ታላቁ የዓድዋ ድል 127ኛ ዓመት ሲዘከር የጀግኖቹ ኢትዮጵያውያን ተጋድሎ መታወስ የሚኖርበት፣ ለአገራቸው ከነበራቸው ጥልቅ ፍቅርና ለዘመናት ከገነቡት ታላቅ የሞራል ልዕልና ጋር ነው፡፡ አፍሪካንና ሌሎች አካባቢዎችን እንደ ቅርጫ ለመቀራመት ከተነሱት የዘመኑ ቅኝ ገዥዎች ኢትዮጵያውያን ጀግኖች አገራቸውን መካላከል የቻሉት፣ ከአገራቸው በፊት የሚቀድም አንዳችም ፍላጎት እንደሌለ ለመረዳት የሚያስችል ዕፁብ ድንቅ የሆነ ሞራላዊ እሴት ስለነበራቸው ነው፡፡ ቀደም ሲል በጉራዕ፣ በጉንደት፣ በሰሃጢና በሌሎችም ሥፍራዎች ወራሪዎችን ድባቅ የመቱት ጀግኖች ከዘመኑ ኃያሎች መካከል አንዱ የሆነውን የጣሊያን ቅኝ ገዥ ዓድዋ ላይ በማንበርከክ፣ ለዓለም ጥቁር ሕዝቦች መነቃቃት ምክንያት የሆነ ታላቅ ገድል መፈጸማቸውን ታሪክ መዝግቦታል፡፡ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ብቸኛዋ ቅኝ ያልተገዛችና የነፃነት ተምሳሌት የሆነች ታሪካዊ አገር መሆን የቻለችው፣ በዘመኑ የነበሩ ጀግኖች ኢትዮጵያውያን በከፈሉት ወደር የሌለው መስዋዕትነት ነው፡፡ በአራቱም ማዕዘናት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ማንነት፣ እምነት፣ ቋንቋ፣ ባህልና ሌሎች ልዩነቶች ሳይበግሯቸው ታሪክ የማይረሳው ጀግንነት የፈጸሙት፣ በከፍተኛ የሞራል ልዕልና እንደሆነ መቼም ቢሆን የማይካድ ሀቅ ነው፡፡ የዘመኑ ትውልድም የሰው ልጆች ቅርስ የሆነውን ዘመን ተሻጋሪ ታላቅ ገድል በክብር ካልዘከረ፣ መጪው ትውልድና ታሪክ ይፋረዱታል፡፡
በዚህ ዘመን የጀግኖቹን ታሪክ አስቀጥለው ለአኩሪ ታሪክ የተዘጋጁ ኢትዮጵያውያን መኖራቸው ባይካድም፣ አላስፈላጊ ድርጊቶች ግን የሕዝቡን አንድነትና ዘመን ተሻጋሪ ማኅበራዊ እሴቶች መሸርሸራቸው በግልጽ እየታየ ነው፡፡ የታላቁ የዓድዋ ድል መሪ የነበሩት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ለመሆናቸው ከኢትዮጵያውያን አልፈው ታላላቅ የዓለም ታሪክ ጸሐፊዎች በሚገባ መዝግበውታል፡፡ እሳቸው በታሪክ አጋጣሚ በዘመኑ ኢትዮጵያን ይመሩ ስለነበሩ መላ ኢትዮጵያውያንን አስተባብረው፣ ይህንን ዘመን አይሽሬ ታላቅ ድል ማስገኘታቸው የታወቀ ነው፡፡ በወቅቱ በተለያዩ ምክንያቶች አኩርፈው የነበሩ ታላላቅ ሹማምንትንና ለጣሊያን አድረው የነበሩትን ጭምር ለአገራቸው በአንድነት እንዲቆሙ በማድረጋቸው፣ ህያውና አንፀባራቂ የሆነው ታሪካዊ ድል እንዲመዘገብ አስችለዋል፡፡ ይህንን ማንም ሊክደው የማይችል ሀቅ በመሆኑ፣ የዓድዋ ድል መታሰቢያ በዓል ሲከበር አውራውን ዳግማዊ አፄ ምኒልክ መዘንጋት አይቻልም፡፡ ከዚህ እውነታ ማፈንገጥ በታሪክ ያስጠይቃል፡፡ የኢትዮጵያዊነት ጨዋነት፣ ኩሩነት፣ ትህትና፣ አርቆ አሳቢነት፣ ጀግንነትና ሰብዓዊነት እሴቶች የተገነቡት በሞራላዊ ልዕልና ላይ መሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡
ኢትዮጵያውያን ታላቁን የዓድዋ የድል በዓል ሲያከብሩ በልባቸው ማኅደር ውስጥ ማስቀመጥ ያለባቸው፣ ከአገር በፊት የሚቀድም አንዳችም ፍላጎት ሆነ ጥቅም አለመኖሩን ነው፡፡ እዚህ ላይ ግን ልብ መባል ያለበት በየዘመናቱ አገራቸውን ከወራሪዎችና ከተስፋፊዎች ሲከላከሉ ክብር መስዋዕትነት በመክፈል ያለፉ ጀግኖች ሲታወሱ፣ የዘመኑ ትውልድ ለአገሩ ምን እያበረከተ እንዳለ ራሱን በሚገባ መመርመር እንዳለበት ነው፡፡ በዚህ ዘመን ከተርታው ሰው ጀምሮ አገር የሚመሩ ሰዎች ድረስ የሚስተዋለው አጓጉል ባህሪ እርምት ያስፈልገዋል፡፡ በአገርና በሕዝብ ስም ቁማር የሚጫወቱ፣ አገርን የሚዘርፉ፣ ሕዝቡን ፍትሕ እየነፈጉ የሚያስመርሩ፣ ወጣቱን ትውልድ ለሞራላዊ ዝቅጠት የሚዳርጉ፣ በአንድ አገር ውስጥ ሁለት ዓይነት ዜግነት የሚፈጥሩ፣ አገርን ከማጠናከር ይልቅ የሚያፍረከርኩ፣ ከአገራዊ አንድነት ይልቅ ማንነትን ብቻ በማቀንቀን ታሪካዊ ትስስርን የሚያላሉና አሳፋሪ ድርጊቶችን የሚፈጽሙ መብዛታቸው ሊጤን ይገባዋል፡፡ እነዚህ ሁሉ ፀያፍ ድርጊቶች የሚከናወኑት ለዓለም ታላቅ ምሳሌ በሆነች አገር ውስጥ መሆኑ ያሳዝናል፡፡ ለሥልጣንና ለጥቅም ሲሉ ብቻ ኢትዮጵያ ብትንትኗ ቢወጣ ደንታ የሌላቸው መኖራቸው ሲታከልበት ያስቆጫል፡፡ ከእንዲህ ዓይነት የረከሰ አስተሳሰብ ውስጥ መውጣት ያስፈልጋል፡፡
ታሪካዊውን የዓድዋ ድል ይህ ትውልድ ሲዘክር ከመጠን በላይ የሚያስቆጩ ጉዳዮችን በማሰላሰል መሆን ይኖርበታል፡፡ የዓድዋን ድል የመሰለ አኩሪ ታሪክ ተሸክሞ እንደ አልባሌ ነገር ሳይጠቀምበት መኖሩ ያስከፋል፡፡ ይህንን የመሰለ ተምሳሌታዊ ድል ሌሎች ለምሳሌ እነ አሜሪካና አውሮፓ ቢጎናፀፉት ኖሮ በሲኒማ፣ በሙዚቃ፣ በቴአትር፣ በቱሪዝምና በመሳሰሉት መስኮች እንዴት ያስተጋቡት እንደነበር ሲታሰብ ያስከፋል፡፡ እነሱ እዚህ ግቡ የማይባሉ የታሪክ ሰበዞችን እየቀጣጠሉ በዓለም ገበያ ውስጥ ሲከብሩባቸው፣ ኢትዮጵያውያን ግን መላውን የዓለም ጥቁር ሕዝብ ከዳር እስከ ዳር ያነቃነቀ ታላቅ ቅርስ ይዘው ዘመናት መንጎዳቸው ያሳዝናል፡፡ ለፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ ምሥረታ ወሳኝ ድርሻ የነበረውን ታላቁ የዓድዋ ድል የአንድነት ማሰሪያ ማተብ ማድረግ ሲገባ፣ ጥቃቅን ልዩነቶችን ከመጠን በላይ በማራገብ አገር የሚያፈርስ ከንቱ ድርጊት ውስጥ መገኘት አስነዋሪ ነው፡፡ ጀግኖቹ ኢትዮጵያውያን አንዳችም ልዩነት ሳይበግራቸው ለአገራቸው ክብር የተዋደቁበትን ታላቅ ዓላማ ማራከስ መርገምት ነው፡፡ ጥንታዊያኑ ጀግኖች ግላዊ ጠባቸው ከአገራቸው እንደማይበልጥባቸው ተገንዝበው ታሪክ ሠርተው ያለፉት፣ ሞራላዊ ልዕልናቸው ለማይረቡ ድርጊቶች ስለማይንበረከክ እንደነበር መረዳት ተገቢ ነው፡፡ ይህ ትውልድ ታላቁን የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሲያከብር ራሱን መመርመር ይኖርበታል፡፡
የዓድዋ ጀግኖችን ገድል ለመዘከር በእነሱ የሞራል ልዕልና ልክ መገኘት ተገቢ ነው፡፡ ይህ በዘመኑ ዓለምን ከዳር እስከ ዳር ያነጋገረና ያስደነቀ ታላቅ ድል ሲዘከር፣ ለሞራልና ለሥነ ምግባር ዝቅጠት ምክንያት የሆኑ ድርጊቶችን በፅናት መታገል ያስፈልጋል፡፡ ትውልዱን የሚያነቅዙና አገሩን እንዲጠላ የሚያደርጉ ፀያፍ ድርጊቶችን ለመታገል ግን፣ በሥነ ምግባር ዝቅጠትና በሞራል ልሽቀት ላይ መዘመት አለበት፡፡ ሞራላዊ ልዕልና እየላሸቀ ሸፍጠኝነት፣ ሴረኝነት፣ ሌብነት፣ አሉባልታና ምግባረ ብልሹነት ተስፋፍተዋል፡፡ ወጣቱ ትውልድ ጥራት ያለው ትምህርት አግኝቶ በዕውቀት መኮትኮት ሲገባው፣ ከቤተሰብ ጀምሮ በትምህርት ቤትና በመንግሥታዊ መዋቅሮች ውስጥ ሳይቀር ለከንቱ ድርጊቶች ሥፍራ ተሰጥቷል፡፡ የትምህርት ሥርዓቱ በመፍረክረኩ የደረሰው ስብራት ይጠገን፡፡ ከዕውቀት ፍለጋ፣ ከጥናትና ከምርምር የተራራቀ ትውልድ ዕጣ ፈንታው ጥፋት ላይ መሰማራት ስለሆነ፣ ከአገር ጉዳይ ይልቅ የረከሰ ድርጊት ነው የሚቀናው፡፡ ኢትዮጵያ በዚህ ዘመን ዕድለኛ ሆና የሚያስቡላት ውስን ልጆች ቢኖሯትም፣ አጠቃላይ ሁኔታው ግን አሳሳቢ ነው፡፡
አፍሪካውያንና ሌሎች ቅኝ የተገዙ አገሮች ኢትዮጵያን በታላቁ የዓድዋ ድል ምክንያት የነፃነት ተምሳሌታቸው ቢያደርጓትም፣ በሌላ በኩል የግጭትና የድህነት ዓርማ ማንጠልጠሏ እንቆቅልሽ ነው የሚሆንባቸው፡፡ ጀግኖች ኢትዮጵያውያን በየዘመናቱ አገራቸውን ለመከላከል በፍቅርና በመተሳሰብ አንድ ላይ እንዳልቆሙ፣ በዚህ ዘመን ጥቃቅን ልዩነቶችን ሳይቀር ከየሥርቻው እያፈላለጉ እርስ በርስ መጠላለፋቸው ሊያስቆጭ ይገባል፡፡ የዓድዋ ድል ሰውን ለማዳን ሰው መስዋዕትነት የከፈለበት የታሪክ ዓርማና ብዙ የተባለበት ገድል መሆኑ እየታወቀ፣ በዚህ ዘመን ለአገር ዘለቄታዊ ልማትና ዕድገት በአንድነት መቆም የማይፈለግበት ምክንያት እንቆቅልሽ ነው፡፡ ጀግኖች ኢትዮጵያውያን ለዘመናት ባካበቷቸው አኩሪ ማኅበራዊ እሴቶቻቸው ልዩነቶቻቸውን ወደ ጎን በማለት፣ ለሚጠቅሟቸው የጋራ ጉዳዮቻቸው ትልቅ ትኩረት በመስጠት ተጋብተው መዋለዳቸውና በጋራ አገራቸውን ሲጠብቁ መኖራቸው ይታወቃል፡፡ የዚህ ዘመን ትውልዶች አካል የሆኑ ልሂቃንና ምሁራን ይህንን አኩሪ ታሪክ መሠረት አድርገው አገራቸውን ወደፊት ማራመድ ሲገባቸው፣ እዚህ ግባ በማይባሉና የታሪክ ማስረጃ በማይቀርብባቸው ብሶቶችና ቁርሾዎች አገር ማመስ የለባቸውም፡፡ በዓለም የታሪክ መዝገብ ደማቅና ህያው ታሪክ አስመዝግበው ያለፉ ጀግኖችን አፅም እረፍት እንዳይነሱ ይጠንቀቁ፡፡ ታላቁ የዓድዋ ድል ሲዘከር የዘመኑ ትውልድ ራሱን በሚገባ ይፈትሽ!