ኢትዮጵያ በበርበራ ወደብ ሊኖራት እንደሚችል የተገለጸው የ19 በመቶ የባለቤትነት ጥያቄን በሚመለከት ከመንግሥት በኩል ‹‹ይኸንን ያህል እፈልጋለሁ›› የሚል አሳሪ ውል ባይኖርም ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ፍላጎት ካለ የሶማሌላንድ መንግሥት ለመነጋገር ዝግጁ መሆኑንና በሶማሌላንድ ፓርላማ የመጨረሻ ውሳኔ እንደሚሰጠው ተገለጸ፡፡
የሶማሌላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢሳ ካይድ (ዶ/ር) ከሪፖርተር ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ ኢትዮጵያ በበርበራ ወደብን ላይ ያላትን የ19 በመቶ ድርሻ በተመለከተ ከዚህ በፊት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የተደረገ ምንም ዓይነት ስምምነት አለመኖሩን ተናግረዋል፡፡
የወደቡ ወቅታዊ የባለቤትነት ድርሻ በተመለከተ ሲያብራሩ፣ 65 በመቶ ወደቡን እያለማ ያለው የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ኩባንያ ዲፒ ወርልድ መሆኑን 35 በመቶ ድግሞ በሶማሌላንድ የተያዘ እንደሆነ ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡
ቀደም ሲል ኢትዮጵያ፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ዲፒ ወርልድና ሶማሌላንድ ወደቡን በጋራ ለማልማትና ለመጠቀም ስምምነት ላይ መድረሳቸው የተገለጸው እ.ኤ.አ. በ2018 ነበር፡፡
ይሁን እንጂ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ይህን ያህል እፈልጋለሁ የሚል የተፈጸመ አሳሪ ውል አለመደረጉን፣ ነገር ግን የሶማሌላንድ መንግሥት ከኢትዮጵያ በኩል በሚቀርብለት ጥያቄ መሠረት ለመነጋገገር ዝግጁ መሆኑን ገልጸው፣ የመጨረሻው ውሰኔ ግን የሶማሌላንድ ፓርላማ የሚለው እየተጠበቀ ነው ብለዋል፡፡
‹‹የኢትዮጵያ የድርሻ ጥያቄ በነባሩ የበርበራ ወደብ ላይ ነው፡፡ ነገር ግን አሁንም እንዴት እንጠቀም የሚለውን ለመነጋገገር ዝግጁ ነን፡፡ አሁን በወደቡ ላይ ያለው ስምምነት የሶማሌላንድ ድርሻ 35 በመቶ ሲሆን፣ ወደቡን እያለማ ያለው ዲፒ ወርልድ ደግሞ 65 በመቶ ነው፤›› በማለት የገለጹት ሚኒስትሩ፣ ያም ሆኖ ግን ዲፒ ወርልድም ሆነ ሶማሌላንድ ከኢትዮጵያ ጋር ለመነጋገር ዝግጁ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ በቀጣይ የቴክኒክ ኮሚቴውና የሚኒስትሮች ኮሚሽን ዝግጁ ሲሆኑ ለመነጋር ይቻላል ብለዋል፡፡
ከአንድ ዓመት በፊት የሶማሌላንድ የገንዘብ ሚኒስትር ሰዓድ አሊ ሽሬ ተናገሩት ተብሎ በወጣ መረጃ፣ ኢትዮጵያ 19 በመቶ ድርሻ አላት ተብሎ የተነገረው የሁለቱ አገሮች ዱባይ በተገናኙበት ወቅት በቃል የነበረ ንግግር እንጂ በፊርማ የተረጋገጠ ምንም ዓይነት ስምምነት አለመኖሩን ተናግረው ነበር፡፡
ለኢትዮጵያ የወጪና የገቢ ንግድ ተጨማሪ በር ይሆናል ተብሎ የሚታሰበው የበርበራ ወደብ የባለቤትነት መብትን አስመልክቶ በሶማሌላንድ መንግሥት የተቀመጠውን ቅድመ ሁኔታ ኢትዮጵያ ማሟላት ባለመቻሏ፣ በወደቡ ላይ የነበራትን የ19 በመቶ ድርሻዋን ማጣቷን ባለፈው ዓመት ተዘግቦ ነበር፡፡
ወደብ አልባዋ ኢትዮጵያ እስከ 90 በመቶ የሚደርሰውን ወጪና ገቢ ዕቃዎቿን በቀጥታ በጂቡቲ በኩል እያስገባች ነው፡፡ በቅርቡ የበርበራን፣ የሱዳንን፣ የኤርትራ፣ የላሙና ሌሎች ወደቦችን በመጠቀም አማራጮችን ለማስፋት እየሠራ ስለመሆኑ የሚናገረው መንግሥት፣ በሚቀጥሉት አሥር ዓመታት ሰባት ወደቦችንና 12 ኮሪደሮችን በመጠቀም የወደብ አማራጮችን ለማስፋት በአሥር ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ ይዟል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ሥልጣን ከያዙ በኋላ ሶማሊያ በመሄድ ከአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ቀጣናውን በተመለከተ ያደረጓቸው ንግግሮች፣ ሶማሌላንድን ያስቀየሙ እንደነበር ይነገር ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ከሰሞኑ ከሪፖርተር ጋር ቆይታ ያደረጉት የሶማሌላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በሁለቱ አገሮች መካከል ያለው የንግድና ዲፕሎማሲዊ ግንኙት መሻሻሉን ጠቅሰው፣ የበርበራ ወደብን ለመጠቀም በሁለቱ መካከል የትራንዚት አገልግሎት ስምምነት ባለመኖሩ የትራንዚት ሥርዓቱን ለመዘርጋት የሚረዳ ስምምነት እንደሚደረግ አስረድተዋል፡፡