በሥርዓተ ምግብ ማሻሻል ላይ የሚተገበሩ ፕሮጀክቶች ዘላቂና ውጤታማ እንዲሆኑ ከተፈለገ፣ ከውጭ ዕርዳታ ተላቀው በአገር ውስጥ የፈንድ ምንጮች ላይ መመሥረት አለባቸው ተባለ፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ የሲቪክ ማኅበራት ጥምረት ለሥርዓት ምግብ ማስፋፋት ንቅናቄ›› ጠቅላላ ጉባዔ የካቲት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. በተካሄደበት ወቅት፣ የሥርዓተ ምግብ ፕሮግራሞችን እያደናቀፉ ያሉ ችግሮች ተነስተዋል፡፡ የፈንድ አማራጮችን ማስፋትና በቅንጅት መሥራት ከአመጋገብ ጋር የተያያዙ አገራዊ ችግሮችን ለመቅረፍ ወሳኝ መሆኑ በጉባዔው ጎልቶ ተንፀባርቋል፡፡
ከ60 በላይ አገር በቀልና ዓለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅቶችን ያሰባሰበው ብሔራዊ የሥርዓተ ምግብ ማስፋፋት ንቅናቄው፣ በተለያዩ አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ችግሮች እየተፈተነ መሆኑ ተመልክቷል፡፡
የሩሲያና የዩክሬን ጦርነት መቀጠሉ ከኮሮና ወረርሽኝ ተፅዕኖ ጋር ተዳምሮ፣ ለፕሮጀክቶች የሚገኘውን የገንዘብና ምግብ ዕርዳታ እንደቀነሰው ተነግሯል፡፡ በሌላ በኩልም በአገር አቀፍ ደረጃ ያለው የፀጥታ ችግርና የምግብ ዋጋ ግሽበት ለሥርዓተ ምግብ ፕሮግራሞች በእንቅፋትነት ተወስተዋል፡፡
የሲቪክ ማኅበራት ጥምረት ለሥርዓተ ምግብ ማስፋፋት ንቅናቄ መሪ ወ/ሮ እስራኤል ኃይሉ ግን፣ እንቅፋቶች ቢኖሩም የሥርዓተ ምግብ ማሻሻያ ግቦችን በታቀደው ጊዜ ኢትዮጵያ ማሳካት ትችላለች ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ዓለም አቀፉን የሥርዓተ ምግብ ማሻሻል ንቅናቄ ከተቀላቀለች አሥር ዓመታት እንደሆናት የጠቀሱት ኃላፊዋ፣ በአጭር ዓመታት ብዙ ውጤታማ ሥራዎችን ሠርታለች ሲሉ አስረድተዋል፡፡
የሰቆጣ ቃል ኪዳንን ተሞክሮ ለዓለም አገሮች ምሳሌ መሆን የቻለ ውጤታማ እንቅስቃሴ መሆኑን ገልጸው፣ የብሔራዊ ሥነ ምግብ ንቅናቄ ስድስት ኔትወርኮች እንዳሉትም አክለዋል፡፡
‹‹ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት ፍጥነት ከሥርዓተ ምግብ ጋር ተያያዥ የሆኑ ሁሉንም ዓይነት ችግሮችን እ.ኤ.አ. በ2030 ወደ ዜሮ ለማድረስ የተገባውን ቃል በአግባቡ ታሳካለች፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በዚሁ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ የተካፈሉት የኒዩትሪሽን ኢንተርናሽናል የኢትዮጵያ ዳይሬክተር አማረ ደርበው (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የሥርዓተ ምግብ ንቅናቄው የአገር አቀፍ ፈንድ ምንጮችን ያማከለ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
‹‹እንደ ኬንያ ያሉ አገሮች ዜጎች ለሥርዓተ ምግብ ፕሮግራሞችና ፕሮጀክቶች በሳንቲም ደረጃ በቀላሉ በስልካቸውና ባመቻቸው መንገድ እያዋጡ እንዲደግፉ ይደረጋል፡፡ ይህን መሰል ተሞክሮ በማምጣት በሞባይልና በቀላሉ አገራዊ ሀብት በማሰባሰብ ፕሮጀክቶቹን ከውጭ ፈንድ ጥገኝነት ማላቀቅ ጠቃሚ ነው፤›› ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ የመቀንጨር ችግርን ለመከላከል የጀመረችው የሰቆጣ ቃል ኪዳን ፕሮጀክት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሳይቀር በውጤታማነት መነሳቱ ይታወሳል፡፡ ብሔራዊ የሥርዓተ ምግብ ማሻሻል ንቅናቄው የሰቆጣ ቃል ኪዳንን ጨምሮ ሌሎች ፕሮጀክቶችን ያቀፈ መሆኑ ተነግሯል፡፡ በዚህ ንቅናቄም የግብርና፣ የጤና፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሮችን ጨምሮ በርካታ አገር በቀልና ዓለም አቀፍ የሲቪክ ማኅበራት ይሳተፋሉ ተብሏል፡፡