Friday, March 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበፋብሪካ የተቀነባበሩ የታሸጉ ምግቦች ማስታወቂያዎች እስከ ምን?

በፋብሪካ የተቀነባበሩ የታሸጉ ምግቦች ማስታወቂያዎች እስከ ምን?

ቀን:

በዓለም አቀፍ ደረጃ በፋብሪካ የተቀነባበሩ የምግብና ከአልኮል ነፃ መጠጥ ማስታወቂያዎች በረቀቀ መንገድ የሚለቀቁ ናቸው፡፡ አብዛኛው ዓላማቸው ደግሞ በራሳቸው መወሰን የማይችሉ ልጆች ላይ ተፅዕኖ መፍጠርና ተጠቃሚዎችን ማብዛት እንደሆነ የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ያሳያል፡፡

በፋብሪካ የተቀነባበሩ የምግብና ከአልኮል ነፃ የመጠጥ ዓይነቶች በቴሌቪዥን፣ በኢንተርኔት፣ በሞባይል ስልኮችና በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ይተላለፋሉ፡፡ የዘርፉ ኢንዱስትሪዎችም በመገናኛ ብዙኃን የሚተላለፉ ፕሮግራሞችን ስፖንሰር በማድረግ በየአጀንዳ መሀል ጣልቃ እየገቡ ምርቶቻቸውን ያስተዋውቃሉ፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት እንደሚለው ደግሞ፣ አብዛኞቹ በመገናኛ ብዙኃን የሚተዋወቁ በፋብሪካ የተቀነባበሩ ምግቦች ከፍተኛ መጠን ያለው ስብ፣ ስኳርና ጨው የያዙ ናቸው፡፡ እነዚህ ግብዓቶች ደግሞ በጤናማ አመጋገብ መርሕ በዝቅተኛ መጠን መወሰድ አለባቸው፡፡

በተለይም እንደ ስኳር፣ ደም ግፊት፣ ስብ በሰውነት ውስጥ መጠራቀም፣ የልብና ሌሎች ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች ምክንያት የሆኑትን ስብን፣ ስኳርንና ጨውን አብዝቶ መጠቀም በተለይ ደግሞ ሕፃናትን አብዝቶ ይጎዳል፣ ላልተገባ ውፍረትና ለተለያዩ  በሽታዎችም ይዳርጋል፡፡

ከዓለም ጤና ድርጅት ጋር የሚሠራው የፓን አሜሪካን ሔልዝ ኦርጋናይዜሸን ጥናቶችን ጠቅሶ እንደሚለው፣ በፋብሪካ የተቀነባበሩ የምግብና ከአልኮል ነፃ መጠጥ ማስታወቂያዎች በተደጋጋሚ መታየትና በሰዎች በተለይም በልጆች አዕምሮ ውስጥ መቀረፅ ሰዎች ከመጠን ያለፈ ካሎሪ፣ ስኳር፣ ስብና ጨው እንዲመገቡ የማድረግ ኃይል አላቸው፡፡

በመሆኑም የዓለም ጤና ድርጅት ኃላፊነት የተሞላበት የምግብና ከአልኮል ነፃ መጠጦች ማስታወቂያ እንዲተላለፍ ለመንግሥታት ምክረ ሐሳብ ካስተላለፈ አሥር ዓመታት ያህል ተቆጥረዋል፡፡

ድርጅቱ እ.ኤ.አ. ከ2013 እስከ 2020 ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ባወጣው የድርጊት መርሐ ግብር፣ የምግብና አልኮል ያልሆኑ መጠጦች ማስታወቂያዎችን አስመልክቶ የተለያዩ ምክረ ሐሳቦችን አስቀምጧል፡፡ የምክረ ሐሳቡ ዋና ዓላማም በተለይ ሳቢና የተጋነኑ የምግብና ከአልኮል ነፃ መጠጦች ማስታወቂያዎች ላይ ቁጥጥር በማድረግ ልጆችን ሊገጥማቸው ከሚችል የጤና ጉዳት መታደግ ነው፡፡

በኢትዮጵያ በኩልም ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች አንድ ምክንያት ሊሆን የሚችለውን በፋብሪካ የተቀነባበሩ ምግብ ነክ ምርቶች በመገናኛ ብዙኃን ሲተዋወቁ  መከተል ያለባቸው መርሕ ተቀምጧል፡፡

የኢትዮጵያ የምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን የምግብ ተቋማት ቁጥጥር ኃላፊ አቶ በትረ ጌታሁን እንደገለጹልን፣ ምግብና መጠጥን አስመልክተው የሚሠሩ ማስታወቂያዎችን በመተመለከተ ባለሥልጣኑ በአዋጅ ቁጥር 11/12 በተሰጠው ሥልጣንና ኃላፊነት መሠረት የምግብ በተለይም የሕፃናት ምግብ ማስታወቂያዎችን መመሪያ አውጥቶ እየተቆጣጠረ ይገኛል፡፡

በዚህ መሠረት ማናቸውም የምግብ ማስታወቂያዎች እንዲያሟሉ የሚጠበቅባቸውን መስፈርት በተመለከተ መመሪያ አውጥቶ ማስታወቂያዎች ሲተላለፉ ክትትል የማድረግ ሥራ እየሠራም ነው፡፡

ነገር ግን አንድ የምግብ ማስታወቂያ ሲሠራ ሳንሱር ስለሚባል፣ ቀድመው የማስታወቂያውን ይዘት አይገመግሙም፡፡ ከሚተዋወቀው ምግብ ወይም ከአልኮል ነፃ መጠጥ ጋር የማይጣጣም ማስታወቂያ ተላልፎ ሲገኝ ግን፣ ከብሮድካስት ባለሥልጣን ጋር በመነጋገር ማስታወቂያው እንዲቆም እንደሚደረግ አቶ በትረ ይናገራሉ፡፡

ባለሥልጣኑ ማስታወቂያውን ያስነገሩ ድርጅቶችን ሲጠይቅ፣ ያስተላለፉ ሚዲያዎች ደግሞ በብሮድካስት ባለሥልጣን በኩል እንዲጠየቁ የማድረግ ሥራ እንደሚሠራ የገለጹት አቶ በትረ፣ የምርቱ ባለቤት ችግሩን እንዲያስተካክል የሚደረግበትና ካላስተካከለ ደግሞ ሕጋዊ ዕርምጃ የሚወሰድበት አሠራር መኖሩን ጠቁመዋል፡፡

መመርያው በዋናነት የሕፃናት ምግቦች ማስታወቂያዎች ላይ ቢሆንም፣ ሁሉንም የምግብ ማስታወቂያዎች እንዲጨምር እየተከለሰ መሆኑንና በርካታ የተቀነባበሩ የምግብ ማስታወቂያዎች ከተለቀቁ በኋላ እንዲነሱ መደረጋቸውን ገልጸዋል፡፡  

የሕፃናት ወተት በተለይም የኢንፋንት ፎርሙላ ሙሉ ለሙሉ እንዳይተዋወቅና እነዚህን ሲያስተዋውቁ የነበሩ ድርጅቶችም ሙሉ ለሙሉ እንዲያቆሙ መደረጋቸውን አክለዋል፡፡

የምርቱን ባህሪ በማይገልጽ መልኩ የተሠሩ የምግብ ማስታወቂያዎች እንዲቆሙ መደረጋቸውን፣ ለምሳሌ ከዚህ ቀደም ጁስ እየተባሉ የሚቀርቡ በርካታ የምርቶች ማስታወቂያዎች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተወሰደ ዕርምጃ ማስታወቂያዎቹ የምርቱን ትክክለኛ ባህሪ እንዲያስተዋውቁና የማንጎ ከሆነ የማንጎ ተብሎ እንዲነገር እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

‹‹እጅግ በጣም የተጋነኑ ማስታወቂያዎች እንደሚነገሩ እናያለን›› ያሉት አቶ በትረ፣ ይህንን ከሚዲያዎች ላይ እየገመገሙና ማስታወቂያው ምርቱን ይገልጻል ወይ? የሚለው እየታየ የማስተካከያ ዕርምጃ እየተወሰደ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ችግሩ በአብዛኛው የሚዲያዎች መሆኑን፣ ድርጅቶች ይተዋወቅልን ብለው ለሚመጡበት አገልግሎት ትክክለኛነቱን ማረጋገጥና መገምገም እንደሚገባቸውም ጠቁመዋል፡፡

‹‹ድርጅቶች ብዙ ወጪ አውጥተው ካስተዋወቁ በኋላ እኛ ዕርምጃ እንወስዳለን፣ ድርጅቱም ለኪሳራ ተዳርጎ ዳግም ማስታወቂያውን ያስተካክላል፤›› ሲሉም፣ ችግሩን ለመቅረፍ ሚዲያዎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ማስታወቂያውን ከማስተላለፋቸው በፊት ቢነጋገሩ ይመከራል ብለዋል፡፡

ማስታወቂያዎቹን የማስታወቂያ ባለሙያ ሲሠራ በሚስብ መልኩ ተጋኖ ይሠራል እንጂ ምግቡ በውስጡ ምን ይዟል? የሚነገርለት ምርትና ምርቱ ተገናኝተዋል ወይ? የሚለው ትኩረት እየተሰጠው እንዳልሆነ መታዘባቸውን፣ በማስታወቂያ የሚነገሩ ምግቦች የምርቱን ባህሪ አብረው መግለጽ እንደሚጠበቅባቸውና የምርቱ ባህሪ ጋር ግንኙነት ከሌለው ስህተት መሆኑንም በምሳሌ አስረድተዋል፡፡

ለምሳሌ አንድ ጁስ በማስታወቂያ ጁስ ተብሎ ሊተዋወቅ የሚችለው የሚሠራበትን ፍራፍሬ ዓይነት 30 በመቶና ከዚህ በላይ በተፈጥሮ ሲይዝ መሆኑን ለአብነትም የማንጎ ጁስ ቢሆን 30 በመቶ የተፈጥሮ ማንጎ መያዝ እንደሚገባው፣ ይህንን ሳያሟላ ጁስ ተብሎ ከተዋወቅ ትክክል እንደማይሆንም ተናግረዋል፡፡

