የእንስሳት መድን ዋስትና ፖሊሲ ማዕቀፍ አለመኖር፣ የመድን አገልግሎት በሁሉም አርብቶ አደር አካባቢዎች ተደራሽ ማድረግ አለመቻሉን፣ ዓለም አቀፍ የእንስሳት ምርምር ተቋም፣ የማኅበረሰብ ተነሳሸነት አመቻች ዕርዳታ (CIFA) እና አዩዳ ኢን አክሲዮን ኢትዮጵያ የተሰኙ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች አስታወቁ፡፡
በአርብቶ አደር አካባቢዎች በጥቂት ወረዳዎች ሲተገበር የቆየው የእንስሳት መድን አገልግሎት፣ በመላው ኢትዮጵያ ተግባራዊ ለማድረግ የፖሊሲ ማዕቀፍ አለመኖር እንቅፋት ሆኖብናል ብለዋል፡፡
የዓለም አቀፍ የእንስሳት ምርምር ተቋም የእንስሳት ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ዋቆ ሶራ እንደተናገሩት፣ በኢትዮጵያ ሁሉም የኢንሹራንስ ዓይነቶች ጠቅላላ ፖሊሲ አላቸው፡፡
ነገር ግን የአንስሳት መድን አገልግሎት የሚያግዝና የሚደግፍ ፖሊሲ አለመኖሩን ጠቁመው፣ የመድን አገልግሎቱን ከአንድ ኢንሹራንስ ኩባንያ ውጪ ሌሎች ኩባንያዎች አልተሳተፉም ብለዋል፡፡
የእንስሳት ኢንሹራንስ አገልግሎት እስካሁን በሙከራ ደረጃ ተግባራዊ ሲደረግ መቆየቱን፣ ሙከራው ቢሳካም በፖሊሲ የተደገፈ ባለመሆኑ በመላው አገሪቱ ተደራሽ አልሆነም ሲሉ አስረድተዋል፡፡ ዘርፉ በፖሊሲ ማዕቀፍ ቢደገፍ ለኢንሹራንስ ኩባንያዎች ጠቃሚ መሆኑን፣ መንግሥትም ቢሆን በድርቅ ሳቢያ በአንዴ የሚያወጣውን ገንዘብ በግማሽ ለመቀነስ እንደሚያግዘው ገልጸዋል፡፡
የእንስሳት ኢንሹራንስ እስከ ዛሬ እንደ ማኅበረሰብ ግዴታ እየተወሰደ መሆኑን የተቆሙት አቶ ዋቆ፣ እንደ ቢዝነስ ታይቶ ትኩረት ሊሰጠውና ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ማሳየት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
እንደ አቶ ዋቆ ገለጻ፣ የእንስሳት ኢንሹራንስ አገልግሎት ግብረ ሰናይ ድርጅቶች፣ አርብቶ አደሮችና የኢንሹራንስ ኩባንያ ብቻ የሚሳተፉበት በመሆኑ በዘላቂነት ማስፋፋት አልተቻለም፡፡
የኢንሹራንስ አገልግሎት ከሚሰጥባቸው ጥቂት ወረዳዎች ከሙከራ አልፎ የመንግሥት ፕሮግራም ሆኖ እንዲቀጥል፣ የግድ በፖሊሲ መደገፍ አስፈላጊ ነው ሲሉ የፕሮግራም አስተባባሪው ይናገራሉ፡፡
አሁን ባለበት ሁኔታ በኦሮሚያ ሁለት ዞኖች፣ በደቡብ ክልል አንድ ዞን ብቻ ተግባራዊ እየተደረገ ያለው የእንስሳት ኢንሹራንስ፣ የእንስሳት ሀብትን ለመጠበቅ በሁሉም አካባቢዎች ተግባራዊ መደረግ እንዳለበት ያሳስባሉ፡፡
የአዩዳ ኢን አክሲዮን ኢትዮጵያ የፕሮግራም ዳይሬክተር አቶ ኤርሚያስ ታደሰ በበኩላቸው፣ በኢትዮጵያ የቀንድ ከብቶች ከድርቅና ከሌሎች ችግሮች ለመታደግ የእንስሳት ኢንሹራንስ በፖሊሲ ማዕቀፍ በመንግሥት ደረጃ ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡ ለዚህ እንደ ምክንያት ያነሱት በቦረና የተከሰተው ድርቅ ሲሆን፣ የእንስሳት ኢንሹራንስ በፖሊሲ ማዕቀፍ ቢደገፍ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ከብቶችን መታደግ እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ለ12 ዓመታት በግብረ ሰናይ ድርጅቶች በፕሮጀክት ደረጃ ተግባራዊ እየተደረገ ያለው የእንስሳት ኢንሹራንስ አገልግሎት፣ መንግሥት በባለቤትነት ቢመራው ለአገር ኢኮኖሚ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል፡፡
ግብረ ሰናይ ድርጅቶች የእንስሳት ኢንሹራንስ በፖሊሲ ማዕቀፍ ቢታገዝ ለአገር ውስጥ ምርት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ይላሉ፡፡ በእንስሳት ኢንሹራንስ አገልግሎት እየሰጠ ያለው የኦሮሚያ ኢንሹራንስ ኩባንያ መሆኑን ጠቁመው፣ የፖሊሲ ማዕቀፍ ቢኖረው 18 የኢንሹራንስ ኩባንያዎች አገልግሎቱን ይሰጡ እንደነበር ተናግረዋል፡፡
በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳትና የዓሳ እርባታ ዘርፍ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ጽጌረዳ ፈቃዱ፣ የግብርና ሚኒስቴር ከዚህ ቀደም ሲሠራበት የቆየው የገጠር ልማት ፖሊሲ መኖሩን፣ ይህም በእንስሳት መድን አገልግሎት ላይ ብዙ ክፍተቶች እንዳሉት ገልጸዋል፡፡
እነዚህንም ክፍተቶች ለመሙላት ሚኒስቴሩ በሥሩ ለሚገኙ 22 ዘርፎች የፖሊሲ ማዕቀፎች እያዘጋጀ መሆኑን ጠቁመው፣ ከእነዚህ ውስጥ የእንስሳት መድን ፖሊሲ አንድ መሆኑን ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ተናግረዋል፡፡
ምንም እንኳን የእንስሳት መድን አገልግሎት ፖሊሲ ማዕቀፍ ራሱን ችሎ ያልተዘጋጀ ቢሆንም፣ ከሌሎች ዘርፎች ጋር ያለውን ችግሮች ለመፍታት እየተሠራ ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