Thursday, June 13, 2024

የአፍሪካ በተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ የማግኘት ውትወታ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የፀጥታው ምክር ቤት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ከፍተኛ ሥልጣን ያለው አካል ነው፡፡ ይህ ምክር ቤት 15 አባላት ያሉት ሲሆን፣ አሥር አገሮች በየሁለት ዓመቱ ይቀያየራሉ፡፡ አምስት ቋሚ መቀመጫ ያላቸው ጥቂት የሚባሉ የመጀመርያዎቹ የኑክሌር ኃይል ባለቤት የሆኑ አገሮች ማለትም ሩሲያብሪታንያቻይናዩናይትድ ስቴትስና ፈረንሣይ በበላይነትና በቋሚነት ቦታውን ይዘው የሚዘውሩት ተቋም ነው፡፡

ቋሚ መቀመጫ የሌላቸው በየሁለት ዓመቱ በሚደረገው ምርጫ ተሳታፊ የሚሆኑት አሥር አገሮች በአምስት ምድቦች ውስጥ ተካተው የሚሳተፉበት ነው፡፡ በዚህ መሠረት ሁለት መቀመጫ ለምዕራብ አውሮፓውና ሌሎች ቡድኖች፣ አንድ መቀመጫ ለምሥራቅ አውሮፓ ቡድን፣ ሁለት ለላቲን አሜሪካና ለካሪቢያን ቡድን፣ አምስት መቀመጫ ለአፍሪካና ለእስያ ቡድን ተደልድለዋል፡፡ በየቡድኑ ውስጥ የሚገኙ አገሮች በየሁለት ዓመቱ እየተቀያየሩ ቦታውን በጊዜያዊነት ይይዙታል፡፡

ተመድ በራሱ ቻርተር እንደተገለጸው በማንኛውም አገር መንግሥት የማይወከል፣ ነገር ግን አገሮች ለጋራ ጥቅም በጋራ ስምምነት የተወሰነ ሉዓላዊ መብታቸውን ለዚህ ድርጅት አሳልፈው በመስጠት የመሠረቱት ነው፡፡ በጋራ ሕግ የአገሮችን ደኅንነት፣ ኢኮኖሚያዊ ማኅበራዊ ዕድገት፣ የሰብዓዊ መብት ጥበቃና የአገሮችን ትብብር ለማሳደግ የሚሉ ዓላማዎች አሉት፡፡

ከተመሠረተ ከ70 ዓመታት በላይ ያስቆጠረውና 193 አባል አገሮች ያሉት ተመድ ውስጥ ያለው አጠቃላይ አሠራር፣ እንዲሁም በድርጅቱ ውስጥ ከፍተኛ ሥልጣን ያለው የፀጥታው ምክር ቤት የቋሚ አባላቱ አደረጃጀት፣ ቋሚ አባላቱ ድምፅን በድምፅ የመሻር መብትን (Veto Power) በብቸኝነት መያዛቸውን በተመለከተ ለበርካታ  ዓመታት ከአባል አገሮች በተደጋጋሚ ተቃውሞ ሲነሳበት ነበር፡፡

ለፀጥታው ምክር ቤት ከተሰጡ አሥር ዋና ዋና ተግባራት መካከል በተመድ መርሆችና ዓላማዎች መሠረት ዓለም አቀፍ ሰላምና ደኅንነትን ማስጠበቅ፣ ዓለም አቀፍ ቀውስና ክፍፍል ሊያመጡ የሚችሉ ችግሮች ላይ ምርመራ እንዲካሄድ ማድረግ፣ በአገር ውስጥ ወረራ ሲከሰት የተመድ አባል አገሮች በወራሪው አካል ላይ የኢኮኖሚና ሌሎች ማዕቀቦች እንዲጥሉ ጥሪ ማድረግ፣ አዳዲስ አባል አገሮች ወደ ተመድ ስለሚገቡበት ሁኔታ ምክረ ሐሳብ ማቅረብ፣ በወረራ ወቅት ለወራሪዎች ምላሽ ለመስጠት ሠራዊት ማሰማራትና ሌሎች ቁልፍ የሚባሉ ኃላፊነቶችን የያዘ ነው፡፡

ይሁን እንጂ በዚህ የአገሮችን ስምምነት መሠረት አድርጎ በተመሠረተ ተቋም ውስጥ የተወሰኑ አባል አገሮች በቋሚነት ውሳኔ የሚሰጡበት፣ በሌሎች አገሮች ላይ በብቸኝነት ውሳኔ የሚያስተላልፉበት ሆኖ መቆየቱ ከበርካታ አገሮች ተቃውሞ እየቀረበበት ነው፡፡

ጥያቄው ከበርካታ አገሮች የሚነሳ ቢሆንም በዋነኝነት በቅርቡ እየበረታ የመጣው ጥያቄ ከ193 አባል አገሮች ውስጥ ቢያንስ 54 አገሮች አባል የሆኑበት የአፍሪካ አኅጉር ነው፡፡ የፀጥታው ምክር ቤት በአኅጉራዊ ወይም ቀጣናዊ ስብጥር ቢታይ እንኳ ከምዕራብ አውሮፓ ፈረንሣይና እንግሊዝ፣ ከምሥራቅ አውሮፓ ሩሲያ፣ ከእስያ ቻይና፣ እንዲሁም ከሰሜን አሜሪካ ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ ትገኝበታለች፡፡ ይሁን እንጂ ከአፍሪካ አኅጉር ወካይ አገር አለመኖሩ አባል አገሮቹን በተመድ ኢፍትሐዊ አሠራር በደል እየተፈጸመባት ስለመሆኑ በተለያዩ መድረኮች ሲነሳ ይስተዋላል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2015 ጂ4 በሚል መጠሪያ ብራዚል፣ ጃፓን፣ ጀርመንና ህንድ፣ እንዲሁም ስሙ ያልተጠቀሰ አንድ የአፍሪካ አገርን በማካተት ዓለም ላይ ጠንካራ ኢኮኖሚ ያላቸው አገሮች በተጨማሪነት የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ አባል ይሁኑ በሚል ጥያቄ አቅርበው ነበር፡፡

በተመድ ውስጥ መዋቅራዊና የአሠራር ለውጥ ጥያቄ እንዲነሱ ካደረጉት ምክንያቶችና ከሚሰሙ ተደጋጋሚ ቅሬታዎች መካከል እ.ኤ.አ. ከ1946 ጀምሮ፣ በሥራ ላይ ያሉት የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ አባል አገሮች አሁናዊ ዓለም አቀፍ ሁኔታዎችን ግምት ውስጥ ያላስገባ አሠራር፣ አዳጊና በማደግ ላይ ያሉ አገሮችን ያላካተተና ጂኦግራፊካዊ ስብጥርን ያላሟላ መሆኑ፣ ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት ያላቸው አገሮች የተሰጣቸውን መብት በየጊዜው የሚሸረሽሩትና ለአገራቸው ጥቅም የሚያውሉት መሆናቸው፣ በፀጥታው ምክር ቤት አባላት መካካል የግልጽነትና የአቅም ውስንነነት፣ እንዲሁም በርካታ ሐሳቦች ይነሳሉ፡፡ የፀጥታው ምክር ቤት በርካታ ውሳኔዎችን በአፍሪካ አገሮች ላይ ሲያሳልፍ አኅጉሩን የሚወክል አንድም ቋሚ አባል አለመኖሩ፣ ምክር ቤቱ በአፍሪካ ላይ የሚያደርገው ኢፍትሐዊ አሠራር የበለጠ የሚያጎላው እንደሆነ ይነገራል፡፡

የአፍሪካን አቋም በፀጥታው ምክር ቤት በአንድ ድምፅ ለማሰማት በሚል እ.ኤ.አ. በ2005 የተመሠረተውና የአሥር አገሮች መሪዎችን በውስጡ ያቀፈው የአፍሪካ ኅብረት ‹‹ኮሚቴ አሥር›› የተሰኘው በተለያዩ ጊዜያት የፀጥታው ምክር ቤት ሪፎርም እንዲደረግ ከተመድ ጋር ምክክር ያደረገ ሲሆን፣ በዚህ ሒደት ኮሚቴው አፍሪካ ቢያንስ ሁለት ቋሚ መቀመጫና ከሦስት እስከ አምስት ቋሚ መቀመጫ በሌላቸው የተመድ ድርጅቶች አባል ለመሆን ውትወታ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡

የመዋቅራዊና  አሠራር ለውጥ እንዲደረግ ጥያቄው ከበርካታ አገሮች እየተሰማ ቢሆንም፣ በቅርቡ እየበረታ የመጣው ከአፍሪካ አኅጉር የሚሰማው ጥያቄ ነው፡፡ ለአብነት እንኳ የቀድሞው የዚምባቡዌ ፕሬዚዳንት ሮበርት ገብርኤል ሙጋቤ በአፍሪካ ኅብረት ስብሳባዎችና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መድረኮች በተደጋጋሚ ሲያነሱት እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፣ አሁን ይህን ጥያቄ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድን (ዶ/ር) ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ መሪዎች በአደባባይ ሲያስተጋቡት ይስተዋላል፡፡

በሕይወት ሳሉ በቀደሙት ጊዜያት በጉዳዩ ላይ በተለያዩ መድረኮች አስተያየት በመሰንዘር የሚታወቁት ሮበርት ሙጋቤ፣ እ.ኤ.አ. በ2017 በኒውዮርክ በተካሄደው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ንግግር አድርገው ነበር፡፡ አሁን በሥራ ላይ ያለው የፀጥታው ምክር ቤት መዋቅር ትንንሾችን የሚያበለፅግ ብዙዎችን የሚያደኸይ በመሆኑ ቁልፍ ተብለው የተቀመጡ የ2030 ተመድ አጀንዳዎችን ለማስፈጸም እንደማይችል ተናግረው ነበር፡፡ የፀጥታው ምክር ቤት የሚያደርገው ታሪካዊ ኢፍትሐዊነት በምንም ምክንያት ማስተባበያ የማይቀርብበት በመሆኑ፣ ምክር ቤቱ በራሱ ላይ ሪፎርም እንዲያደርግ ጥሪ ማቅረባቸው የሚታወስ ነው፡፡

አሁም በቀጠለው የመዋቅርና የአሠራር ለውጥ ጥያቄ ከጥቂት ቀናት በፊት በተጠናቀቀው የአፍሪካ ኅብረት 36ኛው የመሪዎች ጉባዔ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት  ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር)፣ አፍሪካ ቢያንስ በፀጥታው ምክር ቤት አንድ ቋሚ መቀመጫ፣ ቋሚ አባልነት በሌላቸው የተመድ ድርጅቶች ከሁለት በላይ መቀመጫዎች፣ እንዲሁም ቡድን 7 እና ቡድን 20 አባል አገሮች ውስጥ ተመጣጣኝ የሆነ ውክልና ያስፈልጋታል ብለዋል፡፡

በአዲስ አበባ ለ36ኛው የአፍሪካ ኅብረት ጉበዔ ተገኝተው የነበሩት የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬስ ለሚዲያዎች በሰጡት መግለጫ አፍሪካ በፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ ማጣቷ ኢፍትሐዊ መሆኑን ገልጸው፣ ነገር ግን ይህ የአባልነት ጥያቄ በአባል አገሮች የሚወሰን እንጂ በዋና ጸሐፊው የሚወሰን አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡ የፀጥታው ምክር ቤት አባላት አፍሪካ ቢያንስ አንድ ቋሚ አባል እንዲኖራት እንደሚስማሙ የጠቆሙት ዋና ጸሐፈው፣ በዚህም መሠረት ጥያቄው መልስ ያገኛል የሚል ተስፋ እንዳላቸው አስረድተዋል፡፡

