Tuesday, March 28, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የስኳር ፋብሪካዎችን ወደ ግል ለማዘዋወር ለወጣው ጨረታ በርካታ ባለሀብቶች ፍላጎት አሳዩ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

መንግሥት ስምንት የስኳር ፋብሪካዎችን ወደ ግል ለማዘዋወር ባወጣው ጨረታ ለመሳተፍ፣ ከሃያ በላይ የአገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች ፍላጎት ማሳየታቸው ታወቀ፡፡

በወርኃ ነሐሴ 2014 ዓ.ም. መንግሥት በገንዘብ ሚኒስቴርና በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ በኩል በአገር ውስጥና ለዓለም አቀፍ ባለሀብቶች፣ የስኳር ፋብሪካዎችን ወደ ግሉ ዘርፍ ለማዘዋወር በወጣው ጨረታ እንዲሳተፉ ጥሪ ማቅረቡ ይታወሳል።

የፍላጎት ማሳወቂያ ግብዣውን መሠረት በማድረግ ከ20 በላይ የአገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች በጨረታው ለመሳተፍ ፍላጎት ማሳየታቸውን፣ የገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

መንግሥት በዘርፉ ለመሰማራት ፍላጎት ካሳዩ ባለሀብቶች ጋር በዝግጅት ላይ ስላለው የዘርፉ ፖሊሲና የተሟላ የጨረታ ሰነድ፣ ምክክር እያደረገ መሆኑም በመግለጫው ተካቷል፡፡

ለጨረታ የቀረቡት ኦሞ ኩራዝ 1፣ ኦሞ ኩራዝ 2፣ ኦሞ ኩራዝ 3፣ ኦሞ ኩራዝ 5፣ አርጆ ደዴሳ፣ ከሰም፣ ጣና በለስና ተንዳሆ የስኳር ፋብሪካዎች ሲሆኑ፣ መንግሥት የግሉ ዘርፍ በስኳር ኢንዱስትሪው የሚያደርገውን ተሳትፎ ለማሳደግ በዘርፉ ማሻሻያዎች ማድረጉን ማሳያዎች መሆናቸውን፣ የገንዘብ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

የገንዘብ ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ በጋራ ባወጡት መግለጫ፣ የስኳር ፋብሪካዎችን ወደ ግል ለማዘዋወር ለወጣው ጨረታ ፍላጎት ያሳዩትን ባለሀብቶች ተሳትፎ አድንቀው፣ በቀጣይ በሚኖረው የጨረታ ሒደት ተሳትፏቸውን እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በነሐሴ 2014 ዓ.ም መንግሥት በኢኮኖሚው ውስጥ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ለማሳደግ የተለያዩ ማሻሻያዎችን አድርጎ ወደ ሥራ መግባቱን በማስታወስ፣ የስኳር ምርታማነትን በማሳደግ የአገር ውስጥ ፍላጎትን ለማሟላት ያለመ በሚል ይፋ ላደረገው ጨረታ ተወዳዳሪዎችን መጋበዙ ይታወሳል፡፡

ለጨረታ የቀረቡት ስምንት ፋብሪካዎች ወደ ግል መዘዋወራቸው፣ ኢትዮጵያ ለስኳር ግዥ የምታወጣውን የውጭ ምንዛሪ በማስቀረት፣ ገቢን ለማሳደግና የሸንኮራ አገዳ አምራቾችን ሕይወት ለማሻሻል እንደሚረዳም ታምኖበታል። ከዚህ ባለፈም ጥሬና ያለቀለት የሸንኮራ አገዳ ምርት ለውጭ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሪ ለማስገኘት እንደሚረዳም ሲገለጽ ቆይቷል።

የገንዘብ ሚኒስቴር ለሽያጭ ያቀረባቸው ሰምንት ግዙፍ የመንግሥት ፋብሪካዎች፣ በመንግሥት ዋስትና ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ከውጭ መንግሥታት ተበድረው ያልመለሱት ከፍተኛ ዕዳ ቢኖርም፣ ከዕዳው ነፃ ሆነው በሚወጣው ዓለም አቀፍ ጨረታ ተወዳድረው ለሚያሸንፉ ባለሀብቶች እንደሚተላለፉ ከዚህ ቀደም መገለጹ አይዘነጋም። 

እ.ኤ.አ. በ2021/2022 የኢትዮጵያ የስኳር ፍላጎት በነፍስ ወከፍ 11 ኪሎ ግራም እንደሆነ ሲገመት፣ በዚህም መሠረት አጠቃላይ የአገሪቱ ዓመታዊ አጠቃላይ የስኳር ፍጆታ 1.3 ሚሊዮን ቶን መሆኑ ይገለጻል። ይህ የስኳር ፍላጎት በነፍስ ወከፍ እስከ 2029/30 ድረስ በየዓመቱ አንድ በመቶ ያድጋል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ በዚህም መሠረት በትንሹ የኢትዮጵያ አጠቃላይ ዓመታዊ የስኳር ፍላጎት 1.7 ሚሊዮን ቶን እንደሚሆን የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

በአገሪቱ የሚገኙት ፋብሪካዎች የአገር ውስጥ ፍላጎትን እየሸፈኑ ባለመሆናቸው፣ መንግሥት የአገሪቱን ዓመታዊ የስኳር ፍላጎት ለማሟላት ከውጭ ግዥ እንደሚፈጽም ይታወቃል። 

ለአብነት እ.ኤ.አ. በ2020 የአገር ውስጥ የስኳር ፍላጎትን ለማሟላት መንግሥት 153 ሚሊዮን ዶላር ወጪ በማድረግ ከውጭ የስኳር ግዥ ፈጽሞ ለገበያ አቅርቧል፡፡ እ.ኤ.አ. በሰኔ 2022 ብቻ 100,000 ሜትሪክ ቶን የስኳር ግዥ እንደፈጸመ የገንዘብ ሚኒስቴርን ሰነድ ዋቢ በማድረግ መዘገባችን ይታወሳል። ኢትዮጵያ ስኳር ከምትሸምትባቸው ዋናዎቹ አገሮችም ህንድ፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ፣ ብራዚልና ደቡብ አፍሪካ መሆናቸውን መረጃው ያመለክታል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች