Thursday, March 23, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርመንግሥትና ሕዝብ ካልተደማመጡ አገር ከቀውስ ውስጥ አትወጣም!

መንግሥትና ሕዝብ ካልተደማመጡ አገር ከቀውስ ውስጥ አትወጣም!

ቀን:

በፈይሳ ገለታ

እንደ ሠለጠነው ዓለም የዴሞክራሲ ዕሳቤ መንግሥት ማለት ከሕዝብ የወጣ፣ ለሕዝብ የቆመና የሕዝብ አካል ማለት እንጂ ሌላ አካል አይደለም፡፡ ቁጥሩ ይብዛም ይነስም በአንድ አካባቢም ሆነ ማኅበረሰብ መስተጋብር ውስጥ የተገነባ የዜጎች ስብስብ ደግሞ፣ ሕዝብ እንደሚባል ከጥንት እስከ ዛሬ የታወቀ ጉዳይ ነው፡፡ አገር የሚቆመው ደግሞ በሕዝብና መንግሥት ተነሳሽነት፣ ቅንነት፣ አገር ወዳድነትና ትብብር ብቻ ሳይሆን በመደማማጥና ሕግ መከበር ሲችል ነው፡፡

ለዚህም ቢያንስ አብዛኛው ዜጋ የሚግባባበት መንግሥት፣ የፀጥታ መዋቅርና የፍትሕ አካል እንዲሁም የሕግ ማዕቀፍ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህም በላይ አገራዊ መግባባት የተፈጠረባቸው የጋራ እሴቶችን የመንከባከብና የመጠበቅ ብልህነት ነገሩን ይበልጥ በማስፋት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ያግዛል፡፡ በምንገኝበት ሁኔታ ባለፈ ታሪክም ሆነ ነገን በማያማክል አካሄድ ዛሬን ለመራመድ መሞከር ግን፣ መደማማጥን ካለማስፈኑ ባሻገር ከጥቅሙ ጉዳቱ ማመዘኑ አይቀሬ ነው፡፡

አሁን አገራችንን ከገጠማት ቀውስ አንፃር ለመንግሥት ብቻ ሳይሆን ለሕዝቡ (በተለይም ለአሁኑ ትውልድ) ተደማማጥ፣ ተከባበር፣ አብረህም ለመርህ ቁም ማለት የሚበጀው ለዚህ ነው፡፡ “ምክርን ስማ፣ ተግሳጽንም ተቀበል” የሚለውን ጥቅስ መሰንዘርም አስፈላጊና ግድ ነው፡፡ ይህ ጸሐፊው ከሚያውቀው መጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፈ ምሳሌ ምዕራፍ 19 ቁጥር 20 ላይ የሚገኝ ቁልፍ መልዕክት፣ በሌሎች የእምነት ሕግጋትና ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥም ጎልቶ እንደሚታይ ይገመታል፡፡

በመሠረቱ እንኳንስ አንድ የነበረና አሁንም የሆነ ሕዝብና መንግሥት፣ ምክርን የማይሰማ ተግሳጽንም የማይቀበል አንድ ሰውም ቢሆን ዕውቀት አይወድም… ጠቢብም አይሆንም… ፍፃሜውም አያምርም… እጅ በእጅም ሳይቀጣ አይቀርም፡፡ እንጂማ አገርን በሚያፈርስ የእርስ በርስ መጠፋፋት ድርጊት ውስጥ መጠመድ፣ ለሥልጣን ተብሎ አንድ ሕዝብን መነጣጣልና የአገርን ህልውና ለአደጋ ማጋለጥ ቀርቶ ለራስ ወዳድነትና ለስግብግብነትም ስንት የምክር ዓይነት እንዳለ የታወቀ ነው፡፡

እዚህ ላይ ጸሐፊ ሻለቃ ግርማ ለማ (ነፍሱን ይማረውና) ከናይጄሪያውያን ሥነ ጽሑፍ ውስጥ አገኘሁት በሚል በአንድ ወቅት ያወገኛን ታዋቂ የሆነች አንዲት አጭር ታሪክ ማንሳት እሻለሁ፡፡ አሞስ ቱቶላ የተባለ ከእነ ወሌ ሶየንካ የማይተናነስ  ጸሐፊ የጻፋት ነች፡፡ ትንሽ ልቆንጥርላችሁ፡፡

በድሮ ጊዜ ነው አሉ፡፡ አንድ የአዳኝነት ልማድ ያለው ሰውዬ ነበረ፡፡ ባለትዳር ነው፡፡ ሚስቲቱ ማርገዟን የሰሙ የሠፈር ሽማግሌዎች ለአዳኙ ባል ምክር ሊለግሱት ቤቱ ሄዱና መከሩት፡፡ ‹‹አንተ ሰውዬ በእኛ ባህል መሠረት አንድ ሰው ሚስቱ ካረገዘችበት ቀን ጀምሮ እስከተገላገለች ድረስ አደን አይኬድም፡፡ ምክንያቱም በሚስቱ እርግዝና ወቅት አደን ወጥቶ የዱር አራዊትን ከገደለ ከተገደሉት አራዊት መካከል የአንዱ አውሬ ክፉ መንፈስ በልጁ ላይ ያድርና መጥፎና ጨካኝ ልጅ ይሆናል፡፡ የአውሬውን ባህርይ ይወርሳል፡፡ ለያዥ ለገናዥ ያስቸግራል፣ ደብረ በጥብጥ ይሆናል፡፡ ለወላጆቹም ለጐረቤቶቹም የማይመች ለሠፈሩም የማይበጅ ርኩስ ልጅ ይሆናል፡፡ ይህ ዓይነቱ መጥፎ አጋጣሚ እንዳይደርስብህ ባለቤትህ እስክትገላገል ድረስ አደን አትውጣ፡፡ አውሬም አትግደል፣ በኋላ ችግር ይሆንብሃል፣ ተጠንቀቅ፣ ውርድ ከራስ…›› ብለውት ሄዱ፡፡ ሰውዬው ግን፣ ‹‹ይኼ የጥንት ሰዎች አባባል ነው… ተረት ነው… ወሬ ነው… መሠረተ ቢስ ውሸት ነው… የጠላት ወሬ ነው… የምቀኛ ወሬ ነው…›› ምናምን እያለ የሸማግሌዎቹን ምክር ሳይቀበል ቀረና አውሬ መግደሉን ቀጠለበት፡፡

ዘጠኝ ወር የሚባለው ደረሰና ሚስትየዋ ወንድ ልጅ ከእነ ቃጭሉ ወለደች፡፡ ጉዱ ተጀመረ፡፡ ልጁ ገና ከእናቱ ማህፀን እንደወጣ መናገር ጀመረ፡፡ ‹‹ምን ዓይነት አስቀያሚ ወደ ሆነ ዓለም ነው የመጣሁት እባካችሁ… እኔ እኮ ዓለም ሲባል እንደ ገነት ያማረና ምቹ ቦታ ይመስለኝ ነበር፡፡ እንዲህ ከሆነማ ተመልሼ ወደ መጣሁበት ገነት መሄድ አለብኝ እዚህ መቆየት አልችልም…›› አለ፡፡

ከዚያም ስፖንጅና ሳሙና አንስቶ ውኃ ወደ አለበት ሄዶ ደሙን ከላዩ ላይ አጠበና ተመለሰ፡፡ በዙሪያው የነበሩ ሰዎች ሁሉ ደነገጡ፣ ተገረሙ፡፡ ‹‹ምን ጉድ መጣብን…›› እያሉ አንሾካሸኩ፡፡ የልጁ ወሬ ወዲያውኑ በሠፈሩ ነዋሪዎች ዘንድ እንደ ሰደድ እሳት ተዛምቶ አገር ሁሉ ሰማው፡፡ የሕዝብ መዓት ቤቱን ከበበው፡፡ ሰዎች ወሬ ፍለጋ ከያሉበት መጡ፣ የልጁ ጉድም ቀጠለ፡፡

