Saturday, April 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ልማት ባንክ የተበላሹ ብድሮችን እስከ ሰኔ ወር ወደ ሁለት በመቶ አደርሳለሁ አለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የተበላሹ ብድሮቹን አሁን ካለበት ሦስት በመቶ እስከ መጪው ሰኔ ድረስ ወደ ሁለት በመቶ ለማውረድ ማቀዱን አስታወቀ፡፡

ባንኩ ይህን ያለው የካቲት 13 ቀን 2015 ዓ.ም. አራተኛ ዙር አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ሥልጠና ማስጀመሪያ በማስመልከት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው፡፡ የባንኩ ካፒታል ከዓመት በፊት 7.5 ቢሊዮን መሆኑን፣ በተበላሹ ብድሮች ምክንያት ወደ ሁለት ቢሊዮን ብር ዝቅ ብሎ እንደነበር የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት ዮሐንስ አያሌው (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

ልማት ባንኩ ከዚህ ችግር ለመላቀቅ በርካታ ሥራዎች መሥራቱን አስታውሰው፣ ከዚህ ቀደም 40 በመቶ ደርሶ የነበረውን የተበላሸ ብድር ወደ ሦስት በመቶ መቀነስ መቻሉን ጠቁመዋል፡፡

በብዙ ችግሮች ውስጥ የቆየውን ባንክ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የተበላሹ ብድሮቹን በመቀነስ ከኪሳራ ወጥቶ ወደ ትርፍ ማስገባት መቻሉን ፕሬዚዳንቱ አስረድተዋል፡፡

እንደ ዮሐንስ (ዶ/ር) ገለጻ፣ በብዙ ችግሮች ውስጥ የነበረው ባንክ አሁን ላይ ችግሮችን ተቋቁሞ ያለው ካፒታል ወደ 36 ቢሊዮን ደርሷል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ልማት ባንክና በዓለም ባንክ ትብብር የአነስተኛና መካከለኛ አንቀሳቃሽ ኢንተርፕራይዞች አራተኛ ዙር ሥልጠና የሚሰጠው ከየካቲት 14 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ነው፡፡

በዚህ ሥልጠና 435,000 ዜጎች የተመዘገቡ መሆኑን፣ ከእነዚህ ውስጥ 112,000 ሥልጠናውን የሚያገኙ ናቸው ተብሏል፡፡

በመላው ኢትዮጵያ የሚከወነው መርሐ ግብር በ57 ከተሞችና በ95 የሥልጠና ማዕከላት መዘጋጀቱ ተጠቁሟል፡፡

በዚህ የሚሰጠው የሥልጠና ዓይነቶቹም ዘርፍ ብዙ መሆናቸውን፣ እነሱም ጨርቃ ጨርቅ፣ በቆዳ ዘርፍ፣ ግብርና፣ ዕርባታ፣ መካከለኛ ክሊኒኮች እንዲሁም በማዕድን ማውጣት ዘርፎች ሥልጠና ከሚሰጥባቸው ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

በዚህ መርሐ ግብርም 35 በመቶ የሚሆኑ ሠልጣኞች ሴቶች መሆናቸውን ተጠቅሷል፡፡

ለአራተኛው ዙር ሥልጠና ከዓለም ልማት ባንክ የ200 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ማድረጉን ፕሬዚዳንቱ አክለው ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የድጋፍ መጠኑ ባይገለጽም፣ ሌሎች ዓለም አቀፍ ረጂ ድርጅቶችም አስተዋጽኦ ማድረጋቸው ተጠቅሷል፡፡

ባንኩ ካለው ዓመታዊ ካፒታል መጠን ውስጥ ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የ14 ቢሊዮን ብር ብድር እንደሚሰጥ ፕሬዚዳንቱ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች