በተሾመ ብርሃኑ ከማል
ሰሞኑን በቦረና ስለተከሰተው አደገኛ ድርቅና ስላስከተለው ጉዳት ብዙ እየተባለ ነው፡፡ እኔ ደግሞ የድርቅና የረሃብ ታሪካችንን በአጭሩ በማስታወስ፣ ከዚህ ችግራችን ምን መማር አለብን በማለት ይህንን ጽሑፍ አዘጋጅቻለሁ፡፡ ‹‹ረሃብ›› የሚለውን ቃል ስንሰማ ከብዙ ሁኔታዎች ጋር ልናያይዘው እንችላለን፡፡ የተለያዩ አገሮች ሕዝቦችም ስለረሃብ አንድ ዓይነት አመለካከትና ትርጉም አይኖራቸውም፡፡ ከተሜዎችና ገጠሬዎችም እንዲሁ። ሕፃን ይርበዋል፣ ያለቅሳል፣ ሲያለቅስ የሚበላው ይሰጠዋል፡፡ ዝም ይላል፡፡ አዋቂም ባያለቅስም በተወሰነ ጊዜ ምግቡን ካላገኘ ይራባል፡፡ ነገር ግን ከድርቅ ጋር የተያያዘው ረሃብ ከተራው ረሃብ ይለያል፡፡
የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ የድርቅና የረሃብ ሰለባ ከሆኑ ወገኖቹ ጋር በ1955፣ በ1957፣ በ1977 ዓ.ም. በሰቆጣ፣ በኮረም፣ በመቀሌ፣ በአዲስ አበባ እንዳየው… ለአንድ የአገራችን ገበሬ ረሃብ ማለት ዝናብ ባለመጣሉ ምክንያት መሬት የዘሩባትን ሳታበቅል ስትቀር፣ በዚህም ሳቢያ በእረኝነት የተሰማሩ ልጆች በፀሐይ ሐሩር የተቆላውን ከታረሰው ማሳ እየለቀሙ ሲበሉ፣ ወንዞችና ምንጮች የተደፉ ቡሃቃ ወይም ሊጥ የፈሰሰባቸው መስለው ሲደርቁ፣ በጥልቀት ቢቆፈሩ እንኳን እንጥፍጣፊ ሲታጣባቸው፣ ላሞች፣ በጎችና ፍየሎች ወተትም፣ ሥጋም፣ ቆዳም የማይገኝባቸው ሲሆኑ አስቀድመው ግልገሎቻቸው፣ በኋላም ራሳቸው ማለቅ ሲጀምሩ፣ ትንሽ አቅም የነበራቸው የመጨረሻዎቹ እንስሳት በየበረታቸው ውስጥ ጣዕረ ሞት ይዟቸው እየተንፈራፈሩ ሲሞቱ፣ በዚህም ምክንያት በቅድሚያ ከቤተሰብ ደካሞችና በሽተኞች በያሉበት ሲሞቱና በአንድ መንደር ውስጥ በቀን ከአምስት ስድስት ጊዜ በላይ የአቃብሩኝ ልፈፋ ወይም ጥሪ መሰማት ሲጀምር፣ ከዚያም ጠንካሮቹ እየደከሙ ወደ የማይቀረው የዘለዓለም ቤታቸው ሲጓዙና ቀባሪ አጥተው በየቤት ሲቀሩ፣ ቀዬውንና አካባቢውን ትቶ ሕዝብ መሰደድ ሲጀምር፣ ወዘተ ያኔ ረሃብ መጥቷል፡፡
እስቲ ከራሴ ልምድ ላካፍላችሁ፡፡ በ1950 ዓ.ም. አካባቢ በዋግ ኽምራ ዞን ረሃብ ይከሰታል፡፡ የሚሸጥና የሚለወጥ እህል ይጠፋል፡፡ ገበሬ ለራሱም ስላልነበረው ማምጣት አይችልም፡፡ ከትግራይና ከበለሳ እንዳይበደር እዚያም ድርቅ ሆነ፡፡ ትንንሽና ትልልቅ ወንዞች ደረቁ፡፡ የተዘራው የጓሮ በቆሎ፣ አተርና ባቄላ እዚያው ቀረ፡፡ ዱባ አላፈራም አለ፡፡ በሐምሌና በነሐሴ ይበቅሉ የነበሩ ቅጠላ ቅጠሎች ከመሬት ብቅ እንዳሉ ቀሩ፡፡ ፍየሎች በአጭር ጊዜ ውስጥ እከክ ጨረሳቸው፡፡ ሰው እንኳን ሊበላቸው በማያስችል ፍጥነት አለቁ፡፡ ትንሽ ለምልሞ የታየው ዱባም ቢሆን አላፈራ አለ፡፡ ያፈራውም አልፋፋ አለ፡፡ እና ምን ይደረግ? ለጊዜ በቤታቸው የተገኘው ጥፍጥሬ ነበር፡፡ ጥፍጥሬውን እየቀጠቀጡ ከውስጡ ያለውን ነገር እያበሰሉ በሙቅ መልክ መጠጣት፡፡ እሱም ለራት ብቻ ነበር የሚገኘው። ዱባ ከብርቱካን መጠን በላይ ሊጨምር ባለመቻሉ የተቀቀለ መብላት ተጀመረ፡፡
ሌላ ጥሬ ወዳለበት አካባቢ ተኪዶ እንዳይገዛ የሸማኔውን፣ የልብስ ሰፊውን፣ የአንጥረኛውን፣ የማረሻ ሠሪውን፣ የቅመማ ቅመም ነጋዴውን ምርት የሚገዛው ገበሬ ተርቦ ስለነበር ገንዘብ የለም፡፡ ስለዚህ እልቂት ሆነ፡፡ አንገታችንና ከአንገታችን በታች ያለው አካል እንደ ሸምበቆ እየቀጠነ መጣ፡፡ ጎላ ብሎ የሚታየው ጭንቅላታችን ሆነ፡፡ ረሃብ ግን በዚያ ጊዜ ተጀምሮ በዚያው አላበቃም፡፡ ግን ርሃብ ሲይዝ ምን ይመስላል? ከየትኛውስ ጊዜ እንጀምር? ረሃብን ለማታውቁ እነሆ!
የረዥም ዘመኑን ረሃብ ለጊዜው እናቆየውና የዛሬ መቶ ዓመት አካባቢ በኢትዮጵያ ስለደረሰው ድርቅና ረሃብ በተለይም በፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንከረስት መጽሐፍ የሰፈረውን ስንመለከት፣ በኢትዮጵያ ከደረሱት በጣም ትልቅ የድርቅና የረሃብ ዘመናት አንዱ ከ1888-1892 ማለትም አፄ ዮሐንስ በሞቱበት ጊዜ የነበረው መሆኑን እናረጋግጣለን፡፡ በዚህ ጊዜ የነበሩት የሮም ሚሲዮኖች እንደመዘገቡት፣ የአየሩ ሁኔታ ባልተለመደ መልኩ ሞቃት ሆነ፡፡ ይህም የአየር ንብረቱን አዛባው፡፡ እንደ ሰደድ እሳትም መላውን ምድር አጥለቀለቀው፣ የአየር ንብረቱ መዛባት ለሶማሊያና ለደቡባዊ አገሮችም ተረፈ፡፡ በወቅቱ ኢትዮጵያን የጎበኘ ማርቲ የተባለ ግለሰብ ስለድርቁ ሲገልጽም፣
‹‹በቆሻሻ ጨርቅ የተሸፈነ ሬሳ እዚህም እዚያም ወድቆ ይታያል፡፡ በዚያ ሐሩር ፀሐይ ላይ ወድቀው ከሚታዩት አስከሬኖች ክንዶችና እግሮች ላይ ነፍሳት ሲርመሰመሱባቸው ማየት እጅጉን ያሰቅቃል፡፡ በሕይወት ያሉት ሞታቸውን ሲጠባበቁ፣ የሞቱት ደግሞ የሚቀራመቷቸውን ጅቦች ይጠብቃሉ፡፡ በየሥርቻው የሚሰቃይና የሚያቃስት ድምጽ ይሰማል፡፡ ሥጋው አልቆ በቆዳው የተሸፈነ እጅ እስከ መጨረሻዋ ትንፋሽ መውጣት ድረስ አለሁ ለማለት የፈለገ ያህል ይላወሳል፡፡ እዚህም እዚያም ለሞት የተቃረበ ሰው በመጨረሻ እንቅስቃሴ እያጣጣረ፣ ቀስ በቀስ ቀና ብሎ እንደ መቀመጥ ይቃጣውና ሞጭሙጮ እንደ መስታወት በሚብለጨለጨውና ነፍስያ እንደሌለው በሚያስታውቀው ዓይኑ እንደ መማተር ይላል፡፡ የማይሰማ በከንፈሩ ብቻ የሚላወስ ቃል እንደ ማነብነብ ይልና ቀጭን ድምጽ አሰምቶ ዝልፍልፍ ብሎ ይወድቃል፡፡ ከዚያም ጭጭ ይላል፡፡