በቅርቡ የአሜሪካ የሰላም ተቋም የተሰኘ ድረ ገጽ አማኒ አፍሪካ የተሰኘው የአፍሪካ ገለልተኛ የፖሊሲ ጥናት ተቋም መሥራች የሆኑትን ሰሎሞን ደርሶን (ዶ/ር) ጠቅሶ ባወጣው ጽሑፍ፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቻርተር የተመሠረተው ባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ የሕጋዊነት ጥያቄ ውስጥ ከገባ ስለመቆየቱ ያስረዳል፡፡

 የፀጥታው ምክር ቤት አጠቃላይ መዋቅርና ሥሪት ምዕራባዊ ስለመሆኑና ምክር ቤቱ ከሚመለከታቸው አጠቃላይ አጀንዳዎቹ ከ60 በመቶ የሚሆኑት የአፍሪካ ጉዳዮች ቢሆኑም፣ የጉዳዩ ባለቤት የሆነው አኅጉሩ ምንም ዓይነት ሚና እንዳይኖረው ስለመደረጉ አብራርቷል፡፡

ከአፍሪካ ኅብረት 36ኛው የመሪዎች ጉባዔ ጎን ለጎን አማኒ አፍሪካ በተሰኘው የሪሰርች ተቋም አማካይነት በተካሄደ አፍሪካና ባላብዙ ወገን ዓለም አቀፍ ተቋማት ሪፎርም በተሰኘ መድረክ፤ አፍሪካ በፀጥታው ምክር ቤት ሊኖራት ስለሚገባው የቋሚ መቀመጫ ጉዳይ አስመልክተው ንግግር ያደረጉት የቀድሞው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ አምባሳደር ተቀዳ ዓለሙ (ዶ/ር)፣ በአፍሪካ ላይ ለዘመናት ተጭኖ የቆየውን ኢፍትሐዊነትና ከቋሚ አባልነት ተግልላ የቆየችበትን አሠራር ለመቀየር በፀጥታው ምክር ቤት ላይ ሪፎርም እንዲደረግ አፍሪካውያ ግፊት እያደረጉ ስለመሆናቸው፣ በዚህ በሚደረገው ግፊት ልክ ደግሞ አኅጉሩ በባለ ብዙ ወገን ዲፕሎማሲ በዓለም ላይ ያሉ ጫናዎችን እኩል በመቀበልና እኩል በመሸከም ለችግሮች ሁሉ ተጋፋጭ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ለበርካታ ዓመታት ሲነሳ የቆየውን ይህን የአባልነት ጉዳይ የተሰናባቹ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር የሴኔጋል ፕሬዚዳንት ማኪ ሳልም ሆኑ፣ በእሳቸው እግር የተተኩት የኮሞሮስ ፕሬዚዳንት አዛሊ አሱማኒ፣ እንዲሁም በርካታ የአፍሪካ አገሮች የአፍሪካ ኅብረት በፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ የማግኘት ጉዳይ አቀንቃኝ ናቸው፡፡  ይሁን እንጂ ጉዳዩ ከኅብረቱም ሆነ ከአባል አገሮቹ ትኩረት ያገኘ ቢሆንም፣ በቀጣይ ይህንን አጀንዳ አስተባባሮ ወደ  ተመድ በመውሰድ ትኩረት እንዲያገኝ ማድረጉ  ግን ትልቁ የቤት ሥራ ይሆናል ነው የተባለው፡፡ በሌላ በኩል በአፍሪካ ኅብረት የአባልነት ጥያቄ አፍሪካን በአንድ ድምፅ ሊወክል የሚችል ወካይ ድምፅ ማግኘት ይቻላል ወይ? የሚለውን ጉዳይ የሚያነሱም አልጠፉም፡፡

