Tuesday, March 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊለተማሪዎች ለመስጠት የታቀደው የሴቶች የወር አበባ ንፅህና መጠበቂያ  የት ደረሰ?

ለተማሪዎች ለመስጠት የታቀደው የሴቶች የወር አበባ ንፅህና መጠበቂያ  የት ደረሰ?

ቀን:

በአበበ ፍቅር

በአፍሪካ ከወንድ ተማሪዎች ይልቅ ሴት ተማሪዎች በተለያዩ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ምክንያቶች ከትምህርት ገበታቸው እንደማይገኙ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡

ልጃገረድ ተማሪዎች በመደበኛ የትምህርት ገበታቸው ላይ እንዳይገኙ ከሚያደርጉዋቸው መሠረታዊ ምክንያቶች መካከል ደግሞ የሴቶች የወር አበባ የንፅህና መጠበቂያ (ሞዴስ) እጥረት አንዱና ዋነኛው እንደሆነ ይጠቀሳል፡፡

ዩኒሴፍ ከዚህ በፊት ባወጣው ሪፖርት፣ በአፍሪካ ከአሥር ልጃገረዶች አንዳቸው በወር አበባ ንፅህና መጠበቂያ ዕጦት ምክንያት ከትምህርት ገበታቸው እንደሚቀሩ ጠቁሟል፡፡

ለችግሩ መከሰት እንደ ምክንያት ካነሳቸው ውስጥም የመንግሥት ትኩረት ማነስ፣ ቋሚ በጀት ያለመኖርና የለጋሽ አካላት ቁጥር መቀነስ የሚሉት ይገኙበታል፡፡

በኢትዮጵያም ችግሩ ተመሳሳይ ነው፡፡ ችግሩ በገጠሪቱ የኢትዮጵያ ክፍል በሚማሩ ሴት ተማሪዎች ላይ ጎልቶ ይታይ እንጂ በከተማም ይስተዋላል፡፡

በ2014 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ሴቶች ሕፃናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ በመዲናዋ ውስጥ ባሉ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ላይ አስጠናሁት ባለው የዳሰሳ ጥናት፣ ችግሩ በገጠርና በከተማ ባሉ ትምህርት ቤቶች በስፋት እንደሚስተዋል አመላክቷል፡፡

በጥናቱ መሠረትም፣ በአዲስ አበባ ውስጥ ከሚገኙ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች 54 በመቶ የሚሆኑት ሴት ተማሪዎች በወር አበባ ወቅት በሚከሰት የንፅህና መጠበቂያ እጥረት ምክንያት በመደበኛ የትምህርት ገበታቸው ላይ እንደማይገኙ ማረጋገጡን አንስቶ ነበር፡፡

በወቅቱ የዳሰሳ ጥናታቸውን ያቀረቡት አቶ መለሰ ድንቁ ከአምስተኛ እስከ አሥራ ሁለተኛ ክፍል በሚገኙ ሴት ተማሪዎች ላይ ችግሩ የጎላ መሆኑን ገልጸው ነበር፡፡

በዚህም ቢሮው ለገንዘብ ሚኒስቴር ለዘጠኝ ወራት ያህል ባደረገው ውትወታ ጉዳዩ በአዋጅ ተደንግጎ በምገባ ኤጀንሲው በኩል ተካቶ ለተማሪዎች እንዲቀርብና ከውጭ ለሚያስገቡ ነጋዴዎች ከ30 በመቶ የጉምሩክ ቀረጥ ወደ አሥር በመቶ በመቀነስ ማስገባት እንደሚችሉና ከተጨማሪ ታክስ ደግሞ ነፃ እንዲሆን መደረጉን የአዲስ አበባ ሴቶች ሕፃናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ከዚህ ቀደም ለሪፖርተር ተናግሮ ነበር፡፡

በዚህም በ2015 ዓ.ም. ከ300 ሺሕ እስከ 400 ሺሕ ሴት ተማሪዎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ መጠቆሙ ይታወሳል፡፡

የልጃገረዶች የንፅህና መጠበቂያ በነፃ እንዲሰጥ በአዋጅ የተፈቀደ መሆኑንና ለ2015 የትምህርት ዘመን ተግባራዊ ለማድረግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር  እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑንም አንስቶ ነበር፡፡

በያዝነው የትምህርት ዘመን ተግባራዊ ይሆናል የተባለው የሴት ተማሪዎች የንጽህና መጠበቂያ የመስጠት ፕሮግራም ከምን ደረሰ የሚለውን በአዲስ አበባ በሚገኙ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ሪፖርተር ተዘዋውሮ ባደረገው ምልከታ፣ በሴቶች ሕፃናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ በኩል ለትምህርት ቤቶች ይሰጣል የተባለው የንፅህና መጠበቂያ እንዳልተጀመረ ለማረጋገጥ ችሏል፡፡

ይሁን እንጂ ትምህርት ቤቶቹ ከራሳቸው ዓመታዊ በጀትና ከተለያዩ በጎ አድራጎት ድርጅቶች በሚያገኙት ዕርዳታ ለሴት ተማሪዎቻቸው የንፅህና መጠበቂያ እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል፡፡

በቂርቆስ ክፍለ ከተማ የአፄ ቴዎድሮስ የቅድመ አንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ዋና ርዕሰ መምህር የሆኑት አቶ ወንድምሁን ፍቅረ ማርያም በበኩላቸው፣ እስካሁን በየትኛውም የመንግሥት አካል ለሴት ተማሪዎች የንጽህና መጠበቂያ ተብሎ የተሰጣቸው ነገር እንደሌለ ተናግረዋል፡፡ ከትምህርት ቤታቸው ዓመታዊ በጀት በዓመት ከ18 እስከ 20 ሺሕ ብር በመበጀት ለሴት ተማሪዎች የንጽህና መጠበቂያ እንደሚያሟሉ ተናግረዋል፡፡

ርዕሰ መምህሩ ይኼን ይበሉ እንጂ፣ ስሜ እንዳይጠበቅ ያለችው የትምህርት ቤታቸው ተማሪ ምንም ዓይነት የንፅህና መጠበቂያ (ሞዴስ) ተሰጥቷት እንደማያውቅ ይልቁንም እሷና የትምህርት ቤት ጓደኞቿ እንደተቸገሩ ተናግራለች፡፡

ከልጆቹ ሐሳብ በመነሳት ለርዕሰ መምህር ወንድምሁን ፍቅረ ማርያም ከተናገራችሁት ጋር አይጋጭም ወይ? በማለት ሪፖርተር ላቀረበላቸው ጥያቄ አቶ ወንድምሁን ምናልባት በመደበኛነት በየወሩ ስለማይሰጥ ይሆናል ብለዋል፡፡

በቋሚነት ወር ጠብቃችሁ ውሰዱ ባይባልም ማንኛውም ተማሪና የትምህርት ቤተ ሠራተኞች በፈለጉት ጊዜ ወስደው መጠቀም እንደሚችሉ አቶ ወንድምሁን ተናግረዋል፡፡

በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 02 የሚገኘው ማርችኤይት ቅድመ መደበኛና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ዋና ርዕሰ መምህር አቶ አታላይ ሽብሩ በበኩላቸው፣ በአዲስ አበባ ሴቶች ሕፃናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ወይም በምገባ ኤጀንሲው በኩል ለሴት ተማሪዎች የንፅህና መጠበቂያ ተብሎ የደረሳቸው ነገር እንደሌለ ተናግረዋል፡፡

ይሁን እንጂ የነገሩን አሳሳቢነት በመገንዘብ ትምህርት ቤታቸው እንደ ፕላን ኢንተርናሽናል፣ ብሪቲሽ ካውንስልና የመሳሰሉ በጎ አድራጊ ተቋማቶች ጋር በመነጋገር በዕርዳታ እንደሚያገኙ ገልጸዋል፡፡

የሴቶች ሕፃናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት የችግሩን አሳሳቢነት ተገንዝበው ለአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች ለማቅረብ መወሰናቸውና በአዋጅ ማፅደቃቸው መልካም ጅማሮ ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ይኼም በቀጣይነት ቢለመድና ወደ ተግባር ተገብቶ እንደ ምገባው ትኩረት ተሰጥቶት ቢሠራ በትምህርት ላይ በጎ አስተዋጽኦ ያበረክታል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

በአዲስ አበባ የተማሪዎች ምገባ ኤጀንሲ ሥር ተካቶ ሊሰጥ ስለመሆኑ ዕውቅና እንደሌላቸው የተናገሩት አቶ አታላይ፣ ነገር ግን ጉዳዩ መሠረታዊ ችግር በመሆኑ ለትምህርት ቤታቸው ቢሰጥ የተሻለ ነው ብለዋል፡፡

የችግሩን አሳሳቢነት ተገንዝቦ በተያዘው የትምህርት ዘመን በምገባ ኤጀንሲው በኩል ተግባራዊ ይደረጋል የተባለው ለተማሪዎች የወር አበባ ንፅህና መጠበቂያ የማቅረብ ፕሮጀክት ከምን ደረሰ? ሲል ሪፖርተር ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምገባ ኤጀንሲ ጥያቄ አቅርቧል፡፡

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ አንችነሽ ተስፋዬ እንዳሉት፣ ጥናቱ ከተሠራ በኋላ ወደ ተግባር ለመግባት በዝግጅት ላይ ናቸው፡፡ ከሳምንት በፊትም ‹‹ከቀረጥ ነፃ ማስገባት ትችላላችሁ›› የሚል ደብዳቤ ከገንዘብ ሚኒስቴር ደርሷቸዋል፡፡

ከዚህ የዘለለ ዝርዝር መረጃ ለመስጠት እንደማይችሉም አክለው ገልጸዋል፡፡  

ከዚህ ቀደም  የወር አበባ ንፅህና መጠበቂያን ጨምሮ ሌሎች የሴቶች ንፅህና መጠበቂያ ምርቶች አለመኖር በተለይም ታዳጊ ሴቶችን እየጎዳ መሆኑን ትምህርት ሚኒስቴር ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡

በኢትዮጵያ 26 ሚሊዮን ያህል ታዳጊዎች በትምህርት ቤት ውስጥ ሲኖሩ፣ ከዚህ ውስጥ የሴቶች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑንና በወር አበባ ንፅህና መጠበቂያ እጥረት ምክንያት አንድ ሴት ተማሪ በአማካይ በወር ሦስት ቀናትን ከትምህርት ገበታ ውጪ እንደምትሆንም እንዲሁ፡፡

በዓመት ደግሞ አንድ የወር አበባ ማየት የጀመረች ሴት ተማሪ አቅርቦቱ ባለመኖሩ ምክንያት የ30 ሰዓታት ትምህርት እንደሚያመልጣትና ይህም ሴቶችን ለሌሎች ውስብስብ ችግሮች እያጋለጣቸው መሆኑን ሚኒስቴሩ ማስታወሱ አይዘነጋም፡፡

በኢትዮጵያ አሁን ላይ ከሰባት እስከ 10 የወር አበባ የንፅህና መጠበቂያ የሚይዝ እሽግ እንደ ዓይነቱ ከ50 ብር እስከ 100 ብር ድረስ በመሸጥ ላይ ነው፡፡ ከ100 ብር በላይ የሚሸጡም አሉ፡፡ ምርቱ ከቀረጥ ነፃ እንዲገባ ቢወሰንም፣ በአገር ውስጥ የሚመረቱትም ሆነ ከውጭ የሚገቡት በየጊዜው ዋጋቸው ጨምሯል፡፡

በዋጋ መናር ምክንያትም 72 በመቶ የሚሆኑት በገጠር የኢትዮጵያ ክፍል የሚኖሩ ወጣት ሴቶች የንፅህና መጠበቂያ ምርቶችን እንዳማያገኙ የኢትዮጵያ የሥነ ሕዝብ፣ ጤናና አካባቢ ጥበቃ ጥምረት የተሰኘ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ያጠናው ጥናት ያሳያል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹ከኦነግ ሸኔ ጋር ያለውን ግጭት በሰላም ለመፍታት ከፍተኛ ፍላጎት አለን›› ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ

መንግሥት ከ‹‹ኦነግ ሸኔ››ጋር ያለውን ግጭት በሰላም ለመፍታት ከፍተኛ ፍላጎት...

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...