‹‹ሰሎሞን ይርጋ ለዕውቀት ከፍተኛ አክብሮት ነበረው፡፡ አንዳንድ አንኳር የሆኑ ሳይንሳዊ ትችቶችን፣ ለብዙ ግለሰቦች በማዳረስ ሒደት ፈር ቀዳጅ ሚና ነበረው፡፡ ይዘታቸው ሳይንሳዊ፣ ባህልንና እምነትን የሚዳስሱ አከራካሪና አወዛጋቢ የሆኑ መጻሕፍት በአካባቢያችን በብዛት አይታዩም እሱ በዚህ ረገድ አዲስ በር ከፋች ነበር፡፡
‹‹ሰሎሞን ይርጋ የተሠማራበት የዕውቀት/የሙያ ዘርፍ ‹ሰብ አስተኔ ዝግመተ-ለውጥ› ሲሆን፣ ያካሄዳቸው ምርምሮችም ዝግመተ ለውጥ ላይ ሲሆኑ፣ እነሱም ‹በሥነ ቅርስ ሕይወት› ላይ ያተኮሩ ነበሩ፡፡ በተጨማሪም ሳይንሳዊ ዕውቀትን በአገር ቤት ቋንቋ ማዳረስ ይቻላል የሚል ፅኑ እምነት ነበረው፡፡ በዓለማችን ላይ የተከማቸ ዕውቀትን፣ ግንዛቤን ለማካፈል፣ በተለይ ዕድል ገጥሟቸው ያንን ዓይነት ግንዛቤ በውጭ ቋንቋ ከተዘጋጁ መጻሕፍት ለመቅሰም ዕድል ላላገኙ ግለሰቦች፣ የዕውቀት ተቋዳሽ መሆን አለባቸው ብሎ በማመን፣ ለዚህ ተግባር ከፍተኛ አስተዋጽዖ አድርጓል፡፡ ስለሆነም የብቸኛ ዝርያዎች መንስኤ – ቻርልስ ዳርዊን (ትርጉም)፣ ህልውናና አጥቢዎች በሚሉ ርዕሶች፣ ሦስት መጻሕፍትን ለአገር ቤት አንባብያን አበርክቷል፡፡››
ይህን ታሪካዊ ምስክርነት ስለሥነ ሕይወት ምጡቅ ምሁሩ ሰሎሞን ይርጋ (ዶ/ር) በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ዓውደ ምሕረት ላይ የሰጡት መምህራቸውና የሙያ አጋራቸው ሽብሩ ተድላ (ፕሮፌሰር) ናቸው፡፡
በየካቲት መባቻ በአሜሪካ በሕክምና ላይ ሳሉ ያረፉት ተባባሪ ፕሮፌሰር ሰሎሞን ይርጋ ሥርዓተ ቀብር ባረፉ በዘጠነኛው ቀን ላይ በአዲስ አበባ ሲፈጸም የመጨረሻ ሸኝት ላይ ትውስታቸውን ሲያጋሩ፣ የነፍስ ኄር ሰሎሞንን አርዓያነት በማጉላት ነበር፡፡
እንዲህም አንፀባረቁ፡- ‹‹በተለይ ሳይንስ ነክ የሆኑና ይዘታቸው በአገር፣ በወሰን ሳይገታ፣ ስለሰው ልጅ ጠቅለል ባለ መልክ የሚተቹ መጻሕፍት በአካባቢያችን ብዙ አይታዩም፡፡ በተጨማሪ በእሱ ጽሑፎች የቀረቡትን ታሪክና ሕይወት ነክ ጸሑፎች በውጭ ቋንቋዎች የተደረሱ መጻሕፍትን ማንበብ በአካባቢያቸን የተለመደ ብሎም የዳበረ አይመስልም፡፡ የእሱ መጻሕፍት ያንን ክፍተት ለመሸፈን የተደረጉ ሙከራዎች ናቸው፡፡ የእሱን ተምሳሌነት አንግበው በተመሳሳይ ተግባር የተሰማሩ ግለሰቦች አሉ፣ እኔም አንዱ ነኝ፡፡››
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ ፕሮፌሰር የነበሩት ሰሎሞን ይርጋ በመጽሐፎቻቸው የኢትዮጵያ አስተዳደር በቀና መንገድ እንዲጓዝ ምክረ ሐሳብን ከማቅረብ አልቦዘኑም፡፡ በ1990ዎቹ የጻፏት፣ የኅትመት ብርሃን ያገኘችውና በብዙኃን አንባቢያን ዘንድ ይበልታን የተጎናጸፈችው ተጠቃሽ ናት፡፡
በመጽሐፏ እንዲህ ብለው ነበር፡-
‹‹በመጨረሻ ላነሳው የምሻው የችጋር መከላከያው መንገድ አጠቃላይ ዕድገት መሆኑን ነው፡፡ ሰላም የዕድገት አንደኛው ቁልፍ መሆኑን ገልጫለሁ፡፡ ዕድገት ስል የአገራችን ሰው የማይራብበት፣ ከውርደት ነፃ የሆነበት፣ ጤናው የተጠበቀበት፣ ልጆቹ ዕውቀትን የሚቀስሙበት፣ እያንዳንዱ በሥራ የተሠማራበት፣ የኑሮ ዋስትና የሚያገኝበት ለማንኛውም ጥቃት ሰለባ የማይሆንበት፣ ወዘተ ሁኔታ ማለቴ ነው፡፡ ይህንን ሁኔታ እንደ ምንድነው የምናመጣው? የኢትዮጵያ ሕዝብ ይህ ነው መንገዱ ብሎ በአንድ ድምፅ የሚስማማበት ሥርዓት መኖሩን እጠራጠራለሁ፡፡ በግሌ ብዙ ዓይነት ጎዳና ወደ ዕድገት የሚወስደን ይመስኛል፡፡ የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ (ካፒታሊዝም) ነው የሚሻለው ከተባለ አያሳድግም ለማለት አልችልም፡፡ በአሁኑ ወቅት የሚሆነው ብሔራዊ ካፒታሊዝም ያለበት ፍዳ ቢታየኝም፣ ‹የማደጊያው መንገድ ይህ ሊሆን አይችልም› ለማለት ይከብደኛል፡፡ ለዚህም ግን መንግሥታችን ለባለ ካፒታሉ የሙሉ አገራችንን ድንበር ሊያሳየው ይገባል፡፡ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ባሻው የኢትዮጵያ ምድር ሊሠራ፣ ሊያመርት፣ ሊሸጥና ሊለውጥ ቢፈልግ ምንም የሚያግደው ነገር ሊኖር አይገባም፡፡››
ስለቋንቋ ትምህርትም ሲናገሩም ‹‹በቀላሉ መንገድ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች በሙሉ ከሚናገሯቸው ሰዎች በላይ እንዲማሯቸውና እንዲዳብሩ ማድረግ ይቻላል፡፡ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ተማሪ እንደ አካባቢው ሕዝብ ፈቃድ ሁለት ቋንቋዎች እንዲማር አድርጎ፣ ከሁለቱ ቋንቋዎች አንደኛው ኢትዮጵያዊኛን (አማርኛ) እንዲሆን ማድረግ ይቻላል፡፡ እንዲህ አንድ የመግባቢያ ቋንቋ እንዲኖረንና ሁሉም ቋንቋዎችን እንዲዳብሩ ይሆናል፡፡
የኢትዮጵያን ሥርዓተ መንግሥት አስመልክቶ የሄዱበት መንገድም ተጠቃሽ ነው፡፡ እንዲህም ህልውና ባሉት መጽሐፋቸው ላይ ከተቡ፡-
‹‹በዘር የተካለለ አገር ራሱን ከማንም ዓይነት አደጋ ሊሠውር አይችልም፡፡ የዕድገት ተስፋውም ጨለማ ይመስኛል፡፡ የሚፈጥረው ሁኔታም የተጨማሪ ችግሮች ነው፡፡ ያለብንን ሁኔታ አሥጊነት ስመለከተው በገደል ጫፍ ላይ እንዳለን ይሰማኛል፡፡ ይህም ነው ምንም እንኳን መከፋፈል ለሚገዙ የሚቀል መሆኑን ባውቅም፣ ደፍሬ ትክክል አይደለም ብዬ እንድል የሚያስገድደኝ፡፡ ለችግር መፍትሔ ከሰጠን፣ በተለያዩ መስኮች የሰው ኃይላችን ካሠለጠንን፣ አንድነታችንን ካጠነከርን የምንሠራው ሥራ አብዛኛው የበለጠ የሚያሳድገን መሆኑ አይቀርም፡፡››
ትውልዳቸውና ጉዟቸው
ከአባታቸው ከኮሎኔል ይርጋ የሱፍና ከእናታቸው ከወ/ሮ ፋናዬ ገብሬ በቀድሞ የሐረርጌ ጠቅላይ ግዛት ኅዳር 26 ቀን 1940 ዓ.ም. የተወለዱት ሰሎሞን ይርጋ፣ የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በሐረር መድኃኔዓለም ትምህርት ቤት ተከታትለዋል፡፡ የመጀመርያ ዲግሪ ትምህርታቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በባይሎጂ የትምህርት መስክ በከፍተኛ ማዕረግ በመመረቅ፣ የሁለተኛና የሦስተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን በጃፓን አገር ከሚገኘው ኪዮቶ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል፡፡
በሥራው ዓለም ከ1980 እስከ 1982 በደንና ዱር አራዊት ባለሥልጣን የደን ዛፍ ዘር ማዕከልና ላቦራቶሪ፣ የዱር ሕይወት ባዮሎጂስት፣ ስምጥ ሸለቆና ብሔራዊ ፓርክ ኃላፊ በመሆን፣ ከ1980 እስከ 1990 የፖስት ዶክተራል ተመራማሪ፣ ከ1990 እስከ 1991 ዓ.ም. የኒውዮርክ ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ ተመራማሪ፣ ከ1996 እስከ 2004 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በረዳት ፕሮፌሰርነት፣ ከ2004 ዓ.ም. ሕይወታቸው እስካለፈበት ጊዜ ድረስ በዚሁ ዩኒቨርሲቲ በተባባሪ ፕሮፌሰርነት አገልግለዋል፡፡ ገጸ ታሪካቸው እንደሚያመለክተው፣ በአገር ውስጥና በዓለም አቀፍ የምርምር መጽሔቶች ላይ 19 የምርምር ሥራዎችን አሳትመዋል፡፡
በተወለዱ በ75 ዓመታቸው ያረፉት ተባባሪ ፕሮፌሰር ሰሎሞን ይርጋ (ዶ/ር) ባለትዳርና የአንዲት ሴትና የአንድ ወንድ ልጆች አባት ነበሩ፡፡
በሥርዓተ ቀብሩ ማሳረጊያ በዓውደ ምሕረቱ ላይ የመሸኛ ዲስኩር ከመወድሳቸው ጋር አስተሳስረው ያቀረቡት ፕሮፌሰር ሽብሩ ተድላ እንዲህ አወደሱት፡-
‹‹ብዙ በቅርብ ሰሎሞን ይርጋን የሚያውቁት፣ ለብዙ ዘመን አብሯቸው የሚዘልቅ ትውስት፣ የማይረሱት፣ ከሁላችንም የላቀ የማስታወስ ችሎታውን ነው ብዬ እገምታለሁ፡፡ ሰሎሞን ይርጋ የከበደ ሚካኤልን ግጥሞች ሆነ፣ የኢትዮጵያን የተለያዩ መዝሙሮች በቃሉ ሲያነበንብ፣ ለአዳማጭ የሚያነብ እንጂ የሚያነበንብ መስሎ አይገመትም ነበር፡፡
የሰለሞን ትዝታ ለዘመናት አብሮን ይኖራል፡፡ በአንድ ወቅት የሕይወት መከሰትንና ያላቋረጠ ሒደት – «ኢቮሉሽን» – ለማብራራት ለሚጥረው ለሰሎሞን በጥር 2003 ‹የዚች ምድር ፀጋ› በሚል ርዕስ አንድ መወድስ አበርክቼለት ነበር፡፡ ያችም መወድስ የስንኝ ማሰሮ በምትባል የግጥሞች መድበል ውስጥ ሠፍራ ትገኛለች፡፡ እነሆ የተከለሰች በቅንጭብ፡-
ብትኖርምን አንተ ነህ፣ ባትኖርም አንተ ነህ፣
ሰው ተብለህ ታውቀህ፣ አሊያም ትውስት ሆነህ፣
ከአዕላፍ በላቀ፣ አሻራ ያሠፈርክ፤
በዕውቀት የተገራህ፣ የትውስት ጎተራ፣ የጽናት-ሃብል ነህ፡፡
የማሳረጊያው ማሳረጊያ ከሰሎሞን ይርጋ የህልውና ጓዳ
‹‹አንድ ዋነኛ የመሰለኝን ጉዳይ ላመልክት፡፡ ባለንበት ዘመን የአንድ አገር ዕድገትም ሆነ ነፃነት ዋስትናው የሚወስነው ባለው ምሁር ጥራትና ብዛት ነው፡፡ ዕድገታችንንና ነፃነታችንን የማይሹ ሁሉ ቀንደኛው ጠላታቸው ምሁራችን ነው፡፡ በዚህ ዘመን ምሁር አልባ አገር አንጎሉ ከራስ ቅሉ የወጣበት ግለ አካል ዓይነት ነው፡፡ ሕዝብንማ ጃንሆይ ኃይለ ሥላሴም ‹የሚወደንና የምንወደው› ሲሉት፣ ደርጎቹም በሞቃቸው ቁጥር ‹ድል አድራጊው› ሲሉት፣ የአሁኖቹም ‹ደግፎናል፣ መርጦናል› ሲሉት ነው የኖሩትና የሚኖሩት፡፡ እነዚህ ሁሉ ሄደዋል፣ ይሄዳሉ፡፡
‹‹አገራችን ግን መኖር አለባት፡፡ የምትኖረው ከሁሉም በላይ በሁሉም መስኮች ጥራት ያላቸው አገልጋይ ምሁራን ሲኖራት ነው፡፡ እነዚህ ከሕዝብ የሚፈልቁ ምሁራንን ማፍራት የኢትዮጵያ ዕድገትና ሕልውና ዋስትና ነው፡፡ እነዚህ ከሌሉን ለቅኝ ግዛት ቋምጠው ዓለምን የሚያምሱት ‹ጉልበተኞች› ሐሳብ ሠመረላቸው ማለት ነው፡፡ ኢትዮጵያን አጣን ማለት ነው፡፡ ተከታዩ የሕዝባችንም መጥፋት ይሆናል፡፡ በዚህ የተነሳም የአገራችንን የትምህርት አቅጣጫ የሚወስነው ዋነኛ ጉዳይ፣ ዕድገትና ነፃነት ሊሆን ይገባዋል፡፡ ለዕድገትና ለነፃነትም ቁልፉ አስቀድሞ አገሩን የሚወድ ምሁር ማፍራት ላይ ማተኮር ነው፡፡ በከፍተኛ ትምህርት በኩል የአንድ መንግሥት ጥረት መለኪያውም ‹ምን ያህል ታማኝ አሽከር አፈራ?› ሳይሆን ‹አገሪቱ ምን ያህል የተሳለ ጭንቅላት ያለው ንቁና ቀልጣፋ ምሁር አፈራች?›፣ ‹አገሩን የሚወድና ለአገሩ የሚጠቅም ጉዳይ የጨበጠ ምሁር ነው?› የሚል መሆን አለበት፡፡ ግምታችን የሚመዘነው እንዲህ እንዲህ በመሰሉ ጥያቄዎች ላይ ተመሥርቶ ነው፡፡››