‹‹በጠኔ የተጎሳቆለች እናት መናገር አቅቷት፣ ሕጻን ልጇን እያወዛወዘች ምስኪን ነኝ፣ ምስኪን፣ እያለች ላመል ያህል በሚሰማ ቆርፋዳ ድምጽ ምፅዋት ትለምናለች፡፡ የእኛን ዕርዳታ የሚፈልጉ ብዙ አፅም የመሰሉ ፍጡራን አጋጥመውኛል፡፡ ምስኪን ነኝ እያሉ እየተውተረተሩ፣ እየተነሱ እየወደቁ ያቅማቸውን ያህል ለመከተል እየሞከሩ ምፅዋት ይጠይቁናል፡፡ ሴቶች እኛን ሲያዩ ጨቅላዎቻቸውን ከመሬት ብድግ አድርገው፣ የደረቀና የሟሸሸ ጡታቸውን በእጃቸው እያሳዩን በለቅሶና በዋይታ እየለመኑ ይከተሉናል፡፡ አንዳንዴ ሊሬ ጣል እናደርጋላቸዋለን፡፡ ነገሩን አሁን ሳስበው፣ ከአንድ ሰዓት በላይ ዕድሜ ለማይኖራቸው ረሃብተኞች ገንዘብ መስጠት ምን ዓይነት ትርጉም የለሽ ሞኝነት ነው እላለሁ። እንዲህ ያለውን ሳይና ከአካባቢው ለመሽሸ ስደናበርም ዓይኖቼ ከግመሎች ዓይነ ምድር ፍራፍሬ እየፈለጉ ከሚለቅሙ ትንንሽ ልጆች ጋር እየተጋጩ እቸገራለሁ፡፡ ከእንዲህ ያለው አስቀያሚ ትዕይንት ለማምለጥ ስሞክር፣ ዘበኞች ከሞተ ፈረስ አጠገብ፣ አሞሮችን ሲያባርሩ እመለከታለሁ፡፡ ልጆቹ ከጅብ የተረፈ የፈረስ አንጀት ለስላሳ ስለሚሆንላቸው በጥርሳቸው ይገዘግዙታል፡፡ በዚህ ጊዜ ከማየት በስተቀር በሰቀቀን ምንም ለማድረግ ባለመቻሌ እየተደናበርኩ ከአካባቢው በረሃ ጥፋ የሚል ግፊት ይመጣብኛል፡፡ የተንጠለጠለውን የኪሴን ሰዓት ወርውር ወርውር ያሰኘኛል፡፡ ጧት የበላሁትን ቁርስና የሚጠብቀኝን ምሳ ሳስብ በራሴ ላይ እፍረት ይሰማኛል፤›› ብሏል፡፡ (ትርጉም መስፍን ሀብተማርያም)
ድርቅና ረሃብ መቼ ተከሰተ? ምንስ ጥፋት አደረሰ?
እንዲህ ያለው ድርቅ የተከሰተው ከ1888-1892 ብቻ አልነበረም፡፡ እንደ ማርቲን ያለ ጸሐፊ አያጋጥመው እንጂ በኢትዮጵያ የረሃብ ታሪክ ማህደር ሰፍሮ እንደምናገኘው፣ ከ1131-1145፣ በ1258፣ በ1261፣ በ1262፣ በ1274 ረሃብና በሽታ ደርሶ ነበር፡፡ ሆኖም መንስዔዎቻቸው እንደ አየር ንብረት መዛባትና ሰው ሠራሽ ችግሮች ሳይሆን እንደ ፈጣሪ ቁጣና አንድም ሕዝቡ ለንጉሦች ባለመታዘዙ ወይም ንጉሦች የተሰጣቸውን መለኮታዊ አደራ ባለመወጣታቸው እንደተከሰተ ተደርጎ ሲጠቀስ ቆይቷል። ስለዚህም ጉዳይ የታሪክ ጸሐፍቱ ሲገልጹ፣
‹‹እግዚአብሔር የረሱትን መንግሥታት በበሽታ፣ በረሃብና በጦርነት ይቀጣል፡፡ እነዚህ መንግሥታት እውነተኛውን እምነትና የተቀደሱ ሕግጋቱን ትተው በሐሰት ስለሚበከሉ የጥፋትንና የእርግማንን መንገድ የሚከተሉ ናቸው›› ይሏቸዋል፡፡
በተለይም ከ1315-1344 በነበረው የአፄ አምደ ጽዮን ዘመን መንግሥት እጅግ አስከፊ ድርቅና ረሃብ እንደነበር ይነገራል፡፡ ይህንንም የድርቅ ዘመን አቡነ አሮን የተባሉ በቤጌምድር የነበሩ ቅዱስ ሰው፣ በአምደ ጽዮንና በሰይፈ አርአድ ዘመነ መንግሥት (113-1372) በተከሰተው ድርቅ፣ ረሃብና በሽታ በመላው ኢትዮጵያ ተስፋፍቶ እንደነበር ያወሳሉ፡፡ ያኔ ከአቡነ አሮን ተማሪዎች ብቻ 1,400 ሞተው ቤተ ክርስቲያኗን ሞልተዋት ነበር፡፡
የደብረ ቢዛን (ትግራይ) ገዳም መነኩሴ የነበሩት አባ ዮሐንስ (በኮንቲሮዝ ግምት ከ1369-1448) ባለው ጊዜ ድርቅ በገዳሙ እንደተከሰተና የገዳሙን መነኮሳት እንደጨረሳቸው ጠቅሰዋል፡፡
በ15ኛው ክፍለ ዘመን የደረሰውን የረሃብ እልቂት በተመለከተ የተጠናከረ መረጃ ባይርም አል-ማግሪቢ የተባለ የአረብ ታሪክ መዝጋቢ፣ በአፄ ዘርአያቆብ ዘመነ መንግሥት (1434-1568) በተለይም ከ1434-6 በነበረው ጊዜ ብዙ ሕዝብ እንደ ፈጀና በመላው አገሪቱ የሕዝብን ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ እንደቀነሰ ዘግቧል፡፡
ከ1508-1540 በነበረው የአፄ ልብነድንግል ዘመን መንግሥትም በዝናብ እጥረት ምክንያት በርካታ ሰዎች አልቀዋል፡፡ ከአፄ ልብነድንግል በኋላም በተለይም በአፄ ገላውዲዮስ ዘመነ መንግሥት (1540-1569) ታይቶ ተሰምቶ የማይታወቅ ቸነፈር ደርሶ ነበር፡፡ በ1611 ማንንትታ፣ በ1683 ለባብል፣ በ1693 ታናካ የተባሉ በሽታዎች ብዙ ሕዝብ ጨርሰዋል፡፡
በአፄ እያሱ ዘመን መንግሥት በተለይም በ1706 የደረሰው ረሃብ፣ የጎንደርን ሕዝብ ከዚህ መቅሰፍት አድነን በማለት ንጉሠ ነገሥቱን እንዲማፀን አድርጎታል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በ1747 እና በ1748 በተከታታይ አንበጣ ሰማዩን እንደ ጉም ይሸፍነው እንደነበርና ይኸም ክፍተኛ ቁጥር ያለው የአንበጣ መንጋ የቆላውንና የደጋውን ሕዝብ ለረሃብ እንዳጋለጠው እንዲሁም ለጉንፋንና ለሌሎችም ብዙ በሽታዎች በመዳረግ ክፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ ከምድረ ገጽ እንዳጠፋ ይታወቃል፡፡
ከ1772/73 በነበረው ዘመን ቀጭኔ የሚባል ረሃብ እንደገባ፣ ከ1750-1769 በምጽዋ በተለይም በሐርቂቆ የተከሰተው ረሃብ ወደ ሌላው የአገሪቱ ክፍል የተስፋፋ ሲሆን ከዚያም ከ1788/89 መላውን ክልል አዳርሶ፣ በ1796 ብዙ ወረዳዎችን አጥፋቷል፡፡ በ1842 ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ የነበረው ቻርልስ ጆንሰን የተባለ እንግሊዛዊ ሐኪም እንደገለጸው፣ ከ1828-29 በሸዋ ውስጥ አሰቃቂ ድርቅና ረሃብ ደርሷል፡፡ በዚህም ጊዜ ጆይ ኤል ክራፍ የተባለ ሚሲዮናዊ፣ ረሃቡ የወሎን ሕዝብ እንደ ቅጠል አርግፎ እንደጨረሰው ዘግቧል፡፡ በ1889 በሸዋ፣ በሶማሌ፣ በከፋና በጅማ – በጥቅምት፣ በኅዳር፣ በግንቦት ብዙ ሰዎችንና ከብቶችን ገድሏል፡፡
ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ቀደም ሲል የተጠቀሰውን ‹‹ዘ ሂስትሪ ኦቭ ፋሚን ኤንድ ኤፒደሚክ ኢን ኢትዮጵያ ፕራየር ቱ ዘ ትዌንቲዝ ሴንቺሪ›› በሚል ርዕሰ ባሳተሙት መጽሐፍ በርካታ የታሪክ መጻሕፍት አጣቅሰው ሲያቀርቡ፣ ፕሮፌሰር መሥፍን ወልደማርያም ደግሞ ከዚያ ቀጥሎ ያለውን የረሃብ ዘመን ‹‹ሩላር ቨልነረብሊቲ ቱ ፋሚን ኢን ኢትዮጵያ›› በሚል ርእሰ ባሳተሙት መጽሐፋቸው በዝርዝር አቅርበውታል፡፡ በመግቢያቸው ላይ ስለረሃብ ምንነት ሲገልጹም፣
‹‹ረሃብ የተመሰቃቀለ ትዕይንትን ይፈጥራል። የሕመም ስቃይ ዝቅተኛ መሆንን፣ ተስፋ መቁረጥንና በአንደበት የማይገለጥ ነገር ግን አጥንት በአጥንት ከሆነ ፊት የሚነበብ ውስጣዊ ብስጭትን ያስከትላል፡፡ ረሃብ ለመሞት የብዙ ወራት ጉዞ የሚደረግበት ነው፡፡ ረሃብ የሚታይ ጭንቀት፣ ሰቆቃና ፍርሃት ነው፡፡ ከሰዎች መካከል የታደሉት አይተውት ይሆናል፡፡ ግን ሞት አፋፍ ላይ ያለው ወይም ከእውነተኛው ሞት ጋር ፊት ለፊት የተጋፈጠው በዕውን የሚያየውን ያህል አይሆንም። የረሃብን ያህል ሰው በሰው ላይ የሚፈጽመውን ኢ-ሰብዓዊነት የሚያጋልጥ የለም፡፡ የባህልና የሃይማኖት ዋጋ ግብዝነትና መመጻደቅ እንደሆነ የሚያሳይም ረሃብ ነው፡፡ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሥርዓት አልበኝነት የሚፈጥርም ረሃብ ነው፡፡
‹‹…ያለፉትን በመቶ የሚቆጠሩ የረሃብ ዓመታት በትዝታ ዓይን እያየን እንለፋቸው እንዳንል የአዲስ አበባ ሕዝብ እንኳን ምንነቱን የማያውቀው ረሃብ ትግራይ ላይ በ1958 ተከስቷል፡፡ በዚያን ጊዜ ረሃቡን የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዳያውቀው ይፈለግ ስለነበር ለቤተ ክርስቲያንም ይሁን ለመስጊድ ማደሻ፣ ለመንገድም ይሁን ለትምህርት ቤት ማሰሪያ… ብቻ ለምን እንደሆነ ለማያውቀው ጉዳይ ግን መዋጮ እንዲያዋጣ ተጠየቀ፡፡ ረሃቡ በገባ በሦስተኛ ዓመቱም በ1961 ላይ የአሜሪካ መንግሥት 7.5 ቶን እህል ሲረዳ መቶ ሺሕ ያህል ሕዝብ አልቆ ነበር፤›› ይላሉ፡፡
ረሃብ ሲከሰት በሽታም ይከተላል፡፡ ያኔ ፈንጣጣ፣ ተስቦ፣ ክፉኝ፣ ወባና ሌሎችም በሽታዎች ምሕረት የለሽ ክንዳቸውን ያሳዩበትና ሕዝብ እንደ ቅጠል የረገፈበት ጊዜ ነበር፡፡ ድርቁ በአንድ አካባቢ ብቻ አልረጋም፡፡ ወደ ሰሜን ወሎ በተለይም ወደ ዋግና ላስታ ተዛምቶ ሕዝቡን በጭካኔ ረፍርፎታል፡፡ ይህ ረሃብ ከሰሜን ወደ ማዕከላዊ አገር ተዛመተ፡፡ ተመሳሳይ እልቂትም ፈጽሞ ወደ ደቡብ ሸዋ ስምጥ ሸለቆ፣ ሐረርጌ፣ ሲዳም፣ ጋሞጎፋ፣ ኢሉባቦር፣ ወለጋ፣ ጎጃም ተስፋፋ፡፡ በ1975/77 ደግሞ በድርቅ ተጠቅተው የማያውቁት አርጆ፣ ባህርዳር፣ ደብረ ታቦር፣ ጨቦና ጉራጌ፣ ሳይቀሩ በረሃብ ተወገሩ፡፡ ምንም እንኳን የአፄ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ረሃቡ በኢትዮጵያ ሕዝብና በዓለም ሕዝብ እንዳይታወቅ ለማፈን ቢፈልግም የሚቻል አልሆነም፡፡ በ121 አውራጃዎች 6,478,760 ማለትም በማዕከላዊ ግምት በየአውራጃው 53,543 ሰዎች ድርቁ ባስከተለው ረሃብ አልቀዋል፡፡ በዚህም ስሌት መሠረት፣ በ20 ዓመት ውስጥ የረሃብ ሰለባ የሆነው ሕዝብ 25,111,887 ይደርሳል፡፡ የመንግሥት መረጃ ደግሞ በ63 አውራጃዎች 263,578 እንደሆነ ያመለክታል፡፡ ይህስ ቢሆን በወቅቱ ደራሽ አጥቶ ታፍኖ ማለቅ ነበረበት?
ድርቅና ረሃብ የሚያስከትሉት ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ቀውሶች
ከአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት በፊት በነበሩ መንግሥታት በፈጣሪ ቁጣ ወይም ነገሥታቱን ባለመታዘዝ ወይም በጥጋብ እንደተከሰተ ተደርጎ ሲወሰድ፣ ለአፄ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ደግሞ መንኮታኮቻ ምክንያት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ነገሩ ‹‹አንበሳን ፈርተው ዛፍ ላይ ቢወጡ ነብር ጠበቃቸው›› እንደሚባለው ሆነ እንጂ የዚያን ሥርዓት ፈላጭ ቆራጭነት ባህርይም የበለጠ ጉልህ አድርጎታል። ድርቅና ረሃብን በተመለከተ ገና በብዛት መጠናትና መጻፍ ያለበት ቢሆንም ከጤና አኳያ ከተነተኑት መካከል አብርሃ ግዛው የተባሉ ምሁር ‹‹ኤኮሎጂ ኦፍ ሄልዝ ኤንድ ዲዝዝ ኢን ኢትዮጵያ›› በሚል ርዕስ ዜይን አህመድ ዜን እና ሄልመት ኩልስ ባዘጋጁት መጽሐፍ (1988) ላይ እንዳሰፈሩት፣ ምንም እንኳን ከአብዮቱ በኋላ የዕርዳታ ማስተባበሪያና ማቋቋሚያ ኮሚሽን ረሃብ ከመድረሱ በፊት የቅድሚያ ጥንቃቄ አገልግሎት እንዲሰጥ ጭምር ቢመሠረትም ረሃቡ እየተባበሰ እንጂ እየተሻሻለ ሲሄድ አልታየም፡፡ እንዲያውም በወሎና በትግራይ የተከሰተው ዓይነት ረሃብ፣ በ1977 በኦጋዴንና በባሌ በተለይ በኤልካሬ፣ በኤሊባቦር፣ በተለይም በቡኖ በደሌ፣ በሰሜን ሸዋ ተስፋፋ፡፡ በ1979 ላይም ከፍተኛ ምርት በማምረት በምትታወቀው በአርሲ፣ በደቡብ ሸዋ፣ በሲዳሞ፣ በጋሞጎፋ ታየ፡፡ በ1981 ምሥራቅ ጎንደር በድርቅ ተመታ። የድርቁ ጥቃት አይሎ በቀጠበለበት በ1984 ላይ የደርግ መንግሥት ከወሎ 367,016፣ ከሸዋ 108,241፣ ከትግራይ 89,716፣ ከምሥራቅ ጎጃም 16.425፣ ከምሥራቅ ጎንደር 6387፣ በአጠቃላይም 600 ሺሕ ሰፋሪዎችን፣ በወለጋ 253,282፣ በጎጃም 101,785፣ በኢሊባቦር 147,915፣ በከፋ 72830፣ እና በምዕራብ ጎንደር 6378፣ አሰፈረ፡፡ ይህ ግን ድርቁና ረሃቡ የሚያስከትሉትን ችግሮች ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሊያስቀር የሚችል ዕርምጃ አልነበረም፡፡
ከ1983 ወዲህ በአገራችን በተደጋጋሚ የርሃብ አደጋ የተከሰተ ሲሆን ከ1983 በፊት እንደነበረው ግን እጅግ ብዙ ሕዝብ አልጨረሰም፡፡ በአሁኑ ጊዜ ግን የወቅቱን ሁኔታ በሚመለከት መንግሥት መግለጫ ባይሰጥም በትግራይ፣ በሰሜን ወሎ፣ በኦሮሚያ በተለይም በባሌ፣ ድርቅ እየተስተዋለ ሲሆን በመጭው ዓመትም የዝናብ እጥረት እንደሚከሰት ይነገራል፡፡ ስለዚህ ነገሩ ከቁጥጥር ውጭ ከመሆኑ በፊት ርብርብ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ነገሩ ያለ ማጋነን አደገኛ መሆኑም ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡
ድርቅና ረሃብን ለማስወገድ ምን መደረግ አለበት?
