Friday, March 31, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ስምንት የመስኖ ግድቦችን የሚረከበው አካል ማጣቱን አስታወቀ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ግድቦቹ ከ288 ሚሊዮን ብር በላይ ያልተከፈለ ዕዳ አለባቸው

የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ከዓመታት በፊት ለመቋቋሚያ ካፒታል ተብሎ የተረከባቸውን ስምንት የመስኖ ግድቦች፣ ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ በአዋጅ ለሌላ ተቋም ቢተላለፉም የሚረከበው አካል ማጣቱን አስታወቀ፡፡

በ2011 ዓ.ም. የአስፈጻሚ አካላትን ሥልጣንና ኃላፊነት ለመወሰን በወጣ አዋጅ ፕሮጀክቶቹን በባለቤትነት እንዲያስተደዳር ለቀድሞው የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር መተላለፍ የነበረባቸው ቢሆንም ሚኒስቴሩ ሊረከብ ባለመቻሉ፣ ለጠቅላይ ሚንስትሩ ደብዳቤ ጽፈው እንደነበር የኮርፖሬሽኑ የሥራ ኃላፊዎች ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተናግረዋል፡፡

የዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ግኝት እንደሚሳየው፣ የመስኖ ግድቦቹ ከ288 ሚሊዮን ብር በላይ ያልተከፈለ የአገልግሎት ዕዳ አለባቸው፡፡ የመስኖ ግድቦቹ በ2014 ዓ.ም. እንደገና በተካሄደው የመንግሥት ምሥረታ አዲስ የአስፈጻሚ አካል ሲዋቀርና የቀድሞው የውኃና መስኖ ሚኒስቴር ለሁለት ሲከፈል፣ የመስኖ ፕሮጀክቶቹ ባለቤትነት ለመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር መተላለፋቸው ተገልጿል፡፡

ይሁን እንጂ በአዲሱ የአስፈጻሚ አካላት ሥልጣን ድልድል መሠረት ፕሮጀክቶቹን እንዲያስተዳድር በአዋጅ ሥልጣን የተሰጠው የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴርም፣ ግድቦቹን ሊያስተዳድር የሚችል አደረጃጀት የለኝም በሚል ሊረከብ ባለመቻሉ ፓርላማው ለኮርፖሬሽኑ የመፍትሔ ዕገዛ እንዲያደርግለት የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዮናስ አያሌው (ኢንጂነር) ጠይቀዋል፡፡

ዮናስ (ኢንጂነር) ጥያቄውን ያቀረቡት የኮርፖሬሽኑን የፕሮጀክት ግንባታ አፈጻጸም በተመለከተ የተቋሙ የ2013 እና 2014 ዓ.ም. ክዋኔ ኦዲት ላይ ግምገማ ለማድረግ፣ ከቋሚ ኮሚቴውና ከፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ጋር በነበራቸው ቆይታ ነው፡፡

ለመስኖ አግልግሎት የሚውሉት እነዚህ ግድቦች መጀመርያ ኮርፖሬሽኑ እንዲያስተዳድራቸው በአዋጅ ተሰጥቶት እንደነበር፣ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግን ባለቤትነታቸው ለቀድሞው ውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ ከዚያም ለመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር በአዋጅ በመሰጠታቸው በአዋጁ መሠረት ተረከቡን የሚል ደብዳቤ በተደጋጋሚ ቢጽፉም መልስ ማጣታቸውን የገለጹት ዮናስ (ኢንጂነር)፣ ‹‹ስምንቱን ግድቦች በራሳችን ወጪ ይዘናቸው ነው ያለነው፣ የምክር ቤቱ ዕገዛ ያስፈልገናል፤›› ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ ዜና ኮርፖሬሽኑ ላላፉት ስድስት ዓመታት ውኃ ሲያቀርብላቸው የነበሩ ስድስት የመንግሥት ስኳር የእርሻ ልማቶችና የሳዑዲ ስታር እርሻ ልማት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የተሰኘ ድርጅት ወደ 2.8 ቢሊዮን ብር ያህል የተጠቀሙበትን የውኃ ቢል አለመክፈላቸው በኦዲት መረጋገጡ ተገልጿል፡፡ ይሁን እንጂ የስኳር ኮርፖሬሽን ክፍያ እንዲከፍል ሲጠየቅ የውኃ ቢል የማስከፈል ሥልጣን ማን ሰጣችሁ የሚል ምላሽ ማግኘታቸውን ዮናስ (ኢንጂነር) አስረድተዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ ፕሮጀክቶቹን በወቅቱ መረከብ የነበረበት ተቋም መጠየቅ እንዳለበት፣ ገንዝብ ሚኒስቴር ለፕሮጀክቶች ገንዘብ ከመክፈሉ በፊት የሚከናወኑ ፕሮጀክቶች ለታሰበላቸው ዓላማ እየዋሉ መሆናቸውን እንዲያጣራ፣ እንዲሁም የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ፕሮጀክቶች ከመጀመራቸው በፊት በቂ ጥናት ተደርጎባቸዋል ወይ የሚለውንና አገሪቱ ገንዘቡን የማቅረብ አቅም አላት ወይስ የላትም የሚሉ ጉዳዮችን በቅድሚያ እያጠና ፕሮጀክቶች እንዲጀመሩ ጠይቀዋል፡፡

የኦዲት ሪፖርት ውጤቱን ለፍትሕ ሚኒስቴር ጨምሮ ለሚመለከታቸው አካላት ማሳወቃቸውን የገለጹት ወ/ሮ መሠረት፣ በአገር ሀብት ላይ ብክነት ሲደርስ ዕርምጃ መወሰድ ካለበት በአፋጣኝ መታየት አለበት ብልዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ክርስቲያን ታደለ በተሰብሳቢ ሒሳብ ላይ የሚታየው ቸልተኝነት በበጎ አድራት ተቋማት እንኳ የሚታይ አለመሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ በመሆኑም ኮርፖሬሽኑ ለሌላ አካል መተላለፍ ያለባቸውን ግድቦች በቀጣይ 90 ቀናት ውስጥ በአዋጅ ኃላፊነት  ለተሰጠው እንዲያስተላልፍ፣ እንዲሁም ከውኃ አቅርቦት ጋር በተያያዘ ዕዳ ያለባቸው ስኳር ኮርፖሬሽንና ሳዑዲ ስታር ድርጅት ያለባቸውን በሁለት ወራት ውስጥ ገንዘቡን እንዲያስከፍል ማሳሰቢያ ሰጥተዋል፡፡

በተመሳሳይ የፍትሕ ሚኒስቴር ከውል ውጪ በአሠሪና በአመራር ክፍተት በአገር ሀብት ላይ በደረሰ ጥፋት፣ በወንጀልና በፍትሐ ብሔር የሚያስጠይቅ መሆኑ ተጣርቶ ክስ እንዲመሥርት አቶ ክርስቲያን ጠይቀዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ ከሚያስተዳድራቸው ፕሮጅክቶች መካከል ተንዳሆ የግድብና መስኖ ልማት ፕሮጀክት፣ ርብ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት፣ ከሰም ግድብና መስኖ ግንባታ ፕሮጀክት፣ ጊዳቦ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት፣ ተንዳሆ የመጠጥ ውኃ ልማት ተጨማሪ ፕሮጀክቶች ይገኙበታል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች