Friday, March 31, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ሕዝባችን ማንኛውንም ሰላም አደፍራሽ አካል አይታገስም›› አቶ ብርሃኑ ዘዉዴ፣ የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ

በስምጥ ሸለቆና በተራሮች የተከበበው የጋሞ ዞን በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ውስጥ ከሚገኙ ዞኖች አንዱ ሲሆን፣ በቅርቡ ከሌሎች አምስት ዞኖችና አምስት ልዩ ወረዳዎች ጋር በመሆን ‹‹ደቡብ ኢትዮጵያ›› የተሰኘ አዲስ ክልል ለመመሥረት ሕዝበ ውሳኔ አካሂዷል፡፡  ሲሳይ ሳህሉ  ከዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ ዘዉዴ ጋር ስለዞኑ ወቅታዊ ሁኔታና ሊመሠረት ስለሚታሰበው አዲስ ክልላዊ መዋቅር በተመለከተ ያደረገው ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

ሪፖርተር፡- የጋሞ ዞን በተፈጥሮ የታደለ አካባቢ ነው፡፡ በዚህ ረገድ በአካባቢው ያለው ማኅበራዊ መስተጋብርና የልማት እንቅስቃሴ ምን ይመስላል?

አቶ ብርሃኑ፡- የጋሞ ዞን በተለያዩ የተፈጥሮ ፀጋዎች የታደለ ነው፡፡ ሕዝቡም ሰላም ወዳድ፣ አብሮ የመኖርና የዳበረ ባህል ያለው፣ በተለይም ከሌላው ጋር እንዴት ተቻችሎ መኖር እንዳለበትና እርስ በርስ እንዴት ይቅርታ መደራረግ እንዳለበት የሚያስተምር ቱባ ባህል ያለው ነው፡፡ ይህ ትልቅ ፀጋ ነው፣ እንደ አካባቢም እንደ አጠቃላይ ሕዝብም የተሰጠን ነው፡፡ ይህንን ፀጋ ወደ ሀብት እንዲቀየር ለማድረግ ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተዋል፡፡ በተለይ በአካባቢው ያለው የቱሪስት መዳረሻ ሰፊ እንደ መሆኑ መጠን፣  ለቱሪዝም ኢንቨስትመንት አመቺ ተፈጥሮ ስላለ መሠረተ ልማቶችን የማሟላት፣ ቱሪስት መዳረሻ ሥፍራዎችን የማልማትና የማስተዋወቅ ሥራዎችን እንየሠራን፣ እንዲሁም ለቱሪስቶች አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት እንዲበራከቱ በተለየ ሁኔታ ጥረት ስናደርግ ቆይተናል፡፡ በዚህም የተነሳ በርካታ የአገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶች የሚጎበኙት አካባቢ ሆኗል፡፡ ኢትዮጵያውያንና ከውጭ አገሮች የሚመጡ ጎብኚዎች በጋሞ ዞን አርባ ምንጭና አካባቢውን፣ እንዲሁም በአጎራባች ዞኖችና ወረዳዎች ያሉ የቱሪስት መዳረሻዎችን ጎብኝተው እንዲመለሱ ለማድረግ ተሠርቷል፡፡ አካባቢው ከፍተኛ የቱሪስት ፍሰት ያለበት ነው፡፡ ይህ ሁኔታ በቀጣይም ተጠናክሮ ይቀጥላል የሚል ተስፋ አለን፡፡ ምክንያቱም ጥሩ ተፈጥሮ አለ፡፡ ተፈጥሮውን ቱሪስቶችን ማቆየት በሚያስችል ሁኔታ ካለማነው፣ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትን ካበራከትን ልማቱ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡

ከዚህ ውጪ በመደበኛው የግብርና ሥራም ሆነ በሌሎች የልማት ሥራዎች ላይም ጠንካራና ታታሪ ሕዝብ አለ፡፡ ለእርሻ አመቺ አካባቢና ሁሉም ዓይነት የተፈጥሮ ሥነ ምኅዳር ያለው በመሆኑ ለግብርና ሥራ ምቹ ዕድል ይፈጥራል፡፡ እንደ አግሮ ኢኮሎጂው ባህሪ ሁሉንም ዓይነት ሥራ ለመሥራት የሚያግዙ የተፈጥሮ ስጦታዎች አሉን፡፡ በተለይ በአትክልትና ፍራፍሬ አካባቢው ይታወቃል፡፡ በማንጎ፣ በሙዝ፣ በአቮካዶ፣ በብርቱካንና በፓፓያ በስፋት ታዋቂ ነው፡፡ በደጋው አካባቢ አፕልና እንሰት የመሳሰሉ የጓሮ አትክልቶች ይበቅሉበታል፡፡ በእንስሳት ዘርፍም ከፍተኛ የቁም እንስሳት ለማዕከላዊ ገበያም ሆነ ለውጭ ገበያ የሚቀርብበት ዞን ነው፡፡ ከዚያም አልፎ ወተትና የወተት ተዋጽኦ በርከት ብሎ የሚወጣበት አካባቢ ነው፡፡

በዚህ እጅግ የተረጋጋ ሰላም ያለው አካባቢ ከልማት ያልተነጠለ ኅብረተሰብ ሆኖ እንዲቆይ ብዙ ጥረት አድርገናል፡፡ ለቀጣይ ዓመታትም ትልቅ ለውጥ ማምጣት እንችላለን የሚል እምነት አለን፡፡ በሌሎች የማኅበራዊ ዘርፎችም ትልቅ የሚባሉ ሥራዎች እየተሠሩ ነው፡፡ በዞን፣ በወረዳና በከተማ አቅም የተገነቡ የጤናና የትምህርት ተቋማት አሉ፡፡ የክልልና የፌዴራል መንግሥትን ሳንጠብቅ በራስ አቅም ኅብረተሰቡን በማስተባበር የምንገነባቸው ትልልቅ የልማት ሥራዎች አሉ፡፡ ክልሉ ሊሠራቸው የሚገባቸውን መንገዶች በራስ አቅም ሠርተናል፡፡ ይህም ተሞክሮ ይሆናል ተብሎ በክልልም ዕውቅና የተሰጠው አካባቢ ነው፡፡ ስለዚህ ኅብረተሰቡ ተረጋግቶ ልማት ላይ እንዲሳተፍ ካደረግን አካባቢው ትልቅ ፀጋ ያለው ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የጋሞ አካባቢ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ውስጥ በመልካም አስተዳደርና በልማት፣ እንዲሁም በሌሎች ጥያቄዎች የተነሳ በክልልነት ለመደራጀት ከጠየቁ አካባቢዎች አንዱ ነው፡፡ በአካባቢው ያለው የልማት ሁኔታ ምን ይመስላል?

አቶ ብርሃኑ፡- ትንሽ መልከዓ ምድሩ ተራራማ ቦታዎች ያሉት ነው፡፡ ለዞኑ የመንገድ መሠረተ ልማት ትልቅ ኢንቨስትመንት የሚፈልግ የልማት ዘርፍ ነው፡፡ በመሆኑም አብዛኛው ሕዝብ እንዳይገናኝ ያደረጉ የመንገድ ችግሮች አሉ፡፡ በተወሰነ መንገድ የፌዴራል መንግሥት የተወሰኑ ከፍ ያሉ ፕሮጀክቶችን እየገነባ ይገኛል፡፡ በጨረታ በግንባታ ላይና ተጠይቀው እየተጠበቁ ያሉ የመንገዶች ፕሮጀክቶች አሉ፡፡ እንዲሁም በክልል ገጠር መንገድ የሚለሙ ውስን መንገዶች አሉ፡፡ ነገር ግን በዋናነት የገጠር ተደራሽ መንገድን በኅብረተሰብ ተሳትፎ ሰፋ ያለ የመንገድ መሠረተ ልማት ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት ወረዳን ከዞን፣ ዞንን ከዞን፣ ቀበሌን ከቀበሌ፣ ወረዳን ከቀበሌ የሚያገናኙ መንገዶች ላይ ትኩረት አድርገን የተሠሩትን የመጠገንና አዳዲስ መንገዶችንም የመክፈት ሥራ ሠርተናል፡፡ በልዩ ዘመቻ በተለይ በቀበሌዎች ውስጥ ያሉ መንገዶች እንዲከፈቱ በኅብረተሰብ ተሳትፎና አስተዋጽኦ እንዲከፈት አድርገናል፡፡ ኅብረተሰቡ የማሽን ኪራይና የነዳጅ ችሎ መንገድ እንዲፈከት ካደረገ፣ መንግሥት ጠጠር የማልበስና የመንገድ የውኃ ማፍሰሻና ሌሎች የቅርፅ ሥራዎች እየሠራን በርከት ያሉ አካባቢዎች እንዲገናኙ አድርገናል፡፡ አሁንም በግንባታ ላይ ያሉ መንገዶች አሉ፡፡ በቀጣዮቹ ሁለትና ሦስት ዓመታት ከመንገድ መሠረተ ልማቶች ጋር ያሉ ችግሮች መፈታት አለባቸው የሚል አቋም እንደ ዞን ዕቅድ አስቀምጠን እየሠራን እንገኛለን፡፡

ከጤና ተቋማት አኳያ በዞናችን አሁን አገልግሎት እየጀመረ ያለ የሪፈራል ሆስፒታል በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አማካይነት እየተገነባ ነው፡፡ ይህ ሆስፒታል በቅርቡ ወደ አገልግሎት ይገባል፡፡ በርካታ ሥራዎች ተከናውነው ተጠናቋል፡፡ በሌላ በኩል የአርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል በዞኑ ይገኛል፡፡ አሁን ይህን ስንመለከት ሁለት አጠቃላይ ሆስፒታሎች አራት የመጀመርያ ደረጃ ሆስፒታሎች፣ አንድ ሪፈራል ሆስፒታል በቅርቡ ወደ ሥራ ይገባሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በሥራ ላይ ያሉ በርከት ያሉ የጤና ጣቢያዎች አሉን፡፡ ከላይ ከጠቀስኩልህ ውስጥ ሁለቱን በተለየ በራስ አቅም ኅብረተሰቡን በማስተባበር፣ በእኛ በራስ  በጀት ብዙ ጊዜ የክልል መንግሥት ይገነባቸው የነበሩትን እኛ የክልልን እጅ ሳንጠብቅ በራሳችን አቅም ያስገነባናቸው ተቋማት ናቸው፡፡ በእያንዳንዱ ወረዳና ጤና ጣቢያ አምቡላንስ ኖሮ ሕዝብ ማገልግል እንዲቻል፣ የመንገድ ጥርጊያ ጭምር ተስተካክለው ሥራ እንዲሠሩ ተደርጎ ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡ ምንም እንኳ የሚቀሩ ሥራዎች ቢኖሩንም ጥሩ ስኬት የተመዘገበበት መስክ ነው ማለት እንችላለን፡፡ ከኤሌክትሪክ ተደራሽነት አኳያ እንደ ዞን መሠረታዊ ችግር አለብን፡፡ የሕዝቡ የኤሌክትሪክ ሽፋን ከሃያ በመቶ በላይ የዘለቀ አይደለም፡፡ ይህንን ሁልጊዜ ከክልልም ከመብራት ኃይልም ጋር የምንጮኽበት ነው፡፡ የቅድሚያ ቅድሚያ ተሰጥቶ ይሠራሉ የተባሉ ቀበሌዎች ሁሉ ተደራሽ ያልሆኑና ትኩረት ያላገኘ ስለሆነ፣ በቀጣይ በዚህ ረገድ ብዙ ሥራ ይጠበቃል፡፡ በእኛ የሚታዘዝና በእኛ በጀት የሚንቀሳቀስ ተቋም ባለመሆኑ፣ በራሱ ዕቅድ የሚመራ በመሆኑ ቢያንስ ተቀራርበን የሕዝባችንን ፍላጎትና ያለውን ችግር መፍታት እንዲቻል ከመብራት ኃይል ጋር እየተጻጻፍን እንገኛለን፡፡ 

ሪፖርተር፡- ከመብራት ኃይል ጋር የገጠማችሁ ጉዳይ ምንድነው?

አቶ ብርሃኑ፡- አንዱ ችግር የመብራት አቅራቢ ድርጅት ትኩረት ማነስ ነው ብለን ነው የምናስበው፡፡ በተለይም የቅድሚያ ቅድሚያ መሠራት አለባቸው የሚባሉ ፕሮጀክቶች ሲጠየቁ የሚቀርቡ ምክንያቶ አሉ፡፡ አገራዊ ሁኔታና የበጀት እጥረት ይነሳል፡፡ ግን እነሱ ሌላ ምክንያት ሊያቀርቡ ይችላሉ፡፡ እንደ እኛ ግን የትኩረት ማነስ  ነው፡፡ በተለይ ለአካባቢው ትኩረት አለመስጠት የሚል እምነት ነው ያለን፡፡ የክልሉ መንግሥት ግፊት እንዲያደርግ ምክክር አድርገናል፡፡ የክልል መንግሥት ምላሽም መብራት ኃይል ችግሩን እንዲፈታ እንደተነገረው፣ ነገር ግን ለጥያቄው ምላሽ ሳይሰጥ እንደቆየ ይነሳል፡፡ በቀጣይ ትኩረት እንዲሰጥ እንፈልጋለን፡፡

ሪፖርተር፡- በዞኑ ምን ያህል ሕዝብ ነው ያለው?

አቶ ብርሃኑ፡- 1.9 ሚሊዮን፡፡  

ሪፖርተር፡- በዞኑ በርካታ ወጣቶችንና በዕድሜ ገፋ ያሉትን ጭምር ስናናግር የሥራ አጥነት ችግር ትልቅ ተፅዕኖ እንደፈጠረባቸው ይናገራሉ፡፡ በዞናችሁ ያለው የሥራ አጥነት ችግር እንዴት ይገለጻል?

አቶ ብርሃኑ፡- የሥራ አጥነት ችግር በዋናነት እንደ አገር ቅድሚያ የሚሰጠው ተብሎ ይነሳል፡፡ በርካታ ዜጎች ሥራ አጥ ናቸው፡፡ ለእነሱ የሥራ ዕድል መፍጠር አለብን ብለን እናምናለን፡፡ በእርግጥ ወደ ገጠሩ አካባቢ ችግሩ ጎልቶ ላይነሳ ይችላል፡፡ ከተሞች አካባቢ ግን ሰፋ ያለ የሥራ ዕድል መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ አካባቢው ከፍተኛ የግብርና ምርት፣ እንዲሁም የፋብሪካ ብረቶች ያለበት ቢሆንም በዚያው ልክ ኢንዱስትሪዎች የሉም፡፡ የአካባቢውን ምርት የሚረከቡ ኢንዱስትሪዎች አልተስፋፉም፡፡ በዚህም የተነሳ ሰፋ ያለ የወጣቶች ቁጥር በሥራ አጥነት ያለበት አካባቢ ነው፡፡ በእኛ አቅም በተቻለ መጠን ብዙ ሥራ ለመፍጠር ብዙ ጥረት አድርገናል፣ በየዘርፉ አቅደን እየሠራን ነው፡፡ ነገር ግን ካለው ፍላጎት አኳያ የሚመጣጠን አይደለም፡፡ በተለይ ይህን የሥራ አጥ ወጣት ቁጥር የሚመጥን ሥራ ለመፍጠር የክልልና የፌዴራል መንግሥት ጣልቃ ገብተው መፍትሔ ሊሰጡት የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡ አርባ ምንጭ ትልቅ ከተማ ነው፡፡ የጋሞ ዞንም ትልቅ  ነው፡፡ በአካባቢው ያለው ሀብትም ትልቅ ኢንቨስትመንት ይፈልጋል፡፡ ስለዚህ ያንን መሸከም የሚችሉ ገዘፍ ያሉ ኢንዱስትሪዎች ያስፈልጉታል፡፡ በተለይ ደግሞ በኢንዱስትሪው ዘርፍ የተመረቁ ወጣቶች ሥራ አጥተው በስፋት እናስተውላለን፡፡ በዚህ አካባቢ ስለዚህ የአካባቢውን የተፈጥሮ ፀጋ በማየት የኢንዱስትሪ ልማት ቢስፋፋ የሥራ አጥነቱን ችግር ማቃለል ይቻላል፡፡ እስካሁን በዞናችን ውስጥ 40,000 ወጣቶች ሥራ አጥ መሆናቸውን ለይተናል፣ አብዛኛው ከተማ ውስጥ ይገኛሉ፡፡  

ሪፖርተር፡- የግብርና ምርት የሚመረትበት አካባቢ እንደ መሆኑ መጠን ገበሬው አምርቶ ተረካቢ በማጣቱ የደረሰባችሁ ጉዳት አለ ማለት ይቻላል?

አቶ ብርሃኑ፡- አዎ፣ በጣም ከፍተኛ ጉዳት አለ፡፡ በስፋት ወደ ማዕከላዊ ገበያ ከሚወጡት ምርቶች ውስጥ ሙዝና አፕል ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ሌሎች ምርቶችም በስፋት ይወጣሉ፡፡  ነገር ግን እነዚህ ሁለቱ ምርቶች ሲታዩ አርሶ አደሩ ያመርታል፣ መሀል ላይ ደላላው ዋጋ ይተምናል፡፡ ከፈለገ ምርቱ ከማሳው እንዳይጫን ያደርጋል፡፡ ካሻው ደግሞ ምርት ተጭኖ ሄዶ እንዲበላሽና እንዲጣል ያደርጋል፡፡ ደላላ ራሱ በሚፈልገው ካልሄደና ራሱ ዋጋ ካልተመነ የፈለገውን ያደርጋል፡፡ ይህ የደላላ  ጉዳይ የቆየ ችግር ነው፡፡ መፈታት አለበት በሚል ብዙ ጥናቶችን ስናደርግ ቆይተናል፡፡ ውይይት አድርገናል፡፡ አንዱ መፍትሔ የአካባቢውን ምርት የንግድ ምልክት በማድረግ ብራንድ መፈጠር አለበት በሚል፣ ከፌዴራል ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ ጋር በመሆን የአርባ ምንጭ ሙዝና የጨንቻ አፕል ስያሜ እንዲያገኝ ሠርተን ስያሜ ተሰጥቷል፡፡ ስለዚህ አሁንም የምርት ጥራቱን ማስጠበቅና ጥራቱን በማስተካከል በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ፣ በተጨማሪ ጥራትና መጠን ላይ መሥራት ይኖርብናል፡፡ በተቻለ መጠን ደላላው በተለይ አርሶ አደሩ ተጠቃሚ እንዳይሆን የሚያደርገውን ለመከላከል ብዙ ጥረቶች አድርገናል፡፡ በዚህ ረገድ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፈቃድና ትብብር ለአርሶ አደሮችና ለአምራቾች መሸጫ ቦታ ለማዘጋጀት እየሠራን እንገኛለን፡፡ ሌሎች ከተሞችንም እንዲሁ ጠይቀን ጥሩ ምላሽ ሰጥተውን አርሶ አደሮች እየተጠቀሙ ይገኛሉ፡፡ ስለዚህ ከምርት ገዥ ማጣት ጋር ያለው ሁኔታ ትልቅ ተግዳሮት ነው ማለት ይቻላል፡፡ አሁን ለአዲስ አበባ ከተማ ጥያቄ አቅርበናል፣ ጥሩ ምላሽ እንጠብቃለን፡፡ ምክንያቱም ሁለቱንም ተጠቃሚ የሚያደርግ አሠራር በመሆኑ መሀል ላይ ያለውን ደላላ ማስወጣት ይቻላል፡፡ አርሶ አደሩም ምርቱን  በቀጥታ መሸጫው ላይ ሲያቀርብ በሸማቹ ላይ ያልተፈለገና ያልተጋነነ ዋጋ እንዳይኖር ያግዛል፡፡ ይህ አሠራር የሸማቹን ጫና ያቀላል፡፡ ለአርሶ አደሮች በኅብረት ሥራ ማኅበራቸው አማካይነት ምርታቸውን ተደራጅተው ለሸማቹ ምርት ማቅረብ እንዲችሉ፣ እንዲሁም ምርታቸውን ሊያቆዩበት የሚችሉባቸው ቦታዎችን ነው የጠየቅነው፡፡  

ሪፖርተር፡- የጋሞ ዞን ‹‹ደቡብ ኢትዮጵያ›› የተሰኘ ክልል ለመመሥረት ሕዝበ ውሳኔ አካሂደው ውጤቱን ከሚጠባበቁበት ውስጥ አንዱ ነው፡፡ ለዚህ ጥያቄ ምን አነሳሳችሁ?

አቶ ብርሃኑ፡- እንግዲህ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ከጅምሩ ሲዋቀር ቀድሞ አምስት የነበሩ ክልሎች ያለ ሕዝብ ይሁንታ፣ የተወሰኑ ፖለቲከኞችና የተወሰኑ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በነበራቸው መግባባት ሁሉንም ወደ አንድ አምጥተው ሐዋሳን ዋና ከተማ መቀመጫ ያደረጉበት አሠራር ነበር፡፡ የጋሞ ሕዝብም ሆነ ሌሎችም አካባቢዎች በዚህ የክልል አመሠራረት ተቃውሞ ነበራቸው፡፡ ያ ተቃውሞና ቅራኔ ቆይቷል፡፡ ሁለተኛ ደግሞ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት ላይ ሕዝቡ ከፍትሐዊ ተጠቃሚነት ጋር ያነሳው የነበረ ቅሬታ አለ፡፡ ሁሉንም ሕዝብ እኩል የሚያይ አይደለም በሚል ማለት ነው፡፡ በአንድ ላይ መሆኑ ኅብረ ብሔራዊነቱ፣ አንድነቱና ለሕዝብ ያለው መቀራረብ ትልቅ ፋይዳ ቢኖረውም በልማት ረገድ የመንግሥት የልማት ፕሮጀክቶች እንኳ ሲመደቡ ፍትሐዊ ያልሆነና ሕዝብን እኩል የማያይ ሆኖ በፖለቲከኞች ፍላጎት ነው ሲመደብ የነበረው፡፡ ስለዚህ ሁሉንም እኩል ለመሆን ያስቻለ ክልል አይደለም የሚለው ቅሬታ በስፋት ተነስቷል፡፡ ያ በኢኮኖሚና በልማት ዘርፍ ነው፡፡ ከዚያ ባሻገር በፖለቲካውም ዘርፍ ያለው ተሳትፎ ሁሉንም እኩል ያሳተፈ አይደለም፡፡ አንዳንዱን ያገለለ፣ አንዳንዱን ደግሞ ያጋነነ የፖለቲካ ተሳትፎ ያለበት ክልል ነው የሚል ቅሬታም ስለነበር፣ የራሳችን ክልል ይሰጠን የሚል ጥያቄ በተለይ ለውጥ ከመጣ ጀምሮ ከሕዝቡ ይነሳና ሲንሸራሸር ስለቆየ ነው፡፡ በኋላ ላይ እንዴት ቢደራጅ ይሻሻል ተብሎ ከሕዝቡ ጋር ምክክር ተደርጎና ሕዝቡ መክሮበት ቢወስን የተሻለ ነው በሚል፣ ሕዝብ የተሻለውን መንገድ ራሱ ቢወስን በሚል ላለፉት ሁለት ዓመታት እጅግ ሰፊ ውይይት በሕዝቡ ዘንድ ሲደረግ ቆይቷል፡፡ አሁን ግን ወደ መቋጨት ማድረስ ተችሏል፡፡ ወደ እዚህ ሒደት ሲደርስ ዞኖችና ወረዳዎች ብዙ ውይይት ካደረጉና አማራጮችን ካቀረቡ በኋላ፣ በአማራጮች ላይ እንዴት መደራጀት እንደሚቻል መክረውና በየራሳቸው ምክር ቤት ወስነው ለፌዴሬሽን ምክር ቤት  አሳውቀው፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤትም የሕዝቡ ፍላጎት ምንድነው የሚለውን በመወሰን ይህን የሕዝብ ውሳኔ እንዲካሄድ አድርጓል፡፡

ሪፖርተር፡- በቀጣይ በሕዝበ ውሳኔ ውጤት መሠረት አዲስ ክልል የሚመሰረት ከሆነ በውስጡ በርካታ ብሔረሰቦችና የዞን አስተዳደሮችን ይዞ ነው የሚመሠረተው፡፡ አዲስ በሚመሠረተው ክልል ውስጥ የመልካም አስተዳደር ጥያቄና ራሳችንን እንቻል የሚሉ ሌሎች ዓይነት ጥያቄዎች ቢመጡ እንዴት ልታስተናግዱ ትችላላችሁ?

አቶ ብርሃኑ፡- እንግዲህ የአደረጃጀት መዋቅር ሲበዛ በከፍተኛ ደረጃ የአስተዳደር ወጪ ይጨምራል፡፡ በዚህ ውስጥ ደግሞ ሊፈጠር የሚችለው ማነቆ ይታወቃል፡፡ ማለትም ከፍተኛ ጫና እንደሚፈጥር ግልጽ ነው፡፡ ከዚያ ውጪ ደግሞ እነዚህ ሕዝቦች አብረው የኖሩ ናቸው፡፡ ከዚህ ቀደምም በጠቅላይ ግዛትና በክፍለ አገር አወቃቀሮች አብረው እዚሁ ቀጥለው የነበሩ ናቸው፡፡ ለመደራጀት የጠየቁት፡፡ ከዚያም አልፎ በመልከዓ ምድርም በሥነ ልቦናም የተቀራረበ ሕዝብ ስለሆነ፣ እንዲሁም በሕዝቡ መልካም ፈቃድ የመጣ በመሆኑና ቀደም ብዬ እንዳነሳሁልህ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እንዲፈርስና እንደገና እንዲደራጅ ሐሳቡ በከፍተኛ ቅሬታ ግፊት እንዲደረግ የተደረገበት ምክንያት አለ፡፡ ይህም  ለቀድሞው ክልል በነበረ ቅሬታ በመሆኑ በዚያም የተነሳ እያንዳንዱ ዜጋ ዕድል ተሰጥቶት በነፃ ፈቃዱ እንዲወስን ተደርጓል፡፡ ስለዚህ ይበጀኛል የሚለውን ነው ሕዝቡ የመረጠው፡፡ ምናልባት በሒደት አዳጊ ፍላጎቶች መጥተው ጥያቄ ሊነሳም፣ ሊቀጥልም ይችላል፡፡ ነገር ግን ለአሁኑ አብሮ መኖርና መደራጀት እንደሚቻል፣ በሕዝቦች የጋራ ፈቃድ ላይ የተመሠረተ ክልል ስለመሆኑ ተረጋግጦ ስለሚዋቀርና በዋናነት መሠረታዊ ችግር ተብለውና ለክልል አደረጃጀት ጥያቄ ምክንያት ናቸው ተብለው የቀረቡ አሉ፡፡ እነሱም የኢኮኖሚና የልማት ኢፍትሐዊነት ማስወገድና እኩል ዕድል ለሁሉም ማበጀት፣ ሕጎቹን ማሻሻልና ለሁሉም የሚበጁና ሁሉንም ሕዝብ እኩል የሚያዩ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ያ ካልሆነ እንዳልከው ክልልነቱ በራሱ ዋስትና አይኖረውም፡፡ ሕዝቡ መርጦ እንደራጅ ብሎ ቢደራጅም፣ ፍትሐዊነትን ማረጋገጥና ለሁሉም እኩል የሚጨነቅና የሚሠራ ክልል ማድረግ ካልተቻለ ጉዳዩ ጥያቄ ውስጥ ስለሚገባ ያንን ማስተካከል አለብን፡፡ ያንን ማድረግ ከተቻለ ሕዝቦች ባህላቸው ተቀራራቢ፣ አኗኗራቸውም እንዲሁ ተቀራራቢ ነው፡፡ በመልከዓ ምድራዊ አቀማመጣቸውም በብዙ ሁኔታ የተሳሰሩ በመሆናቸው ትስስሩ ከፍ ያለ ነው፡፡ አመራሩ ካገዛቸው ሕዝባችን አብሮ የመኖር ዕድላቸው ሰፊ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በዚህ ሕዝበ ውሳኔ አዲሱ ክልል የሚመሠረት ከሆነ ተያይዘው የሚመጡት የዋና መቀመጫ፣ ዓርማ፣ የሰንደቅ ዓላማና መሰል ጉዳዮችን በተመለከተ ምን ታስቧል?

አቶ ብርሃኑ፡- አዲሱ ክልል በፌዴሬሽን ምክር ቤት ሁሉም ዞኖችና ወረዳዎች በጋራ ተስማምተው ባቀረቡለት መሠረት፣ ‹‹የደቡብ ኢትዮጵያ›› ክልል በሚል የሚዋቀር ይሆናል፡፡ በቀጣይም ይፀድቃል ብለን ነው የምንጠብቀው፡፡ ከሰንደቅ ዓላማ፣ ከዓርማ፣ ከመቀመጫና አብረው ከሚመጡ ጉዳዮች ጋር ያሉ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው፡፡ የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤትና ኮሚቴ ተቋቁሞ በቀጣይ ለውይይት ሊቀርቡ የሚችሉ ጉዳዮችን ተወያይቶ ለማስቀመጥ የሚረዳ ሐሳብ ይመጣል፡፡ በዋናነት የታሰበው በተለይ ከዋና መቀመጫ አንፃር ሁለትና ከሁለት በላይ ዋና ከተሞች ይኖሩታል በሚል መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡ ነገር ግን የት? እንዴት? በምን መልኩ? የሚለው ጉዳይ በቀጣይ በምክክር ይወሰናል፡፡ 11ዱም የዞንና የወረዳ መዋቅሮች ተወያይተው የሚወስኑት ነው የሚሆነው፡፡ ያም የሚሆነው በአገልግሎት በሚያመች፣ ምክንያታዊና ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ የሌሎች አገሮችን የልማት ተሞክሮ በማየት በዚህ መነሻ የሚወሰን ይሆናል፡፡ ሁለተኛ ከዚያ በላይ ከተሞች ይኖሩታል ሲባል የክልሉ ዋና ከተሞች ሲመሠረቱ የሕግ አውጭ፣ አስፈጻሚና ተርጓሚውን ታሳቢ ያደረገ የከተሞች ምሥረታ ይሆናል በሚል ነው፡፡ በቀጣይ ሕግም እየተዘጋጀለት ነው፡፡ የዘርፉ ባለሙያዎች ተሳትፈውበት የተሻለው አማራጭ ይወሰዳል፡፡  

ሪፖርተር፡- እንደ ዞን ሊነሱ የሚችሉ ችግሮች ምንድን ናቸው?

አቶ ብርሃኑ፡- ትልቅ እሴታችን ነው ብለን የምናስበው ጉዳይ የሰላም ሁኔታ ነው፡፡ ሕዝቡ ተባባሪ ነው፡፡ ሕዝባችን ማንኛውንም ሰላም አደፍራሽ አካል አይታገስም፣ አይሸከምም፡፡ ችግሮች እንኳ ቢኖሩ በውይይት ያምናል፣ ቀርቦ ሐሳብ በመስጠት መስተካከል ያለበትን እንዲስተካከል በማድረግ ችግሮቹን በማጥበብ ሰላም ለመፍጠር የሚያምን ሕዝብ ነው፡፡ እውነት ለመናገር የተወሰኑ የልማት ሥራዎች አሉ፡፡ ያም ሊሆን የቻለው በሰላማችን ውጤት ነው፡፡ ስለዚህ ይህን የምናስቀጥል ይሆናል፡፡ በቀጣይ ልዩ ትኩረት የሚፈልጉ ጉዳዮች ከምንላቸው ውስጥ አንዱ አርባ ምንጭና አካባቢው የተለያዩ የተፈጥሮ ፀጋዎች ያሉት አካባቢ ነው፡፡ ያን ፀጋ ማስጠበቅ ያስፈልጋል፡፡ ካሉን ፀጋዎች ውስጥ በዓባያና በጫሞ ሐይቆች፣ እንዲሁም በነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ ላይ የተደቀኑ አደጋዎች አሉ፡፡ በአደጋዎቹ ላይ ብዙ ጥናት አድርገናል፡፡ በእኛ አቅም እነዚህን ተፅዕኖዎችን ለማስቀረት ከፌዴራል ተቋማት ጋር እየሠራን እንገኛለን፡፡ ነገር ግን ችግሩ በጣም ትኩረት የሚያሻው በመሆኑ፣ የፌዴራል መንግሥትና የዓለም አቀፍ ተቋማት ተፈጥሮን የማስጠበቅ ሥራ ላይ እንዲተባበሩ ጥሪ እናቀርባለን፡፡ ዓባያና ጫሞ ላይ የሚታየው ችግር በዋነኝነት የአፈር ደለል፣ የሐይቆቹ ተፋሰስ መነሻ ከተለያዩ ዞኖች ከክልላችንም ውጪ  በመሆናቸው ከፍተኛ የሆነ የደለል ችግር ከተፋሰሶች ይመጣል፡፡ የነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ በተመሳሳይ በሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎች ተጎድቷል፡፡ በሕገወጥ መንገድ ወደ ፓርኩ የሚደረጉ ሠፈራዎችና እንቅስቃሴዎች ከኦሮሚያም ከደቡብ ክልልም በኩል አደጋ ተደቅኖበታል፡፡ ሁለተኛው አካባቢው ከፍተኛ የግብርና ምርቶች የሚወጡበት በመሆኑ፣ ማልማት የሚችል ባለሀብትም ይሁን የመንግሥት አካላት በዚህ አካባቢ ማልማት የሚፈልጉትና የሚችሉ አካላትን፣ በተለይም በኢንዱስትሪው ዘርፍ የተሰማሩ ኢንቨስተሮችን በመላክ ቢያግዙን ለአገርም ይጠቅማል፡፡ አቅምና ሀብት መፍጠርና ወደ አገር ኢኮኖሚ ብዙ ሀብት መቀላቀል ይቻላል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ሥራ ከጀመረ አራተኛ ወሩን የያዘው ፀሐይ ባንክ ካፒታሉን ወደ አምስት ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ወሰነ

በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ የግል ባንኮች በተለየ ሁኔታ በ373 ባለአክሲዮኖች...

ጎህ ቤቶች ባንክ ወደ ቤት ልማት ለመግባት ብሔራዊ ባንክን ፈቃድ ጠየቀ

በስምንት ወራት ውስጥ 7.9 ሚሊዮን ብር ማትረፉን አስታውቋል ኢትዮጵያ ውስጥ...

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ18 ቀናት ግዢ መፈጸሚያ ብቻ እንደሚሆን አይኤምኤፍ ተነበየ

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ0.6 ወር ወይም...

ሒጂራ ባንክ የ143 ሚሊዮን ብር ኪሳራ አስመዘገበ

በኢትዮጵያ ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነፃ ባንክ አገልግሎት ለመስጠት ወደ...