ370 የምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ በ357 (96.5%) ጣቢያዎች በመራጮች ምዝገባ ወቅትና በድምፅ መስጫ ቀን የተረጋገጡት መጠነ ሰፊ ጥሰቶች፣ በዞኑ በሚገኙ አብዛኞቹ ጣቢያዎች የምርጫ ማጭበርበር መፈጸሙን ለቦርዱ የሚያሳምኑ መሆናቸው ተብራርቷል፡፡

በአጠቃላይ በ11 አደረጃጀቶች ውስጥ የሚገኙ ከሦስት ሚሊዮን በላይ ድምፅ ሰጪዎች እንደተመዘገቡ ቢገለጽም፣ በወላይታ ዞን ለተከሰቱ የሕግ ጥሰቶች ምክንያት በሕጉ መሠረት ለመምረጥ የተመዘገበውንና አጠቃላይ ወጥቶ የመረጠውን የሕዝብ ቁጥር ለማወቅ እንደማይቻል ሰብሳቢዋ ተናግረዋል፡፡ የሕዝበ ውሳኔ ምርጫውን ያካሄዱት በደቡብ ክልል ሥር በሚገኙ ስድስት ዞኖች ኮንሶ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ወላይታ፣ ጋሞ፣ ጌዴኦ፣ ጎፋና አምስት ልዩ ወረዳዎች ቡርጂ፣ በባስኬቶ፣ አሌ፣ አማሮና ደራሼ ናቸው፡፡

በወላይታ ዞን ተከሰተ ስለተባለው የሕግ ጥሰትና ሕዝበ ውሳኔውን በተመለከተ ሪፖርተር አስተያየት የጠየቃቸው የወላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ (ወብን) ፕሬዚዳንት አቶ አማኑኤል ሞጊሶ፣ የወላይታ ሕዝብ ከጅምሩ ሕዝበ ውሳኔውን እንደማይቀበለው ሲገልጽ እንደነበርና በዚህም የተነሳ ሕዝቡ ለመምረጥ የምርጫ ካርድ አለማውጣቱን አስረድተዋል፡፡

የወላይታ ሕዝብ ጥያቄ በራሱ ክልል ሆኖ ለመደራጀት እንጂ ከሌሎች አደረጃጀት ጋር ሆኖ ክልል የመመሥረት ፍላጎት እንደሌለው የገለጹት አቶ አማኑኤል፣ ነገር ግን የወላይታን ጥያቄ ወደኋላ በመመለስ ከሕገ መንግሥቱ ውጪ በአንድ ፓርቲ (ብልፅግና) ውሳኔ ተደራጅቶ ክልል እንዲመሠረት መደረጉ ለዚህ ሁሉ የሕግ ጥሰት መፈጠር ምክንያት ነው ብለዋል፡፡

ሕዝቡ የወላይታ ክልል እንዲመሠረት ይፈልግ እንደነበርና ነገር ግን ዕድሉ እንዳልተሰጠው፣ በዚህም ሳቢያ ካርድ አላወጣም ብለው ገልጸዋል፡፡ ‹‹ነገር ግን የአካባቢው ካድሬዎች ካርድ በሕዝቡ ስም እያወጡ ሲያድሉ ስለነበር ባወጡት ካርድ የሚመርጥ ሰው ባለማግኘታቸው ወደ ስህተት ገብተዋል፤›› ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል የወላይታ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ወሕዴግ) ፕሬዚዳንት አቶ ጎበዜ ጐአ በበኩላቸው፣ የወላይታ ሕዝብ ፍላጎት ሕገ መንግሥቱን በጣሱ ፖለቲከኞች መወሰኑ ለዚህ ሁሉ የምርጫ ሕግ ጥሰት መዳረጉን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

የምርጫ ምዝገባ ሲከናወን በቀበሌ፣ በወረዳና በዞን ካድሬዎች የምርጫ ካርድ ሲያድሉ ቢታይም በምርጫው ወቅት ሕዝቡ ያለ ፍላጎቱ ምርጫውን መሳተፍ ባለመፈለጉ በርካታ የሕግ ጥሰቶች ተፈጽመዋል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

በመሆኑም በቀጣይ ምርጫ ቦርዱ ሕዝበ ውሳኔውን ለማካሄድ ወደ ሥራ ከመግባቱ በፊት የሕግ ጥሰት የፈጸሙ አካላትን ተጠያቂ እንዲያደርግ፣ ወላይታ እንደ ክልል ሆኖ መቋቋም ለሚፈልጉ አካላት ሦስተኛ አማራጭ ኖሮ ሕዝቡ ድምፅ እንዲሰጥ ዕድል ሊሰጠው ይገባል ብለዋል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ በ6ኛው ጠቅላላ ምርጫ ወቅት ምርጫ ባልተካሄደባቸው አካባቢዎች ምርጫ ለማካሄድ አስፈላጊውን ዝግጅትና ማጣራት እያከናወነ መሆኑን፣ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢዋ ወ/ሪት ብርቱካን ተናግረዋል፡፡ ‹‹በፀጥታ ችግር ምርጫ ያልተካሄደባቸው አካባቢዎች የፀጥታ ችግሩ መሻሻሉን እያጠናን መረጃ እየሰበሰብን ነው፤›› ብለዋል፡፡

ለዓመታት የዘገየውን የአካባቢ ምርጫን ለማካሄድ ምርጫው የሚካሄደው በክልል ሕጎች መሠረት በመሆኑ፣ የየክልሎቹ ሕግ ምን ይመስላል የሚለውን ሁኔታ፣ ቦርዱ በሕጎቹ ላይ ግምገማ በማድረግና ጥናት በማካሄድ ችግራቸው ምንድነው? ምን መስተካከል አለበት? የሚለው ለሁሉም ክልሎች ተገልጾላቸው ማስተካከያ ካላቸው አስተካክለው እንዲልኩ መረጃ የተሰጣቸው ቢሆንም፣ እስካሁን ቦርዱ በሰጠው የአንድ ወር ጊዜ ውስጥ አስተካክሎ የመጣው የጋምቤላ ክልል ብቻ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም ሌሎችም ክልሎች ሕጎቻቸውን አይተው በአፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጡ ሰብሳቢዋ ጠይቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተወግዘው የነበሩ ሦስቱ ሊቀጳጳሳትና 20 ተሿሚ ኤጲስ ቆጶሳት ውግዘት ተነሳ

_ቀሪዎቹ ሦስት ህገወጥ ተሿሚዎች የመጨረሻ እድል ተሰጥቷቸዋል ​ ጥር 14...

በሕወሓት አመራሮች ላይ ተመስርቶና በሂደት ላይ የነበረው የወንጀል ክስ ተቋረጠ

በቀድሞ የትግራይ ክልል ፕሬዚደንት ደብረጽዮን ገብረሚካኤ,(ዶ/ር)ና ባለፈው ሳምንት በተሾሙት...

[የምክር ቤቱ አባል ላቀረቡት ጥያቄ በተሰጣቸው ምላሽ አቤቱታቸውን ለክቡር ሚኒስትሩ እያቀረቡ ነው]

ክቡር ሚኒስትር እየሆነ ያለው ነገር ትክክል ነው? ምነው? ምክር ቤቱም ሆነ...

የጉራጌ የክልልነት ጥያቄ ትኩሳት

ቅዳሜ መጋቢት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. በጉራጌ ዞን ወልቂጤ...