Thursday, April 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበጉራጌ ዞን አገልግሎት መስጠት ያቆሙ ተቋማትን ችግር መንግሥት እንዲፈታ ተጠየቀ

በጉራጌ ዞን አገልግሎት መስጠት ያቆሙ ተቋማትን ችግር መንግሥት እንዲፈታ ተጠየቀ

ቀን:

በደቡብ ክልል በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ ከውኃ አቅርቦት ጋር ተያይዞ በተከሰተ የፀጥታ ችግር፣ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አገልግሎት እየሰጡ ባለመሆናቸው፣ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ ችግሩን እንዲፈታ እናት ፓርቲ ጠየቀ፡፡

እናት ፓርቲ መንግሥት ትኩረት እንዲሰጥ የጠየቀው፣ በዞኑ ወልቂጤ ከተማ ከውኃ አቅርቦት ጋር በተያያዘ በተፈጠረው የፀጥታ ችግር አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አገልግሎት እየሰጡ አለመሆናቸውን ጠቅሶ፣ ሰኞ ጥር 13 ቀን 2015 ዓ.ም. ባወጣው ወቅታዊ ጋዜጣዊ መግለጫ ነው፡፡

ከተፈጠረው ክስተት ጋር ተያይዞ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በተገቢው መንገድ አገልግሎት እየሰጡ እንዳልሆነ የጠቀሰው እናት ፓርቲ፣ በተፈጠረው የፀጥታ ሥጋት የነዋሪዎች የዕለት ተዕለት እንቅስቀሴ በእጅጉ የተገታ በመሆኑ ተገቢው ትኩረት እንዲሰጥ አሳስቧል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በተገቢው መንገድ አገልግሎት የማይሰጡ ተቋማት እነማን እንደሆኑ ከሪፖርተር ጥያቄ የቀረበላቸው የእናት ፓርቲ ዋና ጸሐፊ አቶ ጌትነት ወርቁ፣ ከውኃ አገልግሎት ባሻገር የባንክ፣ የትራንስፖርት፣ የገበያ (ሱቅና ጉሊት) አገልግሎቶች መቋርጣቸውን ተናግረዋል፡፡

አቶ ጌትነት እንደገለጹት፣ ፓርቲው ባለው መረጃ መሠረት ሰባት ሰዎች ደረትና ጭንቅላታቸው በአልሞ ተኳሽ ተመትቶ ተገድለዋል፡፡ ሰላሳ ሰዎች ደግሞ በጥይት ተመትተው ቆስለዋል ብለው፣ የክልሉ የፀጥታ ኃይሎች በነዋሪዎቹ ላይ እስርና ወከባ መፈጸማቸውን እንዳላቆሙና የውኃ አቅርቦት ችግር ያለው በወልቂጤ ከተማ ብቻ ሳይሆን በዞኑ ጭምር መሆኑን አስረድተዋል፡፡

እናት ፓርቲ ባወጣው ወቅታዊ መግለጫ፣ ‹‹በዞኑ የተስተጓጎለው የዜጎች ሰላማዊ እንቅስቃሴ ወደነበረበት እንዲመለስ አጥብቀን እንጠይቃለን፤›› ብሏል፡፡ ‹‹ሕዝብ በመንግሥት ላይ መከፋቱንም መደሰቱንም በተለያዩ አማራጮች ሊገልጽ ይችላል፡፡ መንግሥት በበኩሉ ደስታውንም፣ ተቃውሞውንም በልክ፣ በሕግ አግባብና ለትምህርት በሚሆን መንገድ መያዝ ይገባዋል፤›› ሲልም ፓርቲው አሳስቧል፡፡

እናት ፓርቲ በመግለጫው፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሕዝብ ለሚያነሳቸው ጥያቄዎችና የአደባባይ ተቋውሞዎች፣ የፀጥታ ኃይሎች ምላሽ በእጅጉ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን ጠቅሶ፣ ‹‹ችግሩ በተለይ በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች፣ እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም ጠንከር ብሎ፣ አልፎም ጭካኔ የተሞላበት መሆኑን እያስተዋልን ነው፤›› ብሏል፡፡

ከሰሞኑ በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ ከውኃ አቅርቦት ጋር በተያያዘ፣ ውኃ ጥም ጊዜ ስለማይሰጥ የከተማው ነዋሪዎች ጥያቄያቸውን በሰላማዊ መንገድ አደባባይ ወጥተው ማቅረባቸውን የጠቀሰው እናት ፓርቲ፣ ‹‹ሆኖም የክልሉ ፀጥታ ኃይል ፍፁም ጭካኔ በተሞላበት መንገድ ውኃ ጠምቷቸው የወጡ ዜጎችን ገድሏል፣ ደብድቧል፡፡ አስለቃሽ ጭስ በመተኮስ ለከፍተኛ ሥቃይና እንግልት ዳርጓቸዋል፤›› ሲል ወቅሷል፡፡

‹‹በዚህም ክቡር የሆነው ሰው ልጅ ሕይወት ጠፍቷል፤›› ያለው እናት ፓርቲ፣ የዞኑና የከተማው ማኅበረሰብ ከዚህ ቀደም ክልል እንሁን ጥያቄ ጋር በተያያዘ፣ ፓርቲው በተከታተላቸው ተቃውሞዎች በሙሉ በሰላማዊ መንገድ ጥያቄ ሲቀርብ እንዲሁ ሰፋ ያለ እስርና ወከባ እንደተፈጸመበት የቅርብ ጊዜ ትዝታ እንደሆነ በመግለጫው አትቷል፡፡

‹‹አሁንም ከዚያው ተቋውሞ ጋር በተያያዘ ቂም በመወጣት በሚመስል ሁኔታ ባዶ ጄሪካን ይዛ የወጣችን እናት፣ የኃይል አማራጭ ተጠቅሞ የውኃ ጥም ጥያቄዋን በመግደል ለማርካት መሞከር የጭካኔ ጥግ ይመስለናል፤›› ሲል በመግለጫው አሥፍሯል፡፡

ይህንን ተከትሎም እናት ፓርቲ በመጨረሻም በሚከተሉት መሠረታዊ ነገሮች ላይ መንግሥት ትኩረት እንዲሰጥ በመግለጫው ጠይቋል፡፡

በመጀመሪያም የዞኑና የከተማው ነዋሪ የውኃ ጥያቄ መሠረታዊ፣ ፍትሐዊና አጣዳፊ በመሆኑ መንግሥት ጉዳዩን በልዩ ትኩረት መፍትሔ እንዲሰጠው ማሳሰቢያ ሰጥቷል፡፡

ጥያቄዎችንና ቅሬታቸውን በሰላማዊ መንግድ እየገለጹ የነበሩ ንፁኃንን በጭካኔ የገደሉና ያንገላቱ የፀጥታ አካላት በአፋጣኝ ለፍርድ እንዲቀርቡም ጠይቋል፡፡

በአጠቃላይ የፀጥታ ኃይሎች (በተለይ የክልሉ ልዩ ኃይል) ግብር ከፍሎ በሚያስዳድራቸው፣ ይጠብቁኛል ብሎ ወደ የሚመካባቸው ሕዝብ ኮሽ ባለ ቁጥር አፈሙዝ የሚያዞሩበት አሠራር፣ በመሠረታዊነት እንዲፈተሽ በመግለጫው የጠየቀው ፓርቲው፣ ‹‹ለሕዝብ ውግንና የሌላቸው ኃይሎች ከሆኑም ተቋማቱ ተመርምረው እስከ መፍረስ የሚደርስ እርማት እንዲወሰድባቸው ሕዝብ እንዲጠይቅ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፤›› ብሏል፡፡

ከተፈጠረው ክስተት ጋር ተያይዞ በዞኑ የተስተጓጎለው የዜጎች ሰላማዊ እንቅስቀሴ ወደ ነበረበት እንዲመለስ ፓርቲው አፅንኦት ሰጥቶ ጠይቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...