Tuesday, March 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

የ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

ቀን:

የዛሬ አምስት ዓመት ገደማ ይመስለኛል ድሬዳዋ ከተማ ውስጥ አመሻሽ ላይ በእግራችን ከድሬ ወዳጆቼ ጋር ስንንሸራሸር፣ የድሮ ወሬ ተነሳና የልጅነታችንን ጣፋጭ ጊዜያት እያነሳን ስንሳሳቅ አንድ ጉዳይ የሁላችንንም ትኩረት ሳበው፡፡ ከእኛ በዕድሜ በለጥ የሚለው አንዱ ወዳጃችን ያነሳው ጉዳይ ወላጆቻችን ከጠዋት እስከ ማታ ድረስ በተለያዩ ምክንያቶች ሲጣሉ፣ ሲጨቃጨቁና ሲሰዳደቡ ቢውሉም አንዳቸውም ቤታቸው ገብተው እከሌ ወይም እከሊት እንዲህ አደረገችኝ ብለው ቂም ሲይዙ ወይም ሲያሙ ተሰምተው እንደማያውቁ ነበር፡፡ ‹‹በዚህ ዘመን ግን ምን እንደነካን እንጃ ሁላችንም ሊባል በሚባል ሁኔታ ተበለሻሽተን ልጆቻችንን እየመረዝናቸው ነው…›› ብሎን፣ ‹‹እኔ በበኩሌ ከእኛ ተማርን ከምንባለው ይልቅ እነዚያ ያልተማሩ፣ ነገር ግን አስተዋይ የነበሩ ወላጆቻችን ፍቅራቸው ይናፍቀኛል…›› ሲለን አንጀታችንን ነበር የበላን፡፡

‹‹…ምግብማ ሞልቷል አምላክ መች ነሳኝ፣ የፍቅር ረሃብ ነው እኔን የጎዳኝ…›› የሚለውን የሙዚቃውን ንጉሥ ጥላሁን ገሠሠ ዘመን ተሻጋሪ ዘፈን ከማስታውስባቸው ምክንያቶች መካከል አንዱ፣ ለምን ይሆን በዚህ ዘመን ፍቅር ቀዝቅዞ ጠብ ላያችን ላይ የነገሠው የሚለው ነው፡፡ እርግጥ ነው እንኳን እኛ ከችጋርና ከጠኔ ጋር ከልጅነት እስከ ዕውቀት አብረን የምንኖረው፣ በዚህ ዘመን በሥልጣኔ ወደፊት የገፉ አገሮች ሳይቀሩ በኑሮ ውድነት እየተጠበሱ እንደሆነ እየታዘብን ነው፡፡ በቀደም ዕለት አንድ የሥራ ባልደረባዬ በአሁኑ ወቅት ከአጠቃላዩ ሕዝባችን ውስጥ 65 በመቶ የሚሆነው፣ ከፍተኛ የሆነ የምግብ ችግር እንዳለበት ሪፖርት መውጣቱን ሲነግረኝ ነበር፡፡ እኔ ግን ችለነው ከምንኖረው ችጋርና ጠኔ ይልቅ ሰላምና ፍቅር ነበር እያሳሰበኝ የነበረው፡፡

እንደ እኔ ዓይነቱ ዓለማዊ ሰው ከፈጣሪ ትዕዛዛት ውጪ እየነጎደ ሲሄድ ያለበት ጭንቀትና ሰቆቃ ምን ያህል እንደሆነ በሚገባ እገነዘባለሁ፡፡ በራሴም ሆነ በወዳጆቼ በየጊዜው በሚደርስ ጭንቀትም አውቀዋለሁ፡፡ በዚህም ምክንያት ‹ንሰሐ ግቡ› ሲባል ልባችን ወከክ ሲልም ይታወቀኛል፡፡ ከድሮ ጀምሮ ‹‹የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው›› ሲባል፣ ከዓለም ኃጢያት በመራቅ የፈጣሪን መንገድ መከተል እንደሚገባም አውቃለሁ፡፡ ነገር ግን ለምድርና ለሰማይ የከበዱና የፈጣሪን ሥልጣን በውክልና የያዙ ሰዎች ከእኔ ዓይነቱ ከንቱ በታች ሆነው፣ ሰማያዊውን ዓለም ረስተው ዓለማዊነት ይዟቸው ጭልጥ ሲል ድንጋጤው ከሚታሰበው በላይ ነው የሚሆንብኝ፡፡ ምነው እንዲህ ዓይነት አስፈሪ ዘመን ላይ ደረስን ብዬም እጨነቃለሁ፡፡

ባለፈው ሰሞን የገጠመን ቀውስ እስካሁን ድረስ ከውስጤ ሊወጣ አልቻለም፡፡ እኔ ከንቱ ኃጢያተኛ ልፈጽመው ቀርቶ ላስበው የማልደፍረው ዓለማዊነት፣ በተከበሩ አባቶች ላይ ሲንፀባረቅ በቴሌቪዥን ስመለከት ልቋቋመው የማልችለው ስሜት ነበር የተሰማኝ፡፡ ምንም እንኳ በዚህ የኩዳዴ ፆም ዝርዝር ውስጥ ገብቼ ትዝብቴን መናገር ባልፈልግም፣ ወገኖቼ የገጠመን ፈተና በሰው ልጅ አቅም የሚፈታ ባለመሆኑ ተግተን መፀለይ ይገባናል እላለሁ፡፡ ምክንያቱም ሰይጣን ቀዳዳ ካገኘ ያሰበው ከማሳካት ወደኋላ ስለማይል እሱን ማሸነፍ የሚቻለው ወደ ፈጣሪ በመቅረብ በፆምና በፀሎት ነው፡፡ ፖለቲከኞች ወይም ሌሎች አካላት ለመሸምገል ወይም ለማደራደር እንቅስቃሴ ሲያደርጉም፣ በተቻለ መጠን ፈጣሪን ከዕቅዳችን ውስጥ ባናወጣው መልካም ነው እላለሁ፡፡

ጊዜው ራቅ ቢልም ትዳር ይዤ የራሴን ጎጄ ከመቀለሴ በፊት በኪራይ እኖር ነበር፡፡ አከራዬ ለረጅም ዓመታት በመምህርነት አገራቸውን ያገለገሉ የ75 ዓመት አዛውንት ነበሩ፡፡ እሳቸው ትግራይ፣ ጎንደር፣ ወሎ፣ ወለጋ፣ ሐረር፣ ጂማ እያሉ አዲስ አበባ ድረስ በመምህርነት አገልግለው በመጨረሻ ትምህርት ሚኒስቴር ዋናው መሥሪያ ቤት ከሠሩ በኋላ ነበር ጡረታ የወጡት፡፡ እሳቸው ታዲያ በዞሩባቸው አካባቢዎች ሁሉ የሕዝባችንን መልካምነትና ለጋስነት አውስተው አይጠግቡም ነበር፡፡ የአገሩ ሕዝብ እርስ በርሱ ብሔርና እምነት ሳይለይ በፍቅር ሲኖር፣ የፖለቲከኞች ነገር ግን በጣም ግራ ያጋባቸው እንደነበር ሲናገሩ በሐዘን ነበር፡፡ ታዲያ አንድ ቀን ለሕይወትህ መርህ ይሁንህ ብለው፣ ‹‹ልጄ ከምንም ነገር በላይ ፈጣሪህን ፍራ፣ ሕዝብን ደግሞ ትልቅ ትንሽ ሳትል አክብር…›› ነበር ያሉኝ፡፡ እስከ ሕይወቴ መጨረሻ የሚሆን ስንቅ ነበር የሰጡኝ፡፡

በዚህ ዘመን ግን ትናንት ከፍተኛ ድጋፍ የተለገሳቸው ግለሰቦች ለምን ብለው ሕዝብ እንደሚያስቀይሙ ግራ ያጋባኛል፡፡ ከመሪ ጀምሮ እስከ ተርታ ግለሰብ ድረስ የሚስተዋለው አሳዛኝ ባህሪ ድንቅ ይለኛል፡፡ አንድ የሥራ ባልደረባዬ ለአለቆቹ ማደግደግ ከመውደዱ የተነሳ ለሥራ ባልደረቦቹም ሆነ ለበታቾቹ ደንታ አልነበረውም፡፡ እሱ ወሬ እያመላለሰ የሰው ሕይወት ማመሰቃቀል ዋና ተግባሩ ነበር፡፡ አለቃ ሲያይ ጭራውን እንደሚቆላ ውሻ አቅሉን ስለሚያስተው ብዙዎች ይንቁት ነበር፡፡ ዋና ሥራ አስኪያጃችን በዕድገት ወደ ሌላ መሥሪያ ቤት ሄደው አዲስ አለቃ ሲመጡ እንደለመደው መርመጥመጥ ሲጀምር ጠርተውት፣ ‹‹ሰማህ ወዳጄ፣ እኔ የምፈልገው የሥራህን ውጤት እንጂ ይህንን አስመሳይ ባህሪህን አይደለምና ተጠንቀቅ…›› ብለውት አንገቱን ያስደፉት አይረሳኝም፡፡ የመሥሪያ ቤታችን የጥበቃ ኃላፊ የነበሩ መልካም ሰውም፣ ‹‹አቶ እከሌ፣ ፈጣሪህን እያሰብክ ለሰው ፍቅር ቢኖርህ እኮ እንዲህ አንገትህን አትደፋም ነበር…›› ያሉት፡፡

አሁንም ለሰው ልጅ ፍቅር ነፍገው በነጋና በመሸ ቁጥር ሴራ የሚጎነጉኑ ሰዎች እየበዙ መምጣታቸውን ሳስብ እፈራለሁ፡፡ ያ ሁሉ መልካምነትና ለሰዎች አሳቢነት ከአገራችን እንጥፍጣፊው እየጠፋ የገዛ ወገንን መጨፍጨፍ፣ መዝረፍ፣ ማፈናቀልና በክፋት ዓይን ማየት ለምን ላያችን ላይ ተንሰራፋ ሲባል ዋናው ምክንያቱ ፍቅርና ሰብዓዊነት በመጥፋታቸው ነው፡፡ በሁሉም ቦታ ሌብነት፣ ውሸት፣ ክፋት፣ አሉባልታና ጥላቻ እየተዘራ የነገው ትውልድስ ምን ይማራል የሚለው ያሳስባል፡፡ የእምነት አባቶች፣ ሽማግሌዎች፣ ምሁራንና ለአገር የሚጠቅሙ ዜጎች ሳይቀሩ ፍቅር ቀዝቅዞ ጥላቻ ሲበዛና ትውልዱ ሲመረዝ ለምን ዝም ብለው ያያሉ የሚለው ያሳስበኛል፡፡ ፈጣሪን ስንዘነጋና ዓለማዊ ነገሮች ላይ ብቻ ስናተኩር፣ በፍቅር ፋንታ የሰይፍ ሰለባ መሆናችን ለምን አይታሰበንም ካልተባለ መከራችን ገና ነው ማለት ነው፡፡ ለሌላው ያሰብነው እኛ ላይ ላለመድረሱ ማስተማመኛ የለምና፡፡

(ናኦድ ባዚን፣ ከዊንጌት)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹ከኦነግ ሸኔ ጋር ያለውን ግጭት በሰላም ለመፍታት ከፍተኛ ፍላጎት አለን›› ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ

መንግሥት ከ‹‹ኦነግ ሸኔ››ጋር ያለውን ግጭት በሰላም ለመፍታት ከፍተኛ ፍላጎት...

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...