Thursday, March 23, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ያለፍርድ የታሰሩ ሰዎች ሕክምና መከልከላቸው ተገለጸ

በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ያለፍርድ የታሰሩ ሰዎች ሕክምና መከልከላቸው ተገለጸ

ቀን:

  • ያለፍርድ የታሰሩ ሰዎችን የሰብዓዊ መብት ጥሰት መንግሥት እንዲያስቆም ኢሰመጉ ጠይቋል

በወልቃይ ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ከ2013 ዓ.ም. ጀምሮ ያለፍርድ የታሰሩ የአካባቢው ነዋሪዎች፣ ሕክምና እንዳያገኙ መከልከላቸውን የታሳሪ ቤተሰቦች ገለጹ፡፡

የታሳሪ ቤተሰቦች ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ያለምንም ከሳሽና ያለፍርድ ከታሰሩት ሰዎች መካከል የታመሙ ሰዎች እንዳሉ ገልጸው፣ ወደ ሕክምና ለመውሰድ ቢፈልጉም መከልከላቸውን አስረድተዋል፡፡

ከታሳሪዎቹ መካከል በወባ በሽታ የተጠቁ ሰዎች በመኖራቸው ወደ ሕክምና ለመውሰድ የሚመለከታቸውን አካላት ቢጠይቁም እንዳልተፈቀደላቸው አክለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) በበኩሉ በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ያለፍርድ የታሰሩ ሰዎች እንግልትና ድብደባ እየደረሰባቸው መሆኑን ሰኞ የካቲት 20 ቀን 2015 ዓ.ም. ባወጣው አስቸኳይ ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል፡፡

ኢሰመጉ በመግለጫው ‹‹መንግሥት በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን በፍርድ ቤትና ዓቃቤ ሕግ ዕጦት ምክንያት እየተጣሰ ያለውን ፍትሕ የማግኘት መብትና እየደረሰ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲያስቆም›› ሲል ጠይቋል፡፡

በሰሜን ኢትዮጵያ በነበረው የሰላምና ፀጥታ ችግር ምክንያት የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አስተዳደር የፈረሰ መሆኑን የጠቀሰው ኢሰመጉ፣ ከ2013 ዓ.ም. ጀምሮ እንደ አዲስ የዞን አስተዳደር ቢቋቋምም፤ በአካባቢው የፍርድ ቤትና አቃቢ ሕግ ቢሮዎች ተቋቁመው ሥራ ባለመጀመራቸው በአካባቢው ሰዎች ያለአግበብ እስር እየተፈጸመባቸው መሆኑን አስታውቋል፡፡

ለእስር የተዳረጉ ሰዎች ያለምንም ከሳሽ በፖሊስ ጣቢያ እንግልትና ድብደባ እየደረሰባቸው ለረዥም ጊዜ ማለትም ከሁለት እስከ ዘጠኝ ወራት ታስረው እንደሚገኙ ኢሰመጉ ካሰባሰባቸው መረጃዎች ለማወቅ መቻሉን በጋዜጣዊ መግለጫው አስፍሯል፡፡

በአካባቢው የሚገኙ እስረኞች ክስ ሳይመሰረትባቸውና ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ከሁለት ወር እና ከዚያ በላይ ታስረው እንደሚገኙ የጠቀሰው ኢሰመጉ፣ የገንዘብ አቅምና ቤተሰብ ያላቸው የተወሰኑ እስረኞች ወደ ጎንደር ከተማ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምድብ ችሎት በመቅረብና የአካል ነፃነት አቤቱታ በማቅረብ መለቀቅ መቻላቸውን ጠቁሟል፡፡

ነገር ግን በአካባቢው ያለው የአስተዳደር አካል በተደጋጋሚ የዋስትና መብታቸው እንዲጠበቅ ትዕዛዝ የተሰጠላቸውን ሌሎች እስረኞችን ለመልቀቅ ወይም የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ ለማክበር ፈቃደኛ ባለመሆኑ፣ ጥቅምት 24 ቀን 2015 ዓ.ም. የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጎንደር ምድብ ችሎት ጉዳዩ ከአቅሙ በላይ መሆኑን ገልጾ የሚመለከተው አካል መፍትሔ እስኪሰጥ ድረስ ይህንን ጉዳይ እንደማያስተናግድ የሚገልጽ ማስታወቂያ በማውጣት ያሳወቀ መሆኑን፣ ይህ ጉዳይ የሰዎችን ፍትህ የማግኘት መብት ለማስጠበቅ የፍትህ ተቋማት ሥራቸውን በአግባቡ መሥራት ባለመቻላቸው ያለ ከሳሽ በፖሊስ ጣቢያ የታሰሩ ሰዎች እንግልትና ድብደባ እየደረሰባቸው መሆኑን በመግለጫው ተመላክቷል፡፡

በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የሚመለከተው የፍትሕ አካል፣ በፍርድ ቤት የዋስትና መብታቸው እንዲጠበቅ ትዕዛዝ የተሰጠላቸውን እስረኞች በአስቸኳይ እንዲፈታ፣ የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አስተዳደር ለረዥም ወራት ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ታስረው የሚገኙትን ሰዎች ፍርድ ቤት በማቅረብ፣ ፍትሕ የማግኘት መብታቸውን እንዲያስጠብቅ ኢሰመጉ ጠይቋል፡፡

ኢሰመጉ በሌላ በኩል በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ዋግኸምራ ዞን፣ በሰቆጣና አካባቢው፣ በሰሜን ሸዋ ዞን በደብረ ብርሃን ከተማና አካባቢው ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተፈናቃዮች ከተለያዩ አካባቢዎች በግጭት ምክንያት ተፈናቅለው፣ በከፍተኛ ርሃብና ችግር ውስጥ መሆናቸውን ጠቅሶ፣ ከመንግሥት በኩል እየተደረገ ያለው ድጋፍ እጅግ አነስተኛ በመሆኑ መንግሥት ተገቢውን በቂ ትኩረት እንዲሰጥ አሳስቧል፡፡

በተያያዘም፣ በኦሮሚያ ክልል በቦረና ዞንና አዋሳኝ አካባቢዎች ላይ በተከሰተው ድርቅ ምክንያት በርካታ የቀንድና የጋማ ከብቶች የሞቱ ሲሆን እስካሁን የሰው ሕይወት አለመጥፋቱን የሚመለከተው የኦሮሚያ ክልል መንግሥት አካል ቢገልጽም፣ ችግሩ ግን በዚህ የሚቀጥል ከሆነ በማኅበረሰቡ ላይ የሚፈጠረውን ችግር የከፋ ስለሚያደርገው መንግሥት ለጉዳዩ በቂ ትኩረት እንዲሰጥ ኢሰመጉ ጠይቋል፡፡

ኢሰመጉ አክሎም ‹‹የኦሮሚያ ክልል መንግሥት በድርቁ ምክንያት ለተፈናቀሉና ከፍተኛ ችግር ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች አስቸኳይ ድጋፍ እንዲያደርግ›› በመግለጫው ጠቅሷል፡፡

ዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ቃል ኪዳን (ICCPR) አንቀጽ 9 ንዑስ አንቀጽ 3 በወንጀል ክስ የተያዘ ወይም የታሰረ ሰው ከዳኛ ወይም በሕግ ሥልጣን ከተሰጠው አካል ዘንድ፣ በአፋጣኝ ሊቀርብ እንደሚገባ እንደሚደነግግ ኢሰመጉ በመግለጫው አካቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...