አፍሪካ 118 የተሰኘ ተቋም አንድ መቶ አሥራ አምስት (115) መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን ወደ ዲጂታል ገበያ የሚሸጋገር ፕሮጀክት ይፋ አደረገ፡፡
ፕሮጀክቱ ኢንተርፕራይዞች በዲጂታል አማራጮች አማካይነት ምርታቸውን ለገበያ እንዲያቀርቡና እንዲያስተዋውቁ የሚያግዝ መሆኑን የካቲት 21 ቀን 2015 ዓ.ም. በፕሮጀክቱ ማስጀመርያ ላይ ተገልጿል፡፡
የአፍሪካ 118 ፕሮጀክት ማናጀር አቶ ናኦድ ኢዴሳ፣ ኢንተርፕራይዞቹ ምርትና አገልግሎታቸውን በዲጂታል ማርኬቲንግ አማካይነት እንዲያስተዋውቁና እንዲያቀርቡ የሚያደርግና ያላቸውን ክህሎት የሚያሳድግ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ኢንተርፕራይዞቹ የዲጂታል ማርኬቲንግን በመጠቀም እንዴት ማደግ እንዳለባቸው የሚያግዝ ሥልጠና ያገኙ ሲሆኑ በግብርና፣ በቆዳ፣ በትምህርትና በሌሎችም ዘርፎች ላይ የተሰማሩ መሆናቸው ተገልጿል፡፡
የፕሮጀክት ማናጀሩ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ትልልቅ ድርጅቶች የዲጂታል ማርኬቲንግ ተሳትፏቸው ዝቅተኛ መሆኑን፣ በዚህም ምክንያት ድርጅቶችን እንደ ጎግል ባለ የበይነ መረብ መፈለጊያ ቴክኖሎጂ በቀላሉ ማግኘት አይቻልም ሲሉ ያለባቸውን ክፍተት ያስረዳሉ፡፡
ይህም የየዲጂታል ገበያ ዙሪያ ተቋሞች የዕውቀት ውስንነት እንዳለባቸው የሚያሳይ ነው ብለዋል። የዲጂታል ማርኬቲንግ ላይ የሚሠራው አፍሪካ 118 በዲጂታል ግብይት ላይ የዕውቀት ውስንነት ያለባቸውን 115 ኢንተርፕራይዞች ለይቶ ክፍተታቸውን ለመሙላት እየሠራ ነው ብለዋል፡፡
ፕሮጀክቱ የተመረጡትን ኢንተርፕራይዞች የገበያ ችግር ለመፍታት ያግዛል ያሉት አቶ ናኦል፣ ይህም ከአገር ውስጥ አልፈው በውጭ ገበያ ላይ ምርታቸውን እንዲያስተዋውቁ ዕድል የሚሰጥ እንደሆነ ገልጸዋል።
ፕሮጀክቱ ለአንድ ዓመት የሚዘልቅ ሲሆን በዚህ ፕሮጀክት የሚሳተፉት 115 ኢንተርፕራይዞች በኦንላይን ገበያ ላይ ያላቸው እንቅስቃሴና ስኬታማነት ተመዝኖ አንዲቀጥል ሊደረግ እንደሚችል የፕሮጀክቱ ማናጀር ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ኢንተርፕይዞች በኅብረት ባንክ አማካይነት ብድር እንዲያገኙ ይመቻችላቸዋል ተብሏል። ኢንተርፕራይዞቹ በፋይናንስ አያያዝ፣ በሞባይል ክፍያ ሥርዓት፣ ሥልጠና ከተሰጣቸው በኋላ፣ በባንኩ መሥፈርት መሠረት አዋጭነቱ ታይቶ የፋይናንስ አቅርቦት እንደሚመቻችላቸው ተጠቁሟል፡፡
የኢትዮጵያ አነስተኛ ብድርና ቁጠባ ተቋማት ማኅበር አማራጭ ፋይናንስ አቅርቦት ዘርፍ ማናጀር ወ/ሮ ሙዋረዲ አብዱራማን፣ በማኅበሩ አስተባባሪነት ከ100 የሚበልጡ መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች በዚህ ፕሮጀክት ድጋፍ እንዲያገኙ ይደረጋል ብለዋል።
የፕሮጀክቱ ዓላማም የመካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን የፋይናንስ አያያዝና የዲጂታል ግብይት ክህሎት እንዲገኙና ካሉበት ደረጃ ከፍ እንዲሉ የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ለዚህም በሥራ ላይ የሚገኙ ኢንተርፕራይዞች እንደተመረጡ የገለጹት ወ/ሮ ሙዋረዲ፣ በማኅበራዊ ድረገጽ፣ በዌብሳይት ላይ ሥራቸውን እንዲያስተዋውቁ የሚደረግ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የዚህ ፕሮጀክት በዋናነት ገበያቸው በውስን ደንበኛና በቦታ ለተገደቡ ኢንተርፕራይዞች ትልቅ ተቀሜታ እንደሚኖረው፣ አለፍ ሲልም ለውጭ ገበያ ራሳቸውንና ምርታቸውን ዕቃ በቀላሉ እንዲያስታውቁ የሚያግዝ ነው ብለዋል፡፡
በአፍሪካ 118 አማካይነት ለኢንተርፕራይዞች የሚሰገውን ሥልጠና የተባበሩት መንግሥታት የካፒታል ልማት ፈንድ (UNCDF) በገንዘብ የሚደግፍ ሲሆን፣ ኅብረት ባንክ ደግሞ በዲጂታል ፋይናንስ የክፍያ ሥርዓት አተገባበር ፕሮጀክቱን ይደግፋል ተብሏል።
ወጣት ዳንኤል ደገሙ የፊደል ቲቶሪያል ተቋም ኃላፊ ነው፡፡ ፊደል ቲቶሪያል ልጆችን በቲቶሪያል የሚያስጠን ተቋም ሲሆን፣ ከትምህርት ቤቶችና ከሕፃናት መንደር ጋር ይሠራሉ፡፡
ከዚህ ቀደም በኦንላይን ራሳቸውንና ሥራቸውን ቢያስተዋውቁም፣ ነገር ግን በተፈለገው ልክ እንዳልሆነ ወጣት ዳንኤል ይናገራል፡፡
ስለዚህ አፍሪካ 118 ፕሮጀክት አካል በመሆን የሚሠሩትን ሥራ በመላው ኢትዮጵያ ለማድረስ አስፈላጊ ሆኖ ማግኘቱን ገልጿል።
እስካሁን ከሰባት ትምህርት ቤቶች፣ ከሁለት የሕፃናት መንደር ጋር ከትምህርት ሰዓት በኋላ የድጋፍ ትምህርት በመስጠት ላይ እንደሚገኙ ጠቁሟል፡፡፡
ከዚህ በተጨማሪ በቴሌግራም፣ በፌስቡክና በሌሎች አማራጮች ቲቶሪያል የሚሰጡ መሆኑን ገልጾ፣ ከዚህ በበለጠ በኦንላይን ማስተማር እንደሚፈልጉ ገልጿል፡፡
ኖጳ ማርና ቡና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ ሌላው በፕሮጀክቱ ከሚደገፉ መካከል አንዱ ነው፡፡ ኢንተርፕራይዙን ወክለው የተገኙት ወ/ሪት ፌቨን ክብረ አብ፣ ለሱፐር ማርኬትና ለሆቴሎች ማርና ቡና እንደሚቀርቡ፣ ነገር ግን በአገር አቀፍ ደረጃ ካለው ፍላጎት አንፃር የንግድ እንቅስቃሴያቸው ትንሽ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በተለይም የዲጂታል ፋይናንስ ሥርዓት መጠቀም፣ ራስን ማስተዋወቅና ገበያ ለመሳብ ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል፡፡
በፕሮጀክቱ አማካይነት በቀላሉ ገበያ ለማግኘትና ለማስተዋወቅ የሚያስፈልጉ የቴክኖሎጂ ውጤቶች አጠቃቀምና አስተዳደር በሚመለከት ብዙ ክህሎት ማግኘታቸውን አስረድተዋል፡፡
አፍሪካ 118 የዲጂታል ማርኬቲንግና ዌብሳይት አበልፃጊ ድርጅት ሲሆን፣ የንግድ ተቋማትን መደገፍ ዓላማ አድርገው ከሚሠሩ ሌሎች ድርጅት ጋር የሚሠራ ተቋም ነው፡፡ ድርጅቱ መቀመጫውን ኬንያ ያደረገ ሲሆን፣ በሌሎች ስድስት የአፍሪካ አገሮችም እየሠራ ይገኛል።
በጋራ ከሚሠሩባቸው ተቋሞች መካከል ጎግል አንዱ ሲሆን፣ Google Digital skills በተሰኘ ፕሮግራም ለአምስት ዓመታት ዘልቋል፡፡