የኢትዮጵያ ሕዝብ የትናንት ታሪክ ምርኮኞች የሚከውኗቸውን፣ በቋንቋና በዘር የሚከፋፍሉና በሕዝቡ ውስጥ ቅራኔና ጥላቻ የሚፈጥሩ ንግግሮችንና ተግባራትን እንደ አንድ ሕዝብ አምርሮ ሊቃወም፣ ሊታገልና ከውስጡ ሊያገላቸው እንደሚገባ የአማራ ክልል ኮሙዩኒኬሽን አስታወቀ፡፡
የአማራ ኮሙዩኒኬሽን በይፋዊ የማኅበራዊ የትስስር ገጹ ላይ እንዳሰፈረው፣ ይህ ወቅት መላው ኢትዮጵያዊ አንደ አንድ ልብ ተባብሮ የታሪክ ምርኮኞችን መታገል የሚያስፈልግበት ወሳኝ ምዕራፍ እየሆነ መጥቷል። ሞቅ ቀዝቀዝ በሚል የትግል ሒደት ጠማማ የታሪክ ምርኮኞችና ቅን ልቦና የተሳናቸው የፖለቲካ ቆማሪዎች በኢትዮጵያና በኢትዮጵያውያን ላይ የጋረጡትን አደጋ ማስቀረት የሚቻለው ለእውነትና መርህ በመገዛት መታገል ሲቻል መሆኑን በመግለጫው ተጠቅሷል።
ከታሪክም ሆነ ከአሁናዊ ነባራዊ ሁኔታዎች ላይ ተመሥርቶ የአንድ አገር ሕዝብን በአንድነትና እኩልነት ላይ በተመሠረተ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ሕዝብና አገራቸውን ለመለወጥ ከመታተር ይልቅ፣ ‹‹በየሚዲያው የጥላቻ ተረክን እየነዙ፣ ፖለቲከኞች በፖለቲካ ገበያው ውስጥ ናኝተው ይታያሉ›› ያለው የአማራ ኮሙዩኒኬሽን፣ ታሪክ ትምህርት ቤት መሆኑን በማመን የትናንትናውን መጥፎ ታሪክ ላለመድገም፣ አብዛኛውን በጎውን የጋራ ታሪክ ደግሞ አሻሽሎ ትውልድን ለመጥቀም እንተጋለን፣ ነገር ግን የትላንት የታሪክ ምርኮኞች ሆነን ሕዝባችንን ለፓለቲካ በሽታ የማጋለጥ ፍላጎቱም ትልሙም የለንም። አላማችንም አይደለም ሲል አስታውቋል፡፡
በአቋም መግለጫው እንደተዳሰሰው፣ አሁን አሁን የትናንት ታሪክ ምርኮኛ ፖለቲከኞች ታሪክን እያዛቡ በማመንዠክ ዛሬያችንን ስለነገው ተስፋችን ከመሥራት ይልቅ፣ ስለትላንቱ ተረከ-ታሪክ እሰጥ-አገባ መቆም የትውልዳችን ወትሯዊ ውሎ ሲሆን ይስተዋላል፡፡ የትላንት ታሪክ ምርኮኛዎች ትናንትን ከዛሬ በውል ለይቶ ወደ ነገ መሻገር ሲሳናቸዉ በዘረኝነት ላይ የተመሠረተ ‹‹ቆሞ ቀር›› የፖለቲካ አስተሳሰብን ማመንዠክ ልዩ ክህሎትና መገለጫቸው እየሆነ መጥቷል፡፡
የከፋፋይነት እርካሽ ፖለቲካዊ ብያኔና ፍረጃ የአገርና የሕዝብን ሰላም፣ አብሮነትና ልማት ምን ያህል እያቀነጨረው እንደሆነ ሊገነዘቡት አልቻሉም ወይም አልፈለጉም ያለው አማራ ኮሙዩኒኬሽን፣ ፖለቲካዊ ግልሙትና በሕዝብ ትከሻ ላይ ተንጠልጥሎ ስሁት ትርክት እየነዙ ደም አፋሳሽ በሆነ መንገድ በሥልጣን ለመኖር ካልጠቀመ በስተቀር፣ ለሀገር አንድነትና ሕልውና ፋይዳ ቢስ ስለመሆኑ ከሥርዓተ መንግሥታትና ከነገሥታቱ ታሪክም ሆነ ከዘመናዊው የፖለቲካ ሳይንስ አስተምህሮት መማር ይቻላል ሲል ገልጿል፡፡
ኮሙዩኒኬሽኑ በመግለጫው፣ በዚህ ወቅት በሰፊ አገርና በታላቅ ሕዝብ ውስጥ እየኖሩ፣ የጠበበ ግላዊና ቡድናዊ የጥቅም ፍላጎትን የሕዝብ አስመስሎ በማቅረብ፣ ቡድናዊ ጥቅሜን አስቀጥላለሁ ብሎ ማመን ከትናንቱ ታሪክና ከነገው ተስፋ ጋር ተፃራሪ መሆንን ከማስረገጡ ባሻገር፣ ዛሬን በሕይወት የመኖር ፀጋን ለመንፈግ የፖለቲካ ቁማር ቋሚ ሰልፈኝነትን ያስረዳል ብሎ፣ ይህን መሰሉ አሠላለፍ የአፍታ ተዝናኖት ይሰጥ ካልሆነ በቀር፣ የጀንበር ማብቂያ ያህል እድሜ ያለው ግላዊም ሆነ ቡድናዊ ሕልውነትን አይሰጥም፡፡
‹‹በትናንት የታሪክ ምርኮኞችና በነገው ተስፋችን ቁማርተኞች ሕልውናዋን የማታጣ፣ በጠንካራ የሕዝብ አንድነትና እኩልነት ላይ የፀና አገረ መንግሥት ለማቆም መረባረብ ከሁሉም የሚጠበቅ ኃላፊነት ነው፡፡ ሁሉም ዜጋ ችግሮቻችንን ውጫዊ በማድረግ የሆነን አካል ብቻ እንዲፈታ ከመጠበቅ ወጥቶ፣ የበኩሉን ድርሻ በማድረግና በመተጋገዝ ተደማምጦ በአንድነት ለለውጥና ስኬት በመታገል፣ ተስፋና ለጋ ውጤቶቻችንን በማዝለቅ እንደ ሕዝብ ለገጠመን ፈተና ደግሞ የጋራ መፍትሔ እያበጁ መሄድ ይገባል። አማራጩም ይኸው ነው፤›› ሲል አማራ ኮሙዩኒኬሽን አሳስቧል፡፡