በኢትዮጵያ የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ችግር ውስብስብ በመሆኑ፣ መፍትሔ መስጠት የሚቻለው በዘርፉ ላይ በቂ ጥናት በማድረግ መሆኑ ተገለጸ፡፡
የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ላይ በቀጥታ ከሌሎች አገሮች ተሞክሮ የሚቀዳ ባለመሆኑና በርካታ ውስብስብ ጉዳዮችን በውስጡ የያዘ ስለሆነ፣ ስለጉዳዩ በቂ ጥናት መደረግ እንደሚገባው፣ በዘርፉ ስለፖሊሲ፣ ቴክኖሎጂ፣ ግብይትና መሰል ጉዳዮች ላይ የሚደረጉ ምርምሮችን ማበረታታት አስፈላጊ መሆኑን፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአርክቴክቸርና የሕንፃ ኮንስትራክሽን ኢንስቲትዩት መምህርና ተመራማሪ ዘገየ ቸርነት (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያ የሕዝብ ቁጥር ዕድገት ቀደም ሲል ከነበረበት የዝግታ ሒደት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በልዩ ሁኔታ መፍጠን መጀመሩን፣ የምሥራቅ አፍሪካን ጨምሮ በኢትዮጵያ በሚቀጥሉት ከ10 እስከ 30 ዓመታት እጅግ በጣም ፈጣን ከተሜነት (ሐይፐር ኧርባናይዜሽን) ይንሰራፋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ዘገየ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ ያለው የከተሞች በፍጥነት ማደግ ብቻ ሳይሆን ድንገተኛ መገንፈል ተብሎ ሊገለጽ የሚችል ነው ያሉት ተመራማሪው፣ የከተሜነት መስፋፋት ከአውሮፓና ከእስያ አገሮች የሚለየው ከኢንዱስትሪያላይዜሽንና ከትክክለኛ የከተሜነት ዝመና ውጪ ሆኖ መገኘቱ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ቅዳሜ የካቲ 11 ቀን 2015 ዓ.ም. ባዘጋጀው በመኖሪያ ቤት አቅርቦትና ፍላጎት መካከል ያለውን ልዩነት ለመፍታት ታሳቢ ያደረገ የውይይት መድረክ ላይ፣ ‹‹የመኖሪያ ቤት እንቆቅልሾች ዓውዳዊ ምልከታዎች›› በሚል ርዕስ የጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡት ዘገየ (ዶ/ር)፣ እ.ኤ.አ. በ2050 ኢትዮጵያ ከ100 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ እንደምትጨምር፣ አሁን ያለው የገጠር ኢኮኖሚ መዋቅር ይህንን መሸከም እንደማይችልና ተጨማሪውን ሕዝብ የሚሸከሙት ከተሞች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
አሁን ያለውን የከተማና የገጠር ሕዝብ ባለበት ቢተው በተለይ የገጠሩ ቀርቶ ለሚቀጥሉት 25 ዓመታት ተጨማሪውን ከተሞች ይሸከሙት ቢባል፣ 100 ሚሊዮን ሕዝብ ከተሞች ላይ ይጨምራል የሚል አስደንጋጭ አኃዝ እንዳለ ያስረዱት ተመራማሪው፣ በየዓመቱ አዲስ አበባን ያህል ከተማ መገንባት የሚጠይቅ ከመሆኑ ባሻገር፣ የሲቪል ስትራክቸር ወይም ጣሪያና ግድግዳ ብቻ ሳይሆን ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ መዋቅሮችን ሁሉ መገንባት የሚጠበቅ በመሆኑ ቆፍጣና ዕርምጃ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
‹‹መቶ ሚሊዮን ሕዝብ ለማስተናገድ አሥር ሺሕ ሰዎችን የሚያስተናግዱ፣ አሥር ሺሕ ትንንሽ ከተሞችን እንፍጠር? ወይስ አሥር ሚሊዮን ሕዝብ የሚያስተናግዱ አሥር አዳዲስ ሜጋ ሜትሮፖሊታን ሪጅንስ (ከተሞች) እንፍጠር?›› የሚሉት በአማራጭነት የሚቀርቡ ጉዳዮች መሆናቸውን ዘገየ (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡
በኢትዮጵያ ባለፉት 50 ዓመታት ለዜጎች መኖሪያ ቤቶችን ማዳረስን በተመለከተ የተለያዩ ሙከራዎች ማድረጓ የተገለጸ ሲሆን፣ ሒደቱ ያን ያህል አስጨናቂ ስላልነበረ ከተሞች ውስጥ የነበረው የቤት ፍላጎት ገንፍሎ አለመውጣቱ ተጠቅሷል፡፡
ከ1983 ዓ.ም. በኋላ በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ የቤቶች ልማት ፕሮጀክቶች የሚተቹባቸው ጉዳዮች ቢኖሩም፣ ሥራ በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉ መሆናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ የነበሩት ፕሮጀክቶች የቤት ጉዳይ ምን ያህል ውስብስብና አንገብጋቢ እንደሆነ ትምህርት የሰጡ ናቸው ተብሏል፡፡
ለኢትዮጵያ በፍጥነት፣ በርካሽና ሁሉን አካታች በሆነ መንገድ ቤቶችን ማቅረብ፣ ነገር ግን መሠረተ ልማት የተገደበ በሆነበትና የግብይት አቅርቦት፣ አቅምና ክህሎት፣ እንዲሁም የቴክኖሎጂ አቅርቦቱ የተገደበ በመሆኑ በፍጥነት ርካሽና ሁሉን አቀፍ ቤቶችን ማቅረብ እንቆቅልሽ በኢትዮጵያ እንደተጋረጠ ዘገየ (ዶ/ር) አክለዋል፡፡
‹‹ባለፉት አሥር ዓመታት የመሬት ዋጋ ሰማይ በነካበት ከተማ ርካሽና በፍጥነት ሁሉን አካታች የሆነ ቤት ማቅረብ ይጠበቅብናል፤›› ያሉት ተመራማሪው፣ ‹‹ይህንን ካላቀረብን ከተሞች ለጥቂቶች ይሆኑና እርስ በርስ የሚጣረስ ማኅበራዊ ቀውስ የሚፈጥሩ ማዕከላት ይሆናሉ፣ ይህ ደግሞ አሳሳቢ ነው፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡
እየከተመ ለሚሄድ አገር የቤት እንቆቅልሽን ለመፍታት ከፖሊሲ ጀምሮ እስከ ፕሮግራም ቀረፃ ድረስ የተቀነባበረ፣ በሥርዓት ምልክታ የተደረገበትና ክርክሮች የተደረጉበት ሥርዓት መዘርጋት ይገባል የተባለ ሲሆን፣ ለዚህም ምክንያቱ ቤት መሠረታዊ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና የማኅበራዊ ሥርዓት ፈተና ስለሆነ ነው ተብሏል፡፡
በወይይቱ ወቅት ተሳታፊዎች በኢትዮጵያ ውስጥ በቤት ልማትና በሌሎች ዘርፎች ላይ ከሚስተዋሉ ችግሮች ውስጥ የፖሊሲ ዘላቂነት አለመኖር (Policy Inconsistency) አንዱ መሆኑን ገልጸው፣ ከዚህ በተጨማሪ ሕዝብ ከገጠር ወደ ከተማ የሚያደርገውን ፍልሰት ለማስቀረት የቤት ልማትን ጨምሮ ሌሎች የሚቀርቡ ቴክኖሎጂዎችን እስከ ታች ድረስ ማውረድ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የኦቪድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዮናስ ታደሰ ባቀረቡት የዳሰሳ ጽሑፍ የኢትዮጵያ የመኖሪያ ቤት ልማት ችግር የካፒታል እጥረት ብቻ እንዳልሆነ የሚያጠናክሩ ሐሳቦችን ተናግረው፣ ሳይንሳዊና አዋጭ የሆኑ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በአግባቡ በመጠቀም እየታየ ያለውን የመኖሪያ ቤት እጥረት መቅረፍ እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡
የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ረሻድ ከማል ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር፣ በከተሞች በመኖሪያ ቤት አቅርቦትና ፍላጎት መካከል በየጊዜው እየሰፋ ያለውን ክፍተት ለማጥበብ የሚረዱ የመፍትሔ ሐሳቦችን የማመንጨትና በአገሪቱ አሁን ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ለማሻሻል ኮርፖሬሽኑ ያዘጋጀው ዓይነት የምክክር መድረኮች መዘጋጀታቸው ትልቅ ሚና አለው ብለዋል፡፡