- ክቡር ሚኒስትር ባላንጣዎቻችን የእኛኑ ስልት መጠቀም የጀመሩ ይመስላል።
- እንዴት? ምን አዲስ ነገር ተፈጠረ?
- እስከዛሬ እኛ የምንሰጣቸውን አጀንዳ ተቀባይ ነበሩ። በዚህም በውስጣቸው ልዩነትንና አለመግባባትን መትከል ችለን ነበር።
- አሁን ምን ተፈጠረ?
- ያልጠበቅነውን አጀንዳ ወደ እኛ ሜዳ ወርውረዋል።
- ምን አደረጉ?
- የድርቁን ጉዳይ ወርውረው አጋልጠውናል።
- ታዲያ ምን ይሻላል ትላለህ?
- ችግሩ በጣም አስከፊ ስለሆነ መፍጠን አለብን።
- ምን ያህል አስከፊ ነው?
- ክቡር ሚኒስትር ከሦስት ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ችግር ውስጥ ነው። በተለይ ደግሞ…
- በተለይ ምን?
- በተለይ በቦረና ዞን ያለው ሁኔታ አስከፊ ነው።
- እንዴት?
- በድርቁ ምክንያት ከ3.8 ሚሊዮን በላይ ከብቶች ሞተዋል።
- ግን እኮ ድርቅ ከተከሰተ ከብቶች መሞታቸው አይቀርም።
- ቢሆንም ክብር ሚኒስትር እነዚህ ከብቶች ለአርብቶ አደር ማኅበረሰባችን ህልውና መሠረት ናቸው።
- እሱ መች ጠፋኝ?
- ድርቁ አስከፊ መሆኑን እንዲገነዘቡ ብዬ ነው የችግሩን መጠን በአኃዝ ያቀረብኩት ክቡር ሚኒስትር።
- ይገባኛል። እና ምን መደረግ አለበት ነው የምትለው?
- ክቡር ሚኒስትር ሌሎች ፕሮጀክቶችን ለጊዜው ገታ አድርጎ በጀቱን በማዘዋወር ዜጎችን መታደግ አለብን።
- ለጊዜው ገታ የምናደርገው ፕሮጀክት የለንማ። ሁሉም አስቸኳይና አንገብጋቢ ናቸው።
- ለስድስት ወራት መዘግየት የሚችሉ አንድ ሁለት ፕሮጀክቶች አይጠፉም። እንደዚያ አድርገን የሰው ሕይወት ብንታደግ ይሻላል ክቡር ሚኒስትር።
- የምናዘገየው ፕሮጀከት የለም እያልኩህ? እስኪ ንገረኝ የትኛው ፕሮጀክት ነው መዘግየት የሚችለው?
- ለምሳሌ የቤተ መንግሥት ግንባታውን ለተወሰኑ ወራት ማዘግየት እንችላለን።
- የትኛውን ቤተ መንግሥት?
- አዲስ የሚገነባውን የጫካ ቤተ መንግሥት።
- ቢቻል ጥሩ ነበር። ግን የሚሆን አይደለም።
- ለምን?
- የለውማ! አልተያዘለትም።
- ምን?
- በጀት!
- እና በምን ገንዘብ ነው እየተገነባ ያለው?
- ምርመራ እያደረክብኝ ነው?
- ኧረ በጭራሽ ክቡር ሚኒስትር!?
- ካልሆነ ኤምባሲዎቹ ጋብዘውሃል ማለት ነው።
- ምን?
- ዕራት!
- በጭራሽ ክቡር ሚኒስትር። እንዴት በዚህ ይጠረጥሩኛል?
- ምን ላድርግ ታዲያ?
- እንዴት?
- የማይነካ ነካሃ!
- እኔማ መፍትሔ ይሆናል ብዬ አስቤ ነው። ታዲያ ምን እናድርግ ይላሉ ክብር ሚኒስትር?
- አንድ መፍትሔ አለኝ።
- ጥሩ። ምንድነው?
- ባለሀብቶችን ማንቀሳቀስ አለብን።
- የትኞቹን ባለሀብቶች?
- አብረውን የሚሠሩ ባለሀብቶችን።
- ጥሩ ሐሳብ ነው።
- በተጨማሪም የተወረወረውን አጀንዳ በፍጥነት ማምከን አለባችሁ።
- እንዴት አድርገን እናምክነው?
- ሁሉም የመንግሥት ሚዲያዎች ስለድርቁ እንዲዘግቡ ይደረግ።
- ምንም ነገር መደበቅ የለበትም?
- መደበቅ አያዋጣም። ግን አንድ ነገር መዘንጋት የለበትም
- ምን ክቡር ሚኒስትር?
- የሞተ ሰው የለም!
- Advertisment -
- Advertisment -