Thursday, March 23, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊ‹‹በአዲስ አበባ ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ቤቶች ብቁና ተወዳዳሪ ተማሪዎችን ማፍራት አልተቻለም›› ...

‹‹በአዲስ አበባ ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ቤቶች ብቁና ተወዳዳሪ ተማሪዎችን ማፍራት አልተቻለም›› የትምህርትሥልጠናና ቁጥጥር ባለሥልጣን

ቀን:

በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ቤቶች ላይ የሚያስተምሩ መምህራን፣ ብቁና የተመዘኑ ባለመሆናቸው የተነሳ፣ የመማር ማስተማር ሒደቱ ላይ ከፍተኛ የሆነ ክፍተት መፍጠሩን፣ የትምህርትና ሥልጠና ቁጥጥር ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡

ባለሥልጣኑ ይህንን የገለጸው የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆችን የስታንዳርድ ክትትል ኢንስፔክሽንና ድንገተኛ ቁጥጥርን በተመለከተ ሪፖርት ባቀረበበት ወቅት ነው፡፡

በትምህርትና ሥልጠና ቁጥጥር ባለሥልጣን የአቃቂ ቃሊቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ አብርሃም ምትኩ እንደገለጹት፣ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የመንግሥትና የግል ቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ላይ ደረጃቸውን የጠበቁ መምህራን ባለመኖራቸው የተነሳ ተወዳዳሪ የሆኑ ተማሪዎችን ማፍራት አልተቻለም፡፡

ተቋሙም የ2014 ዓ.ም. የስታንዳርድ ክትትል ኢንስፔክሽን ሥራን አስመልክቶ ያደረገው ክትትል እንደሚያሳየው፣ 52 በመቶ የሚሆኑ ኮሌጆች ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት ከመስጠት አኳያ ክፍተት ያለባቸው መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

በተመሳሳይ በውጭ ኢንስፔክሽን በተሰጠው ግብረ መልስ መሥፈርት፣ መምህራን ለተማሪዎች ከሚሰጡት የተግባር ትምህርት ሥልጠና ላይ የሚታዩትን ችግሮች ለመፍታት የተደረጉ ቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ላይ 52.4 በመቶ የሚሆኑ ኮሌጆች ከእነ ክፍተቱም ቢሆን ጅምር ሥራዎች እየሠሩ መሆኑንና 47.6 በመቶ ግን ሰፊ ክፍተት እንዳለባቸው አክለው ገልጸዋል፡፡

አብዛኛውን የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ከተጠያቂነት ለመውጣትና በዘርፉ ላይ ያሉትን ችግሮች ደባብሶ ለማለፍ ብቻ የሚሠሩ እንዳሉ የገለጹት ሥራ አስኪያጁ፣ እነዚህንም ኮሌጆች ተገቢ የሆነ አሠራር እንዲከተሉ ተቋሙ የክትትል ሥራ እየሠራ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡

ባለሥልጣኑም ቴክኒክና ሙያ ኮሌጆችን የሚፈትሽበት የራሱ የሆነ አሠራር እንዳለው፣ በአሠራሩ መሠረት ባደረገው ክትትል ባለፈው ዓመትም ሆነ በአሁኑ ወቅት ደረጃቸው የተጠበቀ ኮሌጆች ዝቅተኛ መሆናቸውን፣ በዚህም የተነሳ ዘርፉ ላይ ከፍተኛ የሆነ ችግር መኖሩን ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል፡፡

በዚህ መሠረት ባለሥልጣኑ 80 ኮሌጆች ላይ ባደረገው የስታንዳርድ ከትትል ኢንስፔክሽን ሥራ 13 የመንግሥት ኮሌጆች ውስጥ ስምንቱ ደረጃ ሁለት ላይ እንደሚገኙ፣ አምስቱ ደግሞ ደረጃ ሦስት መግባታቸውን፣ ይህም የሚበረታታ መሆኑን አቶ አብርሃም ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ጎን ለጎን ከ64 የግል ኮሌጆች ውስጥ ደረጃ አንድ ላይ የተቀመጡት አራት መሆናቸውን፣ ደረጃ ሁለት ላይ 45 ሲሆኑ፣ ደረጃ ሦስት ላይ 15 እንደሆኑና እነዚህም 49 ኮሌጆች በፍጥነት ከደረጃ አንድና ሁለት መውጣት ይኖርባቸዋል ሲሉ አብራርተዋል፡፡

በተመሳሳይ የግልም መንግሥታዊም ያልሆኑ ሦስት ኮሎጆች መኖራቸውን፣ ከእነዚህም ኮሌጆች ውስጥ ሁለቱ ደረጃ ሁለት ሲሆኑ፣ አንዱ ደግሞ ደረጃ ሦስት ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

አጠቃላይ ሲታይ ከተሠራላቸው 80 ተቋማት አራቱ ደረጃ አንድ ላይ፣ 55ቱ ደረጃ ሁለት ላይ ሲሆኑ፣ 21 ደግሞ ደረጃ ሦስት መሆናቸውንና ይህም ካለፈው ዓመት አንፃር ሲታይ ከፍተኛ የሆነ ለውጥ መኖሩን አስረድተዋል፡፡ 

የትምህርት ሥልጠና ቁጥጥር ባለሥልጣን ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ሕይወት ጉግሳ እንደገለጹት፣ በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙ 108 ኮሌጆች ውስጥ 21 ተቋማት ብቻ ደረጃ ሦስት ላይ ናቸው፡፡

እንደ አጠቃላይ በዘርፉ ላይ ደረጃ አራት ላይ የሆነ ኮሌጅ አለመኖሩን፣ በዘርፉ ላይ ትልቅ ችግር እንዳለ ያሳያል የሚሉት ወ/ሮ ሕይወት፣ ይህንንም አሠራር ለመቀልበስ ተቋሙ ከታች ጀምሮ እየሠራ እንደሚኝ ገልጸዋል፡፡

‹‹የቴክኒክና የሙያና ኮሌጆች ደረጃቸው በተሟላ መልኩ ላይ ናቸው›› የሚባለው፣ ደረጃ ሦስትና ደረጃ አራት ላይ ሲሆኑ ብቻ እንደሆነ፣ ዘርፉ ላይም ከዓመት ዓመት የተሻለ ለውጥ ቢኖርም ችግሩ ግን የጎላ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዚህ መሠረት በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ላይ የሚገኙ ተቋማቶች 34 በመቶ ብቻ እንደሆኑና አብዛኛዎቹ ኮሌጆችም ያሉበትን ሁኔታ ራሳቸውን በመፈተሽ ለውጥ ማምጣት ይኖባቸዋል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

አብዛኛውን ተቋማት ላይ መምህራኖችም ሆኑ የኮሌጁ ዲን ቅንጅት ፈጥረው ባለመሥራታቸው የተነሳ ይህ ችግር መፈጠሩን፣ በዘርፉ ላይ የተሰማሩ ተቋማት ግብዓትም ሆነ የይዞታ ችግር እንደሌለባቸው አክለው ገልጸዋል፡፡

ባለሥልጣኑም የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆችን አስመልክቶ የስታንዳርድ ክትትል ቁጥጥር ኢንስፔክሽንና ድንገተኛ ቁጥጥር ግኝት ሪፖርት ባቀረበበት ወቅት የተሻለ አፈጻጸም ላመጡ ኮሌጆች የዕውቅና ሽልማት አበርክቶላቸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...