በመሠረቱ የተፈጥሮ ሰለባ የሆነችው ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን በሳህል በረሃ ውስጥ የሚጠቃለሉት አገሮች በተለይም ሱዳን፣ ናይጀሪያ፣ ማሊ፣ ኡጋንዳ፣ ሞሪታንያና ሌሎችም አገሮች ጭምር ናቸው፡፡ አንድ የጣና በለስ ፕሮጀክት መጽሔት (1985 አትሙ) እንደገለጸው፣ ‹‹በእነዚህ አገሮች በተለይም በ1977 የደረሰው ድርቅ ባስከተለው የረሃብ ቸነፈር በአጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ ሰዎች ሞተዋል፡፡ የችግሩ ስፋትና ያስከተለው አሰቃቂ ጉዳት መላውን ዓለም ያስደነገጠ፣ የበለጸጉ አገሮች እንዲህ ያለው ጥቃት ለሚደርስባቸው አገሮች የሚቻላቸውን ድጋፍ ሁሉ እንዲያደርጉ ያነሳሳና ሥር የሰደደውን ችግር በአንድ ጊዜ ለማስወገድ ባይቻልም እንኳን ቀስ በቀስ ለመቅረፍ ሐሳብ የቀረበበት፤ የአፈር መሸርሸር፣ የአየር መዛባት፣ የተፈጥሮ ሀብት በትክክል ለመጠቀም አለመቻል ቴክኖሎጂያዊና ኢንዱስትሪያዊ እንቅስቃሴ እንዲዘረጋ የታመነበት ጊዜ ሆነ›› ይላል፡፡
አሰፋ ወልደ ገብርኤል የተባሉ ምሑር፤ ‹‹ዘ ኢኮሎጂ ኦቭ ሔልዝ ኤንድ ዲዝዝ ኢን ኢትዮጵያ›› በሚል ርዕሰ በጻፉት መጽሐፍ እንዳቀረቡት፣ ኢትዮጵያ የግብርና አገር ብትሆንም፣ ከሕዝቧ 86 በመቶ የሚሆነው ገበሬ መሆኑ ቢረጋገጥም፣ አገሪቱ በማንኛውም ጊዜ ሊታረስ የሚችል 15.8 ሚሊዮን ሔክታር መሬት እንዳላት ቢታወቅም፣ 69 ሚሊዮን የቀንድ ከብት፣ 62 ሚሊዮን ዶሮ ቢኖራትም፣ ዕድገቷ ዝቅተኛ በመሆኑ እያንዳንዱ ሰው በቂ ምግብ አያገኝም፡፡
ይህም የሆነው እርሻው የሚታረሰው ኋላቀር በሆነ ዘዴ በመሆኑ፣ በክምችት ወቅት በሚደርሰው ብክነት፣ በቂ የመጓጓዣ አገልግሎት ባለመኖሩ፣ ስለጤንነት ጉዳይ ትምህርት ባለመሰጠቱ፣ ስለአመጋገብና ስለቤተሰብ ቁጠባ ባለማወቅ፣ በአንድ በልምድ በተመረጠ እህል ላይ የተመሠረተ አመጋገብ ጋር የሙጥኝ በማለት፣ በተላላፊ በሽታዎች መስፋፋት፣ ምግብ ለመግዛት አቅም በማጣትና ድርቅ በመኖሩ ነው፡፡ እንዲህ ያለውን ችግር ለማስወገድ ጥረት የተደረገ መሆኑን የሚጠቁሙ መረጃዎች ቢኖሩም ውጤቱ የሚያረጋግጠው ግን ለመፍትሔነት አለመብቃቱን ነው፡፡
ይሁንና የኢትዮጵያ በተደጋጋሚ በድርቅ አደጋ የመጠቃት፣ ከዚህም የተነሳ ሕዝቧ ለረሃብና ለእርዛት የመጋለጡ ጉዳይ በእርግጥ የማይፈታ እንቆቅልሽ ነው? ሁኔታዎች ከተመቻቹለት 85 በመቶ የሚሆነው ገበሬ፣ ራሱን ችሎ 15 በመቶ የሚሆነውን ሕዝብ መደገፍ ይሳነዋልን? ብለን መጠየቃችን አልቀረም፡፡ ነገሩ በጣም ውስብስብም ነው፡፡
በመሠረቱ ያለፈውንም ሆነ ያለውን ሥርዓት በየምክንያቱ እየኮነንን መኖር ብቻውን የትም አያደርሰንም፡፡ ሥር የሰደደው ችግራችን የተከሰተው ደጋግሞ በሚያጠቃን ድርቅ ምክንያት ነው፡፡ የአስተራረስ ዘዴያችን በጣም ኋላ ቀር በመሆኑ ነው፡፡ 85 በመቶ ገበሬ ያለጥርጥር 15 በመቶ የሆነውን ሕዝብ መመገብ ይችላል የሚል ሒሳባዊ ስሌትን መሠረት ያደረገ አመለካከት በመስፈኑ ነው፡፡ ይኸው 85 በመቶ ገበሬ እንኳንስ ተጨማሪ 15 በመቶ የሆነ ሕዝብ ሊቀልብ ራሱንም ቢሆን ከርሃብ አላዳነም፡፡ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ፣ የነጻ ኢኮኖሚ ሥርዓትን የተከተለ አሠራር ይተግበር የሚባለውም ለዚህ ነው፡፡
