Friday, March 31, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ለአምራች ኢንዱስትሪዎች በስድስት ወራት ውስጥ የተለቀቀው የውጭ ምንዛሪ ከሚጠበቀው በታች መሆኑ ተነገረ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ፍላጎታቸው 881 ሊዮን ዶላር ቢሆንም ያገኙት 128 ሚሊዮን ዶላር መሆኑ ተጠቁሟል

በተያዘው ዓመት ስድስት ወራት አምራች ኢንዱስትሪዎች ለጥሬ ዕቃ ግዥ ከሚያስፈልጋቸው አጠቃላይ የውጭ ምንዛሪ ፍላጎት፣ በፋይናንስ ተቋማት የቀረበላቸው 15 በመቶ ብቻ መሆኑን፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

የአምራች ኢንዱስትሪዎች የስድስት ወራት የጥሬ ዕቃ ፍላጎት በአጠቃላይ 881 ሚሊዮን ዶላር ቢሆንም፣ የቀረበላቸው 128 ሚሊዮን ዶላር መሆኑን ያስታወቀው ሚኒስቴሩ፣ ይህም አቅርቦት፣ ክትትልና ድጋፍ ከሚደረግላቸው ኢንዱስትሪዎች ውጪ ያሉትን የሚያጠቃልል ነው ብሏል፡፡

በሌላ በኩል በግማሽ ዓመቱ የአምራች የኢንዱስትሪዎች የፋይናንስ ፍላጎት 14 ቢሊዮን ብር ቢሆንም፣ ከንግድ ባንኮች የቀረበላቸው ግን 3.4 ቢሊዮን ብር እንደሆነና በአንፃሩ የአነስተኛና መካከለኛ ብድርና ሊዝ ፋይናንስ በታቀደው መሠረት መሟላቱ ተገልጿል፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ዘርፉ ከፍተኛ የፋይናንስ አቅርቦት እጥረት ችግር ውስጥ መሆኑን ገልጾ፣ በተደረጉ በርካታ ጥናቶች ከተለያዩ ተግዳሮቶች መካከል ዋነኞቹ የአምራች ኢንዱስትሪ ችግሮች የግብዓት፣ የፋይናንስ (የአገር ውስጥና የውጭ ምንዛሪ)፣ እንዲሁም የመሠረተ ልማት ይገኙበታል ብሏል፡፡

ባለፉት አሥር ዓመታት ወይም እ.ኤ.አ. እስከ 2022 ለአምራች ኢንዱስትሪው የተሰጠው ብድር በአማካይ 15 በመቶውን ይሸፍናል ያለው ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ ይህም ባንኮች ለዘርፉ የሚሰጡት ትኩረት እያነሰ መሆኑን አመላካች እንደሆነ ጠቁሟል፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የንግድ ባንኮች ለአጭር ጊዜ ትርፍ የሚያስገኙ ዘርፎች ላይ ያተኮሩ በመሆናቸው ከአገልግሎት ኢንዱስትሪውና ከሌሎች ብድሮች ጋር ሲነፃፀር፣ ለአምራች ኢንዱስትሪ ያቀረቡት የብድር ድርሻ አነስተኛ መሆኑ ተገልጿል፡፡ በአንፃሩ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ እስከ 90 በመቶ ብድር ለአምራች ዘርፉ እየሰጠ እንደሚገኝ፣ እ.ኤ.አ. ከ2018 ጀምሮ የሚሰጠው ብድርም መጨመሩ ተመላክቷል፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የአምራች ኢንዱስትሪው እያጋጠሙት ያሉ የፋይናንስ ችግሮችን ለመፍታት የካቲት 15 ቀን 2015 ዓ.ም  በኃይሌ ግራንድ ሆቴል ከፋይናንስ ተቋማትና ባለድርሻ አካላት ጋር በተደረገ የውይይት መድረክ ላይ እንደተገለጸው፣ በፋይናስ ተቋማት የብድርና የውጭ ምንዛሪ አሰጣጥ ሒደቱ ግልጽና ቀልጣፋ አለመሆኑ፣ ተበዳሪዎች ለብድር ብቁ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ገለልተኛ ተቋም አለመኖሩ፣ በዲጂታል የፋይናንስ ቴክኖሎጂ የተደገፈ የብድር አሰጣጥ ሥርዓት አለመዳበሩ፣ የአምራች ኢንዱስትሪው ከፋይናስ ተቋማት የሚፈለገውን ዕገዛ እንዳያገኝ ካደረጉት ጉዳዮች ውስጥ ተጠቃሾቹ ናቸው፡፡

በተጨማሪም የብድር ዋስትና ከፍተኛ መሆን፣ የብድር ዋስትናው ዓይነት ዘርፉን ያላገናዘበ መሆኑ፣ ዘርፉን ያገናዘበ ተመጣጣኝ የሆነ የወለድ ምጣኔ (እስከ 18 በመቶ) አለመኖር፣ እንዲሁም የብድር ዘመንና የመመለሻ ጊዜ አጭር መሆኑ፣ በተጨማሪም የዕፎይታ ጊዜ (Grace Period) አለመኖሩ፣ ቢኖርም በቂ አለመሆኑና ሌሎች ተግዳሮቶች መኖራቸውን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የፖሊሲ አማካሪዎች አስታውቀዋል፡፡

የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ የፋይናንስ አቅርቦት በበቂ ሁኔታ ባለማግኘቱ ኢንዱስትሪዎቹ የማምረት አቅማቸውን መጠቀም እንዳልቻሉ፣ የዘርፉ የውጭ ምንዛሪ ግኝት በታቀደውና በሚፈለገው መጠን እንዳላደገ፣ በአገር ውስጥ ሊተኩ የሚችሉ ውስን የውጭ ግብዓቶች በመጠቀም የሚመረቱ ምርቶችን በሚፈለገው ደረጃ እንዳልተተኩ፣ ከዚህ ሁሉ በተጨማሪ አምራች ኢንዱስትሪዎች ከመዘጋት እስከ ሥራ ማቆም ደረጃ መድረሳቸውም በመድረኩ ተጠቅሷል፡፡

የውጭ ምንዛሪ አቅርቦቱና ፍላጎቱ ከፍተኛ ልዩነት ያለው በመሆኑ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦትን ለሚያሳድጉ ኤክስፖርተሮችና ገቢ ምርት ለሚተኩ ኢንዱስትሪዎች ከፍተኛ ትኩረት መስጠት ይገባል የተባለ ሲሆን፣ አምራች ዘርፉን ለመደገፍ የተዘጋጁ  የሰፕላየርስ ክሬዲት፣ ቦንድ ዌር ሐውስ፣ እንዲሁም ኤክስፖርት ጋራንቲ ለሚጠቀሙ አምራቾች በወቅቱ አገልግሎት መስጠት እንደሚገባ ተመላክቷል፡፡

የዘርፉን ባህሪ መሠረት በማድረግ የብድር ወለድ፣ የብድር ዘመንና የመመለሻ ጊዜን፣ እንዲሁም የብድር ዕፎይታ ጊዜን መተግበር ይገባል የተባለ ሲሆን፣ ባንኮች የገንዘብ ፍሰትና ሀብት (Asset) መሠረት ያደረገ የብድር ዋስትና ሥርዓቶችን፣ እንዲሁም የቴክኖሎጂ ሽግግርን በሚያመጣ መንገድ በሊዝ ፋይናንስ ሒደት መደገፍ፣ ለከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች የማሽን ፍላጎት ሊመልስ የሚችል የፋይናንስ አሠራር መዘርጋት እንደሚገባቸው የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አምራች ኢንዱስትሪዎች እያጋጠማቸው ያሉ የፋይናንስ ችግሮች በሚፈቱበት ሁኔታ ላይ ከፋይናንስ ተቋማት ጋር ባደረገው የውይይት መድረክ ላይ ተገልጿል፡፡

በውይይቱ ላይ ሐሳባቸውን የሰጡ የባንክ ኃላፊዎች በበኩላቸው የባንኮች ዋነኛ የገቢ ምንጭ ተቀማጭ እንደሆነ አስታውሰው፣ ይህም በአጭር ጊዜ ተመላሽ የሚሆን እንደ መሆኑ መጠን በአምራች ኢንዱስትሪዎች የሚቀርበውን የረዥም ጊዜ የብድር ጥያቄ ሙሉ በሙሉ ለመመለስ የሚቸግር ነው ብለዋል፡፡

ባንኮች ከሚስተዋልባቸው የተበላሸ ብድር አብዛኛው የሚመዘገበው ከአምራች ኢንዱስትሪዎች በኩል እንደሆነ፣ ከዚህ በተጨማሪም የራሳቸው ይዞታ ሳይኖራቸው ብድር የሚጠይቁ አምራቾችን ጥያቄ መመለስ የራሱ የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊያመጣ እንደሚችል ተጠቅሷል፡፡

ከአምራች ኢንዱስትሪዎች ለባንኮች የሚቀርቡት የአዋጭነት ጥናቶች በአግባቡ የተዘጋጁ ሆነው እንደማይገኙ፣ ከተለያዩ ቦታዎች ተቀድተው የመጡ መሆናቸው ለሚሰጡት ብድር ሌላው ፈተና መሆኑን የፋይናንስ ተቋማት ኃላፊዎች የገለጹ ሲሆን፣ በተጨማሪም ከውጭ ምንዛሪ ጋር በተገናኘ በብሔራዊ ባንክ የተዘጋጁ መመርያዎች የተፈለገውን ያህል እንዳያቀርቡ እንደገቧቸው አስረድተዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ባደረጉት የማጠቃለያ ገለጻ፣ የተሻለ የገንዘብ ክምችት ያላቸው ባንኮች ለአምራች ዘርፉ የሚሰጡትን ብድር ከፍ ማድረግ ያለባቸው መሆኑን፣ በአመዛኙ ከፋይናንስ ችግር ጋር በተገናኘ ሥራ ያቆሙ 239 ኢንዱስትሪዎችን በጋራ መደገፍና ወደ ሥራ ለመመለስ ርብርብ ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች