ለአገር ውስጥ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት የሚውሉ ዝቅተኛ ኤርፖርቶችና ሔሊፖርቶች (ሔሊኮፕተር) ግንባታ ዝቅተኛ በመሆኑ፣ ችግሩን ለመቅረፍ የግል ባለሀብቶች፣ ኢንቨስተሮችና የክልል መንግሥታት በአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንት እንዲሰማሩ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጠየቀ፡፡
በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት አራት በዓለም አቀፍ ኤርፖርት ደረጃ የተሰጣቸውን ቦሌ፣ መቀሌ፣ ጎንደርና ኮምቦልቻ ኤፖርቶችን ጨምሮ 22 መደበኛ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙ ኤርፖርቶች ቢኖሩም፣ ቁጥራቸውና የሚሰጡት አገልግሎት ውስን መሆኑን ባለሥልጣኑ አመላክቷል፡፡
ባለሥልጣኑ ችግሩን ለመቅረፍ ይቻል ዘንድ በግሉ ዘርፍ የተሰማሩ አካላትና ክልሎች በአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንት እንዲሳተፉ ጥሪ ያቀረበው የካቲት 16 ቀን 2015 ዓ.ም በዋና መሥሪያ ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት መስክ ከአፍሪካ ግንባር ቀደም ብትሆንም፣ ካሉት የሕዝብ ብዛትና ሰፊ የቆዳ ስፋት አኳያ፣ ለአገር ውስጥ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት የሚውሉ የአነስተኛ ኤርፖርቶች ልማት ከሌሎች አገሮች ጋር ሲነፃፀር በጣም ዝቅተኛ መሆኑን የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው መንግሥቴ ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ከብዛትም ሆነ ከፍጥነት አኳያ ሲታይ በቂ እንዳልሆነ ያብራሩት አቶ ጌታቸው፣ ችግሩን መንግሥት ብቻ ሊቀርፈው ስለማይችል የግል ባለሀብቶች፣ ኢንቨስተሮች ክልሎች በኤርፖርትና ሔልፖርት ግንባታ መሳተፋቸው አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን አስረድተዋል፡፡
የቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት በመጥበቡ የማስፋፋት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ በመርሐ ግብሩ ተናግረዋል፡፡
ባለሥልጣኑ በኢትዮጵያ ያለውን ዝቅተኛ የኤርፖርትና ሔልፖርት ልማት ለመቅረፍ በግሉ ዘርፍ የተሰማሩ አካላትን በአቪዬሽን ኢንዱስትሪ አንቨስትመንት እንዲሰማሩ ጥሪ ለማቅረብ ሲያስብም የኢንስትመንት ቦታዎችን የማዘጋጀት ሥራዎችን ጎን በጎን እየተሠራ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
የግሉ ዘርፍና የክልል መንግሥታት በኤርፖርትና ሔልፖርት ግንባታ እንዲሳተፉ ጥሪ ያቀረበው ባለሥልጣኑ፣ ለአልሚዎቹ ተገቢውን የቴክኒክ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን፣ ለማሳለጥም ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ጋር የመግባቢያ ሰነድ በመፈራረም በጥምረትም የሚሠራበትን ሁኔታ ተመቻችቷል ብሏል፡፡
ኢትጵዮጵያውያን በአየር ትራንስፖርት መጓጓዝ ገና ብርቃቸው በመሆኑ አቪዬሽኑ በኤርፖርት ግንባታ ብዙ ሥራ እንደሚጠበቅበት ተነስቷል፡፡
የአውሮፕላን ማረፊያ ሥፍራዎች ማስፋፋት የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ተደራሽነትን በማሳደግ መንገደኞችና ዕቃን በፍጥነት ለማጓጓዝ፣ ከፍተኛ ዋጋ ያላቸውንና በቀላላ የሚበላሹ ምርቶችን በአስተማማኝና በጥራት ለማመላለስ፣ የቱሪዝም መዳረሻ ሥፍራዎችን ተደራሽ ለማድረግ፣ ምርታማነትንና ቅልጥፍናን በማረጋገጥ ለሌሎች የኢኮኖሚያና ማኅበራዊ መስኮች መስፋፋት ጉልህ ሚና ቢኖርም፣ ዘርፉ በኢትዮጵያ ገና ያልተነካና ብዙ ሥራ የሚጠበቅበት መሆኑ ተነግሯል፡፡
ይህ ከሆነበት ምክንያት አንዱ የኤርፖርት ግንባታና አስተዳደር በዋናነት በፌዴራል መንግሥት ጫንቃ ላይ በመውደቁ መሆኑ ሲሆን፣ በአነስተኛ ኤርፖርቶችና ሔልፖርቶች ግንባታና አስተዳደር ላይ የግል ባለሀብቶች፣ የክልል መንግሥታትን፣ የከተማ አስተዳደሮችን፣ እንዲሁም መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትን በስፋት ማሳተፍ አስፈላጊ ሆኗል ተብሏል፡፡
ጥሪ የተደረገላቸው የግሉ ባለሀብቶች በዘርፉ ተሰማርተው በኢትዮጵያ ስታንዳርዳቸውን የጠበቁ ኤርፖርቶችን ቁጥር በማሳደግ፣ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ተደራሽ በማድረግ ለዜጎች ኑሮ መሻሻል የላቀ ሚና እንደሚጫወቱ ባለሥልጣኑ እምነት እንዳለው ተነግሯል፡፡