‹‹በጣም እርቦኛል… እዚህ ቤት ምግብ የለም እንዴ?›› ብሎ ወደ ኩሽና ገብቶ ለአራሷና ለጠያቂዎቿ የተዘጋጀ ምግብ አገኘ፡፡ ገንፎና አጥሚት ሳይሆን አይቀርም… ለሃያ ሰዎች የሚበቃ ምግብ ቢሆንም ልጁ ግን ሁሉንም ጠራርጐ ብቻውን በልቶ ጨረሰው፡፡ ተመልካቾች አፋቸውን ይዘው ይመለከታሉ፡፡ የሠፈሩ ሰው እርስ በርሱ ይነጋገራል፡፡ ‹‹ኧረ ይኼስ ምን ዓይነት ፍጡር ነው… የአስፈሪ አውሬ መንፈስ ሳይሰፍርበት አይቀርም… እኛ እንዲህ ያለ ፍጡር ሲወለድ አይተንም አናውቅ… የአማልክቱ ቁጣ ቢሆን ነው እንጂ እንዲህ ዓይነት ልጅ እንዴት ሊወለድ ይችላል…›› ይባባላሉ፡፡ እናቲቱም ግራ ገብቷታል… ደንግጣለች… አፍራለች፡፡

በሰባተኛው ቀን ጠዋት ሽማግሌዎች ተሰባስበው ከልጁ አባት ጋር ተቀምጠዋል፡፡ ዓላማቸው በባህላቸው መሠረት አባትየው ለልጁ የሚያወጣለትን ስም ለመተርጐምና ለማፅደቅ ነበር፡፡ ድንገት ሳያስቡት ያ ጉደኛ ልጅ መጥቶ መሀላቸው ተቀምጦ ተናገራቸው፡፡ ‹‹ለእኔ ስም ለማውጣት ይህንን ያህል ስብሰባ ምን ያደርጋል፣ ለምንስ ትቸገራላችሁ? የእኔ ስም አጃንታላ ነው፡፡ ሌላ ስም አያስፈልገኝም…›› አላቸው፡፡

ለስም ማውጣቱ ሥርዓት ትልቅ ድግስ ተዘጋጅቶ ነበርና የምግቡና የመጠጡ ዘር (ኮላስና የፓልም ወይን ሳይቀር) ዓይነት በዓይነት ቀርቧል፡፡ ሽማግሌዎቹ ሊበሉና ሊጠጡ ሲዘጋጁ አጅሬው አጃንታላ የብረት አንካሴ (ጦር) አነሳና አንደኛው እንግዳ ላይ ሸቀሸቀበት፡፡ ሰዎቹ ተደናገጡ፡፡ አጀንታላ ጦሩን ከሰውዬው ላይ ነቅሎ ሌላኛው ሰው ላይ ሊተክልበት ሲል ሕዝቡ እሪ ብሎ እየተጋፋ አካባቢውን ለቅቆ ሸሸ (ምን ሸሸ ብቻ ፈረጠጠ ጭምር እንጂ)፣ እግሬ አውጭኝ እያለ ተፈተለከ፡፡

አጃንታላ ለዚያ ሁሉ ሰው የተዘጋጀውን ድግስ ብቻውን ድራሹን አጠፋው፡፡ ሸማግሌዎቹ አባትዬውን፣ ‹‹ተው አደን አትውጣ… አውሬ አትግደል ስንለው… ሚስትህ እስክትወልድ ድረስ ይቅርብህ ስንለው አልሰማ ብሎ ይህንን አውሬ ልጅ ወልዶ አስጨረሰን አይደለም? ጉድ እኮ ነው እባካችሁ፣ የጉድም ጉድ…›› እየተባባሉ ከረሙ፡፡

አጃንታላ በበኩሉ አባቱንና እናቱን ጭምር በጥፊ እየመታ (በዘመኑ ካህን በካራቴ እንደሚጥለው ትውልድ መሆኑ ነው)፣ የጐረቤቱን ሰላም እየነሳ ያገኘውን ሰው ሁሉ በብረትና በእንጨት ዱላ እየቀጠቀጠ አካባቢውን እያንቀጠቀጠ ከረመ፡፡ በሁኔታው የተጨነቀችው እናቱ እንደ ምንም ብላ አባብላና አታልላ ሩቅና ጥቅጥቅ ጫካ ውስጥ መንገዱን እንዳያውቀው አድርጋ እያዞረች ወስዳ አንዱ ዛፍ ሥር አስቀምጣው፣ ‹‹ምግብህን ይዤልህ እስክመጣ ድረስ ከዚህ እንዳትንቀሳቀስ…›› ብላ ትታው በሌላ መንገድ ወደ ቤቷ ተመለሰች፡፡

አባትየው ልጁን የት እንዳደረገችው ጠየቃት፡፡ እሷም ይህንን የእግዜር ቁጣ ወስዳ ጫካ እንደጣለችው ነገረችው፡፡ አባትየውም ልጁ የእግዜር ቁጣ አለመሆኑን፣ እሱ የሸማግሌዎቹን ምክር አልሰማ ብሎ የጥንት ሰዎች ተረት ነው ብሎ በማጣጣሉ የተነሳ አውሬ መግደሉን በመቀጠሉ ራሱ ያመጣው ጣጣ መሆኑን ነገራት፡፡

አጃንታላ ጫካ ከገባ በኋላ የሠራቸው ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ታሪኩ ሰፊ ነው፡፡ ለተነሳንበት ዓላማ ያህል ግን ለእኛ ይኸው ይበቃናል፡፡ ዋናው ነገር ምክርን የማይሰማ ተግሳጽንም የማይቀበል ሰውም ሆነ መንግሥት የሚሠራው ሁሉ ውጤቱ ለኅብረተሰብና ለራሱ የማይጠቅም እንደ አጃንታላ ዓይነት ጉደኛና አስፈሪ ይሆናል ለማለት ነው፡፡ ‹‹ምክርን የሚወድ ዕውቀትን ይወዳል፣ ዘለፋን የሚጠላ ግን ደንቆሮ ነው (ምሳሌ 12፡1)›› ይሏል ይህንን ዓይነቱን ነው፡፡

አሁን በአገራችን በተለይ በአንዳንድ ክልሎች እየፋነነ ያለው ሰጋር የውስጠ ፖለቲካ ጥገኛ ትውልድና የአክራሪ ብሔርተኝነት (ሃይማኖተኛም ነይ ባይ ጭምር) መሳከር የሚታየውም ከዚሁ አንፃር ነው፡፡  ወደ አደገኛ መንገድ እየጠመመ ያለው የአንዳንድ ግብዞች አካሄድም ሠርቶና ሕግን ተከትሎ ከመኖር ይልቅ፣ በመንጋና በኃይል ሲሰማራ ሲታይ የአጃንታላን ገጸ ባህሪ የሚያስታውስ ነው፡፡ ተው ሊባልም ይገበዋል፡፡

በዚች አገር ውስጥ ከዘመናት የእርስ በርስ ግጭት፣ ድህነትና ኋላቀርነት በኋላ እንደ ሕዝብ ይነስም ይብዛም በእኩልነት መንፈስ ቀና ተብሎ መራመድ የተጀመረው ካለፉት ሦስት አሥርት ዓመታት ወዲህ ነበር፡፡ የብሔር መካረርና የጥላቻ ውዝግቡ ይበልጥ የተጠነሰሰውም ግን በዚህ ጉራማይሌ  ዘመን መሆኑ ሳይካድ፡፡

በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊና በመሠረተ ልማት መስክ ብቻ ሳይሆን፣ በፖለቲካው መስክ ከእነ ጉድለቱም ቢሆን የሐሳብ ብዝኃነትና ሕገ መንግሥታዊነት ተጀማምሮ እንደነበር ግን አይካድም፡፡ ያንን ጅምር ይበልጥ ያቃናዋል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት  ለውጥ ደግሞ ጭራሽ ጅምሩንም  ወደኋላ ሲመልስና ሲንገዳገድኧ ወይም ወደ አዘቅት ለመግባት ሲንገራገጭ መመልከት ነው ወቅታዊው ኪሳራና ፈተና ብሎ ደፍሮ መናገር ይቻላል፡፡

ምክንያቱም አሁንም በአንድ በኩል ሥልጣንን ለጥቂቶች መጠቀሚያና ለብዝበዛ መሣሪያ ሲያደርጉ የነበሩ ኃይሎች፣ በሌላ በኩል የአክራሪ ብሔርተኝነትና ሕዝቦችን በአንድ ማኖር የማያስችለው አስተሳሳብ ተሸካሚዎች በመዋቅሩ ውስጥም ውጭም ሆነው ተስፋ የተጣለበት የለውጥ ሙከራ ላይ እንቅፋት መሆናቸው እየተደጋጋመ በመታየቱ ነው፡፡ ነባሩ አገረ መንግሥት ተጠናክሮ ስለመቀጠሉም ምልክት አልታይ ብሏል፡፡

የእነዚህ ኃይሎች ለውጥን የመገዳዳር አካሄድ በሰላማዊና በዴሞክራሲያዊ መንገድ እየተከናወነ ቢሆን ብዙም ባልከፋ፣ የባሰው ነገር ግን ሰላምንና አገራዊ ደኅንነትን በማወክ፣ አለመረጋጋትና ቀውስን በማባባስ፣ እንዲሁም መብት በማስከበር ስም በየዕለቱ አዳዲስ የትርምስ አጀንዳ በመቀረፅ አገር እያወኩ ነው፡፡ አንዳንዴም እንደ አጃንታላ የማይነካ በመንካትና ጠንካራውን አገራዊ መስተጋብር በመገዳደር ጭምር ደንቃራ እየፈጠሩ ነው፡፡

እንደ ማሳያም በብሔርና በሃይማኖት ልዩነት ብቻ ንፁኃንን ማሳዳደድና አገር ማሳጣት፣ ብሎም ዋስትና የለሽ ኑሮ ማንገሣቸው ይጠቀሳል፡፡ ይነስም ይብዛም  ወደ ልማት እየገባ ያለን ሰላማዊ ሕዝብ በመግደልና በማፈናቀል፣ በስንት ድካምና መስዋዕትነት የተገነባን የዜጎችና የአገር ሀብትን በማውደምና በመዝረፍና በሕገወጥ ድርጊት በመታጀብ እየተፈጸመ ያለው ድርጊት ጉዳቱ የከፋ፣ የአገር ህልውናንም ለአደጋ የሚጋልጥ እየሆነ ነው፡፡ በቃ ካልተባለም ሕዝብ በእጅጉ እየተማረረ ነው፡፡

ይህ ኢዴሞክራሲያዊና ሕገወጥ ድርጊት ብቻ  ሳይሆን፣ ሕዝብን ከሕዝብ ወደ ማባላትና የብሔርና የሃይማኖት ፍጅት ወደ መቀሰቅስ  የሚሻገር የሽብር ድርጊት ነው፡፡ ትውልድን ለባሰ ኪሳራ የሚዳርገው ይህ አደገኛ ሙከራ ያለ ከልካይ በዚያም በዚህም ሲተወን በመታየቱ፣ የመንግሥትንም ተዓማኒነት እየሸረሸረው ይገኛል፡፡ ከዚህም አልፎ ለዘመናት ተሰናስሎና ተጋምዶ የኖረን ሕዝብ ደም በማቃባት አገርን ወደ ማፍረስ የሚያመራ ፀያፍ ድርጊት እየተንፀባረቀ ነው፡፡

እንግዲህ የእገሌና የእነ እገሌ ሳይባል ይህን ያልተገባ ወንጀል በማውገዝና በመፀየፍ ትውልዱ ወደ ቀልቡ ይመለስ፣ የሚበጀውን ምክርም ይስማ ለማለት የምወደው፡፡ ይህን ትውልድ ይወክሉም አይወክሉም ፖለቲከኞች ይባሉ ጽንፈኛ ኃይሎችም ቢሆኑ ከዚህ የተቃወሰ አካሄድና ለማንም የማይበጅ ድርጊት ይውጡ መባል አለባቸው፡፡ ካልሆነ ግን ያጠፉናል፣ ያለ ጥርጥርም ይበትኑናል፣ እንጠንቀቅ፡፡

የተግሳፁንም ሆነ የምክሩን አስተሳሰብ ለመንግሥትም ቢሆን የምንተወው አይደለም፡፡ በመሠረቱ መንግሥትና የመንግሥት አካላት የአገርና የሕዝብ አደራ የተሸከሙ እንደ መሆናችሁ ጠባያችሁ፣ አሠራራችሁ፣ አካሄዳችሁ፣ አመለካከታችሁ፣ የክስተቶች አያያዛችሁ፣ የችግር አፈታት ዘዴያችሁ፣ ወዘተ ሁሉ በሕግና በሥርዓት የተመራ፣ ከመድልኦና አሻጥር የፀዳ መሆን አለበት፡፡ በአንድ ግለሰብ አይደለም በአንድ ፓርቲ አቅምም እንኳን የሚመራ አገርና ሕዝብ ባለቤቶች እንዳልሆንን መዘንጋት የለበትም፡፡ ታዲያ ማቅማማቱ እስከ መቼ ነው?

እስካሁን በታሪክ እንደታየው መንግሥታዊ አካላት ጉድለት ስለሚታይባችሁ አስተካክሉ፣ መልካሙንም መንገድ ያዙ ሲባሉ እሺ አይሉም ነበር፡፡ ደጋፊም ሆነ ተቃዋሚ ከሚያቀርብላቸው ምክርና ተግሳፅ መካከል ቢያንስ የተሻለውን ሰምተውና መዝነው የማስተካከያ ዕርምጃ ቢወስዱ ጥቅሙ ለራሳቸው መሆኑን መገንዘብም ሲቸግራቸው ነው የቆዩት፡፡ ብልፅግናም ቢሆን ይህንኑ ባህሪ እያሳየ ነው፡፡ እንዲያውም ሕዝብ የጠላውን የመለያየት አዙሪት ሊመላለስበት እያሰበ መሆኑ በሰሞኑ የሃይማኖት አጀንዳ ታይቷል፡፡ ይኼ ታዲያ ምን ይባላል?

ዛሬም እንደ ትናንቱ ሥርዓቱ በማያገባውና ገለልተኝነቱ ጥያቄ ውስጥ በሚወድቅበት ሃይማኖትን በመሰሉ ጉዳዮች መግባቱ ሳያንስ፣ ሕዝቡ ይህ ነገር አይሆንም ብሎ ከዳር እስከ ዳር ያወገዘውን ችግር እንኳን ‹‹የጠላት ወሬ ነው… መሠረተ ቢስ አሉባልታ ነው… ድብቅ ዓላማ ከጀርባው ያዘለ ነው… ምን ያመጣል? የት ይደርሳል?›› የሚል አጉል ግብዝነት ከማሳየት አለመታረሙን ማረጋገጥ ተችሏል፡፡ ይህ ዓይነቱ ወልጋዳ አካሄድ በፍጥነት ካልታረመም ነጋችን ከትናንት ስለመሻሉ ማረጋገጫ የለም፡፡

በዚች አገር ለውጡ ከተጀመረበት ጊዜ ወዲህ ብቻ በግድያ፣ በሴራና በትርምስ ሥልጣን የሚናፍቁ፣ በበቀልና በቁርሾ የናወዙ ኃይሎች ብዙ ደባ ሲፈጽሙና ንፁኃንን ሲያጠቁ ሕዝቡ ትዕግሥትን የመረጠው በመንግሥት ላይ ተስፋ በማሳደሩ ነበር፡፡ ይህ ድርጊት ሲደጋገም ጠበቅ ያለ ዕርምጃ ይወሰድ፣ የሕግ የበላይነት ይከበር አጥፊና ጤነኛው ይለይ ብሎ አገር ወደዱ፣ የሃይማኖት አባቱ፣ አብዛኛው ምሁርና ሕዝቡ ሲናገሩም የከረሙት መንግሥት ሲጠናከር ይታረማል በሚል ተስፋ ነበር፡፡ ችግሩ በመንግሥት በኩልም ድጋፍ እያገኘ ሲመስለው ግን፣ ሥርዓቱ እንደ አጃንታላ እየሆነበት ወዳልሆነ ተስፋ ቆራጭነት እየገባ ይሄዳል፣ መቆራረጡም አይቀሬ ነው፡፡

እንደ ሕዝብና መንግሥት አለመደማመጥና የብልህ አካሄድንም ሆነ ምክርን አለመከተል ግን ጥፋቱ ከፍተኛ ነው፡፡ በተለይ መንግሥት የሁሉምና ሚዛናዊ ካልሆነ በኢፍትሐዊነትም ከተጠረጠረ ችግሩ መባባሱ አይቀርም፡፡ እዚህ ላይ ጥልቅ ምክክር ማድረግና ሁነኛ አማካሪ ሊያገኝም ይገባዋል፡፡ ሁሉም አንድ ዓይነት ሆኖ “ዓይነ ስውርን ዓይነ ስውር ቢመራው ተያይዞ ገደል” ከመግባት የዘለለ ውጤት አይገኝም፡፡ ለዓይናማው ሰው ዓይነ ስውር መሪ (መካሪና አማካሪ) ብንመድብለት ዋጋ የለውም… ምክሪቱም መልካም መሆኗ መረጋገጥ አለባት፡፡ ሐሳብ በመልካም ምክር ትፀናለችና፡፡

ከቅርቡ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስንነሳ ታሪክ እንኳን መማር፣ ቢቻል ጥብቁን ቀኖናም ሆነ የሲኖዶስ ሕግ በዓለማዊው የሥልጣን ክፍፍልና የብሔር አጀንዳ መሥፈርት ለመኮርኮር መሞከር አሳፋሪም፣ ከንቱ ድካምም ሆኖ ነበር የታየው፡፡ በሃይማኖቱ ጉዳይ ውስጥ የጎደለ አሠራር ወይም ተግባር ቢኖር እንኳን መስተካከል ያለበት በራሱ በተቋሙ ሕግና ሥርዓት እንጂ፣ ሕዝብና አማኙን በሚያሳዝንና አገርንም ለአደጋ በሚያጋልጥ አኳኋን አልነበረበትም፡፡ ያውም በሴራ ጭምር በታጀበ ትርክት ድክመትን ለማቃናት ብሎ መነሳትንስ ምን አመጣው? በመሠረቱ በጥላቻ መንፈስ የሚቀርብ ምክር የቱንም ያህል ማር ቢሆን ለተቀባዩ ላይዋጥለት ይችላል፡፡ ለሕዝብ ያውም አማኝ ተብሎ ለሚታመነው ወገን፣ ደግሞ ከቶውንም በእምነቱ ጉዳይ ገብቶ ማንኮር ለመንግሥትም ሆነ ለሌላው እንደማያዋጣ የታወቀ ነው፡፡

የሚበጅም ነገር ቢሆን በዘዴ እያግባቡና እያዋዙ፣ እያለሳለሱ በተቀባዩ ጉሮሮ ልክ እየመጠኑ ካልሰጡት በቀር መልካሚቱ ምክር እሬት ልትሆንበትም ትችላለች፡፡ የታየው ነባራዊ ሁኔታም ይኼ ነበር፡፡ ለቀጣዩም ጊዜ ትምህርት ከተወሰደበት፣ ለሁሉም አሁን በጊዜያዊነት በዕርቅና በድርድር መንፈስ የረገበ መሰለ እንጂ፣ በትዕቢትም ይባል አጉል በማይመለከት ነገር በመደንቀር ተጀምሮ የነበረው ሃይማኖታዊ ሴራ ማንንም የሚበጅ አልነበረም፡፡ በመደመር መንፈስ ጠንካራ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት እንገንባ እየተባለ  በሃይማኖት፣ በብሔር፣ በፖለቲካና በመሰል ልዩነት ሰበብ መወነጃጀሉም ሆነ መጠቃቃቱ ለማንም የሚበጅም አይደለም፡፡ እንደ መንግሥት ለጋራ እሴቶች ዘብ ካልተቆመስ ለማን ሊቆም ነው? ለቀጣዩም የወል እሴቶቻችን አይነኩ፣ ሕዝብ ይደመጥ፣ ይልቁንም ለአገራዊ ሰላምና ደኅንነት ትኩረት ይሰጥ ነው ማሳሰቢያዬ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...