Tuesday, March 28, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር የቢዝነስ ስትራቴጂ እየተጠና መሆኑ ተገለጸ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ካለፈው ዓመት ወዲህ ለኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ተጠሪ የሆነው የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር፣ የቢዝነስ ስትራቴጂ እየተጠና ነው፡፡

የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር የሲቪል ሰርቪስ መሥሪያ ቤቶች ከሚባሉት ተቋማት አንዱ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፣ ተጠሪነቱም ለገቢዎች ሚኒስቴር ሆኖ ቆይቷል፡፡

በ2014 ዓ.ም. የመንግሥት መዋቅር አደረጃጀት ሲደረግ ወደ ልማት ድርጅትነት የተቀየረው ተቋሙ፣ በዚህም የአገልግሎት ሰጪነት ሥራውን ወደ ቢዝነስ ሞዴል መቀየር እንደሚገባው የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ንዋይ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ተጠሪነታቸው ለኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ከሆኑት 26 ድርጅቶች አንዱ የሆነው ብሔራዊ ሎተሪ፣ በተለይም በተያዘው ዓመት የሁለተኛ ግማሽ ዓመት ትኩረቱ የሚሆነው የልማት ድርጅትነቱን መሠረት በማድረግ የቢዝነስ ስትራቴጂ ጥናት ማካሄድ አንዱ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

የቢዝነስ ስትራቴጂ ጥናቱ በዋነኛነት የዲጂታል አማራጮችን በመጠቀም የሚተገበሩ ኢንቨስትመንቶችንና አገልግሎቶችን፣ የቢዝነስ ዕቅድና የፋይናንስ ጉዳዮችን የሚመለከት ይሆናል ተብሏል፡፡

አቶ ቴዎድሮስ እንዳስረዱት፣ ተቋሙ ሁለት ዓይነት የወረቀት ዕድል ጨዋታዎች ከማቅረቡ በተጨማሪ፣ የዲጂታል ሎተሪ ማጫወት ጀምሯል፡፡ እነዚህን  ተጨማሪ አገልግሎቶችን ይበልጥ አክሎ ለማስፋፋት የቢዝነስ ስትራቴጂው እንደሚያግዝ ተገልጿል፡፡

ጥናቱን በበላይነት እንደሚመራው የተገለጸው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ፣ ከሰሞኑ የአስተዳደሩን የግማሽ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ገምግሟል፡፡

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ በርካታ የመንግሥት ሀብቶችን ወደ አንድ ተቋም በመሰብሰብና ውጤታማ የአስተዳደር ሥርዓት በመፍጠር፣ ከሀብቶች የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም በማሻሻል ስትራቴጂካዊ የልማትና የኢንቨስትመንት መሣሪያ ለማድረግ የተቋቋመ መሆኑ ይታወሳል፡፡

ብሔራዊ ሎተሪ በተያዘው ዓመት የመጀመርያው ስድስት ወራት 714 ሚሊዮን ብር አጠቃላይ ገቢ፣ እንዲሁም 231 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ እንዳገኘ የተገለጸ ሲሆን፣ ይህም ድርጅቱ ከሚያቀርበው የሎተሪ ጨዋታና ፈቃድ ሰጥቶ በድርጅቶች በኩል ከሚደረጉ የዕድል ጨዋታዎች እንደሆነ ተነግሯል፡፡

በዓመቱ መጨረሻ 1.99 ቢሊዮን ብር ጠቅላላ ገቢ፣ እንዲሁም 370.8 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ለማግኘት እንደሚጠብቅ ብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር አስታውቋል፡፡

     በመጀመሪያው የግማሽ ዓመት የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት የታክስ ማጭበርበርን ጨምሮ በሕገወጥ የጥቁር ገበያ የውጭ ምንዛሪ ግዥ ወንጀል ድርጊት ተሳታፊ ናቸው በሚል 13 የስፖርት ውርርድ አጫዋቾች ድርጅቶች የባንክ ሒሳብ እንዲታገድ ማድረጉ የሚታወስ ሲሆን፣ ይህም ከዘርፉ ዳጎስ ያለ ገቢ እያገኘ በሚገኘው ብሔራዊ ሎተሪ አጠቃላይ ገቢ ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል የሚል ሐሳብ ሲንሸራሸር ቆይቷል፡፡

አቶ ቴዎድሮስ ድርጅቶቹ አሁንም በሥራ ላይ እንዳሉ ገልጸው፣ የባንክ ሒሳባቸው እንጂ እነሱ ሥራቸውን ቀጥለዋል ብለዋል። የስፖርት አወራራጅ ድርጅቶቹ ሥራቸውን አሁንም ለአስተዳደሩ ሪፖርት እንደሚያደርጉ፣ እንዲሁም የሚጠበቅባቸውንም የኮሚሽን ክፍያ እየከፈሉ መሆናቸውን አክለዋል።

የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር በሕጋዊ መንገድ የሎተሪ ጨዋታዎችን እንዲያጫውት በ1954 ዓ.ም. በአዋጅ የተቋቋመ የ61 ዓመታት ተቋም ሲሆን፣  ታኅሳስ  29  ቀን 1954 ዓ.ም. የመጀመርያ  የሎተሪ  ዕጣ  በጃንሜዳ  ሲወጣ  ዕድለኞቹ  የሐማሴን  አውራጃ (ኤርትራ)  ነዋሪዎች እንደነበሩ ይጠቀሳል፡፡

በመጀመርያ የወጣው ዕጣ አምስት እያንዳንዳቸው 10,000 ብር የሚያስገኙ የሎተሪ ቅጠሎች ነበሩት፡፡ አስተዳደሩ ከ61 ዓመት በኋላ ለሽያጭ በሚያቀርባቸው የሎተሪ ዓይነቶችና ዕድል ጨዋታዎች እስከ አሥር ሚሊዮን ብር ሽልማት ለአሸናፊዎች እያቀረበ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች