- የትግራይ ጦርነትን እንዲመረምሩ ያቋቋመው የስብዓዊ መብት ቡድን ሥራውን እንዳያቋርጥ ጠየቁ
ከ60 በላይ የሚሆኑ ዓለም አቀፍ የስብዓዊ መብት ተሟጋቾች የኢትዮጵያ መንግሥት በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ወቅት የተፈጸመው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በውጭ አካል እንዳይመረመር የሚያደርገው ግፊት እንዳሳሰባቸው ከ60 በላይ የሚሆኑ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ተናገሩ፡፡ ተሟጋቾቹ ተመድ ለዚሁ ዓላማ ያቋቋመውን የመርማሪዎች ቡድን በኢትዮጵያ መንግሥት ግፊት ሥራውን እንዳያቋርጥ ትናንት የካቲት 21 ቀን 2015 ዓ.ም. ለተመድ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
የተመድ የሰብዓዊ መብት ምክር ቤት በታኅሳስ 2014 ዓ.ም. በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የተፈጸመው ጥሰቶችን እንዲመረምር ዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ኮሚሽን ማቋቋሙ ይታወሳል፡፡ መቀመጫውን ዩጋንዳ ያደረገው ኮሚሽኑ በበኩሉ፣ ‹‹ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ ዘልቄ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ማስረጃዎችን እንዳልሰበስብ የኢትዮጵያ መንግሥት ከልክሎኛል፤›› ሲል ቆይቷል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት በተደጋጋሚ ኮሚሽኑ ፖለቲካዊ አጀንዳ ያለውና የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚጥስ በመሆኑ እንዲፈርስ ለተመድ መጠየቁ ይታወሳል፡፡ ይሁን እንጂ ተመድ በድምፅ ብልጫ የኢትዮጵያ ጥያቄ ተቀባይነት ሳያገኝ መቆየቱ ይታወቃል፡፡
ከሳምንት በፊት በአዲስ አበባ በነበረው የአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኰንን ባደረጉት ንግግር፣ የአፍሪካ አገሮችና የአፍሪካ ኅብረት ተመድ ያቋቋመው የመርማሪዎች ኮሚሽን እንዲፈርስ እገዛቸውን ለኢትዮጵያ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡ አቶ ደመቀ በተለይ በቀጣይ በሚኖረው የተመድ ሰብዓዊ መብት ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ጉዳዩን እንደገና ለማንሳት የኢትዮጵያ መንግሥት ዕቅድ ማዘጋጀቱን ጠቅሰዋል፡፡
ይሁን እንጂ ዓለም አቀፍ ተሟጋቾች፣ በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል የሚደረገው ጥረት፣ በሰሜን ኢትዮጵያ በነበረው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ያለው ተጠያቂነትና ያለ ተጠያቂነት ሊቀር ስለሆነ የመርማሪዎች ኮሚሽን እንዳይፈርስ ለተመድ ከወዲሁ ጥያቄያቸውን አቅርበዋል፡፡
ጥያቄውን ያቀረቡት 62 የሰቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አብዛኛዎቹ ከአፍሪካ አገሮች ሲሆኑ ካናዳ፣ አውስትራሊያና አሜሪካ ይገኙበታል፡፡ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ጉባዔ፣ ዓለም አቀፍ ፌደሬሽን ለሰብዓዊ መብትና አምነስቲ ኢንተርናሽናል እንደሚገኙበት ሂውማን ራይትስዎች ባወጣው ሪፖርት ገልጿል፡፡
ከወራት በፊት የፕሪቶሪያ ስምምነት ከተፈረም ወዲህ የኢትዮጵያ መንግሥት የሽግግር ፍትሕ ዝግጅት ላይ እየሠራ እንደሆነ የገለጸ ሲሆን፣ ይህም በጦርነቱ የነበረውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጠያቂነት ይፈታል ብሏል፡፡
ይሁን እንጂ በተለይ የአውሮፓ ኅብረትም አሜሪካ የኢትዮጵያ መንግሥት ምርመራውና የሽግግር ፍትሕ በገለልተኛና የውጭ አካል መሥራት አለባት የሚል አቋሙን ይዞ ቀጥሏል፡፡ ይህም የኢትዮጵያ የውጭ ድጋፍና ብድር ለማግኘት እንደ ቅድመ ሁኔታ እየቀረበ እንደሆነ ተገልጿል፡፡