Tuesday, March 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊለፍጆታ የሚውል ወተት ከደረጃ በታች በመሆኑ በኅብረተሰቡ ጤና ላይ አደጋ መጋረጡ ተገለጸ

ለፍጆታ የሚውል ወተት ከደረጃ በታች በመሆኑ በኅብረተሰቡ ጤና ላይ አደጋ መጋረጡ ተገለጸ

ቀን:

  • ፓስቸራይዝድ የተደረጉ ወተቶችም ክፍተት እንዳለባቸው ጥናቱ አመላክቷል

በኢትዮጵያ ለፍጆታ የሚውለው ወተት ጥራትና ደኅንነቱ ከደረጃ በታች ከመሆኑ ባሻገር፣ ለሞት የሚዳርጉ ባክቴሪዎችን ያዘለ በመሆኑ፣ በኅብረተሰቡ ጤና ላይ አደጋ መጋረጡን ኢንሹር የተባለ ፕሮጀክት ባጠናው ጥናት መረጋገጡ ተገለጸ፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምግብ ሳይንስና ኑትሪሽን ማዕከል ከቢልና ሚሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽንና ከእንግሊዝ መንግሥት በተሰጠው አንድ ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ፣ የኢንሹር ፕሮጀክትን ባለፉት አራት ዓመታት፣ በኢትዮጵያ አራት የወተት መገኛ ናቸው በተባሉ ክልሎች፣ የወተት ጥራት ችግር ዓይነትና ምንጮችን ለመለየት፣ ከወተት አምራች ገበሬዎች ጀምሮ ወተት አቅራቢዎች፣ አቀናባሪ ፋብሪካዎችንና ተጠቃሚዎች ድረስ ያለውን የገበያ ሰንሰለት የተከተለ ሰፊ ጥናት ማድረጉን አስታውቋል፡፡

በሰሜን ኢትዮጵያ በተካሄደው ጦርነት በትግራይ ክልል የተጀመረው ጥናት ሲቋረጥ፣ ለቀሪዎቹ ክልሎች በተደረገው የፕሮጀክት ጥናት በወተት አመራረት፣ አቀነባበርና ግብይት ዙሪያ የሚታዩ ችግሮች በተጠቃሚዎች ላይ የጤና ችግር የሚፈጥሩ መሆናቸውን የኢንሹር ፕሮጀክት ጥናት አሳይቷል፡፡

የኢንሹር ፕሮጀክት መሪ አሻግሬ ዘውዱ (ዶ/ር) ማንኛውም ወተት ሲታለብ ከባክቴሪያ ነፃ እንዳልሆነ፣ ወተት በውስጡ መያዝ ያለበት የባክቴሪያ መጠን በሳይንስ የተቀመጠ መሆኑን፣ በኢትዮጵያ ጥሬ ወተት ሲታለብ አንስቶ የባክቴሪያ ይዘቱ ከፍተኛ ስለሚሆን በሰንሰለቱ ላይ ችግሩ በዚያው ልክ እየቀጠለ እንደሚሄድ አስታውቀዋል፡፡

ከባክቴሪያ ዓይነቶች ‹‹ካምፒሎባክተር›› የሚባለው አደገኛ ባክቴሪያ በወተት ውስጥ ፈፅሞ ሊገኝ የማይገባውና ከበዛ የነርቭ በሽታ የሚያስከትል እንደሆነ፣ ይህ በወተትና በወተት ተዋፅኦ ውስጥ የሚገኝ ባክቴሪያ ለአብነትም ጥናቱ በተደረገባቸው ክልሎች በናሙና በተሰበሰቡት ወተቶች ላይ 16 በመቶ ያህል መገኘቱ ተጠቅሷል፡፡

“ሊስቴሪያ ሞኖ ሳይቶጂንስ” ሌላው ገዳይ ባክቴሪያ ከ12 እስከ 14 በመቶ በወተት ውስጥ እንደሚገኝ የተረጋገጠ ሲሆን፣ ባክቴሪያው በቀዝቃዛ ቦታ ውስጥ ሊቆይ የሚችል መሆኑ ሌላው ስለአደገኝነቱ የቀረበ ማስረጃ ነው፡፡

የባክቴሪያዎቹ መብዛት በራሱ የፀረ ተህዋስያን መላመድ መፍጠሩ የተገለጸ ሲሆን፣ ሰዎች የሚወስዷቸው ፀረ ተህዋስያን መድኃኒቶች ባክቴሪያዎቹን መግደል የማይችሉበት ደረጃ ላይ መድረሳቸው በጥናቱ ተመላክቷል፡፡

ለፍጆታ የሚቀርበው ወተት ከውኃ ጋር ስለሚቀላቀል የንጥረ ነገር ይዘቱን እንደሚያጣ፣ የመጨረሻው ተጠቃሚ እጅ ላይ የሚደርሰው ወተት ከመልኩ ውጪ ንጥረ ነገሩን ያጣ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በኢትዮጵያ የጥሬ ወተት አያያዝ ከአላቢ እስከ አቀናባሪ፣ እንዲሁም እስከ ተጠቃሚ ባለው ሒደት የንፅህና አያያዝ ችግሮች ያሉበትና ሆነ ተብሎ ምርቱ ከውኃ ጋር እንዲቀላቀል እንደሚደረግ፣ ከአላቢ እስከ ተጠቃሚ በሚደረገው ሒደት የአያያዝ ችግር ያለበት በመሆኑ በዚህም የአገሪቱ የወተት ጥራትና ደኅንነት ከደረጃ በታች ነው ተብሏል፡፡ የፕሮጀክቱ ባለሙያና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ የሆኑት አልጋነሽ ቶላ (ዶ/ር) ከፍተኛ ትኩረትና የፖሊሲ ዕርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባ አስታውቀዋል፡፡

ፓስቸራይዝድ ናቸው የሚባሉት ወተቶች በራሳቸው ክፍተት ያለባቸው መሆኑን ጥናቱ ያሳየ ሲሆን፣ ይህም የሆነው ፋብሪካዎች ወተት አቀነባብረው ከጨረሱ በኋላ ባክቴሪያዎች መሞታቸውን የመከታተያ ሥርዓትና አሠራር ስለሌላቸው መሆኑን አሻግሬ (ዶ/ር) አስታውቀዋል፡፡

ወተትን ጨምሮ የምግብ ጉዳይ ከፍተኛ ፍጥነትና ሥራ ይፈልጋል ያሉት አሻግሬ (ዶ/ር)፣ በዚህም መንግሥት የጉዳዩን አሳሳቢነት ተረድቶ የፖሊሲና የስትራቴጂ ዕቅድ ሊኖረው እንደሚገባው ገልጸዋል፡፡

መንግሥት “የሌማት ትሩፋት” በሚባል የእንስሳት ተዋፅኦ ምርቶችን ለማምረት የጀመረው ጥረት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በዚህ ጥረት ውስጥ ማምረት ብቻ ሳይሆን የተመረተው ጥራትና ደኅንነቱ የተጠበቀ ነው የሚለውን አብሮ ማካተት እንደሚገባ ተመራማሪው አክለዋል፡፡

የኢንሹር ፕሮጀክት ጥናት ውጤት እንደሚያመለክተው፣ ዘርፉ የግል ባላሀብቶችን ጠንካራ ተሳትፎ ይፈልጋል፡፡ ምርጥ የወተት ላሞችን በብዛትና በጥራት ለማራባት በቂና ተስማሚ ቦታና ሁኔታዎች ሊቀናጁ እንደሚገባ፣ ለወተት ላሞች ጥራቱን የጠበቀ የመኖና ዘመናዊ የወተት ማምረቻ ተስማሚ ቦታ ማመቻቸት እንደሚገባ፣ በተጨማሪም ብሔራዊ የወተት ዘርፍ ኮሚቴ ሊቋቋም ይገባል ተብሏል፡፡

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ደኤታ አቶ እንዳለው መኮንን ማክሰኞ የካቲት 14 ቀን 2015 ዓ.ም. በሂልተን ሆቴል በተሰናዳው መድረክ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ የወተትና የወተት ተዋፅኦ የኢትዮጵያ ደረጃ ተዘጋጅቶ መፅደቁን አስታውሰዋል፡፡

አቶ እንዳለው አክለውም አስገዳጅ የኢትዮጵያ ደረጃዎቹ በሚተገበሩት ወቅት በተደረገው ቁጥጥር ወተት ከእንስሳት ዕርባታ፣ የመኖ ጥራትና ደኅንነት፣ ከጥሬ ወተት አቅርቦትና አሰባሰብ ሥርዓት፣ በእሴት ሰንሰለቱ እየታዩ ባሉ የተለያዩ ችግሮች፣ እንዲሁም በፋብሪካዎች የአሠራር ሥርዓት ችግር ምክንያት አብዛኞቹ የወተት ፋብሪካዎች የተቀመጠውን ብሔራዊ አስገዳጅ መሥፈርቶች አለማሟላታቸውን ሚኒስቴሩ ከኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን በጋራ በተደረገ የዳሰሳ ጥናት ተረጋግጧል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ከሚገኘው የላም ወተት ምርት ከ55 እስከ 65 በመቶ የሚሸፈነው ከኦሮሚያ ክልል እንደሚገኝና አማራ፣ ደቡብና ትግራይ ክልሎች በቅደም ተከተል አምራች መሆናቸው ኢንሹር ፕሮጀክት በጥናቱ ጠቅሷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹ከኦነግ ሸኔ ጋር ያለውን ግጭት በሰላም ለመፍታት ከፍተኛ ፍላጎት አለን›› ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ

መንግሥት ከ‹‹ኦነግ ሸኔ››ጋር ያለውን ግጭት በሰላም ለመፍታት ከፍተኛ ፍላጎት...

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...