በአውስትራሊያ ባቱረስት ከተማ በተካሄደው የዓለም አገር አቋራጭ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ የተሳተፈው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን የካቲት 14 ቀን 2015 ዓ.ም. ንጋት ላይ አዲስ አበባ ገብቷል፡፡
ረዥም የጉዞ ሰዓት ማሳለፉ የተነገረው ብሔራዊ ቡድኑ በተለያዩ ርቀቶች ላይ የተሳተፉ አትሌቶችን ይዞ ወደ ሥፍራው ከማቅናቱ ጀምሮ በርካታ ችግሮች እንደገጠሙት ተነግሯል፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በዕለቱ ለብሔራዊ ቡድኑ የአቀባበልና የዕውቅና የሽልማት መርሐ ግብር ሲያከናውን ብሔራዊ ቡድኑ በአውስትራሊያ ስለነበረው ቆይታ ማብራሪያ ቀርቧል፡፡
ቡድኑ በአዲስ አበባና በአውስትራሊያ የነበረውን ቆይታ በተመለከተ የቡድኑ የቴክኒክ መሪ አቶ አስፋው ዳኜ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፣ ብሔራዊ ቡድኑ ከመነሻ ጀምሮ እስከ መመለሻው ድረስ ያልተገመቱ ፈተናዎች እንደገጠሙት አብራርተዋል፡፡
እንደ አቶ አስፋው ማብራሪያ ከሆነ፣ ብሔራዊ ቡድኑ ሱሉልታ በተደረገው የጃንሜዳ ኢንተርናሽናል አገር አቋራጭ ውድድር 34 አትሌቶችና ስምንት አሠልጣኞች ተመርጠው ዝግጅት ሲያደርጉ ነበር፡፡
በዚህም መሠረት ከጥር 3 ቀን 2015 ዓ.ም. አትሌቶቹ በሆቴል እንዲያርፉ ከተደረገ በኋላ፣ በጠዋትና ማታ መርሐ ግብር በሱሉልታ፣ ሰንዳፋ፣ እንጦጦ፣ በቃሊቲና በኮተቤ በቂ ልምምድ ሲያደርጉ እንደነበር አቶ ዳኜ አብራርተዋል፡፡
ምንም እንኳን ቡድኑ በቂ ዝግጅት ማድረጉ ቢገለጽም፣ ከልዑካን ቡድኑ መካከል የተወሰኑ አትሌቶች ቪዛ መከልከል፣ እንዲሁም ከ10፡00 ሰዓት ያላነሰ በኳታር ኤርፖርት መቆየታቸውን ከኳታር አውስትራሊያ ለማቅናትም 15 ሰዓታት መውሰዱ ጉዞውን አስካሚ እንዳደረገው ተገልጿል፡፡
በአጠቃላይ ከ24 ሰዓታት ያላነሰ ጉዞ አድርጎ የተጓዘው ብሔራዊ ቡድኑ፣ አውስትራሊያ ከገባ በኋላ ውድድር ወደሚሰናዳበት ባቱረስት ከተማ ለመድረስ አምስት ሰዓታት በአውቶብስ መጓዙም ተገልጿል፡፡ ባቱረስት ከተማ የደረሰው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሞቃታማ የአየር ሁኔታ እንደገጠመውም ተጠቁሟል፡፡
እንደ አቶ አስፋው አስተያየት ከሆነ የመወዳደሪያ ሥፍራው ከዚህ ቀደም ከነበሩ የአገር አቋራጭ ሻምፒዮናዎች የተለየ እንደነበር ያስረዳሉ፡፡
የቴክኒክ ቡድን መሪው ሲያብራሩም፣ የመሰናክሉ ሥፍራ እስከ 60 ሜትር ከፍታ ያለው፣ ዳገታማ የሆነና ጭቃማ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በአገር አቋራጭ ውድድር በተለያዩ ሰው ሠራሽ መሰናክሎች ያሉት መሆኑ ቢታወቅም፣ ዳገታማ መሆኑ ግን እጅግ ፈታኝ የነበረና ከዚህ ቀደም በነበሩት የአገር አቋራጭ ሻምፒዮናዎች ያልተለመደ እንደነበር አስረድተዋል፡፡
ስለአውስትራሊያ የአገር አቋራጭ ውድድር ዝግጅትን በተመለከተ አስተያየታቸውን ለሪፖርተር የሰጡት የብሔራዊ ቡድኑ አሠልጣኞች አጠቃላይ የውድድር ሥፍራው ለአዘጋጇ አገር ብሔራዊ ቡድን እንዲመች ተደርጎ መሰናዳቱን ያነሳሉ፡፡
እንደ አሠልጣኞቹ አስተያየት ከሆነ አዘጋጇ አውስትራሊያ ሻምፒዮናውን ለማሰናዳት ኃላፊነት ከተረከበች ጀምሮ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ሻምፒዮናው ለሁለት ጊዜያት መራዘሙን ተከትሎ፣ በቂ ዝግጅት ስታደርግ ቆይታለች፡፡ በዚህም ውድድር ሥፍራው ለብሔራዊ ቡድኑ በሚመች መልኩ ከመሰናዳቱም በላይ፣ ሻምፒዮናውን በበላይነት ለማጠናቀቅ አቅዳ ስትሠራ መክረሟን ይጠቅሳሉ፡፡
በሌላ በኩል የውድድር ሥፍራው ባልተገመተና ባልተጠበቀ ሞቃታማና ነፋሻማ አየር የታጀበ መሆኑ፣ አትሌቶችን እንደፈተነ የሕክምና ባለሙያዎች ስለሁኔታው ትዝብታቸውን ለሪፖርተር አካፍለዋል፡፡
በተለይ መነጋገሪያ ሆኖ የከረመው የለተሰንበት ግደይ ጉዳይ ይጠቀሳል፡፡ የ5,000 ሜትር፣ 10 ሺሕ ሜትር፣ 10 ኪሎ ሜትርና የግማሽ ማራቶን የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤቷ ለተሰንበት፣ በቂ ዝግጅት ማድረጓና የሱሉልታው አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ላይ የነበራት ድንቅ ብቃት አጨራረስ ምስክር ነበር፡፡
በርካታ የግል ውድድሮችን ወደ ጎን ጥላ በአገር አቋራጭ ኢትዮጵያን ወክላ ወደ አውስትራሊያ ያመራችው ለተሰንበት፣ ጥሩ የልምምድ ጊዜ የነበራት ሲሆን፣ የአዋቂ ሴቶች 10 ኪሎ ሜትር ውድድርን እየመራች ለማጠናቀቅ በቅርብ ርቀት ላይ እያለች ተዝለፍልፋ በመውደቋ ውድድሩን መቀጠል አልቻለችም ነበር፡፡ በአንፃሩ በአሠልጣኟ ድጋፍ አማካይነት ወደ ውድድሩ ብትመለስም ውጤቷ ተሰርዟል፡፡
የውድድሩ ውጤቱ ውድቅ እንዲሆን ያደረገው አሠልጣኟ አትሌቷን በወደቀችበት ቅጽበት ለማንሳት ለማንሳት ድጋፍ መስጠቱ ነበር፡፡
ስለሁኔታው አስተያየቱን ለሪፖርተር የሰጠው የለተሰንበት አሠልጣኝ አቶ ኃይለ ኢያሱ አትሌቷን ዳግም ወደ ሩጫው እንድትመለስ ማድረጉ ውጤቱን እንደሚያሰርዝ ቢረዳም፣ አትሌቷ ያጋጠማት ችግር ምን እንደሆነ ለማወቅና አፋጣኝ ድጋፍ ለማድረግ እንዲያስችል በማሰብ እንደሆነ አስረድቷል፡፡
አሠልጣኙ ለተሰንበት በቂ አቅም እንደነበራት ገልጾ፣ የውድድር ሥፍራው አመቺ አለመሆኑን እንደ ምክንያት እንደነበር አስረድቷል፡፡ ከዚህም ባሻገር በውድድሩ ሥፍራ ከፍተኛ ሙቀት መኖሩና አትሌቶቹ ሙቀቱን መቋቋም እንደተሳናቸው ገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቶች በሞቃታማ ውድድሮች ላይ ሲካፈሉ በሌሎች ተፎካካሪ አገሮች የበላይነት እንደሚወሰድባቸው ይነገራል፡፡
በአንፃሩ የኢትዮጵያ ተቀናቃኝ የሆነችው ኬንያ አጋጣሚውን ስትጠቀመው ይስተዋላል፡፡ ለዚህም ምክንያቱ የኬንያ አትሌቶች በሞቃታማ ቦታ ልምምድ የማድረግ ሰፊ ዕድል እንዳላቸው ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡
በሻምፒዮናው ኢትዮጵያ በሁለት ወርቅ፣ በሰባት ብር፣ እንዲሁም በአንድ ነሐስ፣ በአጠቃላይ በ10 ሜዳልያዎች፣ ከዓለም ኬንያን ተከትላ ሁለተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች፡፡ ኬንያ በስድስት ወርቅ፣ በሁለት ብርና በሁለት የነሐስ በአጠቃላይ በአሥር ሜዳሊያዎች በአንደኝነት ስታጠናቅቅ፣ ዑጋንዳ በአንድ ወርቅና ሦስት ነሐስ አጠቃላይ በአራት ሜዳሊያዎች ሦስተኛ ደረጃ ይዛ ማጠናቀቅ ችላለች፡፡
ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በሻምፒዮናው ለተሳተፉ አትሌቶች እንደ ውጤታቸው ሽልማት ያበረከተ ሲሆን፣ ለወርቅ 45,000 ብር፣ ለብር 30,000፣ ለነሐስ 15,000፣ ለዲፕሎማ 10,000 ብር እንዲሁም ለተሳትፎ 5,000 ብር ሽልማት አበርክቷል፡፡