በመሠረቱ የኢትዮጵያ የግብርና ኢኮኖሚ ደካማ በመሆኑ ሕዝቡ በተደጋጋሚ ለረሃብ ይጋለጣል፣ ሲባልም ሆነ የዕለት ምግቡ ከአማካዩ ዝቅተኛ ካሎሪ እንኳን ያነሰ ነው ሲባል የአንድ ዓመት ወይም የሦስት አራት ዓመታት ችግር ውጤት ሳይሆን ከዚያ በፊት የነበሩት ሃያና ሰላሳ ዓመታትንም የሚዳስስ ነው፡፡
ችግሩ ይህ ከሆነ ጉዳዩ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የሚመለከታቸው ሁሉ የተዘራው እህል በደንብ እንዲታረምና በየእርሻው መሃል ውኃ የሚቋጥር መሬት እየተተለተለ እንዲዘጋጅ ማድረግ ይኖርባቸዋል። ዘሩን ተባይ እንዳያጠፋው በልዩ ልዩ መንገዶች መከላከል፣ መሬቱን ውኃ እንዳያጥበው ገበሬው ነቅቶ እንዲጠብቅ መምከር፣ ዘሩን አፈር ማሳቀፍና ማዳበሪያ መጨመር ያስፈልግ እንደሆነ አቅም የሚፈቅደውን ነገር ሁሉ ማድረግ ሁኔታው ያስገድዳል፡፡ ውርጭ እንዳይመታው ለመከላከል በማንኛውም ጥረት መሞከርና ሌሎችም የአካባቢ የመፍትሔ ሐሳቦችን ለመጠቀም ግንባር ቀደም ዝግጁነት ያስፈልጋል፡፡ ምርቱ ከመድረሱ በፊት እንዳይታጨድ ወይም ጊዜው እስኪያልፍ ድረስ እንዳይጠበቅ፣ ሲከመር ሲወቃና ሲሰበሰብ እንዳይዝረክረክ እስከ መጨረሻው ክትትል ማድረግ በእጅጉ አስፈላጊ ነው፡፡
አገሪቱ ሰፊ የለማ መሬት ስላላት የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ አገር ኢንቨስተሮች ሀብታቸውን በዚህ የኢኮኖሚ መስክ ላይ እንዲያውሉ የበለጠ አመቺ ሁኔታን መፍጠር አስፈላጊ ነው፡፡
የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት አመራር ብሔራዊ ፖሊሲ መነደፍ መሠረታዊ ምክንያት ሕዝብ በተፈጥሮም ሆነ በሰው ሠራሽ ችግሮች ምግብና ሌሎችንም መሠረታዊ ፍላጎቶቹን ማሟላት አቅቶት ኑሮው እንዳይናጋ በመሆኑ፣ ይኸው የተቀደሰ ዓላማ ግቡን ይመታ ዘንድ ፖሊሲውን በትክክል እንዲያስፈጽሙ ኃላፊነት የተጣለባቸው ክፍሎች ሁሉ በንቃት ሊታትሩ ይገባል፡፡
እስካሁን ሕዝብ በተፈጥሮና በሰው ሠራሽ አደጋዎች ምክንያት ሲያልቅ የነበረው አገሪቱ አቅም ስላልነበራትም ሆነ ባይኖራትም እንኳን የዕርዳታ እጁን የሚዘረጋላት የዓለም በጎ አድራጊ ማኅበረሰብ አጥታ አይደለም፡፡ ነገር ግን አቅሟን አቀናጅታ እንዴት እንደምትጠቀምበት ስልት ባለመነደፉ፣ ከልማት ጋር ባልተያያዘ መልኩ ዕርዳታ ሲሰጥ ስለነበረ ነው፡፡ እያንዳንዱ የሥራ ዘርፍ ግንኙነት ካለው ሌላ ዘርፍ ጋር ሊያሠራ የሚችል ፖሊሲ ከተቀየሰ በእርግጥም የአንድ ዓመት ችግር ቀርቶ ምንጊዜም ቢሆን ሰውና ተፈጥሮ የሚያደርሱብንን ችግር ለመቋቋም እንችላለን። ዛሬ በቂ ምግብ ተመግበው የሚያድሩ አገሮች ሁሉ እዚህ ደረጃ ላይ የደረሱት ተክክለኛ የኢኮኖሚ አቅጣጫ በመቀየሳቸው ነው፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው አንጋፋ ጋዜጠኛ፣ ደራሲ፣ የእስልምና ጉዳዮች ተመራማሪ፣ እንዲሁም የታሪክ አጥኚ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው bktesheat@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