Saturday, April 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ማስተንፈሻ!

ሰላም! ሰላም! “ኦ ሰላም በስምሽ ስንት ግፍ ተሠራ!” የሚል ርዕስ ያለው የድሮ መጽሐፍ ወ መዘክር እንደማገኝ የነገረኝ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ነው፡፡ አሁን ሰላም ከአገር እስከ ዓለም በጠፋበት ዘመን ወደ ድሮ ዘመን ተመልሼ ያረጀ መጽሐፍ ላገላብጥ፣ ወይስ እኔም የዘመኔን የሰላም ዕጦት መንስዔ ለመጪው ትውልድ ጽፌ ልለፍ የሚል ሙግት አዕምሮዬ ውስጥ ተሰንቅሮ ከረምኩ፡፡ ለነገሩ እኔ አላቂ ንብረት የማሻሽጥ ደላላ እንጂ ለዚያ ማዕረግ ማን አደረሰኝ ብዬ ነገሩን ልቆርጥ ስታገል፣ አንበርብር ምንተስኖት ምን ነካህ ማንም በፎርጂድ ዲግሪ ተኮፍሶ ከየስርቻው እየመዘዘ በሚያመጣው ወልጋዳ ታሪክና ሐተታ አይደል እንዴ ሰላም ያጣነው የሚል ክርክር ብቅ ይልብኛል፡፡ ለምሁሩ የባሻዬ ልጅ ውስጤ የተፈጠረውን ትርምስ ስነግረው፣ “አንተ ሰውዬ ልብህ የሚነግርህ ካለ ጻፈው አርትኦቱን ለእኔ ተወው…” ሲለኝ፣ ለካ እንዲህም ይቻላል ብዬ እያሟሟቅኩ ነው፡፡ ድሮ በደህናው ዘመን፣ “ማን ይፈራል ሞት ማን ይፈራል፣ ለእናት አገር ሲባል…” ቀልድ ይመስል የነበረው ከባድ እንደነበር የገባኝ ዛሬ ነው ብላችሁ ታምኑኛላችሁ? እኔስ ለምን እመኑኝ ብዬ አስቸግራለሁ፣ ሁሉንም ጽፌ ለግምገማ ለመቅረብ ዝግጁ መሆን ብቻ ይበቃኛል፡፡ በቃ ይኸው ነው!

“ኧረ እኔስ ፈራሁ…” አለች አሉ ሚስቲቱ። ባል ተሰማዋ። በትንሽ ትልቁ እየተሰማን አንዳንዴ እኮ ባሎች ስንባል እናበዛዋለን። “እንዴት! እንዴት! ምን ለማለት ነው እኔ እዚህ ተቀምጨ ፈራሁ ማለት?” ይላል። ጀግንነት የፈታንበት መዝገበ ቃላችን ከተፈጥሮም ከፈጣሪም አራርቆን የለ? እንዲያው እኮ። ሚስት ነገሩ ወዴት እንደሄደ ገብቷት (መቼም ሴት ልጅ ብልህ ናት፣ ብልጠት ከሥልጣኔ ጋር አጉል ሰዓት ተገናኝተው አጉል እያደረጉዋት ተቸገረች እንጂ) “እህ ሰው አይፈራም? ይፈራል እኮ!” ብላ ባልን በሙሉ ዓይኗ ሳታየው መለሰችለት። ባል ቱግ ብሎ በአሽሙር፣ “ለነገሩ የሴት ወጉ ነው መፍራት…” ብሎ ላይ ታች ሲገላመጥ ሚስት ቀበል አድርጋ፣ “ታዲያ ወንድነትስ ከየት የመጣ ይመስልሃል?” አለች አሉ። በአሉ እንጀምረው ብዬ እኮ ነው፡፡ አስኮብላይና ኮብላይ ልብ ለልብ ይተዋወቃል ይባላል። እኛን ያስቸገረን ግን ራስን ማወቅ ሳይሆን አይቀርም። እውነቴን እኮ ነው። ደርሶ ግንፍልተኛው አልበዛባችሁም? በበኩሌ ጦር ጠማኝ ባለፍ ባገደምኩበት እየተከተለ እየለከፈኝ ተቸግሬላችኋለሁ፡፡ በተለይ ፈገግ ብላችሁ ተረጋግታችሁ፣ በራሳችሁ መተማመን እንዳላችሁ ቀና ብላችሁ ስትራመዱ የታያችሁ እንደሆነ ሽሙጡ አይጣል ነው።

