Thursday, March 23, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል አዲስ ቦርድ ሰየሙ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ኤግዚቢሽኑን ይመራ የነበረው ምክር ቤት ሥጋት እንዳደረበት ተጠቁሟል

በአዲስ አበባ ንግድ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ቦርድ ሲመራ የቆየው የአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል፣ የከተማ አስተዳደሩ በሾማቸው የቦርድ አባላት እንዲመራ ስምንት አባላት ያሉት ቦርድ በከንቲባ አዳነች አቤቤ መሰየሙ ተገለጸ፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በከንቲባ አዳነች አቤቤ ተፈርሞ በወጣ ደብዳቤ አስተዳደሩ የሰየማቸው ስምንቱ የቦርድ አባላት ማዕከሉን በበላይነት እንዲመሩ የተሰየሙ መሆናቸውን ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በአስተዳደሩ የተሰየመውን ቦርድ በሊቀመንበርነት እንዲመሩም የከተማ አስተዳደሩ የንግድ ቢሮ ኃላፊ አቶ አደም ኑር የተመደቡ መሆኑ ታውቋል፡፡

በአዲሱ ቦርድ የአስተዳደሩ የተለያዩ ቢሮ ኃላፊዎች የተካተቱ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ የሰላምና ደኅንነት ቢሮ ኃላፊዋ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ፣ የኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊው አቶ ግርማ ሰይፉ እና የካቢኔ ጉዳዮች ኃላፊው እንደተካተቱበት እኚሁ ምንጫችን ገልጸዋል፡፡

አስተዳደሩ ከንግድ ምክር ቤቱ ጋር በነበረው ስምምነት መሠረት፣ ኤግዚቢሽን ማዕከሉን ለማስተዳደር ሙሉ ኃላፊነቱን ለንግድ ምክር ቤቱ ሰጥቶ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ አሁንም ንግድ ምክር ቤቱ ይህንን ሥራ እየሠራ ቢሆንም፣ እስካሁን ባልተለመደ ሁኔታ የቦርድ አባላት መሰየሙ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡

አስተዳደሩ ለኤግዚቢሽን ማዕከሉ ቦርድ ሲሰይም የመጀመርያ ጊዜ መሆኑን የጠቀሱት ምንጮቻችን፣ እስካሁን ማዕከሉ በንግድና ዘርፍ ማኅበራት ቦርድና ቦርዱ ባቋቋመው ንዑስ ቦርድ ይመራ ነበር፡፡ ተጠሪነቱም በቀጥታ ለአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ቦርድ እንደነበር አስታውቀዋል፡፡

የማዕከሉ ሥራ አስኪያጅም ከዚህ ቀደም የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ይሰይም እንደነበር ያስታወሱት ምንጮቹ፣ ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) ወደ ኃላፊነት ከመጡ በኋላ በቀጥታ ለማዕከሉ ሥራ አስኪያጅ መሾማቸውን ይናገራሉ፡፡ እንዲህ ያሉ ተከታታይ ዕርምጃዎች በንግድ ምክር ቤቱና በአስተዳደሩ መካከል ከ18 ዓመታት በላይ የዘለቀውን በጋራ የሚሠሩትን ሥራ ጥያቄ ውስጥ ሊከተው እንደሚችልም ምንጮቹ ይጠቁማሉ፡፡

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትና በከተማው አስተዳደር መካከል በተደረሰ ስምምነት መሠረት፣ ንግድ ምክር ቤቱ ከኤግዚቢሽን ማዕከሉ ሌላ በቅርቡ የመስቀል አደባባይ ፓርኪንግና ተያያዥ አገልግሎቶችን እንዲያስተዳድር ፈቅዶለት እየሠራ የሚገኝ መሆኑ ይታወቃል፡፡

በጉዳዩ ዙሪያ የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤትን ለማነጋገር ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች