Tuesday, March 28, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ለነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚዎች የቴሌ ብር አካውንት ያልከፈቱ ማደያዎች ነዳጅ እንዳይራገፍላቸው ሊደረግ ነው

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • በሶማ ክልል ካሉ 89 ማደዎች 37 ብቻ በቴሌ ብር ይጠቀማሉ

ከታለመለት የነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚ ተሽከርካሪዎች ጋር የሚኖራቸውን ግብይት ለማቀለጠፍ የቴሌ ብር አካውንት ያልከፈቱና ከፍተውም አገልግሎት እየሰጡ ላልሆኑ የነዳጅ ማደያዎች፣ ነዳጅ እንደማይራገፍላቸው የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡

የታለመለት የነዳጅ ድጎማ ሲጀመር ማደያዎች ከሐምሌ 2014 ዓ.ም. አንስቶ የቴሌ ብር የነዳጅ ድጎማ መተግበርያ አካውንት ከፍተው፣ ከነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚዎች ጋር ግብይቱን በቴሌ ብር ብቻ እንዲያቀላጥፉ ተወስኖ ነበር። ሆኖም የተወሰኑ ማደያዎች እስካሁን የመተግበሪያውን አካውንት ባለመክፈታቸውና የተወሰኑት ደግሞ ከፍተውም ‹‹ከአቅም በላይ ባልሆነ ምክንያት አገልግሎት እየሰጡ ባለመሆናቸው›› ውሳኔውን ማስተላለፉን ባለሥልጣኑ አስታውቋል።

ከማክሰኞ የካቲት 21 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ እንዲሆን የተላለፈው ውሳኔ፣ የካቲት 15 ቀን 2015 ዓ.ም. በባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሳሃርላ አብዱላሂ ተፈርሞ በወጣው ደብዳቤ መሠረት ነው፡፡

ደብዳቤው እስከ የካቲት 20 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ ቀነ ገደብ አስቀምጦ የነበረ ሲሆን፣ እስከ ተጠቀሰው ዕለት ድረስ አካውንቱን ላልከፈቱና መተግበሪያውን መጠቀም ላልጀመሩ ማደያዎች፣ ከጂቡቲ የሚቀርበው ነዳጅ እንዲቋረጥባቸው እንደሚደረግ ያስታውቃል።

ዋና ዳይሬክተሯ ወ/ሮ ሳሃርላ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ አብዛኛዎቹ ማደያዎች መተግበሪያውን በመጠቀም አገልግሎት እየሰጡ እንደሆነና አፈጻጸሙም ከክልል ክልል የሚለያይ ነው። በአሁኑ ጊዜ በአገር አቀፍ ደረጃ አገልግሎት ከሚሰጡ 1,120 ማደያዎች ውስጥ 1,015 ቴሌ ብርን ለግብይት የሚጠቀሙት መሆናቸውን ተመዝግበውም ሥራ ያልጀመሩ የተወሰኑ እንዳሉና ኩባንያዎቻቸውም ከኔትወርክ ጋር በተያያዘ ሥራ አለመጀመራቸውን ሪፖርት እንዳደረጉ ዋና ዳይሬክተሯ ተናግረዋል።

‹‹መመርያው በተላለፈ ጊዜ ኔትወርክ የሌለባቸው አካባቢዎች በቁጥር በርካታ ነበሩ፡፡ አሁን ግን ኢትዮ ቴሌኮም ችግሩን ቀርፎ ሁሉም በሚባል ደረጃ ኔትወርክ አላቸው፤›› ያሉት ወ/ሮ ሳሃርላ፣ እንደ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት አካባቢ ያሉ ማደያዎች ግን አሁንም የኔትወርክ ችግር አለባቸው ብለዋል፡፡

በጥሩ አፈጻጸም ላይ ከሚገኙት አካባቢዎች መካከል አዲስ አበባ አንደኛው መሆኑን፣ ካሉት 141 ማደያዎች 137 ያህሉ በቴሌ ብር ግብይት እንደሚያካሂዱ ገልጸዋል፡፡ በኦሮሚያ ክልል ካሉት 365 ማደያዎች ደግሞ 340 ያህሉ የቴሌ ብርን መተግበርያ በአግባቡ እንደሚጠቀሙ ያስረዱት ዋና ዳይሬክተሯ፣ በአማራ ክልል ካሉት 249 ማደያዎች 239 የሚሆኑት መተግበርያውን እየተጠቀሙ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የተወሰኑ ክልሎች ደግሞ ሙሉ ለሙሉ ባሏቸው ማደያዎች መተግበርያውን እየተጠቀሙት እንደሆነ አክለው ገልጸዋል።

በሶማሌ ክልል ካሉት 89 ማደያዎች 37 ብቻ የነዳጅ ሽያጭ አገልግሎት ቴሌ ብርን በመጠቀም እንደሚሸጡ ዋና ዳይሬክተሯ ገልጸው፣ በአፋር ክልል ካሉት 38 ማደያዎች ደግሞ 23 ናቸው መተግበርያውን የሚጠቀሙበት ብለዋል። ‹‹ሶማሌና አፋር ክልሎች ያሉት ማደያዎች ናቸው ዝቅተኛ አፈጻጸም ያላቸው፤›› ሲሉ የተናገሩት ወ/ሮ ሳሃርላ፣ ነዳጅ ያለማግኘት ችግር ሊገጥማቸው የሚችሉት ተሽከርካሪዎችም በእነዚህ ሁለት ክልሎች ያሉት እንደሚሆኑ ገልጸዋል።

‹‹አሁን ለጊዜው ዕርምጃ እንወስዳለን እያልን ያለነው በቴሌ ብር ባልተመዘገቡና ባልጀመሩት ላይ ነው። በእርግጥ አንዳንድ አካባቢዎች በቴሌ ብር የማይጀምሩት ተደጓሚ መኪና የለም በሚል ምክንያት ነው፡፡ በእኛ በኩል ግን ተደጓሚ መኪና የለም የሚለውን ምክንያት ላለመቀበል ነው ለጊዜው የወሰንነው፤›› ሲሉ ዋና ዳይሬክተሯ ተናግረዋል።

የባለሥልጣኑ ውሳኔ እንደ ሶማሌና አፋር ክልሎች ያሉትን ማደያዎች በአፋጣኝ ወደ አሠራርሩ እንዲካተቱ እንደሚያደርጋቸው የገለጹት ወ/ሮ ሳሃርላ፣ ‹‹የተለያየ ምክንያት ስላላቸው ነው ቴሌ ብር መጠቀም የማይፈልጉት፡፡ ስለዚህ እሱንም ለማስቀረት ይረዳናል፤›› ሲሉ አስረድዋል።

የወረደውን ውሳኔ ተፈጻሚ እንዲያደርግ የታዘዘው የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ነው። የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታደሰ ኃይለ ማርያም ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ትዕዛዙን ተፈጻሚ ለማድረግ ችግር እንደማይኖርባቸውና ነዳጁን አትስጡ ከተባለም ላይሰጡ እንደሚችሉ ተናግረዋል።

ነገር ግን ዋና ሥራ አስፈጻሚው በክልከላ ነዳጅ መስጠት ከቆመ በኋላ ምን ሊከሰት ይችላል የሚለውን ማሰብ እንደሚገባ አሳስበዋል። በመጀመርያ የኢትዮ ቴሌኮም፣ የኩባንያዎችና የማደያዎችን ጨምሮ የሁሉም አካላት ቅንጅት መታየት እንዳለበት የተናገሩት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ መንግሥት ውሳኔ ላይ ደርሶ ችግር ሲፈጠር ውሳኔው ከተቀለበሰ ለአሠራር ስለሚያስቸግር በድጋሚ ጥናት እንዲደረግ አሳስበዋል።

‹‹በአንድ ቀጭን ትዕዛዝ አቁሙ ብንባል እኛ አንጭንም፣ ችግር የለውም፡፡ ነገር ግን ነዳጅ ባይጫን የሚመጣውን ችግር ማሰብ ያስፈልጋል፤›› ሲሉ አቶ ታደሰ አክለዋል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች