Thursday, March 23, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናሕገ መንግሥቱን በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ ለማሻሻል የተቀመጡ አማራጮች አከራካሪ መሆናቸውን ምሁራን...

ሕገ መንግሥቱን በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ ለማሻሻል የተቀመጡ አማራጮች አከራካሪ መሆናቸውን ምሁራን ገለጹ

ቀን:

በሥራ ላይ ያለውን የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት በከፊል ለማሻሻል ወይም ሙሉ በሙሉ ለመቀየር ያሉት አማራጮች፣ አከራካሪና አጨቃጫቂ መሆናቸውን ምሁራን ገለጹ፡፡

ሕገ መንግሥቱ እንዲሻሻል ወይም እንዲቀየር በበርካቶች ዘንድ ጥያቄ ቢኖርም፣ የማሻሻያ ሐሳብ ለማመንጨት፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 104 ላይ የተቀመጡት የማሻሻያ አማራጮች ግልጽነት እንደሚጎድላቸው ተገልጿል፡፡

የአገራዊና የቀጣናዊ የትስስር ጥናት ማዕከል Center for National Regional Integration Studies (ceNRIS) የተሰኘ አገር በቀል ድርጅት፣ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ፣ ከሰሞኑ በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አጠቃላይ ቅቡልነትና ወደ ማሻሻል ቢገባ ሊያጋጥሙ በሚችሉ እንቅፋቶችና ሊደረጉ በሚገባቸው ጥንቃቄዎች ላይ ያተኮረ የምሁራን ወይይት ተካሂዷል፡፡

ውይይቱ የተወላገዱና ጫፍና ጫፍ ረገጥ አስተሳሰብ ያላቸውን ዜጎቸ ለማቀራረብ ምሁራንን ወደ አንድ በማምጣት የውይይት መድረክ መፍጠር ያሰበ መሆኑን፣ የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢብራሂም ሙሉሸዋ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም ሕገ መንግሥት ይሻሻል ወይም ይቀየር ሲባል እንዲያው በደፈናው ይቀየር ወይም ይሻሻል ከሚለው ዕሳቤ ወጣ ባለ መንገድ የማሻሻያ መንገዶቹ ምን ሊሆኑ ይችላሉ? ምን ዓይነት መንገድ መከተል ይቻላል? እነማን ሊሳተፉ ይችላሉና መሰል ዓይነት ጥያቄዎች በሚገባ ካልተጤኑ፣ የማሻሻያ አማራጮቹ አከራካሪና አጨቃጫቂ መሆናቸው አይቀሬ እንደሚሆን አስረድተዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፌዴራሊዝም መምህር ሲሳይ ክንፈ (ዶ/ር)፣ ከጅምሩ ሕገ መንግሥቱ ቅቡልነት የሌለው ስለመሆኑ በሁለት መንገድ ከፍለው ገልጸዋል፡፡ የመጀመርያው ሕገ መንግሥቱ ሲረቀቅ ያለፈበት የአረቃቅ ሒደትና ለማርቀቅ የተሳተፉት አካላት አካታች በሆነ መንገድ ተሳትፎ ያልነበረው፣ ሁሉንም የፖለቲካ ኃይሎች ያላሳተፈና በወቅቱ በብሔር የተደራጁ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንጂ ሕዝቡ ያልተሳተፈበት መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በሌላ በኩል ሕገ መንግሥቱ የሁሉንም ማኅበረሰቦች ችግር ሊፈታ በሚችል ሁኔታ ባለመፅደቁና ሊተገበሩ የማይችሉ አንቀጾች ስለተካተቱበት፣ አፈጻጸሙ ላይ ችግር እንደገጠመው የጠቀሱት ሲሳይ (ዶ/ር)፣ ለዚህም እንደ ማሳያ የጠቀሱት አንቀጽ 39ን ነው፡፡ ባለፉት ሦስት አሥርት ዓመታት ከበርካታ ብሔር ብሔረሰቦች የክልል እንሁን ጥያቄ ሲነሳ የቆየ ቢሆንም፣ መልስ ማግኘት አለመቻሉን አስረድተዋል፡፡ ለዓመታት ሲነሳ ለነበረው ጥያቄ በኋላ መልስ መሰጠት የተጀመረው ከቅርብ ዓመታት ወዲህ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የብሔር ፌዴራሊዝሙ የተመሠረተው አንድን ብሔር መሠረት በማድረግ  በመሆኑና ቅይጥ ማንነት ያላቸውን ዜጎችና የጋራ ግዛት የሚጋሩ በርካታ ሕዝቦችን ዕውቅና የማይሰጥ ከመሆኑም በላይ፣ በብሔር ፌዴራሊዝሙ አወቃቀር የሚታየው ዕውቅና አንድ ብሔር አንድ አካባቢ ብቻ መገኘት አለበት በሚል እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አንድ ማንነት ብቻ ያላቸው ቢሆኑም፣ ሕገ መንግሥቱ ብዙ ቅይጥ ማንነት ያላቸውን ዜጎች ዕውቅና እንደማይሰጥ ተናግረዋል፡፡

በዚህም የተነሳ ሕገ መንግሥቱን ወደ ማሻሻል ከመገባቱ በፊት ለማሻሻል የተቀመጡት ቅድመ ሁኔታዎችና መሥፈርቶች እንቅፋት መሆናቸውን የገለጹት ሲሳይ (ዶ/ር)፣ ከዚህም ባላፈ አሁን ባለው አገራዊ ሁኔታ የተረጋጋና አስተማማኝ የሆነ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ባለመኖሩና መንግሥትም ሁሉንም አካባቢዎች እያስተዳደረ ነው የሚያስብል አስቻይ ሁኔታ ባለመኖሩ፣ ወደ ማሻሻያ ለመግባት ብዙ እንቅፋቶች እንደሚገጥሙ አስረድተዋል፡፡

ሕገ መንግሥቱ ጠንከር ያሉ ማሻሻያዎች የሚያስፈልጉት ቢሆንም ወደ ማሻሻል ለመግባት የተቀመጡት መሥፈርቶች፣ ለምሳሌ ሁሉም የክልል መንግሥታት ምክር ቤቶች እንዲስማሙ የሚጠይቀው መሥፈርት፣ አሁን አገር ባለችበት የሰላም ሁኔታ ከሁሉም ክልሎች ድጋፍ ማግኘት አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችል የፌዴራሊዝም መምህሩ አክለዋል፡፡

በመሆኑም ሕገ መንግሥቱ ውስጥ የሠፈሩት የማሻሻያ መሥፈርቶች ሕገ መንግሥቱን ለማሻሻል መሰናክል ከመሆን አልፈው እንዳይሻሻል የሚገድቡ ሊሆኑ እንደሚችሉ አውስተዋል፡፡ በማሻሻያው ላይ ሊፈጠሩ የሚችሉ ማነቆዎችን፣ በተለይም የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 104 እና 105 ላይ ያሉትን መሥፈርቶች ቀድሞ ማሻሻል አጠቃላይ የማሻሻል ሒደቱን እንደሚያቀለው ተናግረዋል፡፡

ለሕገ መንግሥቱ የማሻሻያ አማራጮች ሊሆኑ ይችላሉ በሚል ካቀረቧቸው ሳይንሳዊና የተለመዱ አሠራሮች መካከል የመጀመርያው፣ ከሕገ መንግሥቱ አለፍ ያለ (Extra Constitutional Model) የተሰኘ መንገድ ነው፡፡ ይህ ሒደት ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ለሕዝብ ጥቅም ሲባል የሚመረጥ አካሄድ መሆኑን፣ በዚህም ሕዝቡ ሕገ መንግሥቱ እንዲሻሻል የሚፈልግ ከሆነ በሕዝብ ስምምነት ሕዝበ ውሳኔ ተደርጎ ወይም በፖለቲካ ምሁራን መካከል ድርድር ተካሂዶ  በሚደረስ ስምምነት ወደ ማሻሻል ሥራ የሚገባበት ነው ብለዋል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ፀረ ሕገ መንግሥታዊ አካሄድ (Anti-Constitutional) የተሰኘ ሲሆን፣ በዚህኛው መንገድ ሊደረግ የሚችለው የማሻሻል ሒደት ሕገ መንግሥቱን በኃይል በማስወገድ ነው በማለት አስረድተዋል፡፡ ይህ ተመራጭ ዘዴ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡ በሦስተኛው ደረጃ የቀረበው አማራጭ ኢሕገ መንግሥታዊ (Unconstitutional) አካሄድ ነው፡፡ ይኼኛውም ዘዴ ሕገ መንግሥታዊ ባልሆነ መንገድ ሕገ መንግሥቱን ማሻሻል ሲሆን፣ ይህም ተመራጭ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሲሳይ (ዶ/ር) እንደሚሉት፣ በተለያዩ አገሮች የተሞከረውና ሳይንሳዊ፣ አራማጅና የተሻለ ተብሎ የሚወሰድው አማራጭ ከሕገ መንግሥት አለፍ የሚለው (Extra Constitutional Model) ሲሆን፣ በዚህ አሠራር ሕዝበ ውሳኔ በማካሄድ በሕዝቡ ድምፅ ውሳኔ መስጠት ተመራጭ ነው፡፡  

ይኼኛውን አማራጭ የተሻለ የሚያደርገው የኢትዮጵያን ሕገ መንግሥት ለማሻሻል በአንቀጽ ተዘርዝረው የተቀመጡት የማሻሻያ መሥፈርቶች ሕገ መንግሥቱን ለማሻሻል እንቅፋት በመሆናቸው፣ በሕዝበ ውሳኔ የሚደረገው የማሻሻያ ዘዴ የተሻለ  በመሆኑ የጋራ መግባባትም ይፈጥራል ብለዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህር ወንድማገኝ ታደሰ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ አሁን ሕገ መንግሥት አለ ወይ ተብሎ በሚጠየቅበት ጊዜ ሥልጣን የያዘው አካል እንደፈለገ ሲጥሰው እንደሚታይ ገልጸው፣ ከዚህም አለፍ ብሎ አንዳንዶች ስለሕገ መንግሥት ሲነሳ የሆነ አንቀጽ በመጥቀስ እሱ ላይ ብቻ በማጠንጠን በሕገ መንግሥቱ ውስጥ ሌላ አንቀጽ ያለ የማይመስላቸው ስለመኖራቸው አስረድተዋል፡፡ ስለዚህ በቀጣይ ሕገ መንግሥት ወደ ማሻሻል ሲገባ አዳዲስ መርሆችን በማካተትና ዘላቂ የሆኑ ተቋማት ግንባታ ላይ በማተኮር፣ ለመጪው ትውልድ የተሻለ ዕሳቤ ሊመነጭ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የሚታየው ፅንፍ ጤነኛ አለመሆኑን በመጥቀስ፣ አንዳንዴ በውይይት የማያምኑ ዓይነት ሰዎች እየታዩ ስለመሆናቸው ወንድማገኝ (ዶ/ር) አብራርተዋል፡፡

ሕገ መንግሥት ይሻሻል ሲባል መታሰብ ያለበት አንቀጽ 39 ወይም የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ከሚለው አንቀጽና ከመገንጠል መብት ጋር ብቻ መገናኘት እንደሌለበት፣ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 39 ከጅምሩ የሚተገበር አንቀጽ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡ ለዚህ ማሳያው መገንጠል በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት ሕጋዊ ነው ወይስ አይደለም የሚል ክርክር ስለመኖሩ በመጥቀስ፣ ‹‹ነገር ግን መልሱ የሚሆነው መገንጠል የሕግ ጉዳይ ሳይሆን የሀቅ ጉዳይ በመሆኑ ጉልበት ካለህ ትገነጠላለህ ከሌለህ ደግሞ በመንግሥት ሕገ መንግሥቱን ለጊዜው በመገደብ ጥያቄው ባለበት እንዲቆም ታደርጋለህ፤›› ብለዋል፡፡

ስለዚህ ሕገ መንግሥት ይሻሻል ሲባል ከአንድ አንቀጽ ጋር የተገናኘ ጥያቄ ብቻ መቅረብ እንደሌለበትና ሕገ መንግሥቱ እንዲሻሻል የሚገፋፉ ሌሎች ጉዳዮች እንዳሉ፣ ለምሳሌ የሰብዓዊ መብት ጉዳይ አተገባበርና አፈጻጸምን በተመለከተ በርካታ ጉዳዮች ሊነሱ እንደሚችሉ ገልጸዋል፡፡ በሌላ በኩል የትርጉም ጉዳይን ያነሱት የሕግ ባለሙያው ለአብነት በሕገ መንግሥቱ ላይ የተጻፈውና በትግበራ ላይ ያለው የብሔር ብሔረሰቦች ዕሳቤ በትግበራ ላይ ያለው አንዱን የሚያጎላና ሌላውን የሚበድል ዓይነት መሆኑን፣ ይህ አሠራር ግን በሕገ መንግሥቱ በጽሑፍ ከተቀመጠው ትርጉም የተለየ ስለመሆኑ ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፌዴራሊዝም ጉዳዮችና የአካባቢያዊ አስተዳደር ተመራማሪው ዘመላክ አየለ (ዶ/ር)፣ ‹‹የሕገ መንግሥት አጨቃጫቂ ጉዳዮች›› በሚል ርዕስ ባቀረቡት የመነሻ ጽሑፍ፣ በሕገ መንግሥቱ የሚያጣሉና የሚያጨቃጭ ብለው ካቀረቧቸው ጉዳዮች መካከል ኢትዮጵያን የሚያይበት መንገድ፣ ውክልናን በተመለከተ ቋንቋና የፌዴራል አወቃቀሩ፣ የሕገ መንግሥት አተረጓጎም፣ የሥልጣንና የሀብት ክፍፍል የሚሉት ይገኙበታል ብለዋል፡፡

በሕገ መንግሥቱ ‹‹የሚጨቃጨቁት እነማን ናቸው›› ለሚለው ጥያቄ፣ ‹‹በዋነኝነት ሁለት ጫፍ የያዙ ቡድኖች ስለመኖራቸውና ለእነዚህም ቡድኖች ዋነኛ ምክንያታቸው ደግሞ በኢትዮጵያ ላይ ያላቸው አተያይ ነው›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡ የመጀመርያው ቡድን ብዝኃነት በአገራዊ አንድነት ውስጥ መካተት እንዳለበትና ይህ አገራዊ አንድነት በሕገ መንግሥቱ እንዲፀና መደረግ አለበት የሚል መሆኑን፣ ሁለተኛው ቡድን ደግሞ መጀመርያ የብሔር ብዝኃነት ላይ ያተኮረ አገራዊ አንድነት መፈጠር አለበት በማለት ያቀነቅናል ብለዋል፡፡

‹‹ሁለቱም ቡድኖች አሁን ባለው ሲስተም ደስተኞች አይደሉም፤›› ብለው፣ ‹‹የመጀመርያው ቡድን የብሔር ብዝኃነት መኖሩንና ነገር ግን ኢትዮጵያ አገረ መንግሥት ናት የሚልና ያለፈ ታሪካችን ማንነታችን ነው፡፡ ቅኝ ገዥዎችን አሳፍረን በመመለስ በአንድነት የኖርን የ3,000 ዓመት ቆንጆ ታሪክ ያለን በመሆኑ፣ ይህንን ታሪክ መጠበቅ አለብን የሚል ነው፡፡ ይህንም ታሪክ በሕገ መንግሥት መረጋገጥ አለበት ብሎ ያምናል፤›› ሲሉ አብራርተዋል፡፡

‹‹ሁለተኛው ቡድን ከ1970 ዓ.ም. ከእነ ዋለልኝ መኮንን እንቅስቃሴ ጀምሮ ሲነሳ የነበረው፣ ኢትዮጵያ የብሔሮች እስር ቤት እንጂ አገር መንግሥት የሚለውን አላሟላችም የሚል፣ አገሪቱ በጉልበትና በኃይል የተፈጠረች ናት የሚል፣ የ3,000 ታሪክ ሳይሆን ከ150 ዓመት ያበለጠ ታሪከ ያለን ነን የሚል ነው፤›› ብለዋል፡፡

ዘመላክ (ዶ/ር) እንደሚሉት፣ አንዳንድ አገሮች የፌዴራል ሥርዓት ሲያቋቁሙ  በሕገ መንግሥታቸው መግቢያ ላይ አገራቸው የማትበተንና የማትከፋፈል መሆኗን በግልጽ ያስቀምጣሉ፡፡ ለዚህም እንደ ምሳሌ የናይጀሪያ፣ የደቡብ አፍሪካና የኬንያ ሕገ መንግሥቶች ናቸው፡፡ በተቃራኒው የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ግን የፌዴራል ሥርዓት ሊበታተን ይችላል፣ በሚልና ኢትዮጵያ የምትባል አገር የሆነ ሰዓት ላትኖር ትችላለች፣ ይህም ችግር የለውም በሚል መነሻ የተቀረፀ ስለመሆኑ ገልጸዋል፡፡

ሁለት ጽንፍ ይዘው ከሚከራከሩት ውስጥ የሁለተኛው ቡድን ፌዴራሊዝሙ አይከፋፈልም አይበታተንም ብሎ በሕገ መንግሥቱ ጽፎ ማስቀመጡ መፍትሔ እንደማይሆን፣ የሚሻለው ሁሉንም ሊያስደስት የሚችል ሥርዓት መዘርጋት እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

በወራቤ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህር አቶ ፉአድ መሐመድ ‹‹ሕገ መንግሥቱ እንዴት ይሻሻል?›› ሲባል ‹‹ማነው የሚያሻሽለው? እንዴት ይሻሻል? የሕዝብ ሚና ምንድነው? የማሻሻሉ ኃላፊነት ለማን የተሰጠ ነው? እስከምን ድረስ ነው የሚሻሻለው? ሙሉ ለሙሉ መተካት?  ወይስ የተወሰነውን አንቀጽ መቀየር?›› የሚሉት በጣም አሳሳቢና በሚገባ መታየት ያለባቸው ጉዳዮች ናቸው ብለዋል፡፡

የወሎ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህር ዘለዓለም እሸቱ (ዶ/ር) ስለሕገ መንግሥት ቅቡልነት ሲነሳ መታሰብ ያለበት፣ የሕገ መንግሥቱ የመኖር ያለ መኖር ሳይሆን፣ ሕገ መንግሥቱ የተሠራበት ሒደትና የአተገባበሩ ሒደት ላይ መሠረት ላይ የሚያጠነጥን መሆን እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ በዚህ ረገድ የሕገ መንግሥት ሥሪት ወሳኝ የሆኑ የፖለቲካ ኃይሎች የተሳተፉበት፣ ማኅረሰቡን አካታች ያደረገ፣ ይዘቱ ከማኅበረሰቡና ከአገሪቱ የፖለቲካና እሴቶች ጋር አብሮ የሚሄድ ከሆነ ቅቡልነትን በተገቢው ሁኔታ ሊያኝ እንደሚችል አስረድተዋል፡፡

ሕገ መንግሥት በሥሪት ወቅት አሳታፊ ካልሆነ ቅቡልነት ሊያጣ እንደሚችል የገለጹት ዘለዓለም (ዶ/ር)፣ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ልኩና ገደቡ የት ድረስ ነው የሚለው ጥያቄ፣ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ በተገቢው ሁኔታ ሊብራራ ይገባል ብለዋል፡፡  በዚህ አሠራር ውስጥ ሕገ መንግሥትን የማሻሻልና የመቀየር ሥልጣን የተሰጣቸው አካላት ገደብ ካልተጣለባቸው አደጋ ሊያመጣ እንደሚችል ጠቁመው፣ ለአብነት ሥልጣን የያዙ አካላት ሕገ መንግሥቱን ለማሻሻል በሚል የመተካት ሥራ (Constitutional Replacement) እንዲያደርጉ ዕድል ይሰጣል ብለዋል፡፡ ‹‹እነዚህ አካላት ሕገ መንግሥቱን የማፍረስ (Democratic Sucide) ውስጥ እንዲገቡ ያደርጋቸዋል፡፡  በመሆኑም በዚህ ሒደት ውስጥ ሕገ መንግሥት አርቃቂዎች ይህን አደጋ ለመቀነስ የሚወስዷቸው ዕርምጃዎች አሉ፤›› በማለት የጠቀሱት ዘለዓለም (ዶ/ር)፣ ሕገ መንግሥትን የመከለስና የማሻሻል ሥልጣን የሚመራባቸው ሥነ ሥርዓታዊ ድንጋጌዎች እንዳሉም ተናግረዋል፡፡ ይህ ማለት ማን ሐሳብ ሊያነሳ ይችላል? ማን ሊያሻሽለው ይችላል? በምን ያህል ድምፅ ሊሻሻል ይችላል? የሚሉትን የሚወስኑ ጉዳዮች በዝርዝር እንደሚቀመጡ አብራርተዋል፡፡ ለምሳሌ በጀርመን የማይነኩ የሕገ መንግሥት አንቀጾች እንዳሉ፣ ከእነዚህ መካከል ዴሞክራሲና የፌዴራሊዝም ሥርዓትን የሚያብራሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

በሥራ ላይ ያለው የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ውስጥ በርካታ የማሻሻያ አንቀጾች የሚነሱበት ቢሆንም፣ ለማሻሻል አስፈላጊ የሆኑ አስቻይ ቅደመ ሁኔታዎችና ተቋማት በበቂ ሁኔታ አለመኖር አከራካሪ እንደሆነም አክለው ተናግረዋል፡፡ ወደ ማሻሻል ሲገባ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 104 እና 105 ላይ የማሻሻያ አማራጮች ተብለው የተቀመጡት ጉዳዮች በቂና አስቻይ አለመሆናቸውን፣ በእንግሊዝኛውና አማርኛው ቅጅ መካከል ያለው ልዩነት በራሱ ክፍተት እንዳለበት አስረድተዋል፡፡

በሕገ መንግሥቱ ላይ የተቀመጡትን የማሻሻያ አማራጮች ለመከተል አስቸጋሪ ስለሚሆን፣ አሁን ያለውን አገራዊ ሁኔታ ማሻሻል እንደማያስፈልግ አክለው ገልጸዋል፡፡ ወደ ሕገ መንግሥት ማሻሻያ የሚገባው በዋነኝነት ለሰላም፣ ለዴሞክራሲና ለአገራዊ ግንባታ ቢሆንም መቼ ይሻሻል የሚለው ጉዳይ በራሱ አጠያያቂና ግጭትን ሊያነሳሳ እንደሚችል አብራርተዋል፡፡ የጊዜ ጉዳይ አጠያቀያቂ መሆኑን ያስረዱት ምሁሩ፣ ከዚህ ቀደም እንደ ምሳሌ እ.ኤ.አ. በ1987 በዩጎዝላቪያ ሰርቦች ሕገ መንግሥቱን ለማሻሻል ሲነሱ፣ በስሎቫኪያና በክሮዋት ፖለቲከኞች መካከል የነበረው ክርክር ለዩጎዝላቪያ መፍረስ በጣም ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል ብለዋል፡፡ ይህም ሊሆን የቻለው በሕገ መንግሥቱ ሰርቦች በነበራቸው ሥልጣን ተጠቅመው በፈጠሩት አቅም የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ሐሳብ ሲያቀርቡ፣ ስሎቫስችና ክሮዋቶች ከዩጎዝላቪያ ለቀው እንዲወጡ ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም በኢትዮጵያ የሕግ ማሻሻያ ሲታሰብ መደረግ ያለበት አገራዊ ስምምነትና የተረጋጋ የሰላም ሁኔታ እንደሚስፈልግ፣ በተጨማሪም በፖለቲካ ምሁራንና በብሔርተኞች መካካል ያለው ጠርዝ በያዘ ክርክርና ነፃ የሆነ እንቅስቃሴ ማድረግ በማይቻልበት ሁኔታ ሕገ መንግሥቱን ለማሻሻልም አመቺ አይደለም ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...