ከዚህ ቀደም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና በአፍሪካ ኅብረት በተለያዩ ጊዜያት ያገለገሉት ቆስጠንጢኖስ በርሔ (ዶ/ር) ለሪፖርተር ስለጉዳዩ ሲናገሩ፣ ከጅምሩ ተመድ ሲመሠረት የኑክሌር ባለቤት የሆኑ አገሮች የፀጥታው ምክር ቤት  ቋሚ አባል ቢሆኑ ይቀላል በሚል እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡

ለዚህም እንደ ዋና ምክንያት የቀረበው ሁለተኛው የዓለም ጦርነት እንዳይደገምና ሦስተኛ የዓለም ጦርነት እንዳይነሳ በሚል ዕሳቤ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት የተሰጣቸው አገሮች በቅርቡ በሩሲያና በዩክሬን መካከል እየተካሄደ ባለው ጦርነት ሩሲያን ለማውገዝ ስብሰባ ሲቀመጡ ኤርትራ ሩሲያን ላለማውገዝ መለየቷን በመጥቀስ፣ ይህ ማለት አፍሪካ ውስጥ ካሉ አገሮች አንዱ በአገራዊ ውጭ ፖሊሲ ምክንያት ምክር ቤቱ አንድ አገር ላይ በሚያቀርበው የውሳኔ ሐሳብ ላይ የተለየ አቋም ካራመደ አኅጉሩን እንዴት ነው ይህን ውሳኔ የጋራ ማድረግ የሚችለው ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

አሁን ያሉት የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ አባላት እያንዳንዳቸው ሉዓላዊ የሆኑ አገሮችና የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ያላቸው በመሆናቸው ውሳኔ ላይ ሲደርሱ ብቻቸውን መሆኑን የጠቆሙት ቆስጠንጢኖስ (ፕሮፌሰር)፣ ከአፍሪካ ኅብረት በኩል የሚነሳው ነገር አንድም እንደ አኅጉር ተወካይ ለመላክ አገሮች በእያንዳንዱ ጉዳይ መስማማት ይችላሉ ወይ? ወይስ ድግሞ ከአኅጉሩ አንድ አገር ይወከላል? ሲባል ሁሉንም የአኅጉሩን አባል አገሮች ፍላጎት ያንፀባርቃል ወይ የሚለውን ጥያቄ መጀመርያ መመለስ አለበት ብለዋል፡፡

የአፍሪካ አገሮች በአንድነት ተሰብስበው የጋራ ድምፅ ኖሯቸው ድምዳሜ ላይ መድረስ ይችላሉ የሚለው ጉዳይ ጥያቄ የሚፈጥር መሆኑን በመግለጽ፣ ለአብነት እንኳ ኅብረቱ ወደ 200 የሚደርሱ ውሳኔዎች አሳልፎ እስካሁን አንዳቸውም ተግባራዊ አለመሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

የአፍሪካ አገሮች አሁን በያዙት አቋማቸው ለምሳሌ የተወሰኑት ከቻይና፣ የተወሰኑት ከፈረንሣይ፣ የተወሰኑት ከእንግሊዝ፣ የተወሰኑት ከአሜሪካ ጋር ቆመው ሲወግኑ የሚታዩበት ሁኔታ እንደሚስተዋል በመግለጽ፣ በዚህ በበዛው የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ አባልነት ውስጥ እንግባ ውትወታ ግን መጨረሻ ላይ በአኅጉሩ ላይ ሊያመጣ የሚችለው አገራዊ ወይም አኅጉራዊ ጥቅም ግልጽ አይደለም ብለዋል፡፡ በመሆኑም ከዚህ በተሻለ አኅጉራዊ ተቋሙን በመጠበቅና በማጠንከር የተሻለ ኅብረት በመፍጠር ሊሰነዘሩ የሚችሉ ጫናዎችን በተሻለ መመከት እንደሚቻል፣ በዚህም የአፍሪካ ኅብረትን የበለጠ ራሱን ተፈላጊ ማድረግ እንደሚቻል አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -