Thursday, March 23, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉኢትዮጵያን “የሉዓላዊ ብሔሮች” ግዛተ ምድር?

ኢትዮጵያን “የሉዓላዊ ብሔሮች” ግዛተ ምድር?

ቀን:

በአንዳርጋቸው አሰግድ

ከ15 ዓመታት በላይ ይሆናል። ከአንድ ከአሜሪካ ለሥራ ጉዳይ ወደ አፍሪካ ከመጣ ኢትዮጵያዊ የዓይን ሐኪም ጋር በማሊ ዋና ከተማ ባማኮ ተገናኘን። ሥፍራው አንድ ቡና ቤት ነበር። ራቅ ራቅ ብለን ተቀምጠናል። እየሰረቀ ያየኛል። እየሰረቅኩ አየዋለሁ። ኢትዮጵያዊ መሆናችንን ተግባብተናል። ማን ይድፈር? ደግነቱ ልበልና፣ የፈረንሣይኛ ቋንቋ ችግር ገጥሞት ለማዘዝ ሲቸገር አየሁት። ቀልጠፍ ብዬ ወደ እሱ ተራመድኩና በእንግሊዝኛ “ልረዳዎት እችላለሁ?” ብዬ ጠየቅኩት። ምንም ሳያንገራግር “አመሠግናለሁ፣ ቁርስ ለማዘዝ ፈልጌ ነበር” በማለት በአማርኛ መለሰልኝ። አስተረጎምኩ። ቁርሱን አዘዘ። ከጠረጴዛው ተዳበልኩ።

በመጀመርያ በአማርኛ ያናገረኝ በደመነፍስ እንደነበር ያስታውቃል። አሁን ከጠረጴዛው ስዳበል፣ የዘመኑ መለያ በሆነው የቋንቋ ጥያቄ ተወረረ። እንዳያስቀይመኝ በመጣር ላይ እንደሆነ ያስታወቅበታል። እንዳይተወኝ በአገር ልጅነት ተዋውቀናል። አስተርጓሚውም ሆኛለሁ። “ያበጠው ይፈንዳ” ስላለ ይመስለኛል፣ “ስንት ቋንቋ ይናገራሉ?” ሲል ጠየቀኝ። “ብሔሬን አይደል የምትጠይቀኝ? አትቸገር” ብዬ መለስኩ። ዘና አለ። “ምን በዛሬ ጊዜ!” አለና እንደ ሰው/ለሰው ወደ መተዋወቅ አቀናን። ባማኮን ለአንድ ሳምንት ያህል አመስናት። ያንን ነፃና ቸር ሰው እንደ አንድ ሰብ ያለውን ሰብዓዊ ነፃነት የገሰሰው ምንድነው? ሰብዓዊ ቸርነቱን ያመቀ ፍጡር ሆኖ እንዲንገላወድ ያደረገው ምንድነው?

የችግሩ ምንጭ ተደጋግሞ ተነግሯል። ብዙ ተጽፎበታል። በርካታ ውይይቶች ተካሂደውበታል። ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 8/1 እና 2 ሥር ‹‹የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤቶች ናቸው። ይህ ሕገ መንግሥት የሉዓላዊነታቸው መገለጫ ነው›› እያለ መደንገጉም አይደለም። ምክንያቱም፣ የፌዴራል አስተዳደር ክፍለ መንግሥታት በሚያስተዳድሩት ክፍለ ግዛት ውስጥ በሕግና ደንብ የተወሰነ ሉዓላዊነት አላቸው። በኢትዮጵያ “ፌዴራል” ሥርዓት ግን፣ የአስተዳደር ክፍለ መንግሥታቱ ሉዓላዊነት ልክ በሕግና ደንብ የተዘረዘረ፣ የተወሰነና የተደነገገ  አይደለም።

የተጠቀሰው አንቀጽ 8 “የሕዝብ ሉዓላዊነት” በተባለ ርዕስ ሥር የሠፈረ መሆኑንም፣ ታዝቦ ብቻ ለማለፍ አይቻልም። ምክንያቱም፣ “የሕዝብ ሉዓላዊነት” የአንድ አገር ዜጎች በገዥዎቻቸው ላይ ያላቸውን ሉዓላዊ ሥልጣን የሚያስረግጥ ጽንሰ ሐሳብ እንጂ፣ ‹‹የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሉዓላዊ ሥልጣን›› ማለት አይደለም። ዜጎች ይህንን ሉዓላዊ ሥልጣናቸውን በተግባር የሚገልጹትና የሚያሳውቁት በተለይም ደግሞ፣ በነፃና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ወቅት ለሚወዳደሩ ፓርቲዎች በሚሰጡት ወይም በሚነፍጉት የመግዛት መብት ድምፅ እንደሆነም ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ግን፣ በአንቀጽ 6 እና 33 ሥር አንድ ግለሰብ ዜጋ ለመሆን ስለሚችልበት ሁኔታዎች ከማተት ባለፈ፣ ዜጋ በመሆኑ ብቻ ስለተጎናፅፈው የዜግነት ሉዓላዊ መብቱ የሚያወሳ አንድም አንቀጽ የለውም። በአንቀጽ 10/2 ስለዜጎች መብት ቢያወሳም፣ ‹‹የዜጎችና የሕዝቦች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ይከበራሉ፤›› እያለ፣ “ዜጎችንና ሕዝቦችን” አደበላልቆ ነው። ስለሆነም ነው፡፡ ኢትዮጵያዊው ዜጋ በምርጫ ወቅት እንደሉዓላዊ ዜጋ ሳይሆን፣ በብሔር ማንነቱ ለብሔር ፓርቲው ለመምረጥ የተገደደ የብሔር ዕቃ (Object) ፍጡር እስከ መሆን ድረስ ወርዶ የተፈረጀው። ስለሆነም ነው፡፡ በ2013 ዓ.ም. ምርጫ ወቅት ለምሳሌ አንዳንድ ክልሎች አንዳንድ ፓርቲዎችን ‹‹በክልላችን እንኳን ለመመረጥ ለመግባትም አትችሉም፤›› እያሉ የዜጎችን ሉዓላዊ መብት እስከ መግሰስ የደፈሩት። እንደ እውነቱም ከሆነ ስለዚህም ነው፣ መራጩ ዜጋ በአቡጀዲ ከተከለለ መጋረጃ ውስጥ ገብቶ “መምረጡ” እና “የምርጫ” ካርዱን ከተደረደሩ ሳጥኖች ውስጥ መወርወሩ ትርፍ የሚሆነው።

ሕገ መንግሥቱ ከዚህ በኋላ በአንቀጽ 46/2 ‹‹የአስተዳደር ክልሎች የሚዋቀሩት በሕዝብ አሰፋፈር፣ ቋንቋ፣ ማንነትና ፈቃድ ላይ በመመሥረት ነው፤›› ማለቱም፣ “የዜጋና የሕዝብ” ምንነት ፅንሰ ሐሳቦችን በማደበላለቅ መቀጠሉን የሚመሰክር ብቻ አይደለም። “የፌዴራል አስተዳደር” ያለውን ሥርዓቱን በቋንቋ መሥፈርት ብቻ ሰፍሮ ለማዋቀር ሆን ብሎ የሄደበትን መንገድና ርቀት የሚያጋልጥ ነው። በሌላ አነጋገር፣ ሉዓላዊ ዜጋን የብሔር ዕቃ እስከ ማድረግ የሄደበትን መንገድ ርቀት የሚያጋልጥ ነው። ስለሆነም ደግሞ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ምድር አንድ የብሔር ፓርቲ፣ የብሔሩን ልጆች በብሔር መብት ስም በመቶ ሺሕ እስከ መማገድ ድረስ ለመሄድ የበቃው። ሌላውም በብሔር መብት ስም መቶዎችን የሚገድለው፣የሚያፈነቃቅለው፣ የሚያግተው፣ የሚዘርፈው።

ስለዚህም ነው፣ በቋንቋ መሥፈርት የተዋቀሩት የኢትዮጵያ ፌዴራል አስተዳደር ሉዓላዊ ክፍለ መንግሥታቸውን ባሻቸውና እንዳሻቸው የሚገዙበት ዓውድ ተንሰራፍቶ የሚገኘው። ገዥዎቹ በሕገ መንግሥቱ ከአንቀጽ 10 እስከ 44 በ34 አንቀጾች ሙሉ የተዘረዘሩትን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የማክበርና የማስከበር ግዴታ የማይሰማቸው። ዶ/ር ሸዋረጋ ሁሴንና ተጉዋዳ አለባቸው በአንድ ጽሑፋቸው እንዳብራሩት፣ ‹‹ሕገ መንግሥቱ መብት የተባለን መብት ሁሉ ከብሔር መብት በታች አደረገ። ስለዚህም፣ ላለፉት 30 ዓመታት የብሔር ማንነት ፖለቲካ ብቻ በከፍተኛ ደረጃ ተንቦገቦገ። ለሌሎቹ የሰብዓዊ መብት ጥያቄዎች ሊደረጉ ይገባቸው የነበሩት ትግሎች ተደፈቁ፤›› (Women’s Rights and Ethiopia’s Future Social Contract Proceedings Between Failure and Redemption 2022)። 

ላለፉት 30 ዓመታት ስለዚህም የአንድ የሌላ ብሔር ተወላጅ የሆነ ሰብ ቀርቶ፣ የራሱ የሉዓላዊው ፌዴራል አስተዳደር ክፍለ መንግሥት ብሔር ተወላጅ የሆነ ግለሰብም፣ ከብሔር ማንነቱ ባሻገር እንደ አንድ ነፃ ሰብ ለማሰብ፣ ለመወሰንና ለማድረግ ከማይችልበት ሁኔታ ውስጥ ተቀርቅሮ ተገኘ። የፌዴራል አስተዳደር ክፍለ መንግሥታት ኗሪ ዜጎች፣ የብሔሩ ተወላጅ ሆኑ/አልሆኑ፣ የብሔሩን ቋንቋ ተናገሩ/አልተናገሩ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸውን የተገፈፉ ሰቦች የተከማቹባቸው ምድር ሆነው አበቁ። የግለሰብን የእምነት ማንነትንም ሳይቀር፣ በፌዴራል አስተዳደር ክፍለ መንግሥታት ሉዓላዊ ማንነት አጥር ውስጥ ለማጠር ጭምር እስከ መንቀሳቀስ ድረስ ተሄደ። ክልልና ድንበር የማያውቁት የእምነት ቤቶችን ንብረት፣ ለሉዓላዊ ክልል ቅርጫ ለመሰዋት እስከ መነሳሳት ድረስ ተዘለቀ። በዚህ ሒሳብ አየር የሚባለው ሀብት የፌዴራል አስተዳደር ክፍለ መንግሥት ሉዓላዊ ሀብት ቢሆን ኖሮ ያሰኛል፣ መተንፈስም በሉዓላዊ ብሔር ማንነት የሚታቀብ ንብረት ይሆን ነበር።

ክፍለ መንግሥታቱ ራሳቸውን በተጨማሪም የሚያዩትና የሚረዱት እንደ ፌዴራላዊ አስተዳደር ክፍለ መንግሥት ብቻ ሳይሆን እንደ አንድ ሉዓላዊ መንግሥት ጭምር ሆነ። ከፌዴራሉ መንግሥት ባላነሰ ታጥቀው የሚወናኙ። የክልል ምርጫን የሚያካሂዱ። የውጭ ግንኙነቶችን የሚመሩ። ግለሰቦችን ከሌላ ክፍለ መንግሥት ገብተው እያፈኑ ለክልላቸው “ፍርድ” የሚያሰጡ። ነገር ግን፣ በብሔር መብት ስም ሲዘርፉ፣ ሲከብሩ፣ መቶ ሺሕ ወገናቸውን በየጦር ሜዳው ሲማግዱ፣ ሲደፍሩ፣ ሲያፈነቃቅሉ፣ ሲያግቱ፣ ቤተ እምነቶችን፣ ትምህርት ቤቶችን፣ የጤና ተቋሞችን ሲያጋዩ ወዘተ. ጠያቂም/ተጠያቂም የማይወጣቸው። ጠያቂው የብሔሩ ተወላጅ ከሆነ በከሃዲነት የሚፈረጅበት፣ የሚገለልበት። ከሌላ ብሔር ከሆነማ፣ “በሉዓላዊ ብሔር” ነገረ ሥራ ውስጥ ምን ዶሎት? 

ደግሞም ግን፣ በብሔር ታጋይነት ስም ራሳቸውን በራሳቸው አግዝፈው የሚወናኙ አንዳንድ የፖለቲካ ድርጅቶችና አንዳንድ ግለሰቦችም አሉ። አቋሳይና አጋጭ ንግግሮችን በብዛት የሚረጩ። አቋሳይና አጋጭ ጽሑፎችን በብዛት የሚበትኑ። አቋሳይና አጋጭ የፌስ ቡኮችና የዩቲዩቦች መልዕክቶችን በብዛት የሚሰዱ። ግለሰብ አንባቢንና አድማጭን አንዱን ከሌላው ለማመዛዘን ቀርቶ፣ ለመከታተልም ፋታ የሌለው ሰብ አድርገው የሚያባክኑ። ንግግሮቹን፣ ጽሑፎቹን፣ ፌስ ቡኮቹንና ዩቲዩቦቹን እየተቀባበል የሚያነጋ፣ የሚያጠባ ሰብ። ከመጠራጠርና ከመቋሰል ውቅያኖስ ውስጥ ተዘፍቆ “አነበብክ/አነበብሽ”፣ “ሰማህ/ሰማሽ” እየተባባለ የአንዱንና የሌላውን ዝብዝብ የሚያመነዥግ። ከአንዱና ከሌላው ጋር እየዋዠቀ ቀናትን የሚገፋ።

ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ ገና በ20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ

‹‹የድሮውም የአሁኑም ኑሯችን እጅግ ያሳዝናል። በመላው ዓለም ላይ ሰላም ሲሰፋ አዕምሮም ስትበራ እኛ በጨለማ እንኖራለን። እርስ በርሳችን መጠራጠርንም አልተውንም። ሕዝቦቹ ሁሉ እርስ በርሳቸው በፍቅር ተቃቅፈው ስለልማታቸው በአንድነት ሆነው ሲደክሙ፣ እኛ አንድ ዘርና ወንድማማች መሆናችንን ገና አልተገለጸልንም። እርስ በርሳችን መፋጀትም እስከ ዛሬ ድረስ ጀግንነት ይመስለናል። ስለዚህም እግዚአብሔር ለብርታት የሚሆነውን ስጦታ ሁሉ ሰጥቶን ሳለ፣ ባለቤቶቹ ሰነፍን። ሌሎቹም ነገሥታት እንደ ሰነፎች ይቆጥሩናል፣ ይንቁናልም፤›› በማለት ስለምንነታችንና ማንነታችን አመልክተው ነበር (የነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ ሥራዎች፣ 2003)።

‹‹የድሮውም የአሁኑም (የ21ኛው ክፍለ ዘመን) ኑሯችን በእጅግ አያሳዝንምን? እርስ በርሳችን መፋጀት እስከ ዛሬም (እስከ የ21ኛው ክፍለ ዘመን) ድረስ ጀግንነት የሚመስለን፤›› አይደለንምን? ‹‹የድሮውም የአሁኑም (የ21ኛው ክፍለ ዘመን) ‘ነገሥታትም’ እንዲንቁን፤›› የተመቻቸነው እኛው ራሳችን አይደለንምን? የደረሰን ታሪክ ለማስታወስ ያህል፣ በ1960ው የወሎና የትግራይ የረሃብና የዕልቂት ዘመን የውጭ ጋዜጦች ስለረሃቡ አብዝተው በክፉ ዘገቡ። አንዳንድ ኢትዮጵያዊያን አገራቸው “በሌሎቹ ነገሥታት” በመናቋ በማፈራቸውና በመሰቅጠጣቸው ምክንያት፣ ራሳቸውን “ጃማይካኒያዊ ነኝ” እያሉ እስከ ማስተዋወቅ ደርሰው ነበር። ዛሬ ዛሬ፣ ወደ ደቡብ አፍሪካና ዓረብ አገሮች በእግራቸው እየመረጡ ናቸው።

እስከ መቼ ለሚለው ጥያቄ መልስ ያለው የፖለቲካም ሆነ የመንፈሳዊ ዓለም መሪ ወይም ምሁር ያለ አይመስለኝም። እንዲያውም ቢባል እውነታ ነው፡፡ የአቋሳይና የአጋጭ ንግግሮች ምንጮች አንዳንድ ጊዜ ራሳቸው የፖለቲካ መሪዎቹ ሆነው መገኘታቸው በራሱ ነገሮችን የከፋ አድርጓል። ስለአደጋው አስከፊነት አብዝተው የሚናገሩትና የሚያሳውቁት ራሳቸው መሪዎቹ ጭምር መሆናቸውም፣ መጭውን ዘመን እጅጉን አስጨናቂና እጅጉን አስፈሪ አድርጎታል። ከነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ ልዋስና፣ ጥቂት የማይባሉ የፖለቲካ መሪዎችና ተዋናዮች እንዲያውም ‹‹እርስ በርስ ማፋጀትንና መፋጀትን የጀግንነት›› ሙያ አድርገውታል ያሰኛል።

የፈለገው ብሔር ተወላጅ ቢሆን፣ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ዛሬ የሚኖረው በየዕለቱ ክፉ ክፉ እየሰማ ነው። ይባስናም ሱዳን የአገሩን ግዛት ወርራ በያዘችበት ኢትዮጵያ ውስጥ ነው። አሁን በቅርቡም፣ “ከደቡብ ሱዳን መምጣቱ” የሚያጠራጥር ታጣቂ እስከ 200 ኪሎ ሜትር ድረስ ገብቶ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እንደደፈረ በሚነገርባት ኢትዮጵያ ውስጥ ነው።

“የሚያጠራጥር ታጣቂ” የምለው ያለ ምክንያት አይደለም። ምክንያቱም፣ የደቡብ ሱዳን መንግሥትም ይሁን አንድ የሆነ የደቡብ ሱዳን የታጠቀ ኃይል፣ የኢትዮጵያን ምድር እስከ 200 ኪሎ ሜትር ድረስ አዘልቆ የሚያስይዝ የሠራዊትም ሆነ የሎጂስቲክስ አቅም የላቸውም። ከሌሎች ምንጮች እንደሚሰማው ይልቁኑም “ወራሪዎቹ” እዚያው ጋምቤላ ውስጥ ከረጅም ጊዜ ጀምሮ የሠፈሩት 270,00 የደቡብ ሱዳን ስደተኞች ናቸው።

በስደተኞቹና በተቀባዩ ማኅበረሰብ መካከል ተደጋጋሚ ግጭቶችና ማፈነቃቀሎች እንዳሉ ይታወቃል። ፋና ገብረ ሰንበት ገና በ2009 ዓ.ም. ባቀረቡት አንድ አጭር ጽሑፍ፣ ግጭቱ እየሰፋና እየተባባሰ እንደሚቀጥል አመልክተው ነበር። አያይዘውም፣ የኢሕአዴግ መስተዳደር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በመስከረም 2008 (እ.ኤ.አ. በ2016) የወሰነውን የስደተኞች እንክብካቤ መመርያ (Comprehensive Refugee Response Framework – CRRF) በሥራ ለመተርጎም መጣሩ የቀጣይ ግጭቶች መነሻ እንደሚሆን አሳስበው ነበር። (Security Implications of Hosting Refugees: The Case of South Sudanese Refugees in Gambella, Southwestern Ethiopia, 2017)፡፡

ውሳኔው እንደሚታወሰው፣ ስደተኞች በየተሰደዱበት አገር ያላቸውን የመደራጀት፣ የመዘዋወር፣ የመማር፣ በግብርናና በንግድ የመሠማራት፣ ለእነሱ በተወሰኑና የተመቻቹ የሥራ መስኮች የመቀጠር፣ ንብረት የማፍራትና የማስተላለፍ ያላቸውን መብቶች የሚደነግግ ነው። የአውሮፓ ኅብረትና የእንግሊዝ መንግሥትም ውሳኔውን በተግባር ለማዋል በ500,000 ዶላር ለመደጎም ቃል የገቡለት ነው። በዚህ መሠረት ኢትዮጵያ ከሌሎች አሥራ አንድ አገሮች (ፓናማ፣ ቤሊዝ፣ ፖርቶሪኮ፣ ጉዋቴማላ፣ ሆንዱራስ፣ ሜክሲኮ፣ ኬንያ፣ ኡጋንዳ፣ ሩዋንዳ፣ ጂቡቲ፣ ቻድ) ጋር ተመረጠች (Randall Hansen,The Comprehensive Refugee Response Framework, June 2018 Tsion Tadesse Abeb, Instituit for Security Studies, March 2018)፡፡ ግጭቱ ውሎ አድሮ ተባባሰ። አሁን የምክር ቤቱ የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ “ወረራውን” በአደባባይ ዘገበው። ዜናው ኢትዮጵያ በኢትዮጵያ ሲኖዶስ ውስጥ በተነሳው ከፍተኛ አገራዊ ውዝግብ በተወጣጠረችበት ወቅት መዘገቡ በራሱ ጥያቄዎችን ያጭራል። ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ በምትዘገጃጅበት ወቅት መሆኑም፣ በደንብ ታስቦበትና ታቅዶ ያልተዘገበ ዜና ነው ላለማለት አያስችልም።

ነባራዊው እውነታ ይህ ሆኖ ሳለ፣ የመንግሥት መገናኛ አውታሮች የስኬት ትርክቶችን (Success Stories) በነጋ በጠባ ያዥጎደጉዳሉ። ሌላው ቢቀር፣ ለአንድም ቀን እንኳን የራሱን፣ የመንግሥት ተቋም የሆነውን የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ዘገባዎች የማያሰሙ። ሌላው ቢቀር፣ በጠራራ ፀሐይ የሚፈጸሙትን ግድያዎችና እስራቶች የማይዘግቡ። በዓውደ ዜና ሰዓታቸው “የጽሑፍ ዜና” የተባለን በቴሌቪዥን መስኮት ላይ እየለበዱ በሚሊዮን የሚቆጠሩትን የኢትዮጵያ ዓይነ ሥውራን የሚያገሉ። ይልቁኑና እነማን እንደሆኑ ባይገለጹም፣ “ስለመንግሥት ገልባጮችና የሕገ መንግሥት ሻሪዎች” ለማውራት የማይሰንፉ። በአጭሩ፣ ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 29/3ለ ‹‹የፕሬስ ነፃነት በተለይ፣ የሕዝብን ጥቅም የሚመለከትን መረጃ የማግኘት መብት ያጠቃልላል፤›› ላለው ቁብ የሌላቸው።

ማንም የሚያውቃቸውና የተመለከቱት አገራዊ ሁኔታዎች ብቻ በራሳቸው ቆም ብሎ ማሰብን አጥብቀው ይጠይቃሉ። በየጎራው ከችቾ መወራወር አሸናፊ ለሌለው አሸናፊነት መባከን ነው። መስተዳደሩም ቆሞ የሚገኘው በግድያና በእስራት ብዛት ሊገታው ከማይችለው ከመሠረታዊ የሕገ መንግሥትና የፌዴራል አስተዳደር ሥርዓት አወቃቀርና ሕግጋት መሻሻል ጥያቄዎች ፊት ነው። በዛሬው የዲጂታል ቴክኖሎጂ ዘመን እየደበቀና እየተደባበቀ ሊዘልቀው ከማይችለው ዓለም አቀፋዊ ዓውድ ፊት ነው። ነገሮችን በአንዱና በሌላው ላይና በፌስቡክና በዩቲዩበሮች እያላከኩ ለመቀጠልም አይቻልም። ለፌስቡከሮችና ለዩቲዩበሮች ራሳቸውን አመቻችተው ያቀረቡት ራሳቸው የፖለቲካ አመራሮቹና ተዋናዮቹ ጭምር መሆናቸው ሊስተዋል ይገባል።

ችግሩ ተደጋግሞ እንደተገለጸው፣ ለ27 ዓመታት የተሄደበት የኢሕአዴግ ልዩ (Unique) የአገዛዝ ሥርዓት (System of Governance) እና የአገዛዝ ዘይቤ (Type of Governance) ውጤት ነው። ልዩ የሆነውንም ያህል፣ ልዩ (Exceptional) አካሄድና መፍትሔ ይጠይቃል። የዶ/ር ዓብይ አህመድ መስተዳደርና የተለያዩት ተዋናዮች ለልዩ ችግር ልዩ መፍትሔ ለመስጠት መነሳሳትና መድፈር ይገባቸዋል። በጊዜ ያልታከመ ቁስል ያመረቅዛል። በጊዜ ያልታከመ የፖለቲካ ማኅበራዊ ሁኔታ ውሎ አድሮ በክፉ ይፈነዳል።

ፈረንጆች መፍትሔ የሌለው ችግር፣ ችግር አይደለም ይላሉ። እውነተኛ ችግር ሁሉ ይዋል ይደር እንጂ፣ መፍትሔ አለው ለማለት ነው። በምሳሌ ለመግለጽ፣ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ችግር ወደጨረቃ ለመጓዝ አለመቻል ነው ለማለት ይቻላል። የዛሬይቱ ኢትዮጵያ እውነተኛ ችግሯ ስላልሆነ ግን፣ መፍትሔ አይገኝለትም። ከ1983 ዓ.ም. ወዲህ በኢትዮጵያ የሰፈነው ችግር እውነተኛ ችግር ነው። ስለሆነም፣ እንደማንኛውም እውነተኛ ችግር መፍትሔ ይኖረዋል። አለው።

የኢትዮጵያ የሕገ መንግሥትና የፌዴራል አወቃቅር መሻሻል ችግር የመፍትሔ ያለህ እያለ ሲጮህ 32 ዓመታት አልፈዋል። ሊፈታ የሚችለው የጋራ ወደፊትን ባማከለ የሰጥቶ/መቀበል ውይይትና ድርድር እንደሆነ ተደጋግሞ ተነግሯል። የዶ/ር ዓብይ አስተዳደር ለእነዚህ የማይታለፉ ጉዳዮች ግልጽና ተስፋዎችን የሚያለመልሙ አመራር ለመስጠት እጅጉን መድፈር ይኖርበታል። እጅጉን መትጋት ይኖርበታል። ተቃራኒው ቀውሶችን ለአፍታ ጊዜ ያህል “እየፈቱ” መቀጠል ይሆናል።

የዛሬው የሕገ መንግሥትና የፌዴራል አወቃቀር መሻሻል ችግር በአጭር፣ በመካከለኛና በረጅም ጊዜ ስለሚሠራውና ስለሚፈጸመው ከመነጋገርና ከመስማማት ያለፈ ጉዳይ ሊሆን አይችልም። ይህች የመጀመርያ ደረጃ የአያያዝ ጥበብ የመቶ ሃያ ሚሊዮኑ ኢትዮጵያዊ መሪ ነን ከሚሉት የኢትዮጵያ የፖለቲካ መሪዎችና ተዋናዮች የተሰወረች ጥበብ ልትሆን አትችልም። ተቃራኒው መንገድ፣ ኢትዮጵያን የአንዲት ሰላማዊትና ዴሞክራሲያዊ አገር ነፃ ሕዝብ ሳይሆን፣ ተዳክመው ለሚቀነጭሩ “የሉዓላዊ” ብሔሮች ግዛተ ምድር ሰውቶ የሩቅና የቅርብ ኃይሎች መጫወቻ ምድር ማድረግ ይሆናል። አትራፊ የማይቆጠርበት። ሁሉም የሚከስርበት።

የኢትዮጵያ ሕዝብ በዚህች የጥር ወር ብቻ እንኳን ብልህነቱንና አርቆ አስተዋይነቱን ደጋግሞ አስመስክሯል። ችግሮችን የመቋቋም (Resilience) አቅሙንና ችሎታውን ከሚያስፈልገው በላይ ሄዶ በበቂ አሳይቷል። ምኞቱና ናፍቆቱ፣ የኢትዮጵያ መሪዎች ወደ ቀልባቸው ተመልሰውና አስፈላጊውን ትምህርት ቀስመው የጋራውን ወደፊት በጋር ለመገንባት የሚተጉበትን የታሪክ ምዕራፍ ለማየት ነው። አስተዋይነቱንና ትዕግሥቱን አብዝቶ መፈታተን፣ ከክፉም የከፋ ዘምንን መጋበዝ ይሆናል። አንዳንዶቹን ጉዳዮች አጠቃለን ብናጤን፣

  • ተቀዳሚ የመንግሥት ኃላፊነት የሆነውን የሕግ የበላይነትን የማክበርና የማስከበር ግዴታ፣ የመስተዳደሩ በሕገ መንግሥቱ መሠረት የመወጣት ነው፣
  • የመስተዳደሩ ግልጽና ተከታታይ አንድ ወጥ አመራርን ለመስጠት የመብቃት ነው
  • የፌስቡክና የዩቲዩብ ነጋዴዎች የሕዝብን ሰላም እንዳያደፈርሱና አገርን እንዳይንዱ፣ የዜጎችን የመረጃ ማግኘት መብት የማክበርና የማስከበር ነው።

አባቶች “ከአነጋገር ይፈረዳል፣ ከአያያዝ ይቀደዳል” እያሉ ያስተምራሉ። በእኔ አተያይ፣ የተቋቋመው የብሔርዊ/አገራዊ ኮሚሽን የኢትዮጵያን ዜጎችና የኢትዮጵያን ብሔሮች ሉዓላዊ መብቶች አስታርቆ ከተጠናቀቀ፣ የኢትዮጵያዊያን ጭንቀትና ሥጋት የሚቀረፍበት ዘመን ይከፈታል። የኢትዮጵያን ዜጎች ሰብዓዊ መብቶችንና የኢትዮጵያን ብሔሮች የብሔር መብቶችን አስታርቆ ከተጠናቀቀ፣ የኢትዮጵያ ሰላማዊ ዘመን ይቀዳል። ያ የባማኮው ቅንና ቸር ኢትዮጵያዊ ሐኪም፣ ሰብ ለመሆን የማይጨነቅባት ኢትዮጵያ ዘመን ያብባል።

ጊዜው፣ እያንዳንዱ የፖለቲካ ተዋናይና የእያንዳንዱ ማኅበራዊ ክፍል ልሂቅ በትርክት የተሸከመውን የታሪክ ጫና አሳርፎ ሁለት ሦስት ዕርምጃዎች ወደኋላ ለመሄድ የወሰነ መሆኑን ይጠይቃል። እያንዳንዱ የፖለቲካ ተዋናይና የእያንዳንዱ ማኅበራዊ ክፍል ልሂቅ የጋራ ወደፊት አናሽና ገንቢ ለመሆን የወሰነ መሆኑን ይጠይቃል። የፖለቲካ መሪዎቿና ልሂቃናቶቿ “እንሞትላታለን” ለሚሏት ኢትዮጵያ ይህ አይበዛባትም። ይህ አይነፈጋትም። እየንዳንዱ የብሔር መብት ተሟጋች “እሞትለታለሁ” ለሚለው ብሔሩ ይህ አይበዛበትም። ይህን አይነፍግም። እያንዳንዱ ኢትዮጵያ “እሞታለሁ” ለሚላቸው ልጆቹና የልጅ ልጆቹ ይህ አይበዛባቸውም። ይህን አይነፈጋቸውም።

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...