Tuesday, March 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊሕገወጥ የዝሆን ግድያን ማስቆም ካልተቻለ በኢትዮጵያ ያሉ ዝሆኖች ሊጠፉ እንደሚችሉ ተገለጸ

ሕገወጥ የዝሆን ግድያን ማስቆም ካልተቻለ በኢትዮጵያ ያሉ ዝሆኖች ሊጠፉ እንደሚችሉ ተገለጸ

ቀን:

የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን በተያዘው በጀት ዓመት ስድስት ወራት፣ ከፍተኛ የዝሆን ጥርሶችና የነብር ቆዳዎች በሕገወጥ መንገድ ሲዘዋወር በቁጥጥር ሥር ማዋሉን አስታውቆ፣ ሕገወጥ አደንና ግድያው በዚሁ ከቀጠለ በተለይ ዝሆኖች ከኢትዮጵያ ሙሉ በሙሉ ሊጠፉ እንደሚችሉ ገልጿል፡፡

ምንም እንኳን በጦርነቱ ወቅት ከነበረው ጋር ሲነፃፀር ሕገወጥ አደኑና የዝሆን ጥርስ ዝውውሩ ባለፉት ስድስት ወራት ቢቀንስም፣ ድርጊቱን ሙሉ ለሙሉ ማስቆም ባለመቻሉ ሕገወጥ የዝሆን ጥርስ ዝውውር በዚህ ከቀጠለ በኢትዮጵያ ያሉ ዝሆኖች በሙሉ ሊጠፉ ይችላሉ ብሏል፡፡

ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ በጋምቤላ ክልል ሰባት የዝሆን ጥርሶች፣ በአርባ ምንጭ ሰባት የነብር ቆዳዎችና አራት የዝሆን ጥርሶች በግለሰብ ቤት፣ ሦስት የዝሆን ጥርሶች በተሽከርካሪ በሕገወጥ መንገድ ሲዘዋወሩ መያዛቸውን፣ የባለሥልጣኑ የዱር እንስሳት ሕግ ማስከበር ዳይሬክተር አቶ ዳንኤል ጳውሎስ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

በጋምቤላ ክልል ሰባት የዝሆን ጥርሶች ሲዘዋወሩ እንደተያዙ የገለጹት አቶ ዳንኤል፣ ሕገወጥ አዘዋዋሪዎቹ እንዳመለጡና ይህ ዘገባ እስከ ተዘጋጀበት ጊዜ ድረስ በቁጥጥር ሥር እንዳልዋሉም አክለዋል፡፡

በአርባ ምንጭና በጋምቤላ ክልል በሕገወጥ መንገድ ሲዘዋወሩ ተገኙ የተባሉት 14 የዝሆን ጥርሶችና ሰባት የነብር ቆዳዎች ለባለሥልጣኑ ገቢ መደረጋቸውን፣ ሦስት የዝሆን ጥርሶች በተሽከርካሪ ጭኖ የተገኘው ግለሰብ አራት ሺሕ ብር፣ እንዲሁም ሰባት የነብር ቆዳዎች ይዞ የተገኘው ግለሰብ አሥር ሺሕ ብር ዋስትና አስይዘው መጥፋታቸውንና በሕግ እየተፈለጉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡   

የዝሆን ጥርስን ጨምሮ የዱር እንስሳት ውጤቶችን ያዘዋውራል ተብሎ የተጠረጠረ ግለሰብ ቤቱ ሲፈተሽ አራት የዝሆን ጥርሶች የተገኙበት ሲሆን፣ አርባ ጥይቶችና አንድ መሣሪያ እንደተገኙበትና በቁጥጥር ሥር ውሎ ጉዳዩ በፍርድ ቤት እየታየ መሆኑን አቶ ዳንኤል አስረድተዋል፡፡

በሕገወጥ የዝሆንና የሌሎች እንስሳት ጥርስ ቀንድና ቆዳ ዝውውር የተሰማሩ አካላትን በቁጥጥር ሥር ማዋል ለባለሥልጣኑ ፈታኝ በመሆኑ፣ በሚቀጥሉት ሦስት ወራት ውስጥ አብዛኛውን ጊዜ የዝሆን ጥርስ ሲዘዋወር በሚገኝበት ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት አራት አነፍናፊ ውሾችን ለማሰማራት እየተሠራ መሆኑ ተገልጿል፡፡

የጥበቃ ሠራተኞች አነስተኛ መሆንና ዘመናዊ መሣሪያ አለመጠቀም ለጥበቃ ፈተና በመሆኑ፣ አነፍናፊ ውሾቹ የዝሆን ጥርስ ያለበትን ቦታ በቀላሉ ማግኘት እንደሚችሉ ስለተረጋገጠ፣ ድርጊቱን ማስቆም እንደሚቻልም ተስፋ መደረጉ ተጠቅሷል፡፡

ባለሥልጣኑ 630 ሬንጀሮች ቢኖሩትም የሬንጀሮች ቁጥር በጣም አነስተኛ መሆኑ፣ በሕገወጥ አደን የተሰማሩ አካላት የሚይዙት መሣሪያ የጥበቃ ሠራተኞች ከሚይዙት እጅግ የተሻለ መሆኑ ሕገወጥ አደንን ለማስቆም ፈታኝ መሆኑ ተብራርቷል፡፡ ይህን ተከትሎም የዱር እንስሳትን ለመጠበቅ የተሰማሩ ሬንጀሮች ስማርት ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም መጀመራቸው የተጠቀሰ ሲሆን፣ ቁጥጥሩን ዘመናዊ ለማድረግ ድሮኖችን ለመጠቀም ዕቅድ እንደተያዘም ተጠቁሟል፡፡

ባለሥልጣኑ በሕገወጥ መንገድ ሲዘዋወሩ የሚያዙ የዝሆን ጥርሶችን እየሰበሰበ እንደሚያቃጥል ስለሚነገር፣ በሕገወጥ ሲዘዋወሩ የተያዙ የዝሆን ጥርሶችን ምን ለማድረግ እንደታሰበ ከሪፖርተር ጥያቄ የቀረበላቸው ዳይሬክተሩ፣ ለ30 ዓመታት በባለሥልጣኑ ተከማችተው የነበሩ 6.1 ሜትሪክ ቶን የዝሆን ጥርሶች መጋቢት 11 ቀን 2007 ዓ.ም. መቃጠላቸውን አስታውሰው፣ በአሁኑ ወቅት ተሰባስበው የሚገኙት ግን ምን እንደሚደረጉ ገና ውሳኔ አልተሰጠበትም ብለዋል፡፡

በባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ምን ያህል ሜትሪክ ቶን እንሚገኝና 14 የዝሆን ጥርሶች መጠናቸውን እንዲያብራሩ ሲጠየቁ፣ ከደኅንነት አንፃር ማብራሪያ መስጠቱ ተገቢ እንዳልሆነ አስረድተዋል፡፡

ሕገወጥነት በመስፋፋቱ በተለይ የኢትዮጵያ ዝሆኖች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መሆኑን ያብራሩት አቶ ዳንኤል፣ ከ40 ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ያሉ ዝሆኖች ብዛት እስከ አሥር ሺሕ ይደርስ እንደነበር፣ በአሁኑ ወቅት ያሉት ግን ሁለት ሺሕ የማይሞሉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በዓለም ላይ ከ35 ሺሕ በላይ የዱር እንስሳትና የዕፅዋት ዝርያዎች በሕገወጥ ዝውውር ለጉዳት እንደሚዳረጉ የሳይተስ (CITES) ዓለም አቀፍ ስምምነት እንደሚያሳይ፣ ከእነዚህም መካከል አምስት ሺሕ ያህሉ የዱር እንስሳት ዝርያዎች (Wild fauna) ሲሆኑ፣ 30 ሺሕ ያህሉ ደግሞ የዱር ዕፅዋት (Wild Flora) መሆናቸውን ባለሥልጣኑ በ2014 ዓ.ም. መጋቢት ወር ይፋ ያደረገው ጥናት ያሳያል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹ከኦነግ ሸኔ ጋር ያለውን ግጭት በሰላም ለመፍታት ከፍተኛ ፍላጎት አለን›› ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ

መንግሥት ከ‹‹ኦነግ ሸኔ››ጋር ያለውን ግጭት በሰላም ለመፍታት ከፍተኛ ፍላጎት...

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...