Friday, March 31, 2023

የጽንፍ ፖለቲካ እያጠላበት ያለው የዓድዋ ክብረ በዓል

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ታዋቂ የታሪክ ጸሐፍትን ምልከታ በአንድ አሰባስቦ የተዘጋጀውና በጳውሎስ ሚኪያስና ጌታቸው መታፈሪያ አርታዒነት ‹‹The Battle of Adwa፡ Reflections on Ethiopia’s Historic Victory Against European Colonialism›› በሚል ርዕስ የታተመው መጽሐፍ፣ ስለታላቁ ዓድዋ ድል ብዙ ቁምነገሮችን ከተለያዩ አቅጣጫዎች ለማቅረብ ይሞክራል፡፡

ወደ ዘጠኝ ታላላቅ የታሪክ ምሁራን በጻፉበት በዚህ ጥናታዊ መጽሐፍ ‹ምኒልክና የዓድዋ ድል› ‘Emperor Menelik and the Battle of Adwa’ በሚለው ምዕራፍ አምስት ንዑስ ርዕስ ሥር፣ ጌታቸው መታፈሪያ (ፕሮፌሰር) ስለድሉ መሪዎች ጠንካራ መረጃዎችን ያቀርባሉ፡፡

‹‹የዓድዋ ድል ስኬት በጊዜው ኢትዮጵያ የነበሯትን መሪዎች የአመራር ብቃት የሚመሰክር ነው፤›› ‘The success at the battle of Adwa is a testimonial to the quality of leadership existed at the time’ በማለት ነው ጌታቸው (ፕሮፌሰር) ሀተታቸውን ያሠፈሩት፡፡

እንደ የታሪክ ምሁሩ ገለጻ ከሆነ በዓድዋ ዓውደ ውጊያ ወቅት ኢትዮጵያን የመሩ መሳፍንትና ነገሥታት ከተለያዩ ማኅበረሰቦች የወጡ ነበሩ፡፡ ከአፄ ምኒልክ ቁልፍ ሚኒስትሮችና የቅርብ ሰዎች ውስጥ ጥቂት የማይባሉት ከሸዋ (መሀል አገር) ውጪ የመጡ ሰዎች ነበሩ ይላሉ፡፡

ራስ ጎበና ዳጬ የምኒልክ ቁልፍ የጦር ጄኔራል ሲሆኑ፣ የኦሮሞ ተወላጅ የነበሩ ሰው ነበሩ፡፡ ምኒልክ በሌሉበት ሁሉ ራስ ጎበና ነበሩ የንጉሡን ቦታ ተክተው ሥራዎችን የሚሠሩት ይሏቸዋል፡፡

ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴ (አባ መላ) ከሸዋ መሳፍንት ውጪ የመጡ የምኒልክ ቁልፍ የጦር ሚኒስትር ነበሩ፡፡ ንጉሡ ከታመሙና የአልጋ ቁራኛ ከሆኑ ጊዜ ጀምሮ ደግሞ የአገር ማስተዳደር ከባድ የሥራ ሸክሞችን በቦታቸው ተክተው የተወጡ ሰውም ነበሩ ይላሉ፡፡

በጦርነቱ ጊዜ የምኒልክ ሌላኛው ቁልፍ የጦር ጄኔራል ደግሞ ራስ አሉላ አባ ነጋ (ቱርክ ባሻ) ሲሆኑ ከትግራይ የወጡ ጀግና የጦር ሰው እንደነበሩ ያስረዳሉ፡፡

በጊዜው ከሸዋ የወጡ ወንዶች መሳፍንቶች በርካታ የሥልጣን ቦታዎችን ቢይዙም፣ ብዙ የምኒልክ የቅርብ ሰዎች የመጡት ግን ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ነበሩ፡፡ ሌላው ቀርቶ የምኒልክ የትዳር አጋርና የመንግሥታቸውም ቁልፍ አመራር እቴጌ ጣይቱ ብጡል የወጡት ከሰሜን፣ የጁና ትግሬ ማኅበረሰቦች ነው በማለትም የታሪክ ምሁሩ ጌታቸው (ፕሮፌሰር) ከትበዋል፡፡ እቴጌ ጣይቱ የፍትሐ ነገሥት ሕግ መጽሐፍን፣ የግዕዝ ቅንቋና የጊዜውን ዕውቀት ተምረው ያደጉ ስለነበሩ በመንግሥታዊ ሥራዎችና ውሳኔዎች ላይ ከባድ ተፅዕኖ አሳዳሪ ሴት ለመሆን አልከበዳቸውም ሲሉም ይገልጿቸዋል፡፡

በጊዜው የየራሳቸው ንጉሣዊ ሥርዓት ይዘው የሚተዳደሩ ማኅበረሰቦች እንደነበሩ ታሪክ ጸሐፊው ይጠቅሳሉ፡፡ በጅማ አባ ጅፋር፣ በከፊል ወለጋ ደጃዝማች ሞረዳ በከሬ፣ በደቡብ ወለጋና በቤኒሻንጉል ደጃዝማች ጆቴ ቱሉ የየራሳቸው መስተዳድር ነበራቸው ሲሉም ያወሳሉ፡፡ በትግራይ ራስ መንገሻ ዮሐንስ፣ በወሎ ራስ ሚካኤል፣ በወላይታ ንጉሥ ካዎ ጦና፣ በጎጃም ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት፣ እንዲሁም በይፋት ወላስማዎች የራሳቸውን አካባቢዎች ይመሩ ነበር ይላሉ የታሪክ ተመራማሪው፡፡

የኢትዮጵያ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካ መሠረት ገና ባልዳበረበትና የአገረ መንግሥቱ መዋቅር ባልጠነከረበት በዚያ ዘመን፣ የኢትዮጵያ መሪዎች ግን ሁሉንም አስተባብረውና አንድ አድርገው በአንድ የጦር ግንባር ለማሠለፍና ታላቁን የዓድዋ ድል ገድል ለመጻፍ በቅተዋል ይላሉ፡፡

የአፄ ምኒልክ መንግሥት በጊዜው ሁሉንም አካታች የሆነ አመራር የፈጠረ ነው የሚሉት ጌታቸው (ፕሮፌሰር)፣ የንጉሠ ነገሥት መንግሥት ሁሉንም አካታች የሆነ አንድ አመራር የፈጠረው ደግሞ የየራሳቸውን ንዑሳን ህልውና (የግዛት አስተዳደር ሥሪት) ሳያፈርስ ያልተማከለ አስተዳደርን በመፍጠር ጭምር ነው ሲሉም ያክላሉ፡፡

የዓድዋ ጦር ሜዳ ጀብድ የተመዘገበው በኅብረ ብሔራዊ አንድነት ነው የሚለውን ትርክት ብዙዎች ይቀበሉታል፡፡ ከሁሉም አቅጣጫ፣ ከሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል የተውጣጡ ጀግኖች የኢትዮጵያ ልጆች በከፈሉት የሕይወት መስዋዕትነት በዓለም ታሪክ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የጥቁሮች ድል የሆነው ዓድዋ ድል መመዝገቡን የሚክዱ ብዙም አይታዩም፡፡

ይሁን እንጂ ይህ ታላቅ ድል የተመዘገበበት ዕለት በየዓመቱ ሲመጣ ቀኑ ተከብሮ የሚውልበት ሁኔታ ብዙዎችን ሲያወዛግብ ይታያል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የዓድዋ በዓል መከበር ካለበት የምኒልክ ስምም ሆነ ምሥል ሳይነሳ መሆን ይኖርበታል የሚለው ሙግት ከባድ የውዝግብ ምንጭ እየሆነ ነው፡፡

በዓሉ በሚከበርበት ሰሞን በባንዲራ፣ በምልክት፣ በጀግኖች ማንነትና ታሪክ ዙሪያ የሚነሱ ሙግቶችና ክርክሮች የፖለቲካ ውዝግብ መነሻ እየሆኑ ነው፡፡ የዓድዋ ድል አከባበር ጉዳይ ባለፉት አራት ዓመታት በማኅበራዊ የትስስር ገጾች ከባድ የቃላት ጦርነት የሚካሄድበት ሁነት እየሆነ መጥቷል፡፡

በዓሉ በደረሰ ቁጥር የቃላት ጦርነቱ በገቢር እየተገለጠ ግጭትና እስራት ሲስተናገድ የታየበት አጋጣሚ እየተደጋገመ ይገኛል፡፡ የዓድዋ በዓል በደረሰ ቁጥር ሰንደቅ ዓላማ፣ ምሥሎችና ምልክቶች ‹መያዝ አይቻልም› የሚል የልዩነት መደብ እየተሰጣቸው ፖሊስ ከዜጎች ጋር ውዝግብ ውስጥ የሚገባባቸው ጉዳዮች እየሆኑ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ የሚቀጥለው እስከ መቼ ነው? ችግሩ ሄዶ ሄዶ የእርስ በርስ ዓድዋ ዓውደ ውጊያ በኢትዮጵያውያን መካከል ከማስከተሉ በፊት መፍትሔ አያሻውም ወይ? የሚለው ጥያቄ ጎልቶ እየተነሳ ነው፡፡

በእንግሊዝ ኬል ዩኒቨርሲቲ መምህር አወል አሎ በ2019 በአልጀዚራ ላይ ‹‹How a Major Anti Colonial Victory Divided Ethiopia›› በሚል ርዕስ የቀረበው ጽሑፍ፣ የዓድዋ ድል ኢትዮጵያውያንን ለረዥም አሥርት ዓመታት ሲከፋፍል የቆየ ጉዳይ ነው ይላል፡፡

123ኛው የዓድዋ ድል በሚዘከርበት ወቅት የወጣው ይህ ጽሑፍ ዓድዋ ምኒልክ ጨካኝ የዘውዳዊ አገዛዙን ያጠነከረበት የታሪክ ምዕራፍ ነው ይላል፡፡ ዓድዋ መታየት ያለበት አሁን በኢትዮጵያ ባለው የፖለቲካና የርዕዮተ ዓለም መነጽር ነው ሲል የሚሞግተው ጸሐፊው፣ ምኒልክ የድሉ ማዕከል ተደርገው መቅረብ የለባቸውም ይላል፡፡

በአፄ ምኒልክ ሥርዓት በደልና ጭፍጨፋ የደረሰባቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች ስላሉ ንጉሡን ዓድዋ በመጣ ቁጥር ማወደስና ማሞገስ፣ የእነዚህን ማኅበረሰቦች ቁስል በእንጨት እንደ መውጋት ይቆጠራል ይላል፡፡

ይህ ጽሑፍ የዓድዋ በዓል መከበሪያ ቦታ ከምኒልክ አደባባይ ይልቅ በሌላ ሁሉም የክብረ በዓሉ ተሳታፊ ሊሆን በሚችልበት ቦታ እንዲሆን ያሳስባል፡፡ አፄ ምኒልክን ከማሞገስ ይልቅ ሁሉንም የሚያግባባ እንደ እቴግ ጣይቱ ያሉ ጀግኖች ጎልተው በበዓሉ ቢዘከሩ እንደሚሻልም ጸሐፊው ሐሳብ ያቀርባል፡፡

አወል ከዚህ ባለፈም ድሉ በኢትዮጵያ ሕዝቦች መካከል ያለው አተረጓጎምም የተለያየ መሆኑን አማራና ኦሮሞን ምሳሌ በማድረግ ለማስቀመጥ ይሞክራል፡፡ ለአንዳንዶች ድሉ የነፃነት ቀንና የእንቢ አልገዛም ባይነት ድል ነው፣ ለሌሎች ግን ድሉ የጭቆናና የበደል ታሪክ ምዕራፍ መጀመርያ ነው ይላል፡፡

የአወል ጽሑፍ በዓድዋ አከባበር ላይ የሚነሱ ውዝግቦችን የበለጠ ለጥጦ የሚያሰፋ፣ በራስ የስሜት ብይን ላይ የተመሠረተ ቢሆንም እንኳን ችግሩን በተመለከተ ውይይት ለመጀመርና መፍትሔ ሊሆኑ የሚችሉ ሐሳቦችን ለመለዋወጥ መነሻ እንደሚሆን ነው የሚገመተው፡፡

በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ሃይማኖት ዓለማየሁ እንደሚናገሩት፣ የዘንድሮን የዓድዋ ድል አከባበር በበላይነት የሚመራው የመከላከያ ሚኒስቴር ነው፡፡

‹‹በመከላከያ ሚኒስቴር ሥር የሚመራ በብሔራዊ ደረጃ ዓብይ ኮሚቴ ተቋቁሟል፡፡ በዚህ ኮሚቴ ውስጥ የእኛም ሚኒስቴር አባል ሲሆን ኤግዚቢሽን፣ የፓናል ውይይትና ሌሎች የበዓል አከባበር መርሐ ግብሮችን አዘጋጅተናል፡፡ በዓሉ ወጥ ሆኖ በአገር ደረጃ መከበር አለበት ስለተባለ አከባበሩን በበላይነት የሚመራው መከላከያ ሚኒስቴር ነው፤›› ሲሉ ኃላፊዋ አብራርተዋል፡፡

ለክብረ በዓሉ መድፍ መተኮስና የዓድዋ ድልድይን ወጣቶች፣ አርበኞችና የሚመለከታቸው አካላት በጋራ የሚሻገሩበት መርሐ ግብር የዕለቱ ቀዳሚ ሥነ ሥርዓቶች መሆናቸውንም አክለዋል፡፡ በሌላ በኩል በፒያሳው የዳግማዊ ምኒልክ አደባባይ የአበባ ጉንጉን የማኖር ሥነ ሥርዓት እንደሚካሄድ የገለጹት ወ/ሮ ሃይማኖት፣ ‹‹ዋናው የዕለቱ የአደባባይ በዓል አከባበር ሒደት ግን በመስቀል አደባባይ ነው የሚሆነው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹የ127ኛው የዓድዋ ድል በዓል ለአገራዊ አንድነት፣ ጀግንነትና ፅናት መልህቅ›› በሚል ርዕስ፣ መከላከያ ሚኒስቴር የዘንድሮውን የዓድዋ በዓል አከባበር መርሐ ግብር አስመልክቶ ያዘጋጀው ዕቅድ ጠቃሚ ጉዳዮችን ያወሳል፡፡

‹‹አሁን የምንገኝበት ሁኔታ ከዓድዋ ብዙ ነገሮችን ለመማር የምንገደድበት ወቅት ነው፡፡ ዓድዋ ላይ ድል የተመታው የቅኝ ግዛት አስተሳሰብ ብቻ ሳይሆን የዘረኝነት አስተሳሰብ ጭምር ነው፡፡ ድል የተመታው ደግሞ በሰው ልጅ እኩልነት፣ ነፃነትና ክብር አምነው በአንድነት በቆሙ የኢትዮጵያ ውድ ልጆች መስዋዕትነት ነው፡፡ አሁን የምንገኝበት ወቅትም ኢትዮጵያውያን ከምንጊዜውም በበለጠ አንድነታችንን በማጠናከር፣ ከፋፋይ የፖለቲካና የዘረኝነት አስተሳሰቦችን ድል እንድንመታ የሚያስገድድ ነው፤›› በማለት በሰፊው ያትታል፡፡ የመከላከያ ሚኒስቴር የክብረ በዓል ዕቅድ 127ኛው የዓድዋ ድል አንድነትን የበለጠ ለማጠናከር እንዲውል ታሳቢ ያደረገ ዕቅድ መሆኑንም ያስረዳል፡፡

ይሁን እንጂ የዓድዋ ድል ቀን ዓመት ቆጥሮ በመጣ ቁጥር የፖለቲካ ውዝግብ መደጋገሙን ማስቀረት ስለሚቻልበት ሁኔታ ግን የመፍትሔ አቅጣጫ የለም፡፡

በዋናነት የዓድዋ ድል በተመዘገበ በሰባተኛ ዓመቱ የዓድዋ ድል መታሰቢያ በዓል መከበር እንደጀመረ ይነገራል፡፡ በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ደግሞ በአዋጅ ጭምር የወጣ ብሔራዊ በዓል እንዲሆን መደረጉ ይታወቃል፡፡

በደርግ ዘመነ መንግሥት በ1967 ዓ.ም. በወጣው የብሔራዊ በዓላት አዋጅ ላይ ዓድዋ ተካቶ ነበር፡፡ የበዓሉን አከባበር በተመለከተም ዝርዝር ድንጋጌዎች አካቶ የቀረበ በመሆኑም ይጠቀሳል፡፡

የማለዳው የመድፍ ተኩስ፣ እንዲሁም የአበባ ጉንጉን ማስቀመጡና የማርቺንግ ባንድ ትርዒቱ ሁሉ የበዓሉን አከባበር በተመለከተ የተቀመጡ መደበኛ መርሐ ግብሮች እንደሆኑ ይነገራል፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ የዓድዋ አከባበርን በሕግና በሥርዓት የመምራት ሙከራዎች በተለያዩ መንገዶች ተፈጻሚነት አጥተው ነው የኖሩት፡፡

ዛሬ ላይ በአከባበር መርሐ ግብሮች የሚነሱ ውዝግቦችና የፖለቲካ ቁርሾዎችን ለመፍታት፣ በዓሉ በሕግና በአዋጅ ተሻሽለው በሚዘጋጁ መርሐ ግብሮች እንዲመራ የሚጠይቁ ድምፆች እየጎሉ መጥተዋል፡፡

ባለሥልጣናት በፈለጉትና የፖለቲካ አመራሩ ባሻው ወቅት የሚቀያይሯቸው የዘፈቀደ መርሐ ግብሮች ሳይሆን፣ ሕጋዊ የአከባበር ሥርዓት ይበጅለት የሚለው ሚዛን እየደፋ የመጣ አስታራቂ ሐሳብ እየሆነ ነው፡፡

በሌላ በኩል መንግሥት ወይም የፖለቲካ አመራሩ የሲቪል ብሔራዊ በዓላት አከባበሮችን ለራሱ የፖለቲካ ትርፍ ለማዋል መሞከሩ ዋና የችግር ምንጭ ነው እየተባለ ይተቻል፡፡

ኅብረተሰቡ ያለ ማንም ቅስቀሳ በራሱ ፍላጎትና ተነሳሽነት ተሰባስቦ በድምቀት ሊያከብራቸው የሚችሉ ብሔራዊ በዓላትን መንግሥት ‹የእኔ ካልሆኑ› ብሎ ሙጭጭ ማለቱ፣ የፖለቲካ ውዝግብ ምንጭ ሆኗል በሚል ይወሳል፡፡

ኢሕአዴግ ሥልጣን ሲለቅ የግንቦት ሃያ አከባበር እንደደበዘዘው ሁሉ፣ ከዚያ ቀደም ሲል ይከበሩ የነበሩት የአብዮትና የዘውድ በዓላትም ሲከስሙ በኢትዮጵያ ታሪክ መታየቱን አንዳንዶች በምሳሌነት ያቀርባሉ፡፡

የዓድዋ ድልን መንግሥታት የራሳቸው ዓላማ ማስፈጸሚያ መርሐ ግብር የማድረግ ትግላቸውን አቁመው ኅብረተሰቡ በራሱ ፈቃድና ፍላጎት የሚያከብረው ብሔራዊ በዓል እንዲሆን ካላደረጉት በስተቀር፣ የካቲት 23 በመጣ ቁጥር የፖለቲካ ውዝግቡ እንደሚቀጥል ነው ግምታቸውን የሚያስቀምጡት፡፡ ይህ ደግሞ ታላቅ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት የተንፀባረቀበትን ታላቅ የጥቁሮች ድል በዓል የጽንፈኝነት ፖለቲካ ጥላውን እንዲያጠላበት እያደረገ ይገኛል ሲሉ ሥጋታቸውን ይገልጻሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -