Friday, March 31, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየኅብረተሰብ ጤና ሥጋት ሆኖ የቀጠለው ኮቪድ-19

የኅብረተሰብ ጤና ሥጋት ሆኖ የቀጠለው ኮቪድ-19

ቀን:

  • በኢትዮጵያ በመደበኛው የጤና ሥርዓት ውስጥ ተካቷል

ኮቪድ-19 ወረርሽኝ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተከሰተ አራተኛ ዓመቱን የያዘበት ዓመት ቢሆንም፣ አሁንም የዓለም አቀፍ የኅብረተሰብ ጤና ሥጋት ሆኖ መቀጠሉን፣ ወረርሽኙ ግን በዚህ ዓመት ሊያበቃ መቃረቡን የዓለም የጤና ድርጅት ዋና አስታውቋል፡፡

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ቴድሮስ አድሃኖም (ዶ/ር) እምነት፣ በቀጣይ ዓመት በዚህ ወረርሽኝ ታመው ወደ ሆስፒታል የሚገቡ ታካሚዎችና በዚህም ሳቢያ የሚከሰተው የሞት መጠን ይቀንሳል፡፡ ጤና ተቋማትም ወረርሽኙን በተቀናጀና ቀጣይነት ባለው የጤና ሥርዓት በማካተት የሕክምና አገልግሎት ይሰጣሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ነው የተናገሩት፡፡

የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትም የዓለም ጤና ድርጅትን አቅጣጫ በመከተልና የቫይረሱን ተለዋዋጭ ባህሪ ግምት ውስጥ በማስገባት፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን የመከላከልና የመቆጣጠር ሥራዎችን ከመደበኛው የኅብረተሰብ ጤና ቁጥጥርና የጤና አገልግሎት ሥርዓት ጋር የሚያቀናጅ ዕቅድ አዘጋጅቶ ለተግባራዊነቱ ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴ በማከናወን ላይ ነው፡፡

እስካሁን በተከናወነው ሥራ ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከዘንድሮ በጀት ዓመት መጀመርያ አንስቶ ራሱን የቻለ ድንገተኛና አስቸኳይ (ኤመርጀንሲ) ከመሆን ተላቅቆ ወደ መደበኛ የኅብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥርና የጤና አገልግሎት አሠራር ሥርዓት ውስጥ መካተቱንና በዚህም አመርቂ ውጤቶች መመዝገባቸውን ነው ኢንስቲትዩቱ ያመለከተው፡፡

የኢንስቲትዩቱ የቅድመ ማስጠንቀቂያና የመረጃ ሥርዓት አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ሻምበል ሀቤቤ በተለይ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ከተመዘገቡትም ውጤቶች መካከል ከአሁን በፊት በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ላይ ብቻ ይሠሩ የነበሩት የጤና ተቋማት ፕሮቶኮሉን በጠበቀ መልኩ መደበኛውንም የጤና አገልግሎት ጎን ለጎን እንዲሰጡ መደረጉ ይገኝበታል፡፡

ከዚህም ሌላ ከአሁን በፊት ተደራሽ ያልሆኑ የጤና አገልግሎቶች ተደራሽ መሆናቸው፣ ኮቪድ-19 ከቁጥጥር ውጪ እንዳይሆን መደረጉ፣ ከአሁን በፊት በአንዳንድ ከፍተኛ የጤና ተቋማትና ማዕከላት ውስጥ ብቻ ይከናወን የነበረው የኮቪድ-19 የላቦራቶሪ ምርመራ በርቀት ላይ ያሉ ጤና ጣቢያዎች ሁሉ ፈጣን የመመርመርያ ኪቶችን በመውሰድ ራሳቸውን ችለው እንዲመረምሩ መደረጉ ተጠቃሽ ነጥቦች ናቸው ብለዋል፡፡  

ታይፈስ፣ ኢንፍሎንዛና ሌሎችም የተለያዩ ሕመሞች ያደረበት አንድ ታካሚ በአቅራቢያው በሚገኝ የጤና ተቋም ቀርቦ ተገቢውን አገልግሎት እንደሚያገኘው ሁሉ፣ ኮቪድ-19 ወረርሽኝ የተጠቃ ማንኛውም ሰው በአቅራቢያው በሚገኘው ተቋም የምርመራ፣ የሕክምናና የክትባት አገልግሎት የሚያገኝበት ሁኔታ ተመቻችቷል፡፡

ለሕሙማን የሚያገለግሉ የሕክምና ማሽኖች በማቅረብ ተደራሽ እንዲሆኑ፣ ለታችኞቹ ጤና ተቋማት የበጀት ድጋፍ መደረጉና ተገቢ የሆነ የአሠራር መመርያ መውረዱ፣ ሁሉም የጤና ተቋማት ለኮቪድ-19 ምርመራ በሚያስፈልጉ ዘመናዊና ቴክኖሎጂ ባፈራቸው የሕክምና መሣሪያዎች መደራጀታቸው፣ የሕክምና ባለሙያዎችም ተከታታይ ሥልጠና መውሰዳቸውንም ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

የማኅበረሰቡ ግንዛቤ ማነስ ግን እንደ ችግር መታየቱን፣ ይህም ማለት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምልክቶች ሲታዩበት ቶሎ ብሎ ወደ ጤና ተቋም የመሄድ ፍላጎቱና ተነሳሽነት የሌለው መሆኑን እንደተደረሰበት ነው ያመለከቱት፡፡

እንደ ሻምበል አባባል የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወደ መደበኛው የኅብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥርና የጤና አገልግሎት ሥርዓት ውስጥ እንዲገባ የተደረገው በዓለም ጤና ድርጅት መመርያ መሠረት መሆኑን ገልጸው ከፍ ብሎ የተጠቀሱት ውጤቶች መመዝገባቸው ሊረጋገጥ የቻለው ደግሞ የስድስት ወራት ዕቅድ አፈጻጸም በተገመገመበት ወቅት ነው፡፡

ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ቀንሷል? ወይስ ጠፍቷል? ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ አቶ ሻምበል ሲመልሱ፣ ኮቪድ-19 ወረርሽኝ አልጠፋም፣ በአጭር ጊዜ ይጠፋል ተብሎም አይታሰብም፡፡ ባህሪውን በመለዋወጥ የዓለም ጤና ሥጋት ሆኖ ይቀጥላል፡፡ ለዚህም በቅርቡ ቻይና ውስጥ በሚሊዮን በሚቆጠሩ ሰዎች ላይ ጉዳት ማስከተሉ በአጭር ጊዜ የማይጠፋ ለመሆኑ አንዱ ማሳያ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ከዚህ ውጪ ግን በአሁኑ ጊዜ ያለው ሁኔታ ሲገመገም እንደቀነሰ፣ በዚህም የተነሳ የፅኑ ሕሙማን ክፍሎች ባዶ ሆነው መታየታቸው አንዱ ማሳያ መሆኑን፣ ማኅበረሰቡም በዚህ ሳይዘናጋ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማስክ ከማድረግ፣ ርቀቱን ከመጠበቅ፣ እጆቹን በሳሙናና በውኃ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ከመታጠብና ሌሎች የመከላከያ ሥራዎችን ከማከናወን እንዳይዘናጋ አሳስበዋል፡፡

የኢንስቲትዩቱ መረጃ እንደሚያሳየው፣ በኢትዮጵያ ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ እስከ የካቲት 13 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ ከ5.4 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የላቦራቶሪ ምርመራ እንደተደረገላቸው፣ ከእነዚህም መካከል 499,872 ሰዎች ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል፡፡ ከእነዚህ መካከልም ሕይወታቸው ያለፈው 7,572 ሲሆኑ፣ ያገገሙት 487,136 ናቸው፡፡ የተከተቡት ቁጥርም 44.3 ሚሊዮን ያህል ደርሷል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተወግዘው የነበሩ ሦስቱ ሊቀጳጳሳትና 20 ተሿሚ ኤጲስ ቆጶሳት ውግዘት ተነሳ

_ቀሪዎቹ ሦስት ህገወጥ ተሿሚዎች የመጨረሻ እድል ተሰጥቷቸዋል ​ ጥር 14...

በሕወሓት አመራሮች ላይ ተመስርቶና በሂደት ላይ የነበረው የወንጀል ክስ ተቋረጠ

በቀድሞ የትግራይ ክልል ፕሬዚደንት ደብረጽዮን ገብረሚካኤ,(ዶ/ር)ና ባለፈው ሳምንት በተሾሙት...

[የምክር ቤቱ አባል ላቀረቡት ጥያቄ በተሰጣቸው ምላሽ አቤቱታቸውን ለክቡር ሚኒስትሩ እያቀረቡ ነው]

ክቡር ሚኒስትር እየሆነ ያለው ነገር ትክክል ነው? ምነው? ምክር ቤቱም ሆነ...

የጉራጌ የክልልነት ጥያቄ ትኩሳት

ቅዳሜ መጋቢት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. በጉራጌ ዞን ወልቂጤ...