Thursday, March 23, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየካፍ ደረጃን ያሟላው የአቃቂ ስታዲየም በ688 ሚሊዮን ብር ወጪ እየተገነባ መሆኑ ተገለጸ

የካፍ ደረጃን ያሟላው የአቃቂ ስታዲየም በ688 ሚሊዮን ብር ወጪ እየተገነባ መሆኑ ተገለጸ

ቀን:

  • የስታዲየሙ 25 ሺሕ መቀመጫዎች ተመርተዋል

በአዲስ አበባ ከተማ እየተገነቡ ከሚገኙ ስታዲየሞች መካከል አንዱ የሆነው የአቃቂ ቃሊቲ ስታዲየም በ688 ሚሊዮን ብር ግንባታው እየተከናወነ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

በግንባታው መቆራረጥ ምክንያት ተጓትቶ የቆየው የስታዲየም ግንባታው፣ የዞናል ውድድሮችን ብቻ እንዲያስተናግድ ታስቦ ግንባታው ቢጀመርም፣ በቅርቡ የካፍ ደረጃን አሟልቶ እንዲገነባ በማቀድ፣ የዲዛይን ክለሳ ከተደረገለት በኋላ ዳግም ግንባታው እንዲጀመር መደረጉ ታውቋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ዲዛይንና ግንባታ ሥራዎች ቢሮ በባለቤትነት እያስገነባው የሚገኘው የአቃቂ ስታዲየም ሲጠናቀቅ የአገር አቀፍ ውድድር ብቻ ሳይሆን፣ የካፍና የፊፋ ጨዋታዎችን ማስተናገድ የሚያስችል ደረጃ እንዲኖረው ተደርጎ እንደሚገነባ ተጠቅሷል፡፡

ከ20 ሺሕ በላይ ተመልካቾች እንዲሁም 140 ቪአይፒ መቀመጫዎችን የመያዝ አቅም እንዳለው የተገለጸ ሲሆን፣ ዋናው ስታዲየም የእግር ኳስ መጫወቻ ሜዳዎች በተጨማሪ፣ ሁለት የማሟሟቂያ ሜዳዎች እንዳሉት ተብራርቷል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ የታዳጊዎች መጫወቻ ሜዳ፣ የመሮጫ ትራክ፣ የአትሌቲክስ ስፖርት ማከናወኛ ሥፍራ፣ የቤት ውስጥ ውድድር ማስተናገድ የሚችሉ ሥፍራዎች ያሉት ሲሆን፣ ከእነዚህም ባሻገር የመሰብሰቢያ አዳራሽ የመልበሻ ክፍሎች፣ ካፍቴሪያና ሌሎች መሠረታዊ ልማቶች መካተታቸውን ተጠቁሟል፡፡

በ2010 ዓ.ም. በ514 ሚሊዮን ብር በጀት ግንባታው የተጀመረው የአቃቂ ቃሊቲ ስታዲየም የኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ የሰሜኑ ጦርነት እንዲሁም ከተቋራጮች ጋር በነበረው አለመግባባት መዘግየቱ ተነግሯል፡፡

በአንፃሩ ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ በአዲስ አበባ ከተማ ዲዛይንና ግንባታ ሥራዎች ቢሮ ባለቤትነት ሥር መተዳደር ከጀመረ በኋላ ዲዛይኖቹ ዳግም ተከልሰው አሁን 64 በመቶ ግንባታ ላይ የደረሰ ሲሆን፣ የኮንስትራክሽኑ 44 በመቶ ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ ክፍያ ተፈጽሟል፡፡

በዚህም የስታዲየሙ የብረት ሥራዎች፣ አጥር፣ የውስጥ ፖልቴሽንና የጂፕሰም ሥራዎች መሠራታቸውን በአዲስ አበባ ወጣቶች ስፖርት ቢሮ የማዕከላትና ስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች ልማት አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ ባዬ ለሪፖርተር አብራርተዋል፡፡

ዳይሬክተሩ አክለውም፣ የመቀመጫ ገጠማ፣ የጣሪያ፣ የትራክ ሥራ፣ የመለማመጃ፣ የፓርኪንግ የሚዲያ ማዕከል እንዲሁም የሕክምና ሥፍራ ግንባታዎች እየተከናወኑ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ጣሪያው በቻይና አገር እየተሠራ እንደሚገኝና 25 ሺሕ ወንበር በአገር ውስጥ ተመርቶ መጠናቀቁ የተገለጸ ሲሆን፣ የጣሪያው ገጠማ ከተጠናቀቀ በኋላ ወደ ወንበር ገጠማው ይገባል ተብሏል፡፡  

የግንባታውን እያንዳንዱ ሒደት የካፍና የዓለም አትሌቲክስ ደረጃን ማሟላት መቻሉ ክትትል እየተደረገበት እንደሚገኝም ዳይሬክተሩ አውስተዋል፡፡  

በፌዴራል ደረጃ እየተገነቡ የሚገኙ አደይ አበባና የአዲስ አበባ ስታዲየም ግንባታዎች መጓተታቸውን ተከትሎ በመዲናዋ ውድድሮች መካሄድ ከቆሙ ሰነባብተዋል፡፡

ከእነዚህም ውድድሮች መካከል የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር እንዲሁም በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የሚዘጋጀው ሻምፒዮና ይጠቀሳል፡፡

የአዲስ አበባ ስታዲየም የዕድሳት ላይ መሆኑን ተከትሎ ከ2012 ዓ.ም. ጀምሮ የሊግ ውድድሮች በክልሎች እየተከናወኑ መሆናቸው ይታወቃል፡፡

በዚህም መሠረት በተለይ መሠረታቸው አዲስ አበባ ላይ የሆኑ ክለቦች ‹‹ውድድሩ ይመለስልን›› የሚል ቅሬታ ሲያቀርቡ ተደምጠዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር የ2015 ዓ.ም. የጨዋታ መርሐ ግብር ይፋ ሲያደርግ የመጨረሻውን ዙር ውድድር በአዲስ አበባ ስታዲየም እንደሚያደርግ ገልጾ ነበር፡፡ የስታዲሙን ግንባታ የመጀመርያው ምዕራፍ መጠናቀቁ ቢገለጽም፣ ሚኒስቴሩ የሁለተኛ ምዕራፍ ግንባታ ውስጥ መጠናቀቅ ያለባቸው ግንባታዎች በመኖራቸው ተጨማሪ የግንባታ ጊዜ መውሰዱ ግድ ነው ብሏል፡፡

በዚህም ምክንያት የሊጉን የማጠናቀቂያው መርሐ ግብር በአዲስ አበባ መከናወኑ ጥርጣሬ ውስጥ ወድቋል፡፡

በአንፃሩ የአቃቂ ቃሊቲ ስታዲየም አሁን በተያዘው ዕቅድ መሠረት ዘንድሮ ይጠናቀቃል ተብሏል፡፡  የስታዲየሞቹ ግንባታዎቹ ከተጠናቀቁ በከተማዋ ነዋሪዎች የተናፈቁ ውድድሮች ዳግም ወደ መዲናዋ ይመለሳሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...