አንዳንድ አገሮችም በፋብሪካ የተቀነባበሩ ምግቦች በማስታወቂያ በሚነገሩበት ጊዜ በምን መልኩ በመገናኛ ብዙሀን  መተዋወቅ እንዳለባቸው ፖሊሲ ጭምር አውጥተው እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ 

በኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ሳይንስ ኢንስቲትዩት የሥነ ምግብ ተባባሪ ተመራማሪ የሆኑ አቶ ክፍሌ ሀብቴ እንደገለጹት፣ አንዳንድ አገሮች ለስላሳ መጠጦችን ጨምሮ በፋብሪካ የተቀነባበሩ ምግቦች ለምሳሌ የታሸጉ ጣፋጭ ጁሶች፣ ከመጠን በላይ የተቀነባበሩ ታሽገው የሚሸጡ ስጋና የስጋ ውጤቶች፣ ለስላሳ፣ ኩኪሶች፣ ኬኮች፣ ቸኮሌቶች፣ ከረሜላ፣ አይስ ክሬሞች እና ሌሎችም ከነዚህ ተመሳሳይ ባህርይ ያላቸው ምግቦች  ላይ ከፍተኛ ታክስ በመጣል ለመቆጣጠር ይሞክራሉ፡፡

ጨውና ስኳር በጣም የበዛባቸው፣ ካሎሪያቸው የበዛና የምግብ ንጥረ ነገር ይዘታቸው ትንሽ የሆኑ ምግቦች ላይ ከፍተኛ ታክስ ከመጣል ባለፈም ማስታወቂያዎች በሚተላለፉባቸው ጊዜያቶች ላይ ገደብ ይጥላሉ፡፡

በፋብሪካ የተቀነባበረ የምግብ ምርትን ተጠቅመው የቆዩ አገሮች የጤና ጉዳቶቹን፣ ዜጎቻቸው ከመጠን ላለፈ ውፍረትና ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች መጋለጣቸውን በመገንዘባቸውም የሚያስከትሉትን ችግሮች በስፋት በኅትመት አውጥተዋል፣ እያወጡም ነው ያሉት አቶ ክፍሌ፣ በኢትዮጵያ በኩል ችግሩ አሁን ላይ ጎልቶ ባይታይም በሌሎች አገሮች ከተከሰተው ችግርና እየሄዱበት ካለው የመፍትሔ አቅጣጫ ልምድ በመውሰድ ችግሩ ሳይጎላ ቀድሞ መከላከል እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡ 

ኢንዱስትሪውም ቢሆን የኅብረተሰቡ ጤና የማይጎዳ አሠራሮችን በመከተል በሽታን ቀድሞ መከላከል ላይ መሠረት ባደረገ መልኩ መሥራት እንደሚገባም አክለዋል።

እንደ አቶ ክፍሌ፣ አሁን ላይ የተቀነባበሩ ምግቦችን ሙሉ ለሙሉ ህብረተሰቡ አይጠቀም ማለት ባይቻልም፣ ከተጠቃሚው ህብረተሰብ እና ጤናማ ከሆኑ ምግቦች አቅርቦት አንጻር አመጣጥኖ መሄድ ያስፈልጋል፡፡

 ወላጆች ለልጆቻቸው የሚሰጡት የተቀነባበረ ምግብ ካለ በድግግሞሽም ሆነ በመጠን ማብዛት የለባቸውም፡፡ በተለይ በጣም የተቀነባበሩ፣ የምግብ ንጥረ ነገር ይዘታቸው ማለትም ሚኒራል፣ ቫይታሚን፣ ፕሮቲን እና የአሰር ይዘታቸው ትንሽ የሆኑ ምግቦችን አብዝቶ ከመጠቀም መጠንቀቅም አለባቸው፡፡ 

እነዚህ ምግቦች በባህሪያቸው ከፍተኛ ካሎሪ (ኃይል ሰጪና ጣፋጭ ነገሮች፣ ስኳር፣ ጨው የበዛባቸው) ሆኖ በተደጋጋሚ እና በብዛት መጠቀም ብዙ የጤና ጉዳቶች ያስከትላሉ።  ከነዚህም ጉዳቶች ለምሳሌ ከጥርስ ህመም ጀምሮ እስከ መጠን ያለፈ ውፍረት፣ ለስኳር እና  ለልብ ህመም፣ ለደም ግፊት መጨመር እና ለተለያዩ የካንሰር አይቶች በቀላሉ ተጠቂ ያደርጋሉ ወይም የመጠቃት እድልን ይጨምራሉ።

በፋብሪካ የተቀነባበሩ ምግቦችን በየቀኑ መመገብ  የጎንዮሽ ጉዳታቸው ብዙ ስለሚሆን ልጆች በየቀኑም ሆነ፣ በአንዴ አብዝተው እንዳይመገቧቸው ማድረግም ከወላጆች እንደሚጠበቅ ይመክራሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...