Monday, June 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊበዋግኸምራ ብሔረሰብ ዞን ሁለት ወረዳዎች 68 ሺሕ ነዋሪዎች ለኩፍኝና ለወባ በሽታ መጋለጣቸው...

በዋግኸምራ ብሔረሰብ ዞን ሁለት ወረዳዎች 68 ሺሕ ነዋሪዎች ለኩፍኝና ለወባ በሽታ መጋለጣቸው ተነገረ

ቀን:

  • በምግብና በመድኃኒት ዕጦት 578 ሰዎች ሞተዋል ተብሏል

በአማራ ክልል ዋግኸምራ ብሔረሰብ ዞን በሕወሓት ቁጥጥር ሥር ናቸው በተባሉት አበርገሌና በፃግብጅ ወረዳዎች የሚገኙ 68 ሺሕ ነዋሪዎች ለኩፍኝ፣ ለወባና ለሌሎች ተላላፊ በሽታዎች መጋለጣቸውን የወረዳ አስተዳዳሪዎቹ አስታወቁ፡፡

የወረዳ አስተዳዳሪዎቹ ለሪፖርተር በገለጹት መሠረት፣ በነሐሴ ወር 2014 ዓ.ም. ሕወሓት ለሦስተኛ ጊዜ ከቀሰቀሰው ጦርነት ወዲህ በሁለቱ ወረዳዎች ብቻ በመድኃኒትና በምግብ ዕጦት 578 ሰዎች ሞተዋል፡፡

በሕወሓት ቁጥጥር ሥር ናቸው በተባሉት በፃግብጅና በአበርገሌ ወረዳዎች ኩፍኝ፣ ወባና ሌሎች ተላላፊ በሽታዎች (ትክትክና የዕብድ ውሻ በሽታ) በመከሰታቸው፣ ነዋሪዎች እየሞቱ መሆናቸውን የፃግብጅ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ንጉሡ ደሳለኝ ተናግረዋል፡፡

- Advertisement -

ሕይወታቸው አልፏል ከተባሉት 578 ሰዎች መካከል 378 የሚሆኑት በፃግብጅ ወረዳ ብቻ በመድኃኒትና በምግብ ዕጦት ሳቢያ መሞታቸውን፣ የወረዳው አስተዳዳሪ አስረድተዋል፡፡

በወሊድ ችግር፣ በመድኃኒት እጥረትና በረሃብ 378 ሰዎች መሞታቸውን የተናገሩት አቶ ንጉሡ፣ ‹‹ከእነዚህም መካከል 293 ሰዎች የሞቱት በመድኃኒት እጥረት ነው፡፡ 68 እናቶች የወሊድ ችግር ገጥሟቸው 35 ያህሉ ሕይወታቸው አልፏል፤›› ሲሉ አብራርተዋል፡፡

የደም ግፊት፣ የኤችአይቪ/ኤድስና የስኳር ታማሚ የሆኑ 16 ሰዎች መድኃኒት ያለማቋረጥ እንዲወስዱ በሕክምና ታዞላቸው የነበረ ቢሆንም፣ በመድኃኒት ዕጦት 12 መሞታቸውን ከወረዳው በደረሳቸው ሪፖርት ማረጋገጣቸውን አቶ ንጉሡ ገልጸዋል፡፡

በወረዳው የምግብም ሆነ የመድኃኒት አቅርቦት ባለመኖሩ 38 ሕፃናት በምግብ ዕጦት ምክንያት ሕይወታቸው ማለፉንም አክለው ተናግረዋል፡፡

በጦርነቱ ምክንያት ተፈናቅለው በሰቆጣ ከሚገኙ 79 ሺሕ ሰዎች በተጨማሪ፣ በሕወሓት ቁጥጥር ናቸው በተባሉት በአበርገሌና በፃግብጅ ወረዳዎች 68 ሺሕ ነዋሪዎች በከፋ ችግር ውስጥ መሆናቸውንም አብራርተዋል፡፡

በጦርነቱ ምክንያት ሳይፈናቀሉ በአበርገሌ ወረዳ የሚገኙ ከ37 ሺሕ በላይ ነዋሪዎች በመድኃኒትና በምግብ እጥረት ችግር ላይ መውደቃቸውን፣ የአበርገሌ ወረዳ አስተዳደር አቶ ዓለሙ ክፍሌ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

‹‹አበርገሌ ከ80 ሺሕ በላይ ሕዝብ የሚኖርበት ወረዳ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ከ33 ሺሕ በላይ የሚሆኑት ሰቆጣ ተጠልለው የሚገኙ ሲሆን፣ ሌሎቹ አበርገሌ የሚኖሩ ናቸው፡፡ አበርገሌ ውስጥ ደግሞ የመድኃኒት፣ የምግብና የውኃ እጥረት አለ፤›› ያሉት የአበርገሌ ወረዳ አስተዳዳሪ፣ ‹‹የታመመ ሰው አይድንም፡፡ ሕፃናትና እናቶች በጣም ችግር ውስጥ ናቸው፡፡ ባለን መረጃ መሠረት 200 ሰዎች በረሃብና በበሽታ ሞተዋል፤›› ብለዋል፡፡

ይህ ዘገባ በተጠናቀረበት ወቅት፣ ‹‹እስካሁን ድረስ በከፋ ችግር ውስጥ ነን፤›› ያሉት አቶ ዓለሙ፣ ‹‹በአበርገሌ ከተማ ብቻ ከ40 በላይ ሰዎች ናቸው የሞቱት፤›› ብለዋል፡፡ የሟቾች ቁጥር ሪፖርት ከየቀበሌው እየደረሳቸው መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

‹‹የሰላም ስምምነቱን አክብረው ከወረዳው ያልወጡ የሕወሓት ታጣቂዎች ስላሉ ሕዝቡን መመለስ አልቻልንም፤›› ብለዋል፡፡

በአበርገሌ ወረዳ ከሕወሓት ታጣቂዎች ነፃ የወጡት 02 እና 03 ቀበሌ ብቻ በመሆናቸው ወደ ቀዬአቸው የተመለሱት 1,200 ተፈናቃዮች ብቻ እንደሆኑ ገልጸው፣ በሰቆጣ የሚገኙትም ሆኑ ያልተፈናቀሉ ሰዎች መፍትሔ ባለማግኘታቸው በችግር ውስጥ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

በትግራይ ክልል የተከለሉ ቀበሌዎችና ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ ሰዎች የመድኃኒትም ሆነ የምግብ ድጋፍ እያገኙ መሆኑን ጠቁመው፣ በአበርገሌና በፃግብጅ፣ እንዲሁም በሰቆጣ የሚገኙ ሰዎች ግን ድጋፍ ማግኘት እንዳልቻሉ ገልጸዋል፡፡

በሰቆጣ ከተማ መጠለያ ካምፖች የሚገኙ ከ79 ሺሕ በላይ ተፈናቃዮች ቀዬአቸውን ከለቀቁ ሁለት ዓመት ከአምስት ወራት እንዳለፈቸውና የድጋፍ እጥረት እንዳጋጠመናቸው፣ የዞኑ አደጋ መከላከል የቅድመ ማስጠንቀቂያ ቡድን መሪ ወ/ሮ ዝናሽ ወርቁ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ከተፈናቃዮች መከካል ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ 16 ሺሕ ሕፃናት፣ ስምንት ሺሕ ነፍሰ ጡሮችና በርካታ አረጋዊያንና አቅመ ደካሞች በመጠለያ ካምፕ እንዳሉ የገለጹት ወ/ሮ ዝናሽ፣ የክልሉ መንግሥት በየወሩ ከሚሰጠው 15 ኪሎ የምግብ ድጋፍ ተጨማሪ እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል፡፡

ዓለም አቀፍ ዕርዳታ ሰጪ ድርጅቶች በትግራይ ክልል ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን እንደሚያውቁ ተናግረው፣ መንግሥት ሁሉንም ዜጎች በእኩል አይቶ በፃግብጅ፣ በአበርገሌና በሰቆጣ ለሚገኙ ሰዎችም ድጋፍ እንዲደረግ ጠይቀዋል፡፡

የፃግብጅ ወረዳ አስተዳደሪ አቶ ንጉሡ፣ ‹‹ዕርዳታ ሰጪ ድርጅቶች የፀጥታ ችግር ቢኖር እንኳ፣ ሰንደቅ ዓላማቸውን እያውለበለቡ በትግራይ ክልል ዕርዳታ እየሰጡ ነው፡፡ በሁለቱ ወረዳዎች ግን መንግሥት የፈረደባቸው ናቸው ብሎ መደምደም ይቻላል፤›› ሲሉ አማረዋል፡፡

የፃግብጅ ወረዳ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ በጦርነት ቀጣና ውስጥ የሚገኙ ነዋሪዎች በረሃብና በበሽታ እየሞቱ መሆኑን ገልጾ፣ ባለፈው ሳምንት ብቻ 25 እናቶች በምጥ ምክንያት፣ 15 ሰዎች በምግብ ዕጦት መሞታቸውን አስታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...