በአበበ ፍቅር
ነገሥታት በዘመናቸው በርካታ ሁነቶችን አሳልፈውበታል፡፡ ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ (1847-1860) የአንድነት ግዛታቸውን ለማስፋት ወደ ወሎ በመዝለቅ ጀሜ ተራራ ላይ ከትመው እንደነበር ታሪክ ያስረዳል፡፡ ከአፄው ኅልፈት በኋላ ንጉሥ ምኒልክ ወሎን ወደ ግዛታቸው ለማጠቃለል ሲሉ በወቅቱ የወሎ ራሶች በነበሩት በአመዴ ሊበን (አባ ዋጠው) እና በመሐመድ ዓሊ በኋላ ንጉሥ ሚካኤል ላይ ዘምተው እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡
አፄ ዮሐንስ አራተኛም (1864-1881) ወደ ወሎ በማቅናት ወሎን ወደ ግዛታቸው ለማጠቃለል ጥረት ሲያደርጉ እንደነበርና ከዚያም አልፈው ሁለቱን የወሎ ራሶች አመዴ ሊበንንና መሐመድ አሊን ቦሩ ሜዳ ላይ አስቀምጠው አመዴ ሊበንን ራስ ወልደማርያም፣ መሐመድ ዓሊን ራስ ሚካኤል ተብለው እንዲሰየሙ አድርገዋል፡፡
ወሎን ወደ ግዛታቸው ለማጠቃለል ከፍተኛ ፍላጎት እንደነበራቸው የሚነገርላቸው ንጉሥ ምኒልክ ከአፄ ዮሐንስ ጋር ለመነጋገር ወደ ትግራይ ሲያቀኑ ባለቤታቸውን እቴጌ ጣይቱን በያኔው ጀሜ ተራራ፣ በአሁኑ አይጠየፍ ባለቤታቸውን እቴጌ ጣይቱን ለሁለት ወር ያህል አስቀምጠዋቸው ነበር፡፡
አፄ ዮሐንስም በዘመናቸው ቦሩ ሜዳ ድረስ በመዝለቅ ከአካባቢው መሪዎች ጋር የግዛት ስምምነት ፈጽመው እንደነበር ድርሳናት ያሳያሉ፡፡
ሦስቱ ነገሥታት በተለያዩ ምክንያት ወደ አካባቢው ከመዝለቃቸው በተጨማሪ ሌሎቹ አካባቢዎች የስበት ማዕከል እንድትሆን ምክንያት የሆነው አካባቢው የንግድ እንቅስቃሴ ዋና ኮሪደር መሆኑ ነበር፡፡
ከተማዋ ለወደብ ቅርብ ከመሆኗ ጋር ተያይዞ የንግድ እንቅስቃሴው በአራቱም ማዕዘን በኩል አመቺ በመሆኑ ማለትም በጦጣ በር በኩል ወደ ትግራይና አስመራ፣ በገራዶ በኩል ወደ ሸዋና ጎጃም፣ በኩታ በር ባለው ደግሞ ወደ በጌምድር ወይም ወደ ጎንደር፣ በቅርቅር በር በኩል ወደ ላስታና ሌሎችም አካባቢዎች በከፍተኛ ሁኔታ የንግድ እንቅስቃሴ ይደረግበት እንደነበር ታሪክ ይናገራል፡፡
ለደሴ ከተማ መቆርቆር በተለያየ ወቅት በጀሜ ተራራ በአሁኑ አይጠየፍ ላይ ቆይታቸውን ያደረጉ ነገሥታትና ቤተሰቦቻቸው ምክንያቶች ናቸው፡፡ በተለይ ደግሞ ለደሴ ከተማ መመሥረት በዋነኛነት የሚጠቀሱት ንጉሥ ሚካኤል ናቸው፡፡
ንጉሥ ሚካኤል ወሎን ለማስተዳደር በ1885 ዓ.ም. አካባቢ ንግሥና ሲሰጣቸው የንግድ መተላለፊያ ዋነኛ ማዕከል መሆኑን፣ አካባቢው ለሰው ልጅ መኖሪያ ምቹና ለኑሮ አስፈላጊ የሆኑ የግብርና ምርቶች የሚመረቱበት፣ በቂ ውኃና ሌሎች መሠረታዊ የሆኑ ነገሮችን በመያዙ እንዲሁም የጦሳና የአዝዋ ተራሮችን ውበት በማየትና በማጤን መቀመጫቸውን በቋሚነት እንዳደረጉ ይነገራል፡፡
በዚህም በ1880ዎቹ መጨረሻና በ1900ዎቹ መጀመሪያ ላይ የታላቁ የአይጠየፍ ቤተ መንግሥትና አዳራሽ መገንባት በሳምንት አንድ ጊዜ ግብይት የሚካሄድበት ታላቁ የሰኞ ገበያ መቋቋም፣ በ1913 ዓ.ም. አካባቢ የደሴ ከተማ በሠፈር ሹሞች ተከፋፍሎ የመጀመሪያው አስተዳደራዊ መዋቅር መጀመሩ፣ እንዲሁም ንጉሥ ሚካኤል ኋላ ወ/ሮ ስሂን፣ እቴጌ መነንና መምህር አካለ ወልድ የመሳሰሉ ዘመናዊ የትምህርት ተቋማት መመሥረት ለደሴ ከተማ መስፋፋትና መዘመን እንደ ዋነኛ ምክንያት ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ከተመሠረተች አንድ መቶ ሃያ ገደማ ዕድሜ ያስቆጠረችው ደሴ የቀድሞ መጠሪያዋ ላኮመልዛ ትባል እንደነበር ተነግሮላታል፡፡
ደሴ የሚባለውን ስያሜ ማን እንደሰጣት መደምደሚያ ባይገኝም የተለያዩ መላምቶች ይጠቀሳሉ፡፡
አፄ ዮሐንስ ወደ አካባቢው በዘለቁበት ወቅት አካባቢውን ሲቃኙ በልምላሜውና በተፈጥሮአዊ አቀማመጡ ስለተማረኩ ‹‹ደስ›› የሚል ቦታ ነው ሲሉ ደስ ብሎኛል በማለት ደስታቸውን ሲገልጹ በዚያው ‹‹ደሴ››ም የአሁኗን መጠሪያዋን አገኘች ይላሉ፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ከሳቸው በፊት የነበሩት አፄ ቴዎድሮስ በአካባቢው ዘልቀው ጀሜ አካባቢ በሰፈሩበት ወቅት ድንኳናቸውን ተክለው ነበር፡፡ በጊዜው የተከሉት ድንኳንም ‹‹ደስታ›› የሚል ስያሜ ነበራት፡፡ ከዚህ ድንኳን ጋር በማገናኘት ‹‹ደሴ›› እንደተባለችም ይነገራል፡፡
ደሴ የበርካታ ባህላዊና ተፈጥሮአዊ የመስህብ ሀብቶች ባለቤት ናት የጦሳ ተራራ፣ ታሪካዊ መስጅድና ቤተ ክርስቲያን፣ የአራቱ ቅኝቶች ባቲ፣ አንቺ ሆዬ፣ ትዝታና አምባሳል መገናኛ ናት፡፡ የወሎን ወግና ባህል የቀደምት ማንነትና ያለፉትን ነገሥታት መገልገያ፣ የአካባቢውን የቀደምት ሥልጣኔ፣ የአካባቢውን የቀድሞ ሥልጣኔ፣ በ1960ዎቹና 70ዎቹ የነበረውን ረሃብን ጨምሮ ሌሎችን የወሎና በአጠቃላይ የክልሉን ታሪካዊ መስህብ ጠቅልሎ የያዘው የቀድሞው የወሎ የአሁኑ የደሴ ሙዚየም አንዱ ነው፡፡
ሙዚየሙ ከደሴ ወደ አዲስ አበባ መውጫ በስተቀኝ የሚገኝና በተለምዶ ‹‹ዲቪዥን›› በመባል የሚጠራው ኮረብታ ላይ በ1909 ዓ.ም. እንደተሠራ የሚነገርለት የደጃዝማች ዮሴፍ ብሩ መኖሪያ የነበረ ሕንፃ ነው፡፡
ሙዚየሙ የተለያዩ ታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶች በአካል የሚታዩበት ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ብቻ ከሚገኙት ብርቅዬ የዱር እንስሳት መካከል የስሜን ቀይ ቀበሮ፣ ጭላዳ ዝንጀሮና ሌሎች የተለያዩ እንስሳት የውስጥ አካላቸው ወጥቶ ውጫዊ የተፈጥሮ አካላቸው ሳይዛባ ‹‹በታክሲ ደርሚ›› ጥበብ ደርቀው ለዕይታ የቀረቡትና በርካታ ገላጭ ፎቶግራፎች የሚገኙበት ሙዚየም ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ሙዚየሙ በርካታ ታሪካዊ ቅርሶች ለአብነትም በዳግማዊ አፄ ምኒልክ (1981-1906) የነበረው፣ የስልክ መነጋገሪያ፣ አፄ ቴዎድሮስ ራሳቸውን ያጠፉበት ሸጉጥ፣ ናስማስር አምሳያ፣ የንጉሥ ሚካኤል ሰዓትና ማበጠሪያ፣ 3.5 ሚሊዮን ዕድሜ ያስቆጠረ የዝሆን ጥርስ፣ ከ450 ዓመት በላይ ያስቆጠሩ የሸክላ ዕቃዎች የሚገኙበትም ነበር፡፡
ከ1973 ዓ.ም. በፊት በንጉሥ ሚካኤል ቤተ መንግሥት ውስጥ ሆኖ የኢትዮጵያ ሕዝብ ባህል ታሪክና ማንነት የሚያሳዩ ሰነዶች ተሰንደው ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የቆየ መሆኑን የታሪክ ማስረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ሙዚየሙ በ1973 ዓ.ም. የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት ሊቀመንበር በነበሩበት በወቅቱ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ተመርቆ ሥራ የጀመረ መሆኑን የደሴ ከተማ አስተዳደር ባህል ቱሪዝም ስፖርት መምሪያ ገልጿል፡፡
ሙዚየሙ ላይ የደረሰው ዘረፋ
በጦርነቶችም ሆነ በአገር ውስጥ በሚቀሰቀሱ ግጭቶች ወቅት ቅርሶች ይዘረፋሉ፣ ይሰባበራሉ፡፡ ግማሾቹ ከአገር ሲወጡ ቀሪዎቹ በአገር ውስጥ በግለሰብ እጅ ላይ ሆነው ሲታዩ ሌሎች ደግሞ ተቀብረው ለዘመናት ይቀራሉ፡፡
ከጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በፌዴራል መንግሥትና በትግራይ ክልል መካከል በነበረው ጦርነት የበርካታ ሰዎች ሕይወት ከመጥፋቱም ባሻገር በአጋጣሚው በተለያዩ ቦታዎች ያሉ ታሪካዊ ቅርሶች ተዘርፈዋል፡፡ ከእነዚህ መካከልም ከብሔራዊ ሙዚየም ቀጥሎ የሚታወቀው ትልቁ የደሴ ሙዚየም አንዱ ነው፡፡ በነበረው ጦርነት ዝርፊያ ያጋጠመው የደሴ ሙዚየም ሊተኩ የማይችሉ ቅርሶቹ ተወስደዋል ተብሏል፡፡
ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በ1941 ዓ.ም. ከእንግሊዝ ንግሥት ኤልሳቤጥ በስጦታ የተበረከተላቸው ከብር የተሠራ ሻሞላ (ሰይፍ)፣ አፄ ምኒልክ በዓድዋ ጦርነት ወቅት ይጠቀሙበት የነበረው የጦር ሜዳ መነፅር እንዲሁም ሌሎች ውድ ቅርሶች መዘረፋቸውም ተነግሯል፡፡
የሙዚየሙ በሮችና መስኮቶች በጥይት ተበሳስተውና ተሰባብረው እንዲሁም ከመዘረፍ የተረፉት ቅርሶች ተሰባብረው ታሪካዊ ይዘታቸውን ለቀው እንደሚታዩ ሪፖርተር በቦታው በመገኘት ለመታዘብ ችሏል፡፡
የተዘረፉ ቅርሶችን ለማሰባሰብና ሙዚየሙን ዘመኑን በዋጀ ሁኔታ በአዲስ መልክ ለማደስ የኢትዮጵያ ቅርስ ባለአደራ ማኅበር ባደረገው ጥረት ከብሪቲሽ ካውንስል ባገኘው የ25 ሚሊዮን ብር ድጋፍ የሚተገበረውን ፕሮጀክት የካቲት 11 ቀን 2015 ዓ.ም. ይፋ አድርጓል፡፡
የኢትዮጵያ የቅርስ ባለአደራ ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ መቆያ ማሞ በስምምነቱ መሠረት የሙዚየሙን ሙሉ ዕድሳት የኤሌክትሪክና የተለያዩ ጥገናዎች እንደሚደረግ የበጀት ዝርዝር ዕቅድ ባቀረቡበት ወቅት አብራርተዋል፡፡
በተለይ ደግሞ የቅርስ ጉዳይ ከፍተኛ ጥንቃቄን የሚፈልግና ትኩረት የሚሻው በመሆኑ ለዕድሳቱ በሙያው ዕውቀት ያላቸውን ባለሙያዎች ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና ከወሎ ዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ ለመሥራትም ታስቧል ብለዋል፡፡
በቅርቡ በነበረው ጦርነት ምክንያት ቅርሶች ተዘርፈው በግለሰቦች እጅየሚገኙና ርቀው እስከ አፋርና ሌሎች አካባቢዎች የሄዱትን ለማስመለስ ጥረት እየተደረገ ነው ያሉት ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ ለዚህም ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በቅርበት እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በስሜን ተራራ ብሔራዊ ፓርክ በጎንደርና በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች በተደረጉ የዳሰሳ ጥናቶች ላለፉት 23 ዓመታት በጦርነትና በአየር ንብረት መለዋወጥ ምክንያት ከ633 በላይ ቋሚና ተንቀሳቃሽ ቅርሶች ተዘርፈዋል ብለዋል፡፡
ሙዚየሙ ተገንብቶ ሲያበቃ የተሰበሰቡት ቅርሶች በቀጣይ በኃላፊነት ማን ይጠብቃቸው የሚለውን ሐሳብ ታስቦበት ወደ ሥራ መገባቱን አቶ መቆያ አብራርተዋል፡፡
ለሙዚየሙ ዘረፋና ውድመት በዋናነት የሚጠቀሰው የባለቤትነትና የተጠያቂነት አለመኖር ነው ያሉት ደግሞ የደሴ ከተማ አስተዳደር ባህል ቱሪዝምና የሙዚየሙ ኃላፊ አቶ መረሳ ይርጋ ናቸው፡፡
በተለያዩ ጊዜያት በተደጋጋሚ በደረሰበት ጥቃትና ዘረፋ በርካታ ውድ ቅረሶችን ማጣቱን ያስታወሱት የደሴ ከተማ ባህል ቱሪዝምና የሙዚየሙ ኃላፊ አቶ መረሳ ይርጋ ናቸው፡፡
እንደ ኃላፊው ማብራሪያ፣ በ1991 ዓ.ም. 124 ቅርሶት፣ በ1999 ዓ.ም. 15 ቅርሶች በ2013 ዋና ዋና አራት ቅርሶች፣ በ2014 በጦርነት ምክንያት የተዘረፉትን ጨምሮ በአጠቃላይ 490 ቅርሶች ተዘርፈዋል፡፡
በ2014 ዓ.ም. በተደረገው ጦርነት ከተዘረፉት ቅርሶች ዋና ዋናዎቹ ብለው የጠቀሷቸው የዳግማዊ አፄ ምኒልክ ስልክ፣ የቀድሞ ነገሥታት ብርሌዎች፣ የጦር መሣሪያዎች፣ ባህላዊ አልባሳትና መገልገያዎች ይገኙበታል፡፡
የቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ቅርሶቹን ለማስመለስ የተዘረፉ ቅርሶች የት እንዳሉ በማጥናትና በሃይማኖት ተቋማት በኩል ውግዘት በማድረግ በግለሰብ ደረጃ ያሉ ቅርሶችን ለማስመለስ እየሠራን ነው ብለዋል፡፡
በዚህም 15 የጦር መሣሪያዎችንና ሌሎች ቅርሶችን ለማስመለስ መቻሉን ሙዚየሙ በመጎዳቱና በመዘረፉ በዓመት ከአራት እስከ አምስት ሺሕ ጎብኚዎች ይጎበኙት የነበረው ቁጥር ማሽቆልቆሉን አብራርተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ቅርስ ባለአደራ ማኅበር ቦርድ ምክትል ፕሬዚዳንት አሉላ ፓንክረስት (ዶ/ር) በበኩላቸው እንደተናገሩት፣ ያሁኑ ሙዚየሙን በተሻለ መልኩ ለማደራጀት ዕድል የሚፈጥር ታሪካዊ አጋጣሚ ነው፡፡
ሙዚየሙ ሕዝቡ የሚወደው፣ ለሕዝቡም ክፍት ሆኖ የመማሪያ ቦታ ሆኖ እንዲሠራ ማድረግ፣ ባለቤቱም ሕዝቡ መሆን እንዳለበትም አስምረውበታል፡፡
‹‹ወሎ ራሱ የማይዳሰስ ቅርስ ነው›› ያሉት የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አበባው አያሌው፣ ቱሪዝምን ለማጎልበት በአገሪቱ ያሉ ቅርሶችን በተለይም በክልሎችና በአቅራቢያው የሚገኙ ባለቤቶች በኃላፊነት ከዝርፊያና ከውድመት ሊጠብቋቸውና ሊንከባከቡዋቸው ይገባል ብለዋል፡፡