Tuesday, March 28, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በአኅጉራዊ ነፃ የንግድ ገበያ ከመሳተፍ በፊት ከምግብ ደኅንነት ጋር የተያያዙ ጉዳዮች እንዲጤኑ ተጠየቀ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነፃ ንግድ ገበያ ጨምሮ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን ከምታደርገው ጥረት በተጨማሪ፣ በአገር ውስጥ የምግብ ደኅንነት አጠባበቅ ላይ ትኩረት ሰጥታ ልትሠራ እንደሚገባ ተገለጸ፡፡

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና አባል ከመሆኗ ውጭ የዓለም የንግድ ድርጅት (WTO) አባል ለመሆን እያመለከተች መሆኑን ለሪፖርተር ያስረዱት፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምግብ ሳይንስና ኒዩትሪሽን ዲፓርትመንት መምህርና ተመራማሪ አሻግሬ ዘውዱ (ዶ/ር)፣ መስፈርቶቹ ጠንከር ያሉ በመሆናቸው ሒደቱ እንዲራዘም ሲደረግ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡ በተለይም መንግሥት በምግብ ደኅንነት ላይ መሥራት ቁርጠኝነት የሚጠይቅ መሆኑን ሊገነዘብ ይገባል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ገበያ መሳተፏ መንግሥትን ብዙ ገቢ ቢያሳጣም፣ ዜጎች የሚጠቀሙበት ሁኔታ እንደሚፈጥር መንግሥት ራሱ በሥጋትነት ያነሳው ጉዳይ መሆኑን ያስረዱት ተመራማሪው፣ ዜጎች ተጠቃሚ ሆነው አገሪቱ የምታገኘው ገቢ ቢቀንስም፣ መንግሥት ለጤና አጠባበቅ የሚያወጣውን ወጪ የሚያድን መሆኑ ሊታሰብ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

‹‹በኢትዮጵያ ወተትን ጨምሮ በርካታ ዘርፎች ኢንዱስትሪዎቻችን በልዩ ሁኔታ ደረጃውን ሳያሟሉ፣ የሸማቹን ጥቅም ሳያገናዝቡ የተፈቀደላቸው ናቸው፡፡ ስለሆነም ይህ የጥራት ሁኔታ በሁሉም ዘርፍ በፖሊሲ አውጪው ካልተቀየረ፣ ባለሙያውና ታች ያለው ሠራተኛ ይኼንን ሊቀይር አይችልም፤›› ሲሉ  አሻግሬ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

ከጎረቤት አገሮች ኬንያ የምግብ ደኅንነት ፖሊሲ ያላት፣ ምርታማነቷ ከፍተኛ እንደሆነና በአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ትስስር እንደ ግብፅ ገበያውን በጉጉት የምትጠብቅ አገር መሆኗ ተገልጿል፡፡

ሁለቱ የአፍሪካ አገሮች የቤት ሥራቸውን በአግባቡ የሠሩ በመሆናቸው፣ ገበያው ሲጀመር ትልቅ ገቢ እንደሚያገኙ የሚጠበቁ አገሮች እንደሆኑ ተጠቅሶ፣ እንደ ኢትዮጵያ  በጊዜ የቤት ሥራውን ያልጨረሰ አገር ችግር ውስጥ ይገባል ሲሉ አሻግሬ (ዶ/ር) አስታውቀዋል፡፡

በኢትዮጵያ በምግብ ኢንዱስትሪ ዘርፍ የሚታየውን ችግር ከማስተካከል ባለፈ ወደ አዲስ ኢንቨስትመንት የሚመጡትን ዘርፉ ቀላል ተብሎ የሚገባበት አለመሆኑን፣ አቅም ያለውና ምርት በጥራት ማምረት የሚችል ባለሀብት የሚገባበት መሆኑን ማሳየት ተገቢ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

የአፍሪካ ነፃ የገበያ ማዕከልን ለማቋቋም በሩዋንዳዋ ኪጋሉ እ.ኤ.አ. በ2018 በተደረገ ስምምነት መሠረት እስካሁን ከኤርትራ ስተቀር ኢትዮጵያን ጨምሮ 54 አገሮች ስምምነቱን ፈርመዋል። በዚህ ስምምት መሠረትም በአፍሪካ የጋራ የሸቀጣ ሸቀጥና የአገልግሎት ዘርፍን በማጣመር የኢኮኖሚ ቅንጅትን በመፍጠር፣ የአፍሪካን ኢኮኖሚ ለማሳደግ እንደሚሠራ፣ ዘርፉም ከ3.4 ትሪሊዮን ዶላር በላይ አኮኖሚ እንደሚያንቀሳቅስ ይጠበቃል።

ባለፈው ሳምንት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምግብ ሳይንስና ኒዩትሪሽን ማዕከል ከቢልና ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽንና ከእንግሊዝ መንግሥት በተሰጠው አንድ ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ኢንሹር በተባለ ፕሮጀክት፣ ባለፉት አራት ዓመታት በኢትዮጵያ የወተት መገኛ ናቸው በተባሉ አራት ክልሎች ከወተት አምራች እስከ አቀናባሪ ፋብሪካዎችና ተጠቃሚዎች ያለውን የምግብ ደኅንነት ጥናት ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡

በጥናቱ እንደተመላከተው፣ በኢትዮጵያ ለፍጆታ የሚውለው ወተት ጥራቱና ደኅንነቱ ከደረጃ በታች ከመሆኑ ባሻገር፣ የኅብረተሰቡን ጤና አደጋ ላይ የሚጥል በመሆኑ ወተትን ጨምሮ የምግብ ጉዳይ አሳሳቢ በመሆኑ፣ መንግሥት የጉዳዩን አሳሳቢነት በመረዳት የፖሊሲና የስትራቴጂ ዕቅድ ሊነድፍ እንደሚገባ ተገልጾ ነበር፡፡

በኢትዮጵያ ያለው የምግብ ደኅንነት ሥርዓት አብዛኛውን ጊዜ ትኩረቱን የሚያደርገው ቁጥጥር ላይ እንደሆነ፣ ከመነሻው ጀምሮ ያሉ የደኅንነት አጠባበቅ ከገበሬው እስከ መጨረሻው ተጠቃሚ ያለው ሥርዓት ሒደትን የተከተለ መሆን እንደሚገባው፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምግብ ሳይንስና ኒዩትሪሽን ማዕከል ከፍተኛ ተመራማሪ አልጋነሽ ቶላ (ዶ/ር) አስታውቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች