Tuesday, March 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

በውጭ ምንዛሪ እጥረትና በግብዓት እጦት የተፈተነው ዘርፍ

በኢትዮጵያ ለኮንስትራክሽን ግንባታዎች የሚሆኑ ግብዓቶች ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየናረ መጥቷል፡፡ ለግንባታ የሚሆኑ ብረታ ብረት፣ ሲሚንቶ ሌሎች መሰል ምርቶችን የሚያመርቱ አንዳንድ ተቋሞች ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ምርቶቻቸውን ማቆማቸው የኮንስትራክሽን ግብዓቶች ዋጋ ለመናር ምክንያት እንደሆነ ብዙኃኖች ያምኑበታል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ መንግሥት ለዘርፉ ትኩረት አለመስጠቱና የችግሩን አሳሳቢነት ተረድቶ ቁርጠኝነት የተሞላበት መፍትሔ አለማበጀቱ ኢንዱስትሪው እንዲጎዳ አድርጎታል የሚሉም አልታጡም፡፡ በተመሳሳይ በአሁኑ ወቅት አገሪቱ ላይ እየታየ ያለው የውጭ ምንዛሪ እጥረትና የግብዓቶች መወደድ በዘርፉ የተሰማሩ ተዋናዮችን እየፈተነ ይገኛል፡፡ ፈተና ውስጥ ከገቡት መካከል ሲሳይ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ይገኝበታል፡፡ ሲሳይ ኢንቨስትመንት ግሩፕም የዋልያ ብረታ ብረቶችን ጨምሮ በሥሩ ሌሎች ተቋሞችን እያንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ አቶ ሲሳይ ተስፋዬ የዋልያ ብረታ ብረትና የኢንቨስትመንት ግሩፕ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ናቸው፡፡ የድርጅቱን ሥራ በተመለከተ ተመስገን ተጋፋው አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡– የዋልያ ብረታ ብረት ኢንዱስትሪ መቼ ተመሠረተ?

አቶ ሲሳይ፡የዋልያ ብረታ ብረት ኢንዱስትሪ በ1990 ዓ.ም. የተቋቋመ ድርጅት ነው፡፡ ድርጅቱም በ53 ሺሕ ካሬ ሜትር ላይ የተቋቋመ ሲሆን የጥሬ ዕቃ ፍላጎቱን ከቻይና፣ ከዩክሬን፣ ከህንድና ከሩሲያ በማስመጣት የብረታ ብረት ውጤቶችን በማምረት ለገበያ እያቀረበ ይገኛል፡፡ በወቅቱም በዓመት 800 ሺሕ ቶን የማምረት አቅም ስለነበረው በኢትዮጵያ በኮንስትራክሽን ዘርፍ ላይ ለተሰማሩ ተቋማት ትልቅ ዕፎይታን ፈጥሯል፡፡ ድርጅቱም የተለያዩ ውፍረትና ስፋት ያላቸውን የቱቦላሬ (ኤልቲዜድ) እንዲሁም ልሙጥና ሻካራ ላሜራዎችን በዓይነትና በጥራት በማምረት ለገበያ እያቀረበ ይገኛል፡፡ ወደላይም ሰባት ወለል ቁመት ላላቸው ሕንፃዎች ጥራት ባለው መልኩ በማምረት ግብዓቶችን እያቀረበ ይገኛል፡፡ ፈርኒቸር ለሚሠሩ ሆኑ በኮንስትራክሽን ዘርፍ ለተሰማሩ ተቋሞች ከትንሽ እስከ ትልልቅ ብረታ ብረቶችን ማቅረብ ችለናል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ድርጅቱ ዋልያ የተሰኘ የቡና ማቀነባበሪያና መልቀሚያ ተቋም በማቋቋም በጥራት የተቀነባበሩ ቡናዎችን በማምረት ለአሜሪካና ለአውሮፓ ገበያ በማቅረብ ተደራሽ እያደረገ ይገኛል፡፡ በተጨማሪ በብረት ቀለም፣ በኮንስትራክሽን፣ በሪል ስቴት ግንባታና በሆቴል ዘርፍ ላይ ተሰማርቶ ሰፊ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል፡፡ ይሁን እንጂ ድርጅታችን በአሁን ወቅት የብረታ ብረት ውጤቶችን ማምረት ከሚገባው በታች እያመረተ በመሆኑ በሥራችን ላይ ትልቅ እንቅፋት ሆኖብናል፡፡ ድርጅቱም የብረታ ብረት ውጤቶችን ከዚህ ቀደም ሲያመርትበት የነበረው ምርት ዝቅ ሲል የቻለው አገሪቱ ላይ የሚታየው የውጭ ምንዛሪ እጥረትና የግብዓት ችግር በመከሰቱ የተነሳ መሆኑን ድርጅታችን ሊታዘብ ችሏል፡፡ ድርጅቱም አሁን ላይ በሙሉ አቅሙ ማምረት ቢችልም እንኳን በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ማምረት አቁሟል ቢባል ይሻላል፡፡ ይህም የሆነበት ዋነኛ ምክንያት መንግሥት ለኢንዱስትሪው ትኩረት ባለመስጠቱ የተነሳ እንደሆነ ይታመናል፡፡

ሪፖርተር፡– ድርጅታችሁ የተለያዩ አገልግሎቶችን እየሰጠ ይገኛል፣ በሥራችሁ ላይ ምን ዓይነት ተግዳሮቶች ገጥሟችኋል?

አቶ ሲሳይ፡- ድርጅቱ በዋናነት የሚሠራው የብረታ ብረት ውጤቶችን በማምረት በኢትዮጵያ የሚታየውን የገበያ ሁኔታ በከፍተኛ ደረጃ ዕልባት በመስጠት ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ በተለይም ለአዲስ አበባ ቤቶች ኮርፖሬሽን፣ ለኮንትራክተሮች፣ ለፋብሪካዎችና ለሌሎች ተቋሞች ምርቶቻችንን በማቅረብ ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን ሠርተናል፡፡ ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አገሪቱ ላይ በሚታየው ነባራዊ ሁኔታና ለብረታ ብረት ምርት የሚሆኑ ግብዓቶችን ማጣታችን ሥራችን ላይ ከፍተኛ የሆነ ችግር ፈጥሮብናል፡፡ በዚህም የተነሳ በተለያየ ዘርፍ ላይ ተሰማርተው የሚሠሩ የኮንስትራክሽን ድርጅቶች ሥራቸው ላይ እንቅፋት ገጥሟቸው ከሥራ ገበታቸው ሲወጡ ማየት ችለናል፡፡ በዚሁ ከቀጠለ የእኛም ድርጅት ሙሉ ለሙሉ ሥራውን የሚያቆም ይሆናል፡፡ ይህም መንግሥት ምን ያህል ዘርፉ ላይ ያሉትን ተግዳሮቶች መፈተሽ እንዳለበት ያሳያል፡፡ ከዚህ ቀደም ድርጅቱ በዓመት ከስምንት መቶ ሺሕ እስከ አንድ ሚሊዮን ቶን የማምረት አቅም ነበረው፡፡ አሁን ግን ነገሩ የተገላቢጦሽ ሆኖ ተቋሙ የማምረት አቅሙ በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሶ ይገኛል፡፡ ይኼም በሥራችን ላይ ትልቅ ችግር ፈጥሮብናል፡፡ በተለይ በአገሪቱ በተከሰተው የውጭ ምንዛሪ እጥረት የተነሳ በርካታ የኢንዱስትሪው ተዋናዮች እየተፈተኑ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በሌላ መልኩ ደግሞ ከዚህ ሥራ ውጪ የተለያዩ ሥራዎችን ለመሥራት ፈልገን መንግሥትን ቦታ ልናስፈቅድ በምንሯሯጥበት ጊዜ የመንግሥት ተቋማት ነገሩን እያንጓተቱብን ሥራችንን በአግባቡ እንዳንሠራ አድርገውናል፡፡ ይኼም በተለያዩ መስኮች ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶች ሁል ጊዜ ምሬታቸውን ሲያሰሙ መመልከት ችለናል፡፡ ይሁን እንጂ ድርጅታችን እነዚህን ሁሉ ችግሮች ወደ ኋላ በመተው ውጤታማ ሥራ ለመሥራት የዕለት ተዕለት ሥራውን እያከናወነ ይገኛል፡፡

ሪፖርተር፡– ድርጅታችሁ ከብረታ ብረት ምርት ውጪ የተለያዩ ምርቶችን በማምረት በአገር ውስጥም ሆነ ውጭ አገር ለሚገኙ ኩባንያዎች ምርቶችን ያቀርባል? ምርታችሁ ምን ያህል ተፈላጊነትን አግኝቷል?

አቶ ሲሳይ፡- እንዳልከው ድርጅታችን ደረጃውን በጠበቀ መልኩ የተለያዩ ምርቶችን በማምረት አገር ውስጥ ለሚገኙ ተቋሞች ሆነ ውጭ አገር ላሉ ኩባንያዎች በማቅረብ ተፈላጊነቱን አሳይቷል፡፡ በተለይም የብረታ ብረት ምርቶችን በማምረት ቀደምት የሚባል በመሆኑ በርካታ ደንበኞችን መሳብ ችለናል፡፡ ሌላው ደግሞ በዋልያ ብረታ ብረት ሥር ቤስት ቀለምና ዋልያ ቡና፣ ኤስኤች ማኑፋክቸሪንግ፣ ቤስት ፕላስቲክ ኢንዱስትሪና ሌሎች ድርጅቶች መኖራቸው ያሉብንን ችግሮች እንድንፈታ አድርጎናል፡፡ ተቋሞች ከእኛ ድርጅቶች ጥሬ ዕቃዎችን በመግዛት ውጤታማ ሥራዎችን ሲሠሩ አይተናል፡፡ በተለይ በ2010 ዓ.ም. በ5‚000 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈው ዋልያ የቡና ማቀነባበሪያና መልቀሚያ ድርጅታችን በጥራት የተቀነባበሩ ቡናዎች በማምረት ለአሜሪካና ለአውሮፓ አገሮች ማቅረብ ችለናል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ አገር ውስጥ ለሚገኙ የተለያዩ ተቋሞች ምርቶችን፣ በማቅረብ ውጤታማ ሥራ እየሠራ ይገኛል፡፡ በቀጣይም በዘርፉ ላይ ትኩረት በመስጠት ውጤታማ ሥራ ለመሥራት ዕቅድ ይዘን እየተንቀሳቀስን ይገኛል፡፡  

ሪፖርተር፡– በውጭ ምንዛሪ እጥረትና በግብዓት እጦት ምክንያት ተቋሙ ሊፈተን ችሏል፡፡ ይህንን ችግር ለመቅረፍ ምን ዓይነት አሠራር ዘርግታችኋል?

አቶ ሲሳይ፡ዋልያ ብረታ ብረትን ጨምሮ በሥሩ ያሉ አብዛኛዎቹ ተቋሞች በውጭ ምንዛሪ እጥረትና በግብዓት ችግር ምክንያት ከፍተኛ የሆነ ማጥ ውስጥ ገብተዋል፡፡ እነዚህንም ችግሮች ለመፍታት ቡና ወደ ውጭ አገር ኤክስፖርት ማድረግን እንደ አንድ አማራጭ ይዘናል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ከአገር ውስጥ ዕቃዎችን የሚጠቀሙ ኢንዱስትሪዎችን ለመክፈት ዕቅድ ይዘን እየተንቀሳቀስን ይገኛል፡፡ ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ ጥናት እያደረግን ይገኛል፡፡ ይኼም ተፈጻሚ መሆን ከቻለ ዘርፉ ላይ ውጤታማ የሆነ ሥራ መሥራት ይቻላል፡፡ በሌላ በኩል በሲሳይ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ሥር የሚገኙ ተቋሞችን በፐብሊክ ሼር ውስጥ እንዲገቡ ለማድረግ ዕቅድ ይዘናል፡፡ ይህንንም ተፈጻሚ ለማድረግ ባለሙያዎችን መድበን እየተንቀሳቀስን ነው፡፡

ሪፖርተር፡– በቀጣይስ ምን ለመሥራት አስባችኋል?

አቶ ሲሳይ፡- በቀጣይ ድርጅታችን የተለያዩ አገልግሎቶችን ለመስጠት ዕቅድ ይዟል፡፡ በአዲስ አበባ ሆቴልና አፓርታማዎችን ገንብተን ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እንቅስቃሴ ጀምረናል፡፡ ሌላው በኦሮሚያ ክልልም የተለያዩ ኢንዱስትሪዎችን ለመገንባት መሬት ጠይቀናል፡፡ ይህንንም ማግኘት ከቻልን የኢንዱስትሪው ዘርፉን ሰፋ ባለ መልኩ ለማቋቋም ዕቅድ ይዘናል፡፡ እነዚህ ሁሉ ነገሮች ተፈጻሚ ማድረግ ከተቻለ ዘርፉ ላይ ውጤታማ ነገሮችን ማየት ይቻላል፡፡ በሌላ በኩል በተለያዩ አካባቢዎች ትምህርት ቤቶችን፣ የገበያ ማዕከል፣ ሌሎች ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተቋሞችን በመገንባት ውጤታማ ሥራ ሠርተናል፡፡ በቀጣይም እንደነዚህ ዓይነት ሥራዎችን ለመተግበር ዕቅድ ይዘናል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

የኦሮሞን ሕዝብ ታሪክ አልባ በማድረግ ታሪክ አይሠራም

በኢተፋ ቀጀላ​​  ከዛሬ ሃምሳ ዓመት ወዲህ ከተፈጠሩት የኦሮሞ ድርጅቶች መካከል ከኢጭአት በስተቀር፣...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...

ጉራጌን በክላስተር ለመጨፍለቅ የሚደረገውን ጥረት እንደሚቃወም ጎጎት ፓርቲ አስታወቀ

ለጉራጌ ሕዝብ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር እንደሚታገል የሚናገረው አዲሱ...

‹‹ኢኮኖሚው ላይ የሚታዩ ውጫዊ ጫናዎችን ለመቀልበስ የፖሊሲ ሪፎርሞች ያስፈልጋሉ›› ዓለም ባንክ

በዓለም ደረጃ ከተፈጠረው የኢኮኖሚ አለመረጋጋት ጋር በተገናኘ፣ በኢትዮጵያ ውጫዊ...