Friday, March 31, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርዓድዋ ሰው አደረገን

ዓድዋ ሰው አደረገን

ቀን:

(ክፍል አንድ)

በያሬድ ኃይለ መስቀል

ከዳርዊን ዝንጀሮ ወደ ሰውነት የተካሄደ ትግል

ስለዓድዋ ስንጽፍ ወይም ስናከብር ዓድዋን እንደ በፀረ ቅኝ ግዛት ተምሳሌነቱ ብቻ አድርገን ነው የምንዘክረው። ዓድዋ ግን እኔም “ሰው ነኝ” የሚል ትግል ነበር። በዚያን ዘመን ቅኝ መግዛትን እንደ ፍትሐዊና ተቀባይ ያደረጉ ትልልቅ ጽንሰ ሐሳቦች ነበሩ። እነዚህ ጽንሰ ሐሳቦችና የውሸት ሳይንሶች ስለነበሩ ነው በዓድዋ ድል የተመቱት።

ይህንን ለመረዳት ለምን ቅኝ ሊገዙን ፈለጉ የሚለውን መጠየቅ ፍንጭ ይሰጣል? ከዚያም በላይ ደግሞ ለምን እንደሚያሸንፉንና ቅኝ እንደሚገዙን እርግጠኛ ሆነው ወረሩን? የሚሉትን ጥያቄዎች ይህ ትውልድ መመርመርና መመለስ አለበት። ቅኝ ግዛት የመጣበት ምክንያት ትልልቅ ሥር የሰደዱ ጽንሰ ሐሳቦች በጊዜው ተቀባይነት ስላገኙ ነበር።

እነዚህም “የሰው ልጆች ሁሉ እኩል አይደሉም”፣ “ጠንካራው ደካማውን አጥፍቶ ምድርን መውረስ የተፈጥሮ ሕግ እንጂ፣ ወንጀልም ወይም ኩነኔም አይደለም” የሚል ፍልስፍና በ19ኛው ክፍለ ዘመን ተቀባይነት ስላገኘ ነበር። ይህ ጽንሰ ሐሳብ ተቀባይነት በነበረው ዘመን ከዝንጀሮ ትንሽ ሻል አድርገው የመደቡት ጥቁሩ ሰው ነጩን በዓድዋ ድል አደረገ።

ጄኔራል ባራቴሪ ወደ ኢትዮጵያ ከመዝመቱ በፊት በሮም ለተሰበሰበው ሕዝብ ንግግር ሲያደርግ “ምኒሊክን ድል እመታለሁ፣ ኢትዮጵያን ቅኝ እገዛለሁ” አይደለም ያለው፡፡ ይልቁንም “ምኒሊክን በፍግርግር ብረት ውስጥ አስሬ ወደ ሮም አምጥቼ አሳያችኋለሁ” ነበር ያለው። ይህንን ሲናገር የሮም መንጋዎች በጭብጨባና በፏጨት ነበር የሸኙት። ምንድነው በፍግርግር ብረት ውስጥ ለሕዝብ ይታይ የነበረው ብለን ስንጠይቅ ሰው ሳይሆን አራዊት ነበር።

ይህ እንደ ዝንጀሮ በፍግርግር ብረት ታስሮ ሊቀርብ የነበረው ምኒሊክ ድል መታ። በማግሥቱ ለሃምሳ ዓመት የተሰበከው ዓለም የቻርልስ ዳርዊን፣ የሄልበርት ስፔንሰር፣ የኤድዋርድ ቴይለር፣ የኧርነስት ፊሊፕና የእነ ፍራንሲስ ጋልተን ሳይንስ መሳይ ትንታኔዎች ውሸት እንደሆኑና ጥቁር ዝንጀሮ ሳይሆን የሚያስብ፣ የሚያቅድ፣ ሐሳቡን በተግባር ለመተርጎም የረቀቀ ስትራቴጂ የሚጠቀምና በተግባርም የሚተረጉም የረቀቀና አሸናፊ ሆኖ ተገኘ። በዓድዋ ድል ጥቁር ጥቁር ዝንጀሮ ሳይሆን ምጡቅ አዕምሮ ያለው ሰው መሆኑን ተቀበሉ። ዓለምም በዓድዋ ድል ተቀየረ። ጃፓኑም፣ ቻይናውም፣ ህንዱም፣ ዓረቡም ነጭን መታገልና ማሸነፍ እንደሚቻል በተግባር አየ። ትግልም ጀመረ።

ከጦርነቱ በፊት “ዝንጀሮ፣ ሳቬጅ፣ አረመኔ” ብለው የጠሩት ምኒሊክ ድል ሲመታ የበላይ ዘር ነኝ ያለው በጥቁር ድል በመመታቱን ለመሸፋፈን፣ እንዲሁም ሌላው ጥቁር፣ ህንድ፣ ቻይናው በቅኝ ገዥው ላይ እንዳይነሳሳ ፈጥነው “ምኒሊክ ትንሽ ከከንፈሩ ወፈር ከማለቱ በቀር ካውኬሽያን (የነጭ ዘር) ነው” ብለው ጻፉ።

ለዚህ ነው ዓድዋ የአዳምን ዘር ሁሉ እኩል ሰው ተብሎ እንዲቆጠር ያስቻለው። እኛ አገር ያላነበቡና ያልተማሩ ካድሬዎች የሰበካቸውን እንደ እግዚአብሔር ቃል የወሰዱ በድንቁርና የጥላቻ ሲኦል ተቀምጠው ቢሰቃዩም ዓድዋ ቻይናውን፣ ጃፓኑን፣ ህንዱና ዓረቡን ሳይቀር ሰው ተብሎ እንዲቆጠር ያስቻለ ድል ነው። አዲሱ ትውልድ አያቱ ዝንጀሮ ተብሎ ተመድቦ እንደነበር አያውቅም። በዓድዋ ድል ምክንያት ነው የፈረንጅ ዩኒቨርሲቲ ሊገባ የቻለው። ይህ ለጉራ ሳይሆን በመረጃ ተደግፎ በዚህ ጽሑፍ ይዘከራል፣ ለልጆቻችሁ አንብቡላቸው።

የዓድዋ ጠቀሜታ

ዓድዋ ለአፍሪካውያን፣ ለቻይናውያን፣ ለጃፓናውያን፣ ለህንዶች፣ እንዲሁም ለምሥራቅ አውሮፓ ዜጎች ሳይቀር ሰው ተብለው እንዲቆጠሩ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል። ከሁሉም በላይ ደግሞ በዳርዊንያን ሳይንስ ከዝንጀሮ ትንሽ ከፍ ብሎ በስድስተኛ የፍጡር ዝርያ ደረጃ ላይ የተመደበው ጥቁር በተግባር በአርያ ሥላሴ የተፈጠረ ምሉዕ ሰው መሆኑን ያሳየበት ዓውድ ነው።

ዳርዊን መጽሐፉን ባሳተመ ዘጠነኛ ዓመት ማለትም እ.ኤ.አ. በ1968 ሔክል የሚባል አንትሮፖሎጂስት በሥዕል አስደግፎ የሰውን ዘር በሰባት ከፋፍሎ መጽሐፍ አሳትሞ ነበር። በዚህ ሥዕል ላይ እንደሚታየው የመጀመርያው ካውኬሽያ ማለትም የጀርመን ፈረንጅ ሲሆን፣ ከዚያ ፈረንሣዩ፣ ጣሊያኑ፣ ግሪኩ፣ ቻይናው ይደረደርና በስድስተኛው ላይ የተቀመጠው አፍሪካዊ ነበር። ማለትም የእኔና የእናንተ ቅድመ አያት፣ ከዚያ ቀጥሎ ያለው ማለትም  ሰባተኛው ዝንጀሮ ነበር። ዝንጀሮ መጀመርያ የእኛን ቅድመ አያት ሆነ፣ ከዚያ ቻይና፡፡ ከዚያ በዳርዊን አዝጋሚ ለውጥ ነጭ እየሆነ መጣ። ቀለሙ ብቻ ሳይሆን የተቀረው ከፍሬ ለቀማና ውኃ ፍለጋ ከፍ ብሎ ምናባዊ ሐሳቦችን የማስተናገድ አቅምና አዕምሮ እያገኘ መጣ ነው ሳይንስ የተባለው።

ዓድዋ ሰው አደረገን | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

እኔ ዓድዋ ሰው አደረገኝ ስል በማጋነን ሳይሆን በመረጃ ነው። በዓድዋ ጦርነትና በጦርነቱ ማግሥት የነበሩትን ጽሑፎችንና መረጃዎችን በማመሳከር ነው፡፡ እኛ አገር የራሳችንን ማቃለልና የፈረንጅን ማድነቅ በዘመናዊ ትምህርት ተቀምሞ ስለተጋትነው ስለራሳችን፣ ስለአያቶቻችን ገድል ስናወራ እንሸማቀቃለን። ይህንን ሰብረን ካልወጣን ለልጆቻችን የበታችነት ሥነ ልቦና ነው የምናወርሰው። የዓድዋን 127ኛ ዓመት ስናከብር እንደ ድሮው የዓድዋ ድል ከአፍሪካ ሕዝብ የነፃነት ትግል ጋር ብቻ አያይዘን ማየት የለብንም። ዓድዋ ከዚያ በላይ ነው።

ዓድዋ የህንዱም፣ የቻይናውም፣ የቬትናሙም፣ የምሥራቅ አውሮፓም፣ የአይሪሹም ሰው ሆኖ እንዲታሰብና ሰዎችን በፍጥረታቸው የበላይና የበታች አድርጎ ያሳመነውን “የማኅበራዊ ዳርዊንዝም” ሥነ ልቦና መሠረት እንደ ናደ እያሰብን በመረዳት ነው። ለምን እንዲህ ትላለህ የሚል ጥያቄ ከተነሳ ከዓድዋ በፊት ለ100 ዓመት ገደማ ተገኙ የሚባሉትን ትልልቅ የሳይንሳዊ ግኝቶችን፣ የፍልስፍና፣ የሥነ ልቦና ጠበብት ጽሑፎችን ብናይ የሰው ልጆችን በደረጃ የከፋፈለ ነበር።

ነጭ አውሮፓውያን ማለትም እንግሊዙን፣ ጀርመኑን፣ ኖርዲኮችን እንደ ምርጥ ዘር ሲቆጥር፣ እነ አየርላንድን ደግሞ ሊሠለጥኑ የማይችሉ አረመኔዎች (Barbarians) ብሎ ሲመድብ በምሥራቅ ያሉትን ነጮች ደግሞ ስላቪክ (Slavic) የሚባሉትን ግማሽ ሰው (Subhumans) ብሎ፣ ከዚያ ወደ ቻይና ሲሄድ ይወርድና በመጨረሻ አፍሪካውያንን በሰውና በዝንጀሮ መሀል ይመድባል። ይህ ደግሞ እ.ኤ.አ. በ1859 የዳርዊን አዝጋሚ ለውጥ (Evolutionary Theory) መሠረት ላይ ነው። እስከ ዓድዋ እ.ኤ.አ. 1896 ድረስ መረን የለቀቁ የሳይንስና የፍልስፍና ጽሑፎች ተጽፈው አውሮፓን አሳምነው ነበር። እስቲ ስድስቱን ብቻ እንጥቀስ።

፩:  ቻርልስ ዳርዊን (1809-1882) ሁለት ትልልቅ የሥነ ሕይወት ምርምር (Biology) መጻሕፍት አሳተመ። የመጀመርያው “የፍጥረታት አመጣጥ” (On the Origin of Species 1859) ነው። ከዚያም ቀጥሎ “የሰው ልጅ አመጣጥ” (Descent of Men 1871)፡፡ እነዚህ የዳርዊን ጽሑፎች ሁሉም ፍጡር በፉክክር በራሱ እየተመራረጠ ተቀይሮ እዚህ የደረሰ እንጂ አልተፈጠረም ይላል (Natural Selection)። ይህም በፉክክር ጠንካራው ዘሩ እንዲባዛ ደካማውን እያጠፋ የመጣ ነው አለ። ይህም በህርበርትና በስቴንሰር ተስፋፍቶ በማኅበራዊ ሳይንስ ጠንካራው ደካማውን ያጠፋል (Survival of the Fittest) የሚለውን አስተምህሮ ተከለ። ማለትም ጠንካራው ደካማውን ማጥፋት የተፈጥሮ ሕግ እንጂ የክፋት አይደለም ተብሎ ተቀባይነት እንዲያገኝ አደረገ።

ዳርዊን ከዚህም አልፎ በሰዎች መካከል ትልቅ ልዩነት እንዳለና የሠለጠነውና ጠንካራው ዘር ያልሠለጠነውን “ኋላቀር” በማጥፋት ዓለምን መውረሱ የተፈጥሮ ሕግ ነው አለ። የሚከተለውን በእንግሊዝኛ እንደ ወረደ ለመጻፍ የተገደድኩት ሰው ላያምን ይችላል ብዬ ስለሠጋሁ ነው። ዳርዊን በቅርብ ጊዜ ውስጥ የነጭ ዘር ጥቁሩን እንደሚያጠፋ እርግጠኛ ነኝ ብሎ፣ “At some future period, not very distant as measured by centuries, the civilized races of man will almost certainly exterminate, and replace the savage races throughout the world”.

ምክንያቱም ይላል ጥቁሩ ብዙም ከዝንጀሮ አይርቅም “Some, In Fact, Were Pretty Much at the Same Level as Apes” ብሎ ጻፈ። እንዲያውም ይላል እነዚህ ኋላቀር ማለትም ጥቁሮች (Savage) የሚወዱት ደማቅ ቀለምና ከበሮ እንጂ ውስብስብ ጽንሰ ሐሳብ የመቀበል አቅም የላቸውም አለ። የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ዳርዊንን መተቸት ሳይሆን የዓድዋን ጠቀሜታ ለማሳየት ስለሆነ፣ በዚህ ሐሳብ ላይ ተመሥርተው የተጻፉትን የፍልስፍና፣ የሥነ ልቦና፣ የፖለቲካና የወታደራዊ እምነቶችን እንይ፡፡

፪: በዚሁ ዘመን የኖረው ሰር ኤድዋርድ ቴይለር (1832-1917) እንግሊዛዊ አንትሮፖሎጂስትና የባህላዊ አንትሮፖሎጂ መሥራች ነበር። ፕሪሚቲቭ ባህል (Primitive Cultural) በሚለው መጽሐፉ ውስጥ የሰውን ልጅ በሦስት ይከፍለዋል። እነዚህም “Civilized, Barbarians and Savages” ማለትም በዘመናዊው በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ውስጥ እንደተካተተው “ብሔር”፣ “ብሔረሰቦች” እና “ሕዝቦች” እንደ ማለት ነው።

ባህልና ሥልጣኔ ያለው (Civilized) ብሔር ሲሉት ከዚያ መሀል ላይ ያለውና የራሱ ሥልጣኔ የሌለው አረመኔ (Barbarians) ወይም ብሔረሰቦች ሲሉ፣ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ያለውና ከተፈጥሮ ጋር የተቆራኘውን ደግሞ ሕዝብ (Savage) ብለው ነበር የከፋፈሉት።

እንግዲህ ይህ ትልቁ የዘረኝነትና የማበላለጥ ፍልስፍና ነው በጄኔራል ዊንጌት አዳሪ ትምህርት ቤት በማር ተለውሶ ለኢትዮጵያ የተማሪዎች ንቅናቄ የተሰጠው። ይህንን እንደ ዕውቀት ቆጥረው ስድብን እንደ ሙገሳ ሕገ መንግሥት ያደረጉት። ኢትዮጵያ ውስጥ ብሔር ተብለው የተመደቡት አማራ፣ ትግሬና ኦሮሞ ሲሆኑ፣ ደበብ እንዳለ አረመኔ የሚል ስያሜ ነው የተሰጠው። የጉራጌ፣ የጋሞ፣ የሃድያ ባህል ከኦሮሞና ከአማራ በምን እንደሚያንስና አንደኛው የአረመኔ የሌላው ደግሞ የሥልጡን ተብሎ በሕገ መንግሥት እንደፀደቀ ማንም አያውቅም። እነ አቶ መለስ፣ ሌንጮ ለታ፣ በረከት ስምኦን አወቅን ብለው የዘረኞችን ፍልስፍና ግተውናል። “ትንሽ ዕውቀት አደገኛ ነው” የሚባለው ለዚህ ነው።

፫: ሦስተኛውና ትልቁ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሄርበርት ስፔንሰር (1820-1903) ይባላል። በዳርዊን ላይ ተመሥርቶ “ማኅበራዊ ዳርዊንዝም” (Social Darwinism) የሚለውን ሀተታ ማምጣቱ ብቻ ሳይሆን፣ “ጠንካራው የሰው ዘር ደካማውን የሰው ዘር በማጥፋት የራሱን ዘር ማስቀጠሉ የተፈጥሮ ሕግ ነው አለ። እንዲያውም ለመጀመርያ ጊዜ “Survival of the Fittest” የሚለውንና ዛሬ ሁሉም የሚደጋግመውን ዓረፍተ ነገር የቀመረው እሱ ነበር።

በአውሮፓ ይኖር የነበረውን ክርስቲያን “ሁሉም ሰው ከአዳምና ከሄዋን መጣ” ብሎ ያምን ነበር። ይህንን የክርስትና አስተምህሮ የተቀበለ ሁሉ የሰውን ዘር እኩልነት አልቀበልም አይልም ነበር። ይሁንና ይህንን የክርስትና፣ የጁዳይዝምና የእስልምና አስተምህሮ በተሳሳተ ሳይንስ የናደው ዳርዊን ነው። አውሮፓውያን ሰው ሁሉ “በአርያ ሥላሴ” አምሳል  የተፈጠረ ነው የሚለውን እርግፍ አድርገው ትተው ከዝንጀሮ መጣ ብለው ሲቀበሉ፣ የዝንጀሮው የቅርብ አጎት ነው ብለው የመደቡትን ጥቁር በንቀትና በመጠየፍ ለማየት ተገደዱ። ይህ አስተሳሰብ ከዳርዊን በፊት አለመኖሩን የሚያሳዩ ከ12ኛ ክፍለ ዘመን እስከ ዳሪዊን ድረስ የነበሩትን ጽሑፎች ማየት ይጠቅማል።

ለምሳሌ ከዳርዊን በፊት የነበረው ሼክስፒር (1582-1616) ጥቁሩን ኦቴሎን የተከበረ ገጸ ባህሪ ሰጥቶ ነበር የቀረፀው። ከዳርዊን በኋላ ቢሆን ኖሮ ይህ ጥቁር ከነጯ ልጃገረድ ጋር በፍቅር አያስተሳስርም ነበር። ሳሙኤል ጆንሰን (1709-1784) ራሴላስ የአቢሲኒያው ልዑል ብሎ የሚያምር ልብ ወለድ ስለኢትዮጵያ ጽፏል። በጣም የተወደደ ድርሰትና ኢትዮጵያን በጣም ያማረች፣ ሕዝቡ የሠለጠነ፣ ታሪኩም ያማረና ዕውቀትን የሚሻ አድርጎ ነው የሳለው። ጆንሰን እ.ኤ.አ. በ1759 ነው ይህንን ድርሰት የጻፈው። ይህ ማለት ከዳርዊን አንድ መቶ ዓመት በፊት ነበር። ዳርዊን ጥቁሩን ዝንጀሮ ካለው በኋላ ቢሆን ኖሮ ይህ ልብወለድ የተጻፈው የጥቁር ሥልጣኔ አለ ብሎ አይቀበልም ነበር። ዳርዊን የአዳም ልጅ ነው የሚለውን ደምስሶ የሰውን ዘር በደረጃ እንዲደረድር ነው በር የከፈተው። ይህም በሳይንስ የተደገፈ። ይህም ሳይንሳዊ ዘረኝነትን (Scientific Racism) ወለደ። ይህ ነው ዓድዋ ላይ የቆሰለው።

፬: ሌላው አደገኛ ሳይንስ መሳይ ዘረኝነትን በዳርዊን ላይ ተመሥርቶ የመጣው ሰር ፍራንሲስ ጋልተን (1822-1911) ነው። ይህ ሰው የዳርዊን ዘመድ ነበር። የዳርዊን ዘመዶች ሀብታሞች ነበሩ። ስለዚህ ዘረኝነቱን ወደ እንግሊዝ ውስጥ አመጣው። ገዥው መደብ በሥራ፣ በትምህርት፣ ዓለምን በማስተዳደር፣ በውትድርና ተጠምዶ ቶሎ አያገባም ብዙም ልጅ አይወልድም፣ ይልቁኑም ጭሰኛውና ደሃው ዘገምተኛ አዕምሮ ያለው ከመራባት በቀር ሌላ ሥራ የለውምና ይኼ ደግሞ የጠንካራው ደም እየበረዘ የተሻለ ሰው እንዳይፈጠር ያደርጋል ብሎ ሠጋ። መፍትሔ ያሻዋል አለ። ስለዚህ ዬጄኒክስ (Eugenics) የሚለውን ሐሳብ አስተዋወቀ።  ይህ ማለት ደካማው፣ ወንጀለኛው፣ አካለ ጎደሎው፣ አዕምሮው የታመመው እንዳይራባ ማኮላሸት ወይም ሲወለድ መግደል፣ ንፁህና ጠንካራው የኖርዲክ የአርያን ነጭ ዘር ደም ቀጥኖ ደካማ ዝርያ እንዳይፈጠር ያደርጋል ብሎ አሳመነ።

ይህም ትልቅ ተቀባይነት አገኘ። በአሜሪካም 30 ግዛቶች ውስጥ ሕግ ሆነ። ገና ልጅ ሲወለድ ለዶክተሮቹና ለነርሶቹ የመግደል ሥልጣን ሰጠ። በየማደጎው ያሉትንም ከ70 IQ በታች ያመጡትንም ልጆች ዘር እንዳይተኩ ማኮላሸት ተፈቀደ። በአሜሪካ ይህን ሕግ ተከትሎ እስከ 1940ዎቹ ድረስ ከ60 ሺሕ በላይ ዘር እንዳይተኩ ተኮላሽተዋል። በተለይ በካሊፎርኒያ ግዛት ከ20 ሺሕ በላይ ልጆች ተኮላሽተዋል። በቨርጂንያ ደግሞ 8,300፡፡ ሒትለር ወደ ካሊፎርኒያ ሰው ልኮ ይህንን ነገር አስተምሩኝ እንዴት እንደሚቻል መጽሐፉን ስጡኝ ብሎ ብዙ ሚሊዮን ሕዝብ ደም በማጥራት ስም ገደለ። የጀርመንንም ልጆች አዕምሮ ሕመምተኞችን፣ የአካል ጉዳት ያለባቸው ደካሞች ልጅ እንዳይወልዱ ተኮላሹ። ይህን አሰቃቂ ወንጀል ከፈጠረ በኋላ ይህን ልዩ ገዥ ዘር የመፍጠር ዕብደት ቆመ።

፭: ለዳርዊን መነሻ ሐሳብ የሆነው ደግም ቶማስ ማልትስ (Thomas Robert Malthus) የሚባለው ነው። ማልቱስያን ሀተታ (Malthusian Theory) ነው። ይህም የሰው ልጅ መራባት ፈጣን ሲሆን፣ የምድር የምግብ የማብቀል አቅም ደግሞ አዝጋሚ ነው ይልና የሰው ልጅን መባዛት ከምግብ አቅም በላይ ሲያልፍ፣ ሰዎች በጦርነት ወይም በረሃብ መጨራረሳቸው አይቀሬ የተፈጥሮ ሕግ ነው ይላል። ይህ ፍልስፍና ነው የወሊድ ቁጥጥርንም ያመጣው።

፮: ሌላው ትልቅ ተፅዕኖ ፈጣሪን ፍሬዴሪክ ኒቼ (Frederic Nietzsche 1844-1900) የሚባለው የጀርመን ፈላስፋ ነው። ኒቼ “እግዚአብሔር ሞቷል” አለ። (God is Dead)። ይህ ማለት ለደካማ ማሰብ፣ ሞራል፣ ሃይማኖት የደካሞች መጠለያ እንጂ የተፈጥሮ ሕግ አይደለም ለማለት ነው። እንግዲህ የእነዚህ ሁሉ የሳይንስና የፍልስፍና እምነት ውጤት ነው ቅኝ ገዥነትን፣ ዘር ማጥፋትን ፍትሐዊ ተቀባይነት እንዲኖር ያደረገው። ይህ አስተሳሰብ ነው ዓድዋ ላይ ተፈትኖ የተሸነፈው።

ይህ ዝንጀሮ ያሉት ዓድዋ ላይ ሰው ሆኖ ሰው አገኙት። የሚያስብ፣ ሐሳቡን በተግባር ለመተርጎም የሚተባበርና እንደ አንድ ማሽን ተደጋግፎ የሚሠራ፣ ለነፃነቱ፣ ለሃይማኖቱ፣ ለርስቱ፣ ለሚስቱ፣ ለአገሩ ለወገኑ የሚጨነቅና ለነፃነቱ ዋጋ የሚከፍል። የረቀቀ ወታደራዊ ስለላ የተጠቀመ፣ ጠላትን አታሎ ወጥመድ ውስጥ ያስገባ፣ ወታደራዊ ዕቅድ የነደፈ፣ በድፍረትና በፅናት የጠላቱን እሳት በእሳት እየመለሰ ብቃቱን ያረጋገጠ። ከማንም የሰው ልጅ አንሳለሁ ብሎ የማያስብ። በፈጣሪው በአርዓያ ሥላሴ የተፈጠረና ምሉዕ ፍጡር መሆኑን የማይጠራጠረው የብረት ቆሎ ሆኖ ተገኘ።

ይህ ማሰብ የማይችል፣ ከከበሮና ከቀለም በቀር ሌላ የረቀቀ ፍልስፍና፣ ጥበብ፣ ሳይንስ፣ ሙዚቃ፣ ሊቀበል የማይችል አዕምሮ ያለው የዝንጀሮ አጎት ሰው ሆኖ ተገኘ። ይህ ጥቁር ዘር ፈጥኖ በኢቮሊሽን ተቀይሮ ሰው መሆን ሲገባው ሲንቀራፈፍ አሁን መጥፋቱ ግድ ይላል ብሎ ዳርዊን የፈረደበት በአርያ ሥላሴ የተፈጠረ ሰው ሆኖ ተገኘ። በበርሊን አፍሪካን መቀራመት ስብሰባ እ.ኤ.አ. በ1884-85 ከዓድዋ ጦርነት ከ11 ዓመት በፊት ነበር። ይህ ቅርምት ሲካሄድ ከላይ በዘረዘርናቸውና በዚህ ጽሑፍም መካተት ቦታ የማይበቃን እምነቶች ላይ ቆሞ ነበር። ይህም በሳይንቲስት የተደገፈ ዘረኝነት (Scientific Racism) ላይ ቁጭ ብለው ነበር። የኢትዮጵያ ወጣት ትውልድ ይህንን መርምሮ መረዳትና የዓድዋ የጦርና የጋሻና አጠቃቀም ሳይሆን የፍልስፍና ግጭት መሆኑን ይረዳ።

የዓድዋ ጦርነት ዝንጀሮ ሆኖ መኖርንና ሰው ሆኖ የመገኘት ድል የተገኘበት ትንንቅ ነበር። ዓድዋ በአፄ ምኒሊክ መሪነት ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን ጃፓኑንም፣ አይሪሹንም። ቻይናውንም፣ ህንዱንም ከአርያን ጀርመን እኩል ሆኖ መፈጠሩን ያረጋገጠበት ጦርነት ነበር።  ክብር ለዓድዋ ጀግኖቻችን፣ ክብር ለአፄ ምኒሊክ ፅኑ ሰውነት። ነጭ የበላይ ነው የበታች ነው ሳይሉ እኔም ሰው ነኝ፣ እኔም እንደ እናንተው እጅ እግርና ምጡቅ አዕምሮ አለኝ፣ እንቢ ካላችሁ እገጥማችኋላሁ ብለው ምጡቅ አዕምሮ፣ ምጡቅ ወታደራዊ ዕቅድ፣ ምጡቅ የሆነ ትግበራ ተጠቅመው በዝንጀሮ ማስቀመጫ ይዤ እመጣለሁ ብሎ የታበየውን ባራቴሪ አሯሩጠው፣ መድፉን ጥሎ ሠራዊቱን አስጨርሶ ጣሊያን ገብቶ እንደ ሰው ሳይቆጠር ተዋርዶ ሞተ። ሦስት ጄኔራሎቹን አስገድሎ፣ አራት ሺሕ መኮንኖቹንና ሠራዊቱን አስማርኮ፣ በአንድ ቀን ጦርነት ውስጥ 75 በመቶ ጦሩን አስደምስሶ የጥቁርነትን ሰውነት ዓለም እንዲቀበል አደረገ።

በተግባር ያሳየን ዝንጀሮ ሳንሆን ትልቅ ብልጠት ያለው፣ የረቀቀና የተውሰበሰበ ወታደራዊ ስትራቴጂ ማቀድ፣ መምራትና ድል ማድረግ የሚችል ሰው መሆኑን ያስመሰከረበት ትግል ነው። እንደ ማንኛውም ፍጡር የረቀቀ አዕምሮ ያለው፣ ተኩራርቶ ራሱን አንቱ ብሎ የመጣውን የነጭ ጦር በእነ አውአሎ ዓይነት ስላየች አሳስቶ ወጥመድ ውስጥ አስገብቶ በዓለም ላይ ለመጀመርያ ጊዜ በሁለት አገሮች መሀከል በተካሂደና በግማሽ ቀን የተጠናቀቀ ጦርነት ተብሎ ተመዘገበ።

በዓለም ላይ ለመጀመርያ ጊዜ 75 በመቶ ጦር የተደመሰሰበት የረቀቀ የጭንቅላት ጨዋታ እንደነበረ ዓለም ተረዳ። እነዚህ ዝንጀሮዎች እንደተገመቱት ዝንጀሮ ሳይሆኑ የረቀቀ የበለፀገ አዕምሮ ያላቸውና ዳርዊን እንደተነበየው መጥፋት ዕጣ ፈንታቸው እንዳልሆነ አስመሰከሩ። ቻይናውም፣ ምሥራቅ አውሮፓውያም፣ ህንድም፣ ጃፓንም፣ ሜክሲኮም ድሉን ተመልክተው አሃ ለካ ጥቁር ነጭን ያሸንፋል አሉ። በዚህም ተነሳሳ ተነቃቁ፣ እኛም ሰው ነን አሉ። ጥቁር አሜሪካውያን የአቢሲኒያ ቤተ ክርስቲያን ብለው ራሳቸውን አደራጁ። ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ ፈጣሪ ትዘረጋለች የተባለው የእነሱ እንደሆነም ተረዱ። የደቡብ አፍሪካዎች ኢትዮጵያኒዝም ብለው ተደራጁ። ቬትናሞች አሜሪካኖችን ሲገጥሙ ኢትዮጵያን እያሰቡ ፀኑ።  ነጭን ማሸነፍ እንችላለን አሉ። (ክፍል ሁለት ሳምንት ይቀጥላል)

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የኢንቨስትመንት አማካሪ፣ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ፣ ፖለቲካ፣ ማኅበራዊ ችግሮችና ታሪክ ላይ ጽሑፎችን የሚያቀርቡ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው  yaredhm.yhm@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተወግዘው የነበሩ ሦስቱ ሊቀጳጳሳትና 20 ተሿሚ ኤጲስ ቆጶሳት ውግዘት ተነሳ

_ቀሪዎቹ ሦስት ህገወጥ ተሿሚዎች የመጨረሻ እድል ተሰጥቷቸዋል ​ ጥር 14...

በሕወሓት አመራሮች ላይ ተመስርቶና በሂደት ላይ የነበረው የወንጀል ክስ ተቋረጠ

በቀድሞ የትግራይ ክልል ፕሬዚደንት ደብረጽዮን ገብረሚካኤ,(ዶ/ር)ና ባለፈው ሳምንት በተሾሙት...

[የምክር ቤቱ አባል ላቀረቡት ጥያቄ በተሰጣቸው ምላሽ አቤቱታቸውን ለክቡር ሚኒስትሩ እያቀረቡ ነው]

ክቡር ሚኒስትር እየሆነ ያለው ነገር ትክክል ነው? ምነው? ምክር ቤቱም ሆነ...

የጉራጌ የክልልነት ጥያቄ ትኩሳት

ቅዳሜ መጋቢት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. በጉራጌ ዞን ወልቂጤ...