Thursday, March 23, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኦሮሚያ ኢንሹራንስ የእንስሳት መድን ለገዙ አርብቶ አደሮች 19 ሚሊዮን ብር የጉዳት ካሳ ከፈለ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኦሮሚያ ኢንሹራንስ ኩባንያ ድርቅ በተከሰተባቸው ቦታዎች ለእንስሳት መድን ከ19 ሚሊዮን ብር በላይ ካሳ መክፈሉን አስታወቀ፡፡ 

በኦሮሚያ ቦረና ዞን፣ ጉጂ ዞንና ደቡብ ክልል ደቡብ ኦሞ ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች  6,002  አባወራዎች የእንስሳት መድን ሽፋን በ9,836,653  ብር መግዛታቸውን የኦሮሚያ ኢንሹራንስ ኩባንያ የእንስሳት መድን ሥራ አስኪያጅ አቶ ጌታነህ ኢረና ተናግረዋል፡፡

ኢንሹራንስ ኩባንያው በ2015 ዓ.ም. በጀት ዓመት በሁለት ወቅት ካሳ ለመክፈል 55,000,500 ብር በጀት መያዙን፣ ከዚህ ውስጥ 19 ሚሊዮን ብሩ በድርቅ በተጎዱ አካባቢዎች የእንስሳት መድን ገዝተው ጉዳት ለደረሰባቸው አርሶ አደርሮች 19 ሚሊዮን ብር የጉዳት ካሳ መክፈሉን አቶ ጌታነህ አስረድተዋል፡፡

ኩባንያው ከ11 ዓመታት በፊት የእንስሳት መድን አገልግሎት መስጠት መጀመሩን አስታውሰው፣ በአሁኑ ወቅትም በ22 የተለያዩ የኩባንያው ቅርንጫፎች አገልግሎቱ እየተሰጠ ይገኛል ብለዋል፡፡

በተለይም በአየር ለውጥ ምክንያት የዝናብ እጥረት ባጋጠሙ አካባቢዎች፣ የተለያዩ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ስለ ኢንሹራንስ ግንዛቤ በመስጠታቸው አርብቶ አደሮች ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ኩባንያው ለመጀመሪያ ጊዜ ይህንን የእንስሳት መድን ሽፋን አገልግሎት ሲያቀርብ 171 አርብቶ አደሮች የመድን ሽፋኑን እንደገዙ አስታውሰው፣ ከ11 ዓመታት በኋላ 33,000 አርብቶ አደሮች የእንስሳት መድን ሽፋን መግዛታቸውን ጠቁመዋል፡፡

በሁለት ዞኖች ማለትም በቦረናና ምዕራብ ጉጂ የተጀመረው የእንስሳት መድን አገልግሎት ሽያጭ፣ በአሁኑ ወቅት በምሥራቅ ሐረርጌ፣ በደቡብ ክልል፣ በደቡብ ኦሞና ሌሎችም አካባቢዎች መስፋፋቱንና በዚህም በርካታ አርብቶ አደሮች ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የኦሮሚያ ኢንሹራንስ የሚያቀርበውን እንስሳት መድን ሽፋን የሚገዙ አርብቶ አደሮች ባሏቸው የእንስሳት ዓይነቶች የተለያየ መጠን ያለው ክፍያ የፈጽማሉ። በዚህም መሠረት ለአንድ ግመል 7,000 ብር፣ ለእንድ ከብት ደግሞ 500 ብር የሚከፍሉ ሲሆን፣ ለበግና ፍየል ደግሞ በተናጥል 850 ብር እንደሚከፍሉ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ኩባንያው ይህንን የእንስሳት መድን ሽፋን ማቅረብ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በነበሩት 11 ዓመታት ውስጥ ከ33,000 በላይ አርብቶ አደሮች የመድን ሽፋኑን የገዙ ሲሆን፣ ለገዙት የመድን ሽፋንም 21 ሚሊዮን ብር ዓረቦን ለኢንሹራንስ ኩባንያው መክፈላቸውን ገልጸዋል፡፡

ነገር ግን ኢንሹራንስ ኩባንያው ባለፉት 11 ዓመታት ውስጥ የመድን ሽፋኑን ለገዙ አርብቶ አደሮች 37 ሚሊዮን ብር የጉዳት ካሳ መክፈሉን የኩባንያው የእንስሳት መድን ማናጀር አቶ ጌታነህ አረና ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም ኩባንያው አርብቶ አደሩ ለመድን ሽፋኑ ካወጣው ወጪ በላይ ኩባንያው መክፈሉን አቶ ጌታነህ ገለጸዋል። የእንስሳት መድን በአሁኑ ጊዜ አዋጭ ባይሆንም፣ በጊዜ ሒደት አዋጭ ዘርፍ እንደሚሆን አቶ ጌታነህ ይገልጻሉ።

 

አቶ ዋቆ ጎቡ የዓለም አቀፍ የእንስሳት ምርምር ኢንስቲትዩት የእንስሳት ኢንሹራንስ ፕሮግራም አስተባባሪ ናቸው፡፡

ኢንስቲትዩቱ በኦሮሚያ ኢንሹራንስ ኩባንያ አማካይነት በሦስት አካባቢዎች ማለትም ምዕራብ ሐረርጌ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ቦረና ዞን በድምሩ 17 ሚሊዮን ብር ካሳ መከፈሉን አቶ ዋቆ ተናግረዋል፡፡

አጠቃላይ እስካሁን ለካሳ የወጣው ብር አርብቶ አደሩ ለመድን ሽፋኑ ከከፈለው ጋር ሲነፃፀር ከፍ ያለ መሆኑን ተናግረዋል።

እ.ኤ.አ. 2022 በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን በድርቅ ምክንያት የሞቱ ከብቶች ቁጥር 1.8 ሚሊዮን እንደሚገመት የገለጹት አቶ ዋቆ፣ ይኼ ቁጥር ወደ ገንዘብ ቢለወጥ በበርካታ ቢሊዮን ብር የሚገመት ሀብት ጠፍቷል ማለት ነው ብለዋል።

በአንድ ከብት ስምንት ሺሕ ብር ቢሰላ እንኳን እንደ አገር በርካታ ቢሊዮን ብሮች የሚገመት የአርብቶ አደር ሀብት መጥፋቱን የሚያሳይ ነው ብለዋል። ችግሩ ከመከሰቱ በፊት መንግሥት በእንስሳት መድን ሽፋን ዙሪያ ሰፊ ሥራ ሠርቶ ቢሆን ኖሮ ብዙ ከብቶችን ማዳን ይቻል እንደነበር ጠቁመዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች