Friday, March 31, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልሰባት መቶ ኢትዮጵያውያንን ከፋሺስት ጭፍጨፋ የታደገው ግቢ

ሰባት መቶ ኢትዮጵያውያንን ከፋሺስት ጭፍጨፋ የታደገው ግቢ

ቀን:

በአዲስ አበባ ከተማ ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ድልድይ አካባቢ የሚገኘውና ‹‹አሜሪካ ግቢ›› እየተባለ የሚጠራው የቀድሞው የአሜሪካ ሌጋሲዮን፣ በፋሺስት ጣሊያን ወረራ ዘመን (1928 እስከ 1933) ሰባት መቶ ኢትዮጵያውያንን ከየካቲት 12ቱ  ከፋሺስት ጭፍጨፋ ታድጓል፡፡ በእነዚህ ሰዎች ዙሪያ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የተደረገው ጥረት ግን በቂ ባለመሆኑ፣ ቀጣይ ሥራ እንደሚያስፈልገው በቅርቡ የወጣው አንድ ጥናት አመልክቷል፡፡

ከኸርቴጅ ዎች አሶሴሽንና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተውጣጡ ምሁራን ተሳታፊ የሆኑበት ቡድን ካካሄደውና የካቲት 15 ቀን 2015 ዓ.ም. ይፋ ከሆነው ከዚሁ ጥናት ለመረዳት እንደተቻለው፣ የመታደጉ ሥራ የተከናወነው ከጭፍጨፋው ሕይወታቸውን ለማትረፍ ወደ ሌጋሲዮኑ የገቡ ሰዎችን ተቀብሎ መጠለያና መሸሸጊያ በማበጀት ነው፡፡

ሰዎቹ ወደ ግቢው እንደገቡ መጠለያና መሸሸጊያ እንዲዘጋጀላቸው ያደረጉት በወቅቱ በኢትዮጵያ የአሜሪካ ቆንስላ የነበሩት ሚስተር ቫን ኢንገርት ናቸው፡፡

የኸርቴጅ ዎች አሶሴሽን መሥራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ ልዕልት አስቴር ፍቅረ ሥላሴ በተለይ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በአሜሪካ ግቢ ተጠልለው ከፋሺስት ጭፍጫፋ ሕይወታቸውን ያተረፉ ሰዎች ስም ዝርዝር የተገኘው በቀድሞው ቆንስላ የግል ፋይል ውስጥ ሲሆን በአሜሪካ ኮንግረስ ላይብረሪ ውስጥ ይገኛል፡፡

‹‹ሰዎቹ የተጠለሉት በግቢው ወይም በሌጋሲዮኑ ሕንፃ ሥር ባለው ምድር ቤት ውስጥ ነው መባሉ እውነትነት እንዳለው ለማወቅ ተችሏል፤›› ያሉት ልዕልቷ፣ በተረፉ ሰዎች እንቅስቃሴ ዙሪያ መረጃ ለማግኘት ቡድኑ ቢያንስ ልጆቻቸውን ወይም የልጅ ልጆቻቸውን ለማነጋገር ጥረት ማድረጉን፣ በአዲስ አበባ የሚገኙ 36 ድርጅቶችንና 13 የኦርቶዶክስ እምነት ተቋማትን በሮች ማንኳኳቱን ገልጸዋል፡፡

ከእነዚህም መካከል በቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን የሰንበቴ ማኅበር ውስጥ የሦስት ሰዎችን ልጆች እንዳገኘ፣ ልጆቹም ወላጆቻቸው በግቢ ውስጥ ተሸሽገው እንደነበር ማረጋገጣቸውን ከልዕልት አስቴር ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ቡድኑ በተሸሸጉ ሰዎች ዙሪያ ያተኮረ መረጃ ለማግኘት የሚያስችለውን ጥናት ያካሄደው ከግንቦት እስከ ጥር 2015 ዓ.ም. ድረስ ሲሆን፣ ለጥናቱም ማከናወኛ የዋለውን ፋይናንስ የደገፈው በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ መሆኑን ነው ዋና ሥራ አስኪያጇ የተናገሩት፡፡

በእነዚህም ቀናት ውስጥ በቡድኑ እንቅስቃሴ ዙርያ በርካታ ተግዳሮቶች ተደቅነውበት እንደነበር፣ ከተግዳሮቶቹም መካከል በአሜሪካ ግቢ ዙሪያ የሚገኙ የቀድሞ ቤቶች መፍረሳቸውና ነዋሪዎች ወደ ተለያዩ አካባቢዎች መዘዋወራቸው፣ በሌጋሴዮኑ ተሸሽገው የነበሩ ሁሉም መሞታቸው፣ እያንዳንዱ ዜጋ የደረሰበትን የታሪክ አጋጣሚ በሰነድ አያያዞ ለቀጣዩ ትውልድ እንዲተላለፍ ወይም እንዲቆይ የማድረግ ባህል አለመኖር መሆናቸውን ነው ያመለከቱት፡፡

ከዚህ አኳያ በተጀመረውና በተከናወነው ጥናት ብቻ መርካት በቂና ትክክል እንዳልሆነ ልዕልት አስቴር ጠቁመው፣ ጥናቱ ቀጣይነትና ተከታታይነት ሊኖረው እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡

‹‹ከፋሺስት ጭፍጨፋ ሕይወታቸውን ለማዳንና ከለላ ፍለጋ ወደ አሜሪካን ግቢ ከገቡት ኢትዮጵያውያን ባሻገር፣ ሦስት አሜሪካውያን ሚሲዮናውንና 37 ግሪኮችም ጭምር ነበሩ፤›› ያሉት ደግሞ የጥናቱ ቡድን መረጃ፣ የፋሺስቶችን ጭፍጨፋ ‹‹ዘ አዲስ አበባ ማሳከር›› በሚል መጻሐፋቸው የተረኩት የታሪክ ተመራማሪ ኢያን ካምቤል ናቸው፡፡

እንደ ኢያን ካምቤል አባባል፣ የፋሺስት ወታደሮች በተደጋጋሚ ጊዜ ወደ አሜሪካን ግቢ እየመጡ የተሸሸጉ ሰዎች እንዲወጡና እጃቸውን እንዲሰጡ ቆንስላውን ይጨቀጭቋቸው ነበር፡፡ ይህንንም ለመከላከል ሲባል ግቢው ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት በዘበኛ ሲጠበቅ እንደቆየ፣ ከጠባቂዎቹም መካከል አንደኛው ከፋሺስት ወታደሮች በተተኮሰ ጥይት እንደተገደለ ነው የገለጹት፡፡

ሚስተር ቫን ኢንገርት የቆንስላነቱን ሥራ ለማከናወን ባለቤታቸውንና የስምንት ዓመት ልጃቸውን ይዘው ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ፋሺስቱና አምባገነኑ ሞሶሎኒ ኢትዮጵያን ለመውረር ያኮበኮበበት ጊዜ እንደነበር፣ ቆንስላውም በየጊዜው ከአፄ ኃይለ ሥላሴ ጋር ይገናኙና ይወያዩም እንደነበር፣ ንጉሠ ነገሥቱም የቆንስላውን መሾም የሚያረጋግጥ ደብዳቤ በተቀበሉ ማግሥት ወደ መንግሥታቱ ማኅበር (ሌግ ኦፍ ኔሽን) ማቅናታቸውን ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

ከዚህም በኋላ በየካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም. ፋሺስቶች አዲስ አበባ ውስጥ 30 ሺሕ ኢትዮጵያውያንን ማረዳቸውንና ቤቶቻቸውን ማቃጠላቸውን፣ ከተቃጠሉት ቤቶችም መካከል በአሜሪካን ግቢ ዙሪያ የነበሩ ቤቶች እንደሚገኙበት ነው የተናገሩት፡፡

ቆንስሉ በኢትዮጵያ ውስጥ ለፈጸሙት በጎ ሥራ ከፕሬዚዳንት ሩዝቬልት የአድናቆትና ምስጋና እንደተቸራቸው አስረድተዋል፡፡

ጭፍጨፋውም ጋብ ካለ በኋላ በአሜሪካን ግቢ ተሸሽገው የነበሩ ሰዎች ቆንስላውን እያመሰገኑ ወደ የመጡበት መመለስ እንደጀመሩ፣ ሌጋሲዮኑም ከዋሽንግተን ዲሲ በተላለፈው ትዕዛዝ መሠረት እንደተዘጋና ሚስተር ቫን ኢንገርትም ወደ አሜሪካ እንዲመለሱ መደረጉን ከኢያን ካምቤል ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

የአሜሪካን ግቢ አዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙ ዕድሜ ጠገብና ታሪካዊ ከሆኑ ሕንፃዎች መካከል አንዱና ዋነኛው መሆኑን የገለጹት አርኪቴክት ፋሲል ጊዮርጊስ፣ የተገነባውም በ1907 ዓ.ም. እና በ1915 ዓ.ም. መካከል ሲሆን፣ ለመኖሪያነት ያሠሩትም ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

በአሥራ ዘጠነኛው ምዕት ዓመትና በሃያኛው ምዕት ዓመት መጀመርያ አካባቢ በአፄ ምኒልክና በንግሥት ዘውዲቱ ዘመን የነበሩት ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ በተለይ የአፄ ምኒልክ የጦር ሚኒስትር ሆነው ማገልገላቸውን ተናግረዋል፡፡

በዘመኑ የአርመኖች ኪነ ሕንፃ ስታይል በጣም ተፈላጊና ዘመናዊ እንደነበር፣ በዚህም የተነሳ ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ይህንን ስታይል በተከተለ መንገድ ቤቱን እንዳሠሩ፣ በውስጡም የእንግዳ መቀበያ አዳራሽ፣ ለመኝታና ለልዩ ልዩ አገልግሎት የሚውሉ ክፍሎች እንዳሉት፣ የምግብ ማብሰያና የንፀህና መጠበቂያ ቤቶች ግን የተገነቡት ከዋናው ሕንፃ ውጪ መሆኑንም አውስተዋል፡፡

ሕንፃው የሚገኝበት አካባቢ መርካቶ (አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ) ሲሆን፣ በፋሺስት ወረራ ዘመን ግን ‹‹መርካቶ ኢንዲጂኖ›› የሚል ስያሜ እንደተሰጠው፣ ይህም ማለት ተወላጆች ወይም ኢትዮጵያውያንን ብቻ ተገልለው የሚኖሩበት አካባቢ እንደነበር ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ የአፄ ኃይለ ሥላሴ የዘውድ በዓል ከመከበሩ አራት ዓመት በፊት ማለትም በ1919 ዓ.ም.፣ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩ ሲሆን፣ ያሠሩትም ቤት ‹‹የአሜሪካን ሌጋሲዮን›› ወይም ‹‹የአሜሪካን ግቢ›› ሆነ ሲሉ አርክቴክት ፋሲል ተናግረዋል፡፡

ሕንፃው የሌጋሲዮን መገልገያ ከዚያም የቫቲካን ቅድስት መንበር እንደራሴ መቀመጫ ሆኖ ከማገልገሉም ባሻገር፣ በአሁኑ ጊዜ ግን የየመን ማኅበረሰቦች ትምህርት ቤት ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል፡፡

ይህም ሆኖ ቅርስነቱ ተጠብቆ እንዲቆይ ከመደረጉም በላይ የሕንፃውን ኪነ ጥበብ እንዳለ ሆኖ የውስጥ ዕድሳት ተደርጎለታል፡፡ ለዕድሳቱም የሚያስፈልገውን ወጪ የሸፈነው በዓለም ውስጥ የሚገኙ ታሪካዊ ኪነ ሕንፃ (አርክቴክቸር) እና ባህላዊ ቅርሶች ባሉበት ተጠብቀው እንዲቆዩ ሁሉን አቀፍ ጥረት የሚያደርገው ወርልድ ሞንመንት ፈንድ የተባለው ዓለም አቀፍ ድርጅት ነው፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተወግዘው የነበሩ ሦስቱ ሊቀጳጳሳትና 20 ተሿሚ ኤጲስ ቆጶሳት ውግዘት ተነሳ

_ቀሪዎቹ ሦስት ህገወጥ ተሿሚዎች የመጨረሻ እድል ተሰጥቷቸዋል ​ ጥር 14...

በሕወሓት አመራሮች ላይ ተመስርቶና በሂደት ላይ የነበረው የወንጀል ክስ ተቋረጠ

በቀድሞ የትግራይ ክልል ፕሬዚደንት ደብረጽዮን ገብረሚካኤ,(ዶ/ር)ና ባለፈው ሳምንት በተሾሙት...

[የምክር ቤቱ አባል ላቀረቡት ጥያቄ በተሰጣቸው ምላሽ አቤቱታቸውን ለክቡር ሚኒስትሩ እያቀረቡ ነው]

ክቡር ሚኒስትር እየሆነ ያለው ነገር ትክክል ነው? ምነው? ምክር ቤቱም ሆነ...

የጉራጌ የክልልነት ጥያቄ ትኩሳት

ቅዳሜ መጋቢት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. በጉራጌ ዞን ወልቂጤ...