የክፍለ ከተማ ጣጣ፣ የአገር ውስጥ ገቢ እንግልቱ፣ የተበጠበጠ ትዳሩ ብቻ አንዱ ትዝ ብሎት፣ “ምን አቧራ ታቦናላችሁ? አንተ ባይደን ወይስ ፑቲን ነህ? አንጀሊና ጆሊ ወይስ ጄኔፈር ሎፔዝ ነሽ?” እያለ ለዱላ የሚጋበዘውን አፍለኛ ማንም አልቻለውም አሉ። “እንዴት ያለ ነገር ነው ጃል? የሚያማርረን ነገር በዛና ለእያንዳንዳችን አንድ አንድ ፕላኔት ሊሰጠን አማረን ይሆን?” ብዬ ከባሻዬ ልጅ ጋር ሳወራ ከት ብሎ ስቆ፣ “ኮንዶሚኒየም ሳይደርሰን ጭራሽ በስማችን አንዳንድ ፕላኔት?” ብሎ አላገጠብኝ። ቆይ ግን እኔ መቼ ይሰጠን አልኩ? ይኼን እኮ ነው የምላችሁ። ክብደት እንጂ መደማመጥ ቀንሰናል። የሴትየዋ ባል፣ “እኔ እያለሁ ፈራሁ ምንድነው?” እንዳለው ሰው እያደር ተፈጥሯዊ የሆነውን ዑደት ሳይቀር በእሱ ዓይን ብቻ ዓይቶ እየተረጎመ መንገዱን ‘ዋን ዌይ’ ብቻ አድርጎ መድረሻ አጣን። እንዲያው እኮ!

ወደ ባሻዬና ትውስታቸው ልመልሳችሁ፡፡ እንደ ዛሬ ትውስታቸው ሳይዘባረቅ ትናንትን በአካል የሚያዩት ይመስል እንዲህ አሉኝ። “እንዲያው የየጊዜው የትግል ዓይነት ገርሞኝ ነው እንጂ በጃንሆይ ጊዜ የባላባቱንና የጭሰኛውን፣ በደርጉ የአድሃሪውንና የተራማጁን፣ በዚህ ደግሞ መላ ቅጡ የጠፋውን ትግል ሳስበው ይደንቀኛል። ዓይነቱና ጉዳዩ እየተለያየ ኑሮ በትግል ውስጥ እየተፀነሰች መወለዷ ሁሌም ያስደምመኛል ልጅ አንበርብር…” አሉኝ። አዛውንቱ ባሻዬ ነፍስ ካወቁ ጊዜ ጀምሮ በሦስት መንግሥታት የኖሩና በመኖር ላይ ያሉ ሰው ናቸው። ዕድሜ ብልህነትንና አስተዋይነትን እያደር ሲመርቅላቸው፣ ኑሮ ደግሞ እንደ ‘ዲኤስቲቪ’ ‘ቻናሉ’ን እየቀያየረ እውነታን በትዝብት ያስኮመኩማቸዋል። ምሁሩ ልጃቸው ግን ታዝቦ ከማለፍ በቁጭት ስለሚገነፍል፣ “ቁጥጥር የሌለበት ልቅ ሙስና፣ ሕግና ሥርዓት የማይገዛው አካሄዳችነ  እንዲህ ከቀጠለ ሰላምም ሆነ ዕድገት እንዴት ነው ሊኖሩ የሚችሉት?” እያለ ያማርራል፡፡ በየጥጋጥጉና በተናጠል ከመደስኮር ብሎ ደግሞ በዘንድሮው ውል ያጣ ትንቅንቃችን ላይ በግልጽ የመነጋገርን አስፈላጊነት ተነተነ፡፡ የዘንድሮ ችግራችን እንኳንስ ለትንተና ለፀሎትም ያስቸገረ ይመስላል፡፡ ግን ይሁና!

ልቦናዬ አንዳች ዳጎስ ያለ ረብጣ የምቆጥርበት ሥራ እንደማገኝ ደጋግሞ ስለነገረኝ ማልጄ ከቤት ወጣሁ። ሁሉንም ነገር ትቶ ጥቅልል ብሎ ተኝቶ መዋልን በሚያስመኘው የዘንድሮ ውሎ ገባችን ተነስቶ ወደ ሥራ የሚጣደፈውን የሰው ብዛት ሳይ፣ “ዕውን ይኼ ሁሉ ሰው ከእንቅልፉ መጣላት ጀመረ?” ብዬ ከራሴ ጋር ተነጋገርኩ። ግን ከአጠገቤ የሚራመድ አንድ ሰው ሰምቶኝ ኖሮ፣ “ወንድሜ እስካሁን የተኛነው አይበቃም?›› ብሎኝ ሲያበቃ፣ “የድሮ ሰው ምን ይላል መሰለህ? ‘ጠዋት የተነሳ ሰው ሌላው ቢቀር የወደቀ ነገር እንኳ ያገኛል…” ብሎኝ፣ የዕርምጃውን ፍጥነት ጨምሮ ጥሎኝ ሄደ። ከዓመታት በፊት በባሻዬ ሬዲዮ የዛምቢያ መንግሥት የሳምንቱን የሥራ ቀናት ለመንግሥት ሠራተኞች ከአምስት ወደ አራት ማሳጠሩን የሰማሁት ዜና ትዝ አለኝ። ‘በሳምንት አራት ቀን ብቻ ከሠራችሁ ይበቃል፣ ሌላውን ለፀሎትና ለዕረፍት አድርጉት’ ብሎ ማለቱን አልሰማንም እንዳትሉ ብቻ? ባሻዬ እንኳ ታዝበውት፣ ”እግዜሩስ ሳይሠሩ ምን ብሎ ይባርካል?” ማለታቸው አይረሳኝም። ምንም ሰበብ ይሁን ምን እንቅልፍን ድል እየነሳን ለሥራ መሮጥ አብዝቶ እንዲለምድብን እየለመንኩ፣ ያደሩ ቢዝነሶችን ለመከፋፈት ስልኬን መጎርጎር ጀመርኩ። የደንበኛ ስም እንጂ የደንበኛዬን መስመር ለማግኘት ፍዳ የምታሳየኝ ሞባይሌን ስጎረጉር ከግማሽ ሰዓት በላይ አቃጠልኩ። በረባ ባረባው እንደ ደረቅ ቆሻሻ ሲቃጠል የሚውለውን የሰው ጊዜና ጨጓራ ለማስላት ብዬ ቀኔን እንዳላበላሽ መልሼ ተውኩት። ወዲያው አንድ ደላላ ወዳጄ አሳልፌ ሰጥቼሃለሁ ብሎ ቅጥቅጥ አውቶቡስ እንዳሻሽጥ ሲነግረኝ ወደ እዚያው ከነፍኩ። እንኳን ቀን ተቀንሶ ያለው አልበቃ ብሎናል፡፡ መሰንበት ደጉ በጎን ጉድ ያሰማናል!

እንደ ወትሮዬ በቀላሉ አሻሽጬ ዘወር የምልበት ሥራ መስሎኝ ብሄድም ቅሉ ሳይሆንልኝ ቀረ። ታማኝ ያልኩት ደላላ ወዳጄ ለሌሎችም ደላሎች ነግሯቸው ጠበቀኝ። ግርግርና ጭቅጭቅ ከመብዛቱ በፊት ላጥ ብዬ ሌላ ነገር መፈለጌን ቀጠልኩ። አንድ ነገር ላይ ግር ስንል ገና ምንም ከፍተን ያላየናቸው ሥራዎችን ስንዘነጋ ብዙ ጊዜ ታዝቤያለሁ። “ጅብ አንድ ቀን የጠገበበት ቦታ ሲመላለስ አሥራ አምስት ቀን ይራባል” የሚለውን ምሳሌ አውቃለሁ፡፡ እኔ አንበርብር ምንተስኖት ታዲያ ይኼንን እያወቅኩ ለምን ብዬ ልዘን? ሁሉም እንደ እኔ ‘እልፍ ሲሉ እልፍ ይገኛል’ ቢል ይኼኔ ቢዝነሱ በምግብና በልብስ ብቻ ተገድቦ ይቀር ነበር? አይመስለኝም፡፡ እንዲህስ ከሆነ ለምን በምቀኝነት እንታማለን? ለአንድ ትሪ ሃያ ሰው ቢታደም እጅ መጋጨቱ የት ይቀራል? እንዲያው ልፉ ቢለን እንጂ ቆም ብለን እያሰብን ብንሠራ እኮ የሰው ካዝናና ኪስ በመቁጠር ራስ ምታት በፀሐዩዋ ላይ ተጨምሮ መቆሚያ መቀመጫ አያሳጣንም ነበር። ነበር ማለት ዋዛ ሆነ አይደል!

ይኼን እያሰብኩ ስልኬን ዕረፍት ሳልሰጥ ስደዋውል አዲስ አይሱዙ እንዲሸጥለት የሚልግ ሰው እንዳለ ሰማሁ። መርካቶና ለገሃር ዞር ዞር ብዬ ዜናውን ከነዛሁ በኋላ ከሰዓት በኋላ አንድ ገዥ ደውሎ ሳልውል ሳላድር መኪናውን እንዳሳየው ተማፀነኝ። በጉትጎታው ግፊት መኪናውን እንዲያየው ካደረኩ በኋላ፣ “ገዥ ግን እንደዚህ ሲቸኩል አይቼ አላውቅም። በደህና ነው?” ብለው ሊገዛበት ያሰበውን ገንዘብ ያገኘው ከወዳጅ በብድር እንደሆነ አጫውቶኝ፣ ቶሎ ሠርቶ ቶሎ መክፈል እንደሚፈልግና ከወዲሁ ስለያዘው ጭንቀት አወጋኝ። የንግድ ሕይወት በውድድር መንፈስ የሞት የሽረት ፍልሚያነቱ ሲያይል፣ በመሀል ሳይሠሩ ለመክበር የሚፈልጉት መዥገሮችን ስታስቡ ምን ይሰማችሁ ይሆን? መዥገሮችማ የአገር ደም መጠው ጠብድለዋል፡፡ በሕዝብ ጫንቃ ላይ የሠፈሩ መዥገሮችን ዘርጥጦ መጣል ያቃታቸው ወይም ፍርኃት የገባቸው መሪዎቻችን ፀጥ ብለዋል፡፡ እኔ ደላላው ግን የአገር መዥገሮች የበለጠ እየደለቡ ከሄዱ እንደ ማፊያ ያሻቸውን ከማድረግ አይመለሱም እያልኩ ነው፡፡ ሰሚ ጠፋ እንጂ!

ጉድ እያየሁ፣ ታሪክ እየሰማሁ፣ ኮሚሽኔን እየተቀበልኩ፣ ውዬ እያደርኩ ሳለሁ አንድ ቀን ማንጠግቦሽ፣ “አራስ እንጠይቅ” ብላ የድሮ ጓደኛዋ ቤት ወሰደችኝ። ስለዚህች ጓደኛዋ ደጋግማ ስታጫውተኝ ለጥቅም የተሸጠች የለየላት አምታች እንደሆነች ነበር። “ለምን ብለሽ ነው ማንጠግቦሽ ይዘሽኝ የመጣሽው?” ስላት፣ “ትይህ ብዬ! ንፁህ ፍቅር እንዴት እንደሆነ ለፍቅር ብዬ እንጂ እንደ እሷ ለገንዘብ ብዬ ትዳር እንዳልያዝኩ እንዲገባት ብዬ…” አለችኝ እልህ በተቀላቀለበት የድምፅ ቃና። ይገርማችኋል እንደ ዛሬው ሳይሆን ያኔ እኔና ማንጠግቦሽ ስንተጫጭ ከእኔ ሊነጥሉዋት ያልሞከሩ አልነበሩም ለማለት ይከብዳል። ማጣት የዘር ይመስል ሠርቶ መለወጥን ያስተማረን ስላልነበር፣ የእኔንና የማንጠግቦሽን የመሰለ ፍቅር በአጭር ተቀጭቶ እንዲቀር ያልዶለተ አልነበረም። እኔምለው? ኃያላን አገሮች ብቻ መሷላችሁ እንዴ በውስጥ ጉዳዮቻችን ጣልቃ የሚገቡብን? ስንት የምላስ ኃያላን አሉላችሁ? ሠርቶና ተጋግዞ የመኖርን ጥበብ በአቋራጭ ሂዱ ብለው እያደፈረሱት የሚኖሩ። እነሆ ትዳር በሙስና ከተጀመረም ውሎ አደረ። ይመሥገነውና ለፈጣሪ የእኔና የማንጠግቦሽ ኑሮም ተደላድሎ የጠላትን ቆሽት ያሳርራል። እኔ ግን የአገሬን ጠላት ቆሽት የሚያሳርረው ምን ይሆን እያልኩ ሳስብ ፍቅር፣ መተሳሰብና ብሔራዊ አንድነት እንደሆነ ግልጽ ብሎ ይታየኛል፡፡ ለምን ፍቅር ይርቀናል?

ከማንጠግቦሽ ተለያይተን ከምሁሩ የባሻዬ ልጅ ጋር ግሪሰሩ ቀጠሮ ስለነበረኝ ወደ እዚያው ማቅናት ጀመርኩ። መንገዱ ከዚህም ከዚያም ተዘጋግቶ እንኳን ባለመኪናው እግረኛው መፈናፈኛ አጥቶ ጠበቀኝ። ለአፍሪካ ኅብረት መሪዎች ጉባዔ መሆኑን ስረዳ ግሮሰሪ በጊዜ መድረሴን መጠርጠር ጀመርኩ። ከሥራ የወጣው ሕዝብ እየተተራመሰ አንዱ በአንዱ ላይ ሊወጣ የሚያሰፈስፍ ይመስላል። አንድ ፀጥታ አስከባሪ፣ ‹‹አንዴ ባላችሁበት ቁሙ…›› ብሎ ሲነግረን የእግረኞች ‘ክራውድድ’ ተፈጠረ። ይኼኔ አንዱ እንዲህ አለ፡፡ ‹‹እንግዳ ተቀባይነት ይኼኔ ነው የሚፈተነው…›› ሲል ሌላው፣ ‹‹ወሬ፣ ወሬ ሰለቸን። እስካሁን ስንቴ ተሰበሰቡ? ምን ሥራ ሠሩ? ወሬ ነው። አሁንም የአፍሪካን ዕጣ የሚወስኑት ሌሎች ናቸው። በእኛ የሰላም ስምምነት እንኳ ‹የአፍሪካ ችግሮች በአፍሪካዊ መፍትሔ› ቢባልም ዋናዋ አሜሪካ ነበረች አይደል?›› ከማለቱ ገልመጥ ገልመጥ እየተደራረግን እርስ በእርስ ተያየን። ‘ጠርጥር ከስንዴ ውስጥ እንክርዳድ አይጠፋም’ ነዋ ልማዳችን። ወዲያው እንግዳውን የያዙና ያጀቡ መኪኖች አልፈው ጉዞ ልንጀምር ስንል፣ እንደገና ጠብቁ ተባልን፡፡ “የአፍሪካ መሪዎች ምንም ላይፈይዱ የደሃ ሥራችንን ያስተጓጉሉብናል…” እያለ አንዱ ሲመረር ተገትረን ከማዳመጥ ውጪ ምንም ማለት አልቻልንም፡፡ የትምህርት ጊዜው እንዳያልፍበት የቸኮለ አንድ ለግላጋ ወጣት፣ “እንዴ እዚህም ተዘግቷል እንዴ?” ብሎ ለቅሶ ቀረሽ ጥያቄ ሲያቀርብ ዓይናችንን እያንከባለልን “አዎ!” አልነው በኅብረት በሐዘኔታ፡፡ የታከተው በሚመስል ድምፅ፣ “ኧረ የማስተንፈሻ ያለህ!” እያለ ሲማፀን ጥያቄው ለመንገድ ብቻ አይመስልም ነበር፡፡ መልካም ሰንበት!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት