- በቀጣዩ ዓመት የኤም ፔሳ አገልግሎቱን በኢትዮጵያ ይጀምራል
በኢትዮጵያ የመጀመርያውን የውጭ የቴሌኮም አገልግሎት ፈቃድ ወስዶ ወደ ሥራ የገባው ሳፋሪኮም፣ ኢትዮጵያ በአገሪቱ ዕምቅ የገበያ ዕድሎች ላይ ትልቅ ተስፋ ማሳደሩን መቀመጫውን ኬንያ ላደረገው የዋናው ኩባንያ ባለድርሻዎች ገለጸ።
ዋናው ሳፋሪኮም የካቲት 9 ቀን 2015 ዓ.ም. በኬንያ ባካሄደው የባለድርሻዎች ቀን ስብሰባው የኬንያና የኢትዮጵያ የቢዝነስ እንቅስቃሴዎቹን የተመለከቱ ወቅታዊ መረጃዎችን ለባለድርሻዎቹ ሰጥቷል።
በዚህ ስብሰባ ላይ የተገኙት የሳፋሪኮም የኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አንዋር ሱሳ፣ በኢትዮጵያ የተመለከቱትን የገበያ ዕድሎች አስመልክቶ ገለጻ አድርገዋል።
‹‹ሳፋሪኮም በስፋት የሚታወቅበትን የM-PESA የፋይናንስ አገልግሎት በኢትዮጵያ ማቅረብ የምንችልበት ሁኔታ በመፈጠሩ የዕድገታችን ጉዞ የበለጠ አስደሳች ሆኗል፤›› ሲሉ የM-PESA የፋይናንስ አገልግሎትን በኢትዮጵያ መጀመር እንደ ትልቅ የገበያ ዕድል አንስተውታል።
ይህንን የሞባይል ፋይናንስ አገልግሎት ለመጀመር የንግድና ቴክኒካል ዝግጁነት እያጠናቀቁ መሆኑን በመግለጽም፣ በሚቀጥለው የፈረንጆች ዓመት ሥራ እንደሚጀምሩ አስታውቀዋል።
‹‹ወደ 120 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ ያላትና 35 በመቶ የፋይናንስ ተደራሽነቱ ገና 35 በመቶ ላይ የሚገኝ መሆኑ፣ የሞባይል አገልግሎት ከአጠቃላይ ሕዝብ ብዛት ያለው ምጣኔ 57 በመቶ መሆኑና ዓመታዊ የሪሚታንስ ገቢ (ከውጭ የሚላክ የገንዘብ ልውውጥ) 4.2 ቢሊዮን ዶላር መሆኑ ሲታይ ኢትዮጵያ ትልቅ የገበያ ዕድል ነች፤›› ብለዋል።
በተለይ ፈጠራ የታከለበት አገልግሎት ማቅረብ ላይ እንዲሁም በአገልግሎት ጥራትና በኢንተርኔት ግንኙነት ላይ በትኩረት ከተሠራ ለሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ዕድገት ጠቃሚ የሆኑ ዕምቅ የገበያ ዕድሎች በኢትዮጵያ መኖራቸውን አስረድተዋል።
ከዚህ አኳያ ሳፋሪኮም በኢትዮጵያ የጀመረውን የቴሌኮም አገልግሎት በሚቀጥሉት 10 ዓመታት ውስጥ በኬንያ ደረጃ የማሳደግ ተስፋ እንዳለው አቶ አንዋር ሱሳ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቅርቡ ባፀደቀው አዲስ አዋጅ መሠረት ሳፋሪኮም ኤም ፔሳን በኢትዮጵያ ለመጀመር 150 ሚሊዮን ዶላር የፈቃድ ክፍያ መክፈል ይጠበቅበታል። ከዚህ የፈቃድ ክፍያ በተጨማሪ ሳፋሪኮም አገልግሎቱን ለመጀመር የሚያስችለውን እህት ኩባንያ በ50 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል ማቋቋም ይጠበቅበታል።
ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ አገልግሎቱን ከጀመረበት ወቅት አንስቶ እስከ የካቲት 2015 ዓ.ም. ድረስ ከኢትዮጵያ ሕዝብ አሥር በመቶ የሚሆነውን ዘልቆ መድረስ የቻለ ሲሆን፣ ይህም ወደ ቁጥር ሲቀየር ከ11 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ መሆኑን ዋና ሥራ አስፈጻሚው አንዋር ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪ በ25 ከተሞች ውስጥ 847 የኔትወርክ መቀበያዎችን መዘርጋቱን፣ እንዲሁም አገልግሎቱን ተደራሽ የሚያደርጉ 28,000 ቸርቻሪዎች፣ 103 አከፋፋይ ሱቆችና 5,000 የግዥ ወኪሎችን ማፍራቱን ገልጸዋል።
የሳፋሪኮም አገልግሎት ተጠቃሚዎች የድምፅና የኢንተርኔት አጠቃቀም የአንድ ወር አማካይ በቅደም ተከተሉ መሠረት 64 ደቂቃና 1.9 ጂቢ መሆኑን የኩባንያው መረጃ ያመለክታል።