በአዲስ አበባ ተካሂዶ በነበረው 36ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔን በታዛቢነት ለመሳተፍ፣ በጉባዔው የመጀመርያ ቀን የተገኙትና በኅብረቱ ጠባቂዎች ከአዳራሽ ኢንዲወጡ የተደረጉት፣ የእስራኤል ከፍተኛ ዲፕሎማት ጉዳይ እያነጋገረ ነው፡፡
ቅዳሜ የካቲት 11 ቀን 2015 ዓ.ም. የኅብረቱ አባል አገሮች መሪዎች በሚያደርጉት የመጀመርያ ስብሰባ ከሌሎች አገሮች ታዛቢዎች ጋር በመሆን ለመሳተፍ መቀመጫቸውን ከያዙ በኋላ፣ በኅብረቱ ሠራተኞችና የጥበቃ ሠራተኞች ከመሰብሰቢያ አዳራሹ እንዲወጡ የተደረጉት ዲፕሎማት ቀድሞውንም የመግቢያ ፈቃድ አግኝተው በቦታው መገኘታቸው ነው የውዝግቡ ምንጭ የሆነው።
የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ ማሃማት እሑድ የካቲት 12 ቀን 2015 ዓ.ም. በጉባዔው መዝጊያ ፕሮግራም ላይ ባደረጉት ንግግር፣ የመግቢያ ባጅ ይዘው ወደ አዳራሹ የገቡት የእስራኤል ዲፕሎማት በኮሚሽኑ እንዳልተጋበዙና አዲስ አበባ ሳይኖሩ እንዴት ሊገኙ እንደቻሉ አስፈላጊውን ምርመራ ለማከናወን እየተዘጋጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
‹‹ዲፕሎማቷ የመጡት ከእስራኤል ነው። አንድ ዲፕሎማት ወደ እዚህ ስብሰባ ከውጭ ሲመጣ በኮሚሽኑ ሊቀመንበር ተጋብዞ ነው፡፡ ነገር ግን እኚህ ዲፕሎማት አልተጋበዙም ነበር፤›› ሲሉ ሊቀመንበሩ ተደምጠዋል።
በእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ዲቪዥን ምክትል ዳይሬክተር ሻሮን ባርሊ ከአዳራሹ እንዲወጡ ሲደረግ የሚያሳየው ቪዲዮ በማኅበራዊ የትስስር ገጾች ከተሠራጨ በኋላ በርካታ አስተያየቶች የተሰነዘሩ ሲሆን፣ የእስራኤል በኅብረቱ ላይ ያላት የታዛቢነት ሚና አወዛጋቢነት ለጉዳዩ መነሻ እንደሆነ ተወስቷል፡፡
በሐምሌ ወር 2013 ዓ.ም. የኮሚሽኑ ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ ይፋ እንዳደረጉት፣ የእስራኤል ተወካዮች በኅብረቱ ስብሰባ በታዛቢነት እንዲሳተፉ ፈቃድ እንደሚሰጣቸው ተወስኖ ነበር። የኅብረቱ አገሮች ከሁለት ሦስተኛው በላይ እስራኤል ለታዛቢነት እንድትሳተፍ ፍላጎት በማሳየታችውና በርካታ አገሮችም የታዛቢነቱ ፈቃድ እንዲሰጣት በመጠየቃቸው ነበር፣ እስራኤል የታዛቢነት አግኝታ የነበረው።
ሆኖም በውሳኔው ላይ በዋነኛነት ደቡብ አፍሪካና አልጄሪያ ባሰሙት ተቃውሞ፣ ኅብረቱ እንደ አዲስ በማጤን ካለፈው ዓመት ጀምሮ እያየው እንደነበረ ይታወሳል።
ሊቀመንበሩ በጉባዔው መዝጊያ ላይ ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት፣ ባለፈው ዓመት የእስራኤልን በአፍሪካ ኅብረት የታዛቢነት ቦታ በተመለከተ ስብሰባዎች ተካሂደው እንደነበረና የአገሮች መሪዎች ያሉበት ጊዜያዊ ኮሚቴ በማዋቀር እንዲጤን እንደተወሰነ ነበር።
‹‹ይህ ማለት ተሰጥቷት [ለእስራኤል] የነበረው የታዛቢነት ቦታ ኮሚቴው እስኪወያይና እስኪወስን ታግዶ ነበር፡፡ በመሆኑም የእስራኤሏን ዲፕሎማት ወደ ጉባዔው አልጋበዝንም ነበር፤›› ሲሉ ሊቀመንበሩ ተናግረዋል።
በጉባዔው ላይ ለመታዘብ መገኘት የኮሚሽኑን ሊቀመንበር ግብዣ ማግኘት ግዴታ መሆኑን፣ የእሳቸው ‹‹ግብዣ ሳይደረግላቸው›› በስብሰባው ላይ መግቢያ አግኝተው የገቡት ዲፕሎማትን ጉዳይ በተመለከተም፣ ‹‹አስፈላጊውን ምርመራ ለማድረግ በሒደት ላይ›› እንደሆኑ ሊቀመንበሩ ገልጸዋል።