በአዲስ አበባ ውስጥ በነዋሪነት ቤተሰብ ቅጽ በተለያዩ ምክንያቶች በወላጆቻቸው ሳይመዘገቡ የቀሩና ዕድሜያቸው 18 እና ከዚያ በላይ የሆኑ ወጣቶች፣ ወደ ዩኒቨርሲቲ ለመሄድና ለተለያዩ የሥራ ዕድሎች የነዋሪነት መታወቂያ አገልግሎት ለማግኘት መቸገራቸውን ከታዳጊዎቹና ወላጆቻቸው መቅረቡን ተከትሎ፣ መሥፈርቱን ለሚያሟሉ ወጣቶች መታወቂያ እንዲሰጥ መወሰኑን የወሳኝ ኩነት ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ አስታውቋል።
በመሆኑም እነዚህ በቤተሰብ ቅጽ ውስጥ ያልተመዘገቡ፣ ነገር ግን ከላይ በተጠቀሰው መሠረት ዕድሜያቸው 18 ዓመት ያለፋቸው ወይም፣ ቤት ውስጥ ያደጉ የቤተሰብ አባል የሆኑ ልጆች ፣ ወይም በጉዲፈቻ ወይም በማደጎ ያደጉ ልጆች ለማመሳከሪያነት የ8ኛ ወይም የ10ኛ ወይም የ12ኛ ክፍል የትምህርት ማስረጃዎችን ማቅረብ ይጠበቃል፡፡
ከዚሁ ጎን ለጎንም እንደ አስፈላጊነቱ ሌሎች ትክክለኛ መረጃዎችን በማስቀረብና ልጆቹ በቤተሰብ ውስጥ እየኖሩ ስለመሆናቸው ወላጆች በሦስት ምስክሮች የተደገፈ የምስክርነት ቃለ መሃላ እንዲፈጽሙ በማድረግ፣ በነዋሪነት ተመዝግበው አገልግሎቱ ማግኘት እንደሚችሉ አሳስቧል፡፡
በከተማው የአዲስ የነዋሪነት መታወቂያ ማግኘት የታገደ ሲሆን፣ ነባራዊ ሁኔታዎችን ከግምት በማስገባት፣ በነዋሪነት የቤተሰብ መዝገብ ቅጽ ውስጥ ተመዝግበው 18 ዓመትና ከዚያ በላይ የሆናቸው ወጣቶች የነዋሪነት መታወቂያ አገልግሎት እንዲያገኙ በልዩ ሁኔታ ከኅዳር 22 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ መፈቀዱ ይታወሳል፡፡