Tuesday, March 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናአዲስ የተመሠረተው ‹ትንሳዔ 70 እንደርታ› ፓርቲ የቅድመ ዕውቅና ሰርተፊኬት ማግኘቱን ገለጸ

አዲስ የተመሠረተው ‹ትንሳዔ 70 እንደርታ› ፓርቲ የቅድመ ዕውቅና ሰርተፊኬት ማግኘቱን ገለጸ

ቀን:

በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀስ ‹‹ትንሳዔ 70 እንደርታ›› የተባለ የፖለቲካ ፓርቲ በምሥረታ ላይ መሆኑንና የቅድመ ዕውቅና ሰርተፊኬት ማግኘቱ ተገለጸ፡፡

ጥር 22 ቀን 2015 ዓ.ም. በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ፊርማ የተረጋገጠ የፓርቲ ቅድመ ዕውቅና ሰርተፊኬት ማግኘቱንና ሙሉ ዕውቅና ለማግኘት የሚያስችል እንቅስቃሴ መጀመሩን አስተባባሪዎቹ ተናግረዋል፡፡

በክልል ደረጃ ለመንቀሳቀስ 4,000 አባላትን ማሰባሰብ እንደሚጠይቅ የጠቀሱት አስተባባሪዎቹ፣ ይህን ለመጀመር ዝግጅት መጨረሳቸውን ተናግረዋል፡፡

የትግራይን ሕዝብ እየወረደበት ካለው መከራ መታደግ ዋና ግባቸው መሆኑን የተናገሩት ከአስተባባሪዎቹ አንዱ አቶ ጊዴና መድኅን፣ የተበላሸውን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል ለመቀየር ፓርቲው እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡

‹‹የሶሻል ዴሞክራሲ ርዕዮተ ዓለምን ነው ፓርቲው የሚከተለው፡፡ መበላላት፣ መጠቋቆምና ስም ማጉደፍ የሰፈነበትን የፖለቲካ ባህል በመቀየር፣ አወንታዊ ሚና የሚጫወት ፓርቲ እንዲሆን እንፈልጋለን፤›› ሲሉ አቶ ጊዴና ተናግረዋል፡፡

በሚቀጥሉት አራት ወራት 4,000 አባላትን መዝግበው ጠቅላላ ጉባዔ በማካሄድ ወደ ሥራ ለመግባት ማቀዳቸውንም አክለው አንስተዋል፡፡ ‹‹የትግራይ ሕዝብ የተሻለ የፖለቲካ ውክልና ማግኘት ይገባዋል፡፡ እኛም በሐሳብ ፖለቲካ የሚያምንና በአገሩ የሚኮራ ትውልድ ለመፍጠር እናስባለን፡፡ አገሪቱ ከገባችበት የፖለቲካ ቀውስ እንድትወጣ የበኩላችንን እንወጣለን፤›› ሲሉም ገልጸዋል፡፡ ለምርጫ ቦርድ የቅድመ ዕውቅና ማመልከቻ ባለፈው ሰኔ ማስገባታቸውንና ጥር 22 ቀን 2015 ዓ.ም. ሰርተፊኬቱ እንደተሰጣቸው ተናግረዋል፡፡

ሌላኛው የፓርቲው አስተባባሪ አቶ ከበደ አሰፋ በበኩላቸው አባላት መዝግቦ ጠቅላላ ጉባዔ በማድረግ ሙሉ ዕውቅና አግኝቶ ወደ ሥራ ለመግባት፣ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አሠራር መሠረት የስድስት ወራት ጊዜ ገደብ እንዳላቸው ጠቁመዋል፡፡

‹‹ክልላዊ ፓርቲ ስለሆነ 4,000 አባላትን ማሰባሰብ ይጠበቅበታል፡፡ ከዚህ ውስጥ 60 በመቶው ከትግራይ ክልል ቀሪው 40 ከመቶ ደግሞ ከሌላው የአገሪቱ ክፍል ሊሰባሰብ ይችላል፡፡ ቢሮ ማደራጀትና ድርጅታዊ መዋቅር መዘርጋት እንዲሁም ደጋፊ የማሰባሰብ ሥራ እየሠራን ነው፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡

የትግራይ ፖለቲካ ምኅዳር አሁን ላይ በፓርቲ ፖለቲካ ለመንቀሳቀስ አመቺ ዕድልም ሆነ እንቅፋት እንዳለው የጠቀሱት አቶ ከበደ ‹‹የትግራይ ሕዝብ በአንድ የፖለቲካ ቡድን ብቻ መወከል እንደሌለበት ከመቼውም ጊዜ በላይ ተምሯል፤›› ብለዋል፡፡

ሕወሓት ጥቂት የትግራይ አካባቢዎችን ብቻ ይዞ መቅረቱ፣ በሕዝቡ ቅቡልነት እያጣ መምጣቱ፣ ሕዝቡም ለውጥ መሻቱ ‹ለትንሳዔ 70 እንደርታ› ፓርቲ ምሥረታ ምቹ ዕድሎች መሆናቸውንም አንስተዋል፡፡ በስድስት ወራት ከትግራይ 2,400 አባላትን አሰባስቦ ቀሪውን ከሌላው የአገሪቱ ክፍል አሟልቶ የምርጫ ቦርድ አሠራር በሚፈቅደው መንገድ ፓርቲውን ሙሉ ዕውቅና ያለው ሕጋዊ ፓርቲ ለማድረግ አቅም እንዳላቸውም አክለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹ከኦነግ ሸኔ ጋር ያለውን ግጭት በሰላም ለመፍታት ከፍተኛ ፍላጎት አለን›› ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ

መንግሥት ከ‹‹ኦነግ ሸኔ››ጋር ያለውን ግጭት በሰላም ለመፍታት ከፍተኛ ፍላጎት...

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...